Saturday, 14 January 2017 15:28

የነፋስ ኃይል አምራች ኩባንያው ሥራ ከጀመረ ከ2 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ ጨረታ እንዲገባ መጠየቁ እንዳሳዘነው ገለጸ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(6 votes)

‹አገራችንን ለማሳደግ የምናደርገው ጥረት አለአግባብ ሊደናቀፍ አይገባም››

በደብረ ብርሃን፣ 100 ሜጋ ዋት የነፋስ ኃይል ለማምረት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ የቆየው ‹‹ቴራ ግሎባል ኢነርጂ ዴቨሎፐርስ›› ኩባንያ፤ አዲስ በወጣ መመሪያ መሰረት ጨረታ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እንዲገባ መጠየቁ አግባብ አለመሆኑን ገለፀ፡፡
የኩባንያው ባለቤት ኢ/ር በኃይሉ አሰፋ ከትናንት በስቲያ በደብረ ብርሃን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለ6 ወራት ጥናት አካሂደው፣ የጥናታቸውን ውጤት ለኢትዮጵያ መብራት ኃይል አቅርበው፣ 400 ሜጋ ለማድረስ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ በወጣ መመሪያ፤ “እናንተም እንደ ሌሎች ጨረታ ግቡ” በመባላቸው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ስራ ለማቆም መገደዳቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ እየሰራን ነው ያሉት ኢንጀነሩ፤ “እኛ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካ አሜሪካዊ የነፋስ ኃይል አልሚ ስንሆን ዓላማችንም ኢትዮጵያን ማሳደግ ነው፤ ዜጎቿ ስለሆንን ለኢትዮጵያ መፍትሄ የምንሆነው እኛ እንጂ የሌላ አገር ዜጋ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገሮች ፕሮጀክቶች ሲሰሩ ለቀን ስራ የሚቀጠሩት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሆኑ ጠቁመው፤ “እዚህ ግን በቀን ስራ ላይ ከውጭ አገራት የመጡ ዜጎች ሲሳተፉ ይታያል፡፡ እኛ ስራውን ብንቀጥል ከ750 እስከ 1000 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል እንፈጥር ነበር” ብለዋል፡፡
ጥናታቸውን አቅርበው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከተነገራቸው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ከቻይና የንግድ ባንክ 220 ሚ. ብር ብድር ማግኘታቸውን፣ ተርባይኑን ደግሞ “ጎስድ ዊን” ከተባለ ኩባንያ እንደገዙ ጠቁመው፣ በውጭ ምንዛሪ ልዩነት የተነሳ 800 ሚ. ብር ኪሳራ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ስታቅድ፣ ወዲያውኑ ተግባራዊ ካላደረገች ለትልቅ ወጪ ትዳረጋለች ብለዋል፡፡
አሜሪካ ውስጥ ‹‹ሲልከን ቫሊ›› በተባለ የኮምፒዩተር ማዕከል እንደሚሰሩ የጠቀሱት ኢ/ር በኃይሉ፤ እሳቸውና አብረዋቸው የመጡት፣ ትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ ኢንጂነሮች፣ እዚያ ያካበቱትን ልምድ በአገራቸው ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ማለማቸውን ይገልፃሉ፡፡ “ዲያስፖራ ስለሆንን ሌሎችም ዳያስፖራዎች ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሰሩ ለመሳብ ነገሮችን ቀላል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ የውጭ የነፋስ ኃይል አልሚ ኩባንያ፣ ሀረር አይሻ ውስጥ ኃይል ለማልማት ከ6 ሳምንታት በፊት ሲዋዋል ጨረታ ግባ ሳይባል ነው የተፈቀደለት፡፡ እኛ ሁለት ዓመት ከሰራን በኋላ ጨረታ ግቡ በመባላችን ቅሬታ ተሰምቶናል፡፡ አሁንም ቢሆን በጨረታው አንሳተፍም ብለን ቀደም ሲል ወደ ጀመርነው ስራ ለመግባት ውሳኔያቸውን እየተጠባበቅን ነው” ብለዋል ኢንጂነሩ፡፡  “እኛ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንሰጣለን፤ ለዜጎች የስራ ዕድል እንፈጥራለን፡፡ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ስንሰራ እጃችንን ስመው ነው የሚቀበሉን” ያሉት ኢንጀነር በሃይሉ፤ ‹‹እዚህ አገራችን እንስራ፤ እንለውጣት፣ ሌሎች የሰለጠኑ አገራት ወደደረሱበት እንድትደርስ እርሾ እንጣል ስንል ለምን ችግር እንደሚገጥመን አይገባኝም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

Read 2787 times