Saturday, 14 January 2017 15:38

“ምን ገጠመኝ አለዎት?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የበዓሉ ሰሞን እንዴት ይዟችኋልሳ!
የሆነ መንፈሳችንን የሚያረካ፣ ከዚህ ዘመን ውጥረት ትንሽ የሚያላቅቀን ነገር እናያለን ብለን ቴሌቪዥን ፊት ‘ተጥደን ብንውል’ ጭራሽ ይባስብን! እኔ የምለው…ፈጠራ ምናምን የሚባለው ቀረ እንዴ! ካቻምናም ያው፣ አምናም ያው፣ ዘንድሮም ያው! ኸረ እባካችሁ… ዓለም ላይ ስንት ጉድ እየተሠራ ነው! አርቲስቶች ደግሞ…በየፕሮግራሙ መታየቱ…አለ አይደል…ነገ ተነገ ወዲያ… “አገሩ ውስጥ ያለእነሱ ሰው የለም እንዴ!” ስለሚያስብልባችሁ… አንዳንዴም “አይመቸኝም፣ ልገኝ አልችልም…” ማለት አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ… ከርሞ፣ ከርሞ አሁን እንደገባኝ…አለ አይደል… በበዓል ዝግጅት ቃለ መጠይቆች ላይ “ስለ ተሞክሮዎ ይንገሩን…” ሲባል ለካስ በተዘዋዋሪ “አስቁን…” ማለት ነውሳ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛም የቃለ መጠየቅ ‘ተራ’ ሊደርሰን ይገባል፡፡ የረሳነውን፣ “እንደው የበላው ጅብ እንኳን አልጮህ አለ…“ እንለው የነበረው ሰው ሁሉ በስክሪን “እዚህ ነኝ... እያለ ነው፡፡ እናማ ይሄ ሁሉ የቲቪ ጣቢያ እያለ ብቅ ብለን “እንዲህ እንመስላለን…” ካላልን እኮ አስቸጋሪ ሊሆን ነው፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ይሄ ሁሉ ሰው ካሜራ ፊት ገጭ ለማለት የሚሯሯጠው ከማህበረሰቡ መዝገብ ‘ዲሊት’ እንዳይደረግ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የእኛ ሰው እኮ “ኢሮ! ብራቮ!” ምናምን ብሎ የሚያጨበጭበውን ያህል…አለ አይደል… ሲረሳ ደግሞ በቃ እስከ ወዲያኛው ረሳ ነው፡፡
ከዛማ ከርሞ ብቅ ሲባል “አለሁ፣ እዚህ ነው ያለሁት…” ምናምን ቢባል፣ በፊት “ኢሮ!” ይል የነበረው… “ይሄ ደግሞ ማነው?” ማለት ይመጣል። የምር ግን…አንዳንድ ሰው ግርም አይላችሁም…እዚህ ጣቢያ ስትከፍቱ እሱ ነው፣ እዚያ ጣቢያ ስትከፍቱ እሱ ነው…እንደውም አዲስ ጣቢያም ሲከፈት የመጀመሪያው ቃለ መጠይቅ የሚደረገው እሱ ሊሆን ይችላል፡፡
እናማ… እኛም ተራ ይድረሰና!
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን በቲቪ የሚቀርቡ እንግዶች እንዴት ሽልል ብለው እንደሚመጡ ነገሬ ብላችሁልኛል!
“ይቺ ልጅ እንዲህ መልከ መልካም ነበረች እንዴ!”
“ለካስ ልብስ ነው ሰው የሚያደርገው፣ የቡቱቶ መስቀያ ይመስል የነበረው ሰውዬ እንዴት እንዳማረበት አያችሁልኝ!”
