Saturday, 14 January 2017 15:24

ጌታዋን የተማመነች በግ፤ ላቷን ውጪ ታሳድራለች

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊቶች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው አውጫጪኝ ያደርጋሉ፡፡ የጫካው ንጉስ አያ አንበሦ ናቸው ሰብሳቢው፡፡
የስብሰባውን አላማ እንዲህ ሲሉ ገለፁ፡-
“የስብሰባችን አላማ በየጊዜው በአደን የመጣ ንብረት ይጠፋል፡፡ ዋሻ፣ ቁጥቋጦ፣ ዛፍና የመሳሰሉት ማደሪያና መኖሪያዎቻችን የአንዱን አንዱ

እየወሰደ፣ ጉልበተኛው ደካማውን እየቀማ ስላስቸገረ፤ እነዚህን ለማስተካከል ነው” አሉና “የተወሰደ ንብረት በሙሉ ለባለቤቶቹ ይመለሳል”

ሲሉ ደመደሙ።
በዚህ መካከል ጦጢት እጇን አውጥታ፤ “እኔ ከጫካው ውስጥ ማደሪያዬ የሆነው ዛፍ ጠፍቶብኛልና ሊመለስልኝ ይገባል” አለች፡፡
ይሄኔ ዝንጀሮ እጁን አወጣና፤
“እኔ ጦጢትን እቃወማለሁ፡፡ ተቃውሞዬም ጦጢት በየጊዜው ከአንድ ዛፍ አንድ ዛፍ ስለምትዘል የተወሰነ ዛፍ የላትም” አለ፡፡
ጦጢት መልሳ ዝንጀሮን ተቃወመች፤
“አያ አንበሶ፣ የእኔ ዛፍ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅርንጫፎቹን ማር ቀብቻቸዋለሁ፡፡”
አያ ነብሮ እዚህ ላይ ጣልቃ ገባና፤
“ጦጢት ማሩን ከየት እንዳመጣች እንድትጠየቅልኝ እፈልጋለሁ!” አለ፡፡
ጦጢትም፤
“እጫካ ውስጥ የተሰቀለ ቀፎ አግኝቼ፤ ከዚያ ቆርጬ ነው!” አለች፡፡
ጦጢት ይሄን እያስረዳች ሳለች እነ ቀበሮ፣ እነ ተኩላ፣ እነ ዝንጀሮ የጦጢትን ማር ሊልሱ፣ ከምኔው ሄዱ ሳይባል ወደ ዛፉ ሄደዋል፡፡
ይሄኔ ጦጢት፤
“በቃ በቃ ዛፉ የት እንዳለ አውቄያለሁ” አለች፡፡
“እንዴት አወቅሽ?” አለ አያ አንበሶ፤ ለምን በስብሰባችን ትቀልጃለሽ በሚል የቁጣ ስሜት፡፡
“አያ አንበሶ፤ እነ ዝንጀሮ ወዴት እንደሄዱ ይጣራልኝ፡፡ አሁን እዚህ የነበሩት የት ተወሰሩ?”
ዕውነትም አያ አንበሶና አያ ነብሮ ዞር ብለው ቢያዩ፤ እነ ዝንጀሮ የሉም፡፡ ስለዚህ ነብር ወደ ጫካ ተላከ፡፡ ጦጢት ተከትላ ካልሄድኩ አለችና

አስቸገረች፡፡
አያ አንበሶ፤
“ያንቺን ጉዳይ እያጣራን አንቺ ወዴት ትሄጃለሽ?” አላት፡፡
ጦጢትም፤
“በእነ ዝንጀሮ ጅልነት ልስቅባቸው ነው የምሄደው”
“እንዴት?”
‹‹እኔ የዛፉን ቅርንጫፎች ምንም ማር አልቀባሁም፡፡ እነሱም ግን ዛፉን ስለሚያውቁት ወደዚያው ሂደዋል፡፡ ማሩ የለም! አሁን ማ ሌባ እንደሆነ

አወቅን … አያ አንበሶ!” አለች እየሳቀች፡፡
*   *   *
ማር መላስ የማይፈልግ የለም፡፡ ያም ሆኖ ግን አንዱ አንዱን እየጠለፈ፣ አንዱ የአንዱን እየዘረፈ ወይም ከመንግስት እየመዘበረ፣ የሚኖርበትን

