Saturday, 14 January 2017 15:29

የሃይማኖት አባቶች በሀገሪቱ እርቀ ሰላም ለማውረድ እንደሚተጉ ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ የተፈጠሩ  የህዝብ መቃቃሮች እንዲሽሩ የሃይማኖት አባቶች በእርቀ ሰላም ሥራ ላይ እንደሚተጉ ሲሆን  መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም እናሳስባለን ብለዋል፡
ባለፈው ሳምንት ለሁለት ቀናት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ በተደረገው “ሀገር አቀፍ እርቅና የሰላም የምክክር መድረክ” ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የሃይማኖት አባቶች ወደየመጡበት ሲመለሱ ዋነኛ ተግባራቸው የእርቅ ስራ ይሆናል ተብሏል፡፡
“የእርቁ ዋና አላማ ጥላቻ እየጎለበተ እንዳይሄድና ከወዲሁ እንዲደርቅ ማድረግ ነው” ያሉት መጋቢ ዘሪሁን፤ መሰል ችግሮችን በሃይማኖታዊ መንገድ ማስታረቅ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች መለየታቸውንና እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ችግሮች ከአካባቢው የመንግስት አስተዳደሮች ጋር እንደሚወያዩ የሃይማኖት አባቶቹ ገልፀዋል፡፡
ተመሳሳይ ችግሮች ዳግም እንዳይፈጠሩ ለማድረግ መንግስት የሚሰጠው መፍትሄ ወሳኝ መሆኑን ያስረዱት መጋቢ ዘሪሁን፤ በፌደራል ደረጃም ያሉ የሃይማኖት አባቶች ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እየተወያዩ፤ የህዝብ ጥያቄዎች ለመንግስት በአግባቡ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ በክልል ደረጃም ተመሳሳይ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ለተፈጠሩት ግጭቶች በዋናነት በተለያየ መልኩ የሚገለፁ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የፍትህ መጓደል፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር እና የሙስና መስፋፋት ዋነኛ መንስኤ ሆነው መለየታቸውን መጋቢ ዘሪሁን ደጉ አስታውቀዋል፡፡
ህገ መንግስቱና የመንግስት ፖሊሲ በአግባቡ አለመተግበሩም በግጭቱ መንስኤነት የተጠቀሰ ሲሆን በአንድነት ላይ ሳይሆን በልዩነት ላይ ያተኮሩ የታሪክ ሰነዶች መበራከትና ይህም በማህበራዊ ሚዲያዎች መስተጋባቱ ለግጭቶች መባባስ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው በጉባኤው ተጠቅሷል፡፡ ለረጅም ጊዜ በተከማቹ ቅሬታዎችና ብሶቶች የተነሳ ግጭቶች ሲከሰቱ፣ ሁሉንም ያሳተፈ ፍትሃዊና ፈጣን ምላሽ ያለመሰጠቱ፤ የሀሳብና የአመለካከት ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ገንቢ የውይይት ባህል አለመዳበሩና ይህን ለማዳበር የሚያስችሉ መድረኮች አለመፈጠራቸው ለቀውሱ መባባስ በዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
መንግስት የግጭት አፈታት እንዲሁም፣ የውይይትና የመደማመጥ ስርአትን እንዲያጎለብት ጉባኤተኞቹ የተጠየቀ ሲሆን በክልሎች መካከል ለግጭቶች መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች በስፋት እንዲፈተሹም አሳስበዋል፡፡

Read 3914 times