Monday, 09 January 2017 00:00

በሙስና የተከሰሱት የህንዱ ሚኒስትር በ74 ሚ. ዶላር ልጃቸውን ዳሩ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በወርቅ በተለበጠ የሰርግ ካርድ፣ 50 ሺህ ሰዎች ተጠርተዋል
      በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህንዳውያን በገንዘብ እጥረት ቀውስ በሚሰቃዩበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ የቀድሞው የህንድ ሚኒስትር ዲኤታ ጋሊ ጃናርዳና ሬዲ፤ 74 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ድል ባለ ድግስ ልጃቸውን መዳራቸው፣በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ሴት ልጃቸውን የዳሩበት ይህ ሰርግ፣ በአገረ ህንድ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከተደረገባቸው የቅንጦት ሰርጎች አንዱ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የሰርጉ መጥሪያ ካርድ በወርቅ የተለበጠ፣ ለሰርጉ የተጋበዙ እንግዶች ቁጥርም 50 ሺህ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የቅንጦት ሰርጉ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ፣ የአካባቢው የግብርና መስሪያ ቤት ባለስልጣናት የግለሰቡን የንግድ ድርጅቶች መዝጋታቸውንና ስለ ሰርጉ ወጪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ ሰውዬው ለባለስልጣናቱ በሰጡት ምላሽ፣ በሲንጋፖርና በሌሎች አካባቢዎች ከሚያከናውኑት የቢዝነስ ስራ ባገኙት ገንዘብ፣ የሰርጉን ወጪ መሸፈናቸውንና ለመንግስትም ተገቢውን ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን እንደገለጹ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ሚኒስትሩ በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ለሶስት አመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ፣ ባለፈው አመት በዋስ መፈታታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእስር ከወጡ በኋላም”ክዛር” የተባለውን የማዕድን አውጭ ኩባንያ ማስተዳደር መቀጠላቸውን ጠቁሞ፣ በርካታ ህንጻዎችና ሌሎች የንግድ ኩባንያዎችመም እንዳሏቸው አስታውቋል፡፡

Read 1809 times