Saturday, 14 January 2017 15:39

ትንሽ ገለጥለጥ እንደ መግቢያ

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(3 votes)

ይህ የማሕበራዊ ገጾች (Social Media)፣ በተለየም Facebook፣ የአንድ ሰሞን ውሎ የቀነጫጨብኩት ነው። እስቲ እንየው! እስቲ እንታዘበው! ለማለት ያክል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ እጽፍበታለሁ የሚል ሀሳብ የነበረኝ አይመስለኝም። ሆኖም በማሕበራዊ ገጾች አንዳንዶች ተንኮስ  ሲያደርጉኝ፤  “ልበለው አልበለው!” የሚል ነገር ይመጣብኝ ነበር። ፈረንጅ Thinking Out Loud  የሚለው ሳይሆን አይቀርም። የThinking Out Loud ትርጉሙ ይኸውና:-
‘Thinking out Loud’. means that someone is verbalizing an internal monolog (or dialogue); thinking about something and, possibly inadvertently, saying it out loud. The phrase is mostly used when someone else hears it and thinks the person is talking to him or her. ... I was just thinking out loud.”
ማብሰልሰል ልንለው እንችላለን?
መነሻው
ለዚህ  መነሻ የሆነኝ ሌንጮ ባቲ Facebook ላይ  ስለ ወንድሙ  የሰጠው  አስተያየት ነበር። ”ወንድሙ፤ የኦሮሞ ባንዲራ ካልተውለበለበ በስተቀር ከትምህርት ቤቱ አልመረቅም  ብሎ ባንዲራው ተሰፋለትና በዚያ ባንዲራ ጥላ ተመረቀ” የሚል ነው። የጻፈውን እዚህ እንዳለ ይኸውና ለጥፌዋለሁ።
Lencho Bati
· January 8 at 1:16am · Ambo Bati who was five times all American cross country champion refused to graduate unless the Oromo flag is lined with the flag of nations of the graduates. The college looked for all the companies around the world who produce world flags. Could not find it and order it. Spencer, who is Ambo’s track mates and a close friend, and now a Medical Doctor asked his mother to saw an Oromo flag from a picture presented to her over night. She put the pieces together and Ambo’s wish was fulfilled at Augustana College in Illinois on graduation day. It was 1996.
እስከሚገባኝ ድረስ ሌንጮ ባቲ፤ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት አባል፤ መሪ (እርግጠኛ አይደለሁም)  ነው/ነበረ። ከሁለት አመት በፊት ይሁን እንዲያ፣ በMessenger ይመስለኛል ሰላምታና መልእክት ልኮልኝ መልስ ሰጠሁት። ከዚያ በኋላ አልተመለሰም። መልሴን የወደደው አልመሰለኝም። ስለ ኦነግ የማውቀውን ነግሬው፣ “ብቻ በጣም በጥንቃቄ ብታየው ጥሩ ነው!” የሚል ምክር ነበር። ስለ ኦነግ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ለአስር አመት ተኩል መታሰሬ ዋናው ምክንያት፣ ኦነግና የኦሮሞ ጉዳይ ስለነበር  ምክር መስጠቴ ከዚህ ተመክሮ የሚመጣ ነበር። ከኔ በላይ ስለ ኦነግ በገለልተኝነት ማወቅ “ላሳር ነው!” የሚባለው አይነት መሆኑ ነበር። አሳሩን ቀምሻለሁና!!