ሥርዓት ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ እጅግ የተወሳሰበና የተቆላለፈው የሙስና መረብ፣ በተለይ ከፖለቲካው ጋር ሲተበተብ ለያዥ ለገራዥ

ማስቸገሩን እያየነው ነው!! የሙስናን አሻጥር ለመረዳት በተለይ ዛሬ ዓይንን ማሸት አይፈልግም፡፡ ምን ያህል የሀገርና የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅም

እየዋለ መሆኑን፣ የተጠረጠሩ የሙስና ባለ እጆችን ማስተዋል ብቻ በቂ ነው፡፡ ሆን ተብሎም ሆነ ለጥንቃቄ ተብሎ አሊያም በስህተት የሙስና

ክስ ዘግይቷል ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ አሁንም መፍጠን አለበት፡፡ የሙስና ዘዴው በአብዛኛው የሚታወቅ ነው፡፡ በዘመኑ ቋንቋ የተበላ ዕቁብ

ነው
‹‹እኔም ሌባ፣ አንተም ሌባ
ምን ያጣላናል፤ በሰው ገለባ!››
የሚባልበት ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ጊዜ ነው፡፡ አለቃና ምንዝር ሳንለይ የሚሠርቁ እጆች መያዝ አለባቸው፡፡ ቁጥጥሩ መጥበቅ አለበት፡፡ ፎቆቹ

በአደባባይ ይናገራሉ፡፡ ቤቶቹ በይፋ ያሳብቃሉ፡፡ መሬቶቹ ሊያሸሿቸው የማይችሉ የምዝበራው አካል ናቸው፡፡ ከየት እንደመጣ ማብራሪያ

የማይሰጥበት ሀብት የፊት ለፊት ማስረጃ ነው!! ለባንክ ዕዳ መክፈያ ለሀራጅ የሚቀርቡት ንብረቶች፣ በማያወላውል መልክ በመሞዳሞድ የታጀሉ

ብዝበዛዎችን ያጋልጣሉ!!
‹‹አንድ አንኳር ጨው ውቂያኖስን አያሰማ›› የሚለውን ተረት በጥሞና እያስተዋልን፣ እርምጃው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ዘምቶ የሚቆም መሆን

እንደሌለበት መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ፤ አንድም ሙስናው ውቂያኖስ አከል በመሆኑ፣ አንድም ሙስና የቀጣይነት ባህሪው

ሥር-ሰደድ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ የሙስና ሂደት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የመንግሥት አባላት፣ የፓርቲ አባላት፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና ዐይን

ያወጡ ኤጀንሲዎች ወዘተ … የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝሙ ፓኮ ውስጥ ያሉ ናቸው። እንዲህ በአገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ምዝበራን እንዲያጥጥና

እንዲናኝ የሆነው መዝባሪዎቹ ማንን ተማምነው ነው? የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ የአባት ነው፡፡ ምነው ቢሉ፤ ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን

ውጪ ታሳድራለች›› የሚለው ተረት ፊታችን ድቅን ይላልና! አሁንም ውስጣችንን እንመርምር፡፡ ጥልቅ ተሐድሶ የዕውነት ጥልቅ መሆኑን

በተግባር እናረጋግጥ! ልባዊ እንጂ አፍአዊ አለመሆኑን እናጣራ!
‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህንም›› አስብ! ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ፣ አጥሩን አይነቀንቁን›› አንርሳ!
“ያሳር እሳት የሚጫረው”
ጥንትም በእፍኝ ጭራሮ ነው!
የሚለውን በመሰረቱ እንገንዘብ፡፡
በሼክስፒር ብዕርና በፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት፤
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፣
ተው ነው መጀነኑ በቅቶን፤
ጉራ መንዛት መዘባነን፣
የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!”
የሚለውን በጭራሽ አንዘንጋ፡፡
መልካም የጥምቀት በዓል
ክርስትና ዕምነት ተከታዮች!!

Read 6076 times Last modified on Saturday, 14 January 2017 15:28