የምንባባለው  ልክ ነዋ… “ማን በአደባባይ ሰው አፍ ይገባል!”…. ታዲያላችሁ ያንኑ ሰው በማግስቱ ድንገት መንገድ ላይ ብታገኙት፣ የቡርኪና ፋሶ ቺስታ ገበሬ አርጅቶበት የጣለው የሚመስል ኮትና ሱሪ አድርጎ ታገኙታላችሁ፡፡
ስሙኝማ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንድ የምታዝናና የቃለ መጠይቅ መክፈቻ አለች። ጠያቂው…የሰውየውን ስም፣ የሥራ አይነት ምናምን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እንግዳችን በመጀመሪያ ስምዎትንና በምን ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ቢነግሩን…” ይላል፡፡ እኔ ወደፊት ቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ገጭ ብዬ ልክ ይሄን ስጠየቅ የምለውን እያሰብኩበት ነው…
“ስሜ እንደየአስፈላጊነቱ ሊለዋወጥ ስለሚችል፣ ይሄ ነው ብዬ አንድ ስም ለመናገር ያስቸግረኛል…” (የጠያቂዬ ድንጋጤ ይታየኛል፡፡)
“ለምሳሌ ያህል ቢጠቅሱልን…”
“ለምሳሌ ባህሪውን ለማልወደው ሰው ከሆነ ስሜ ሰጥአርጋቸው ይሆናል፣ የሆነች ቆንጆ ከሆነች ደግሞ ስሜ አሌክስ ይባላል…”  የስም ነገር እንዲህ ቢሆን ኖሮ አሪፍ አልነበረም! እነማን ዘንድ ስደርስ ስሜ ወደ ‘ድፋባቸው’ እንደሚለወጥ እኔ ነኝ የማውቀው!
እናማ… እኛም የቃለ መጠይቅ ተራ ይድረሰና!
ደግሞላችሁ …የምጠየቃቸው ጥያቄዎች ላይ አስቀድሜ  ካልተስማማሁ ስቱድዮ አልገባም፡፡ አሀ…ማን ፉል አለና ነው! ‘ስምምነት የተደገረባቸውን’ ጥያቄዎች እናውቃቸዋለና!
“አንድ የገጽ ብዛቱ መቶ ሰማንያ የሆነ ልብወለድ አጠናቀህ ማተሚያ ቤት እንዳስገባህ ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው እንዴ?” አይነት የፕሮሞሽን ጥያቄ እኮ…በወጣቶቹ ቋንቋ ‘ነቄ’ ተብሎባታል፡፡ ልክ እኮ “የሉሲ ባል አጽም ተገኘ የሚባለው እውነት ነው እንዴ?” አይነት ጥያቄ እናስመስለዋለን፡፡
እናላችሁ…በበኩሌ ለምሳሌ “ሎተሪ ቢደርስህ ገንዘቡን ምን ታደርገዋለህ?” የሚል ጥያቄ ብጠየቅ አሪፍ ነው፡ በመጀመሪያ ነገር አይደርስኝም…አራት ነጥብ፡፡ ሁለተኛ ነገር ሚሊዮን የሚለውን ቁጥር የማውቀው ከመሬት እስከ ጸሀይ ባለው የኪሎሜትር ርቀት ላይ ስለሆነ፣ ሚሊዮን ብር ‘ምን እንደሚደረግበት’ ገና አማካሪ መፈለግ አለብኝ፡፡
ልጄ… ይሄን ተናግሮ ማን ሰው አፍ ይገባል!
“በእርግጠኝነት የምነግርህ ሎተሪ ቢደርሰኝ ግማሹን ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች አከፋፍላለሁ…” በዘንድሮ ነገራችን ሰዉ በየቤቱ ይሄን ሲሰማ ያጨበጭብልኛል ብሎ የሚያስብ የእኔ ቢጤ ሞኝ ምክር ያስፈልገዋል፡፡
እናማ ገና ሳልጠየቅ ‘መልሶቼን ጨርሼ’ ነው የምገባው፡፡
“የመካከለኛው ምስራቅን ሁኔታ እንዴት ነው የሚያዩት?”
“ማለት…”
“ማለት የሶሪያን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?”  
‘ይቺን ይወዳል!’ አለ የጉኑ አባት፡፡ ለእኔ ሲሉ ከፈለጉ ለምን እስከ ሦስት ሺህ ዓመት ሲጠዛጠዙ አይኖሩም! ጦርነቱን እኔ አልጀመርኩት!