ይህ የኦሮሞ ባንዲራ ካልተውለበለበልኝ አልመረቅም ብሏል የተባለው የሌንጮ ባቲ ወንድም፤ አምቦ ባቲ፣ ነገር ገርሞኝ እዚያው Facebook  ላይ”ነገሩ ለካ እዚህም ደርሷል እንዴ!” በሚል ትንሽ አስተያየት ሰጠሁ። ይህ ዛሬ በሐይማኖትም ሆነ በሀገር፤ በብሔረሰብ ሽፋን በመላው ዓለም የተፈለፈሉትን ጽንፈኞች፤ በተለይም ፈንጅ ታጥቀው ራሳቸውንም ሌላውንም የሚያጠፉትን ወጣቶች አስታውሶኝ መሆን አለበት። ፖለቲካ ማለት “የመቻቻል ጥበብ ነው” The Art of Compromise የሚባለው ቀርቶ የመጥፊያ፤ የማጥፊያና የመጠፋፊያ መሳሪያ መሆኑ፣ እያሳዘነኝም እየደነቀኝም “ለመሆኑ  እንዴት እዚህ ደረስን!?” ከሚልም ነበር።
ከዚያ ወረዱብኝ! ተራ ዘለፋና ስድብ ነው። እኔ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ሰው የሆነ ሰው ሁሉ ጸያፍ ቃል ሲሰነዝር ይሰቀጥጠኛል። እዚህ አሜሪካኖቹን እንኳን ስንት ጊዜ፣ Mind Your Language እላለሁ። “ቃላቶችህን ልብ በላቸው!” ለማለት ነው። እኛ ቤት እንኳን ጸያፍ ቃል ከአፋችን ሊወጣ፣ ባለጌ ናቸው ከሚባሉ ልጆች ጋር ከታየን እንወገራታለን። ከማቱኬ አጆ ጋር ቀልድ የለም። “አሳዳጊ የበደለው ታሰኙኛላችህ!” ነው ዋናው መልእክትዋ። ይህንኑ ይኸው ከልጆችዋ፣ ለልጅ ልጆችዋ አድርሰናል። ታዲያ ይህንን ማሕበራዊ ገጽ ላይ የማየውን ጸያፍ ቃላት ስታዘብ፣ ያ “አሳዳጊ የበደለው!” ፣ዛሬ ጥዋት የተባለ መስሎ ብልጭ ይልብኛል።ይልልኛል!
ቢቸግረው መሰለኝ ወዳጄ፤ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና መልስ ሰጠ። ያ መልስም ይኸው:-
Fekade Shewakena Why do we employ so much vitriol even if the issue may be contentious and emotional. It doesn’t help anybody. Let’s read what Ato Assefa Chabo is going to write. We will all read and judge his views and write back to him if we don’t agree with him. Some of you like Macaaf Tuulema and Tolessa Gosomssa above should be ashamed of yourselves for the kind of language you use in this discussion. Even the most sacred of your beliefs can be questioned. You may have to respond calmly so that the rest of us who have no knowledge could learn
ገባ ተብሎ ሲታይ
Facebook ላይ መልስና አስተያየት ከሰጡት ሰዎች ውስጥ አንዱ በፈቃዱ ሞረዳ ነበር። በፈቃዱን በስም አውቀዋለሁ። የሚጽፈውንም የሚገጥመውንም አነባለሁ። በፈቃዱ የጻፈውን እንዳለ እዚሁ ልለጥፍ:-
