Saturday, 14 January 2017 15:30

‹‹ሰማያዊ››፤ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ደረሰብኝ ባለው ጫና ዙሪያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ተወያየ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(9 votes)

ሰማያዊ ፓርቲ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በመንግስት ተደርጎብኛል ባለው ጫና ዙሪያ፣ ከአውሮፓ ህብረት ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን፣ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ገለፁ፡፡ የአውሮፓ ህብረት ኃላፊዎች፤ ፓርቲው ደረሰብኝ ባለው ጫናና ባነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ጋር ለመወያየትና ጥያቄዎችን ለማቅረብ ቃል መግባታቸውን አቶ አበበ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከአውሮፓ ህብረት በተደረገላቸው የውይይት ግብዣ፣ በህብረቱ የፖለቲካ የፕሬስና የኢንፎርሜሽን ኃላፊ ከሆኑት ሚስተር ሳንዲ ዌድ እና ከባልደረቦቻቸው ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን አቶ አበበ ገልፀው፤  ህብረቱ ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ሐላፊ ጋር ለመገናኘት ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም፤ እርሳቸው ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ታስረው የተሐድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ ስለነበሩ መገናኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከእስርና ከስልጠናው በቅርቡ ከወጡ በኋላ በተደረገላቸው ግብዣ፣ በተወያዩበት ወቅት በፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነ፤ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በፍቅሩ ማሩ መዝገብ ተከሰው ከታሰሩት 38 እስረኞች አንዱ፣ አግባው ሰጠኝ፤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል በመሆኑ ጥፋቱን በማረሚያ ቤት በግድ እንዲያምን መደረጉን ለፍ/ቤት ቢያስረዳም ባለመለቀቁ፤ ከዚያም አልፎ በቤተሰብና በወዳጅ ዘመድ እንዳይጠየቅ መከልከሉ ፓርቲውን እንዳሳሰበው ለኃላፊዎቹ መግለፃቸውን አብራርተዋል፡፡
ከፓርቲው ደጋፊዎች መካከል ኤልያስ ገብሩ፣ አናንያ ሶሪ፣ ዳንኤል ሺበሺና ሌሎችም እስረኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡም ሆነ ወደ ተሀድሶ ስልጠና ሳይወሰዱ በማረሚያ ቤት እየተሰቃዩ እንዳሉና ፓርቲው የእነዚህን እስረኞች ጉዳይ ለመከታተል መቸገሩን ለኅብረቱ አስታውቀናል፤ ያሉት የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፤ መንግስት፡- የምርጫ ህጉን አሻሽላለሁ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እወያያለሁ፤ ቢልም ለውይይት የተመረጡትን ሽማግሌዎች ገፍቶ ድርድሩን ማቆሙንና፣ ይህም የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የኋሊት እንደሚመልሰው ማስረዳታቸውን አቶ አበበ ገልፀዋል፡፡
በተለይ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ፓርቲው፡- የመሰብሰብ፣ የመወያየት፣ መፅሄት የማተምና መሰል እንቅስቃሴዎችን እንዳያከናውን መከልከሉን ለሀላፊዎቹ መናገራቸውን አውስተው፤ መንግስት ተቃዋሚዎችን፣ ‹‹ደካሞች ናቸው›› እያለ ከመውቀስ ይልቅ ትንሽም ቢሆን እድል እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን አቶ አበበ አክለው ተናግረዋል። በውይይቱ መጨረሻም፣ የህብረቱ ሀላፊዎች፣ ፓርቲው ደረሰብኝ ያለውን ጫናም ሆነ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ይዘው በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰፊ ውይይት እንደሚያደርጉ ቃል እንደገቡላቸው የፓርቲው ሓላፊ አስታውቀዋል፡፡

Read 4036 times