“እ ምን መሰለህ…ይሄ ነገር ሊፈታ የሚችለው በጠረጴዛ ዙሪያ ብቻ ነው…”
ሳልጠየቅ መልሴን ጨርሼ ነዋ የምገባው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሀሳብ አለን፡፡ በሬድዮ ቃለ መጠይቅ ሲደረግልን ስለ ሁኔታችን መግለጫ ይሰጥልንማ…
“እንግዳችን አለባበሳቸው እንደነገሩ ሆኖ፣ ጉንጫቸው ላይ ትኩስ ሰንበር ይታየኛል፡፡ ምናልባትም ጠዋት ከቤት ሲወጡ ሚስታቸው ያጮሏቸው ሊሆን ይችላል…” ይባልልን፡፡  ወይም ደግሞ…
“የዛሬው እንግዳችን ዓይኖች የአብዮት አደባባይን የትራፊክ ቀይ መብራት ይመስላሉ። ከቤታቸው ከአልጋ ወርደው ይምጡ፣ ከባንኮኒ ባለጌ ወንበር ላይ ወርደው ይምጡ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም…” ይባልልንማ!
ልክ ነዋ… “የሚያስቅ ገጠመኝ አለዎት…” ምናምን ከሚለው ‘የጥያቄዎች ጆከር’ ይልቅ ይሄ መግለጫ ይሻላል፡፡
“እንግዳችን ስለ አዲስ አበባ መዘመን ምን የሚሉት ነገር አለ?”
“እንግዲህ ምን መሰለህ…በአዲስ አበባ እድገት ዓለም ሁሉ እየተደነቀ ነው፡፡ እኔ እነኚህን ሁሉ ህንጻዎች ሳይ ቺካጎ ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ ደግሞ ቀላል ባቡሩን ሳይ አዲስ አበባ ኒው ዮርክን ትመስለኛለች…”  
ልጄ… “አይደለም ኒው ዮርክን፣ ኒው ዮርክ ካፌን አይተኸው ታውቃለህ?” ብሎ የሚያፋጥጥ አይኖርማ!
እግረ መንገዴን…እኔ የምለው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ህንጻ ሲሠራ፣ “አዳሜ ከሳጥን ቅርጽ ውጪ እሠራለሁ ብትዪ ወዮልሽ!” ምናን የሚባል ነገር አለ እንዴ! እኔን ኒው ዮርክ ያድርገኝ!
ለምን ይዋሻል ----- የብዙ ‘ቦሶች’ ቃለ መጠይቅ ምናምን ብዙም አይመቸንም፡፡ አሀ…ሳይመቸንስ! እንደውም ስናያቸው ሆድ ይብሰናል። ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ ቁም ነገሩን ከመናገር ይልቅ “እ…” እያሉ በሆነ ነገር ‘ቦስነታቸውን’ ሊያሳውቁን የሚፈልጉ ይመስላሉዋ!
“እንደሚያውቁት…አዲስ አበባ አሁን ፓሪስና ኒውዮርክን እየመሰለች ነው…”
ቂ…ቂ…ቂ… እኔ የምለው… የለመድናቸው አይነት የእርስ በእርስ ቀልዶች ሲከረቸምባቸው ጊዜ እንዲህም መቀለድ ተጀመረ እንዴ! ‘እኔን ፓሪስ ያድርገኝ’ የሚል ግጥም ከእለታት አንድ ቀን የሚጻፍ ይመስለኛል፡፡
እኔ የምለው…ጥያቄ አለን፣ ገጠመኝ ከሌለን ቃለ መጠይቅ ላንቀርብ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… “ምን ገጠመኝ አለዎት?” በሚባለው ጥያቄ ላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ይዘጋጅልንማ! አሀ…ሁልጊዜ ከሌሎች መቅዳት እንዳይሆንብን፣ አንዳንዴ እነ ቢቢሲም ከእኛ ‘ተሞክሮ’ ይማሩዋ!
መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!




Read 5188 times