Befekadu Moroda አቶ አሰፋ…እንዴትም ይሁን ለምን፣ ስለ ኦሮሞ ማሰብዎ/መጠበብዎ ለእኔ ችግር የለዉም፡፡ እንዲያዉም ከዚህ የበለጠ እንዲያሳስብዎትና እንዲያናግርዎት ነዉ ፀሎቴ። የኦሮሞ ሕዝብ በቅጡ የሚጠቀምበት ከሆነ የወዳጁም ሆነ የጠላቱ ሐሳብ ያስፈልገዋል። ይጠቅመዋልም፡፡ እርስዎ ኦሮሞን እንዴትም ይጥሩት ዋናዉ ቁምነገር ‹‹እንደዚያ›› የሚባል የራሱ ታሪክ፣ ባሕል፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ማኅበራዊ ስነልቦና በአጠቃላይ እርሱን ከሌሎች የሚለዩት፣ እንዱሁም የሚያመሳስሉት የተከበረ ማንነት ያለዉ ሕዝብ መኖሩን ማወቁ ላይ ነዉ፡፡ ተወደደም፣ ተጠላም፡፡
ስለ እርስዎ ሳስብ ሁሌም ወደ አእምሮዬ የሚመጣዉ ጥያቄ፤ ‹‹አቶ አሰፋ ስለ ኦሮሞ ያሰቡትን፣ የተናገሩትን፣ የፃፉትን ያህል ስለ ጋሞ ግድ ብሏቸዉ ያዉቃል?›› የሚል ነዉ፡፡ ጋሞ ዛሬ በአደባባይ ሊነገርለት የሚገባ ችግር የለዉ ይሆን? ይህን ችግሩን የሚናገርለትስ ልጅ አልወለደ ይሆን? ተስፋ አደርጋለሁ፤ እግዜር ከሰጠዎት ዕድሜ በቀረዎት ጊዜ ስለ ጋሞ ሕዝብ ብዙ የማናዉቃቸዉን ሀቆች ፅፈዉ ለታሪክ ትተዉ ያልፉ ይሆናል፡፡
የበፈቃዱ አስተያየት ብዙ አንድምታ ያለው ይመስለኛል። አንድምታው “ኦሮሞን ለቀቅ አድርገህ ለምን ስለ ጋሞ አትጽፍም!” የሚል ነው። የዚህ አይነት አስተያየት በመጠኑ በየጊዜው ይደርሰኛል። ባለፈው ሰሞን አንድ “ግዕዝን ለቀቅ አድርገህ ጨንቻ ላይ ብታተኩር አይሻልም!??” የሚል ሁለት የጥያቄ ምልክት ያለበት ነበር። ከኦሮሞዎች አካባቢ ከዘለፋው ሌላ “ስለ ኦሮሞ አንተ ምን አገባህ ?”የሚል ተደጋጋሚ አገኛለሁ። አንድ ሌላ የማውቀው ሰው፣ “አሁንማ ሙሴ ሆንክላቸው!” አለኝ። “ለማን?” ብለው፣ “አማራና ነፍጠኛን ባህሩን አሻገርካቸው!” አለኝ። “ወደ ተስፋይቱ፣ ቃል ወደተገባላቸው አገር አሻግሬ ከሆነ ጥሩ ነው!” ብዬ አለፍኩት። የአማራና የነፍጠኛ ደጋፊ ነህ ለማለት መሆኑ ነው።
እዚህ ግልጽ እንዲሆን የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነጥብ ያለ ይመስለኛል። እኔ ስለ ማን፣ ስለ ምን እንደምጽፍ፤ መጻፍ እንደሚገባኝ፤ እንደማይገባኝ ሊነገረኝ፣ ሊያዘኝ የሚችል ሰው በዚህ ምድር ላይ የለም። ይህ መሠረታዊ፤ ሰብአዊ መብቴ ነው። የኔ ብቻ ሳይሆን የማንኛችንም፤ የሁላችንም መሠረታዊና ሰብአዊ መብት ነው። ስለዚህ ያ ለውይይት የሚቀርብ አይደለም!
ሌላው፣ በኦሮሞ፤ በአማራ፣ በጋሞ፤ ብሎም በማንኛቸውም የሰው ዘር ላይ የተለየ የግል መብት (Monopoly) ያለው፣ “እዚህ ድርሽ እንዳትል!” የሚል የለም! ሊኖርም አይገባም!! ብዙ ጊዜ እንዳልኩት፣ “ማንም ሰው ደሴት አይደለም!” ተያይዘን፤ ተቆላልፈን፤ ተነባብረን የምንኖርና የምንጓዝም ነን። የትም ይኑር የትም፣ የአንድ ሰው ደስታው ደስታዬ ነው፤ ሕመሙም ህመሜ ነው።  በፈረንጅ፤ We’re in This Together” የሚል  ዘፈንም አለ። በዚህ መለኪያ ነው የምኖረው! የምጽፈውም!
