Saturday, 14 January 2017 15:32

‹‹ዓመቱ ለኢትዮጵያውያን የጭከና እና የአፈና ነበር›› - ሂዩማን ራይትስ ዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

ባለፈው ዓመት በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ በዜጎች ላይ እየተደረገ የቆየው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች እመቃ መቀጠሉን ያስታወቀው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት የህዝቦችን መብት ማክበርና ማስከበር እንዳለበት፣ አሳሰበ፡፡ ኢትዮጵያ ያለፈውን የፈረንጆች ዓመት በከባድ መከራና የመብት ክልከላዎች ማሳለፏን የጠቆመው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የጅምላ እስርና የማህበራዊ ሚዲያዎች ክልከላ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በሃገሪቱ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉንና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ለእስር መዳረጋቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በእስር ላይ ቆይተው የተፈቱ አብዛኞቹ ዜጎች  ግርፋት እንደደረሰባቸው መናገራቸውን ገልጿል፡፡
የእስረኞች ኢ-ሠብአዊ አያያዝን በተመለከተ መንግስት ትርጉም ባለው መልኩ ምርመራ አካሂዶ የእርምት እርምጃ አለመውሰዱንና የውጭ መርማሪዎች ወደ ሃገሪቱ ገብተው ምርመራ እንዳይካሄድ መከልከሉን ሪፖርት አስታውቋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ መንግስት አላስፈላጊና ከመጠን በላይ ሃይል በመጠቀም፣ ተቃውሞውን ለማስቆም ሞክሯል›› ያሉት የተቋሙ የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪ ፍሌክስ ሆርን፤ ‹‹መንግስት መሰረታዊ የዜጎች መብቶችን ማስከበርና ለሚቀርብበት ትችት አሉታዊ መልስ ከመስጠት ይልቅ ትርጉም ያለው ውይይት ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር ማድረግ ይገባዋል” ብለዋል፡፡ መንግስት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመገደብ ይልቅ ሙሉ ነፃነት ሰጥቶ ዜጎች ያላቸውን ቅሬታ በየመድረኮቹ እንዲገልፁ ዕድል መስጠት እንደሚገባው ያስገነዘበው የተቋሙ ሪፖርት፤ ተቃውሞን መነሻ በማድረግ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎችና ሙዚቀኞች እንዲሁም መምህራንና  የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸውን ገልጿል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በሀገሪቱ የተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና  ነፃ ሚዲያዎችን መንግስት በስልት እንዲያቀጭጭና እንዲዘጋ እድል የሰጠ ሆኗል ያለው ሪፖርቱ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ በመዘጋቱ የተቃውሞ ድምፆች መሰማት የማይችሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል ብሏል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ የህዝቡን ተቃውሞ ተከትሎ ራሱን በጥልቀት በማደስ ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እየጣረ መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለፀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ለፓርላማው ባቀረቡት ማብራሪያ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱን ወደ ቀድሞ መረጋጋትና ሰላም በመመለስ ረገድ የተሳካ ውጤት ማምጣቱን አስታውቀዋል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ለእስር የተዳረጉ ዜጎች ስልጠና እየተሰጣቸው በመፈታት ላይ መሆናቸውን በመግለፅም የሰብአዊ መብት ጥሰት አለማጋጠሙንም አስታውቀዋል፡፡
መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስም ከህዝቡ ጋር ተከታታይ ውይይት እንደሚያደርግና ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የዚሁ ውይይት አካል እንደሚሆኑ  የተገለፀ ሲሆን መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን የበለጠ ለማስፋትና የምርጫ ስርአቱን ለማሻሻል ቃል መግባቱም ይታወሳል፡፡

Read 4372 times