ይህን ካልኩ በኋላ በፈቃዱ ሞረዳ ስለ አነሳውና ስለሰጠሁት መልስ ልሂድበት። መጽሐፌን “የትዝታ ፈለግ” አላነበብክ እንደሁ እባክህ አንብበው።ምእራፍ አስር፤” የዶርዜ ማርያም”፤ ምእራፍ አስራ ሰባት፤ “የፈሩት ይደርሳል”፤ምእራፍ ሀያ ስምንት፤” እንደ ዶርዜ እህቶቼ”፤ ”የትዝታ ፈለገ ፱” ስለ ቀኛዝማች ኢልታሞ ኢቻ ---- የተጻፈው ስለ ጋሞ ነው።
አውስትራሊያ፤ካሳሁን ሰቦቃ በሚያዘጋጀው SBS የራዲዮ ቃለ መጠየቅ፣ ስለ ጋሞ ሰፋ ያለ አስተያየት ሰጥቼ ነበር። እዚያ ውስጥ “እንደኔ እንደኔ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  እንደ ጋሞ ቢሆንልኝ ደስታውን አልችለውም ነበር!” የሚልም አለበት። ከያሬድ ጥበቡ ጋር  “መወያየት መልካም”ፕሮግራሙ ላይ ባደረግሁት ቃለ መጠይቅ፤ ስለ ጨንቻ በሰፊው አውግቼ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ ጨንቻን የሚስተካከል ከተማ ቢኖር አዲስ አበባ፣ ናዝሬት ብቻ ይመስለኛልም ብያለሁ። “ዜናሁ ለጋላ“ ስለተጻፈበት ብርብር ማርያም፣ በዩሱፍ ያሲን “ማንነት .. “ መጽሐፍ ላይ ግምገማ  በሰፊው ጽፌ ነበር። ይህ ሁሉ በFacebook በድረገጾችም፣ በአዲስ አድማስም ወጥቷል  የሚል ነው።
ሁለት ነገር! አንደኛ ይህ  ስለ እኔ አስተያየት ለምን  ተሰጠ የሚል አይደለም። ወድጄ ፈቅጄ “የአደባባይ ሰው”  ሆኛለሁና፣  ያ “የሕዝብ ንብረት” ያደርገኛልና፣ ማንም ሰው ሊተቸኝ፣ ሊያርመኝ፣ ሊነቅፈኝ፤ ሊያስተካክለኝ መብቱ ነው።
ሁለተኛው ግን፤ “ መረጃ ሙሉ ሰው ያደርጋል!” የሚሉት ነው። ስለ እኔ ለመጻፍ፤ የጻፍኩትም፤ የተጻፈልኝም፤የተጻፈብኝም፤የተገጠመልኝም እዚያው አደባባይ ላይ ሞልቶ ተርፏል። Google የማድረግ ጉዳይ ብቻ ይመስለኛል። በዚህ፤ አደባባይ ያለ ማስረጃ ሳያዩ ወይም ሳያስተውሉ ቀርተው ለምሳሌ ያክል  ስለ ጋሞ አትናገርም ማለት ከጭብጡ ውጭ ይመስለኛል። እውነት አይደለምና! እውነቱ ተመዝግቦ ተቀምጧልና!
“እገሌ፣ እነ እገሌ መንደራቸው የት ነው!” ብዬ አይደለም የምጽፈው። ለዚህ ማስረጃ እዚያዉ “የትዝታ ፈለግ ውስጥ ይገኛል። ምእራፍ ሁለት፤ “በግ ካራጁ ጋር..” ስለ ጎንደሬው ዶክተር ካሳሁን መከተ፤ ምእራፍ ስድስት “የኔይቱ ጀግና” ስለ ዘውዲቱ አስማረ ነው። ዘውዲቱ  ወሎዬ ነች። ምእራፍ አስራ ስድስት፤ “በማተቡ ይዳኝ“ ወዳጄና ጓደኛዬም ስለነበረው ስለ ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ ነው። ደበላ ደግሞ ኦሮሞ ነው። ምእራፍ ሶስት፤ “ልብ ያለው ልብ ይበለው”  ስለ ረዘነ ወልዱና  ስለ ወይናይ ነው።ኤርትራዊያን ናቸው። ብቻ ከተነሳ አይቀር ብዬ እንጅ በምጽፈው “ከየት መንደር መጣ!?” የሚል መመዘኛ የለኝም። ሰው መሆኑና፤ በኔ ግምት ሊነገር የሚገባው ነገር አለ ብሎ ማመን በቂዬ ነው። እንዲያ የሚያዩ ደግሞእኔን ወደዚያ ለመጎተት መሞከሩ  ጥሩ አይመስለኝም። በዚህ ዕድሜዬ “አዲስ አሰፋ!” አልሆን ነገር!
ወደ ባንዲራው
ሶስት ነጥቦች አንስቼ ባጠቃልል የሚሻል ይመስለኛል አንደኛው የኦሮሞ ባንዲራ የተባለው የኦነግ ባንዲራ ነው። “ከፍተን ብናየው! ሻአቢያና የኦነግ መስተፋቅር” በሚል የጻፍኩት በየድረገጾች ላይ ከመውጣቱም ሌላ በFacebookና በአዲስ አድማስም ላይ አዲስ አበባ ታትሟል። የወጣው በNovember 26,2016 ነበር። አንድ ሰው በራዲዮ አንብቦትና በUtube ሆኖ ድረገጾች ላይ ተለጥፏል። ይህንን በራዲዮ የተነበበውን ዛሬ ጥዋት ድረስ 154,000 ሰው አድምጦታል። ይህ በአዲስ አድማስ፤ በFacebook እና በየድረገጾች ላይ ያነበቡትን ሳይጨምር ማለት ነው።
በዚህ “ከፍተን ብናየው..” ጽሁፍ ላይ ኦነግን ከውልደቱ ጀምሮ አንስቻለሁ። ሳጠቃልልም፤ “ያንን ታላቁንና ገራገሩን የኦሮሞ ሕዝብ ሥም ተሸክመው፣ ሕዝቡን የሻንጣ ተሸካሚ ተምሳሌት ማድረግ የለባቸውም!” የሚል ነበር። የሚያሳፍርና ሊያፍሩበትም ይገባልም ብያለሁ።
የኦነግ መሪዎች ወንጀለኞችም ናቸው ብያለሁ። ለማስረጃ ያቀረብኩት ሁለት ብቻ ነበር። አንደኛው ከሻአቢያ ጋር ሆነው አሶሳ በሰፈራ ሰፈር የነበሩትን ኢትዮጵያውያን፣ በጥይትና በእሳት ማጋየታቸው ነበር። ሌላው የኦነግ ተዋጊ ወታደር ነው ያሉትን፣ የወያኔ/የሻአቢያ ሻንጣ ተሸክመው አዲስ አበባ እንደገቡ ወያኔ፤ “ወታደር ካምፕ አስገቡ!’ ብሎ ሲያዛቸው አስገቡ። “ድርሻችሁን ጨርሳችኋል፤ ከዚች ኢትዮጵያ ከምትባለው አገር ልቀቁ ወይም ወህኒ ውረዱ!” ብሎ ለኦነግ መሪዎች ትእዛዝ ሲሰጥ ከአገር ወጡ። እነዚህ ወታደር ካምፕ የገቡ የኦሮሞ ልጆች ወደ ወህኒ ወረዱ። እስከ ዛሬ ስለነዚህም ሆነ በብዙ ሺህ  ለሚቆጠሩ በኦነግ ሰበብ-አስባብ ለሚሰቃዩ ወገኖች፣ ትንፍሽ ያለ የኦነግ መሪ፤ ተከታይ ወይም ጭፍራ የለም። ከነዚህ፤ በኔ ላይ ዘለፋ በሚያወርዱትም ሆነ በሌንጮ ባቲ ወይም በበፈቃዱ ሞረዳ ለዚህ ጉዳይ የተሰጠ መልስ፤ ማስተባበያ፤ መደገፊያ ነገር የለም።
ማናቸውም ድርጀት፤ የንግድ ሆነ የፖለቲካ ሲከስር ይዘጋል። ኦነግ በተግባር ከስሮ ከተዘጋ ቆይቷል። አሁን የተያዘው ሥራ በኦሮሞ ስም ንግድ ነው። እንግዲህ የሌንጮ ባቲ ወንድም፤ አምቦ ባቲ፣ መመረቅ አለብኝ የሚለው በዚህ ባንዲራ ጥላ ነው። ጎበዝ!  እየተስተዋለ ቢሆን የሚሻል ይመስለኛል።
ሁለተኛው፤ “ራስን ፍለጋና ትዝብት!” በሚል ርእስ  ጽፌ ነበር። ያም እላይ በገለጽኳቸው የመገናኛ ዘርፎች ሁሉ  ወጥቷል። የዚያ ጽሁፍ ምክንያት የሆነው አንድ አንባቢ  በድረ ገጾች በተለጠፈ ጽሁፍ፣ ጥያቄ አቅርቦልኝ ስለነበር ነው። አንደኛው ጥያቄ፤ “ወያኔ እንደገባ በጎሳ ድርጀት ስም ምክር ቤት ገብተሀል” የሚልና ሌላው ”ኦነግ እርሶ ቢሮ ነው የተፈለፈው!” የሚል። ለዚህ መልስ ሰፋ ባለ መልኩ ሰጥቼ ነበር።
በጎሳ ድርጀት ሽግግር ምክር ቤት ገበተሀል ለተባለው፣ “በጎሳ አይደለም! ኦሞቲክ በሚል ድርጀት ስም ነው” ብዬ ኦሞቲክ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስረዳሁ። በዚያ ሳቢያ የጅማው አባጅፋር ከአጼ ምንሊክ ጦር ጋር 30,000 ወታደር ይዞ ከፋ፤ 10,000 ይዞ ወላይታ ዘምቶ እንደነበር፤ ጅማ ቤተ መንግስቱ፤ ሔርማታ የባሪያ መሸጫ ገበያ እንደነበረ፤ በዚህም ምክንያት ከጋሞ ጭምር አባጅፋር ግማሽ ሚሊዮን ባሪያ እንደነገደ፤ ጅማና ወለጋ የባሪያ ንግዱ አካልና አምሳል መሆናቸውን የሚገልጽ ነበር። በባርነት የተሸጡት ደግሞ በጦርነቱ የተሸነፉት ኦሞቲኮች መሆናቸውንም ገልጫለሁ:: በዚያ  ጽሁፍ ምክንያት ሆኖ ዛሬ  Facebook ላይ ከየቦታው የተሰባሰቡ ታዳሚዎች ጅማ፣ሔርማታ ላይ ለነዚህ በአባጅፋር ተፈንግለው ለተሸጡት መታሰቢያ ሐውልትና ቤተ-መዘክር ለማቋቋም በመነጋገር ላይ ናቸው። እኔንም ሊቀመንበር ሁንልን ብለዋል።
ለዚህ በኦሮሞና ዛሬ የኦሮሞ ምድር በሆነው ለተፈጸመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፣ ከነዚህ ለኦሮሞ ነፃነት እንታገላለን ካሉት ውስጥ ትንፍሽ ያለም የለም። ኦሮሞ ሰው ነው! እነዚህ የተነቀሉትና የተፈነገሉትም ሰዎች ነበሩ! የሰውን ዘር ሁሉ የማይጨምር “ነጻነት” የሚል ቃል ያለ አግባብና ያለ ቦታው የዋለ፤ በውስጡ የተደበቀ ሌላ ተልእኮ ያለው  ይመስለኛል!
ሁለተኛው በዚሁ ጥያቄ ሳቢያ ኦነግ የነበረው፤ እኔአነው ለጋሞ ጎፋ ዋና አስተዳዳሪነት ያሾምኩት፤ መኮንን ገላን፣ ደምሴ ደሬሳ ከሚባል የደርግ አባል ጋር ሆኖ፣ ጋሞ ጎፋን ከጋሞ ጎፋ ተወላጆች አጽድቶ በኦሮሞ ሲተካ እንደነበረም ገልጫለሁ። ከዚህም ሌላ ኦነግን፣ እኔንና ትንሽ ወንድሜን ለእስራት፤ ታላቅ ወንድማችንን ወደ ጦር ሜዳ በመላክ፣ ቤታችንን ያለተጠሪና ጧሪ አስቀርቶ እንደነበር ገልጫለሁ። ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ፊት ለፊት እንድንቆራረጥ ያደረገው አብዩ ገለታ፤ ዶክተር ታደሰ ቀነዓ የሚባል ሰው እንዳስፈታ ጠይቆኝ፣ መንግስቱ ጋር ቀርቤ በነበረበት ጊዜ ነበር።
የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ይመስለኛል፣ ዋሽንግተን ዲሲ፣ በኢሳት ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ስደረግ፣ ይህንኑ አንስቼ ነበር። ከዚህም በላይ ለጋዜጠኛው ሲሳይ አጌና፤ ”እባክህን እነዚህ የኦነግ መሪዎች የሚባሉት እዚሁ አሜሪካ ስለሚገኙ ጋብዘህ እኔ ያልኩትን አንዲያምኑ ወይም እንዲያስተባብሉ አድርግም” ብዬ ነበር። የኢብሳ ጉተማ ስልክ ቁጥር ስለነበረኝ፣ ለሲሳይ አጌና የስልክ ቁጥሩንም ሰጠሁኝ። ሲሳይ ደውሎ ለመቅረብ ፈቃደኛ አልሆነም።
ዛሬም የኦነግ መሥራችና መሪዎች ነን የሚሉ፤ አብዩ ገለታ፤ኢብሳ ጉተማ፤ መኮንን ገላንና ሌንጮ ባቲ ከጨለማ ተገን ወጥተው፣ በአደባባይ ቢያስተባብሉኝ ወይም አምነው ቢቀበሉ በብርቱ የምንማማርበት ይመስለኛል።
ዘለፋዎችን በመሠረቱ የቀሰቀሰው መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ የገለጽኩ አልመሰለኝም። ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ አንዣቦ በሚታየው ፖለቲካ ላይ የተለያዩ መጣጥፎች ላለፉት ሶስት ወራት ለማቅረብ እየሞከርኩ ነው።  ሁለት ይቀሩኛል። አንደኛው፤ “የጋራ  ቤታችን! ቅርሳችንና ውርሳችን!” የሚል ሲሆን ሌላው “ዝም ብንል ብናደባ ..” በሚል ርዕስ ይሆናል። “የጋራ ቤታችን…” የሚለው አሁን ቢያንስ በማሕበራዊ ገጾች በተለየም ዲያስፖራ በሚባለው መድረኩን ያጣበበውን፣ በአማራና ኦሮሞ ስም  የተዘጋ ዶሴ (Dead File) ለመክፈት የሚደረገውን መራወጥ ለመዳሰስ ነው።
”ዝም ብንል..” ደግሞ “እንዲያው በዚህ ሁሉ መራኮት ውስጥ የደቡቡ ኢትዮጵያዊው፣ ኢትዮጵያን እንዴት ሲረዳት ኖረ? አሁንስ እንዴት ያያታል?” የሚለውን ለመቃኘት ነው። የጥሬቴ ነገር-ዓለሙ ይህን ካደረኩ፤ በኔ አስተያየት፣ መሐል መንገድ ላይ ያተኮረ፤ ኢትዮጵያን ያማከለ ውይይት ይፈጥራል የሚል እምነትና ተስፋ ነው። “እኔም የድርሻዬን!” ለማለት ነው። ሁላችንም ድርሻ ድርሻ አለንና!
“የጋራ ቤታችንን”  ጨርሼ፣ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አወጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል  Facebook  ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ ባልተነበበ ጽሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማናውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ይሰውረን ነው? አውቀን የካድነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን? ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ፣ በተለይ አንዳንድ የዲያስፖራው ነዋሪዎች፣ መተዳደሪያም ወደ መሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤ አገር አውቆን፣ ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብን  ነው  የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል።
ለማጠቃለል
 እኔ የምለውን የምለው፤ “እገሌ፤ እነ እገሌ እንዳሉት ብዬ መጽሐፍት ጠቅሼ ነው። መጽሐፍ ካልጠቀስኩ ደግሞ እዚያው አገሪቱ፤ ምድሪቱ፤ ኢትዮጵያ ላይ የተነጠፈውን፣ ድፍን አገር የሚያውቀውን፣ ፀሐይ ሲሞቀው የኖረውን ማስረጃ ጠቅሼ ነው። በከፊል ልክ ላልሆን እችላለሁ! ሙሉ ለሙሉም  ልክ ላልሆን እችላለሁ። ያንን ደግሞ እንዲሁ ታሪክም፤ የአይን ምስክርም፤ ምድሪቱን ጠይቆና ጠቅሶ ማስተባባል፤ ማስተማር ነው። ያ ያባት ነው!  ያ ሲሆን  ነው ወደ ኋላ ሳይሆን ወደፊት የምንጓዘው! ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ ሳይሆን፣ አንድ እርምጃ ወደፊት ይሆናል!
ህግ ውስጥ “ያልተካደ/ያልተስተባበለ ሁሉ እንደታመነ ይቆጠራል!” ይላል፡፡ Silence amounts to acceptance  ይህም ወደ ፍትሐ ብሔር ሕግ ሥነ ስርዓት ገብቶ፣ “በክሱ ማመልከቻ ላይ የተነሳውን ጭብጥ እያንዳንዱን በግልጥ እመን ወይም አስተባብል “ይላል።
ይህ ካልሆነ ዳኛው ወይ እንዳልተካደ/እንደታመነ ቆጥሮ ይፈርዳል። ወይም ኪሳራ ቆርጦ እንዲያስተካክል እድል ይሰጣል። ይህን ያነሳሁት እላይ ለጠቀስኳቸው ሳያገለግል አይቀርም በሚል ነው።
ካህኑ እንደሚለው፤ “አውቆ በድፍረት ሳያውቁ በስህተት ከማሳሳት ይሰውረን!”

Read 2216 times