Print this page
Monday, 09 January 2017 00:00

ትንሹ ልጅ፤ የገና ዕለት

Written by  ደራሲ - ፊዮዶር ዶስቶቭይስኪ ትርጉም፡- መክብብ አበበ
Rate this item
(12 votes)

በአንድ ትልቅ ከተማ በሚቆነጥጠው የገና ዋዜማ ምሽት ቅዝቃዜ ስድስት ዓመት የሚሆነው፣ ምናልባትም ዕድሜው ከዛ የሚያንስና ለልመና ወደ ጎዳና ለመላክ ህፃን ሊባል የሚችል፤ ነገር ግን ዕጣ ፈንታው ይሄ ከሆነ በርግጠኝነት ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ የሚላክ ትንሽ ልጅ አየሁ፡፡
ሕጻኑ አንድ ጠዋት በቆሻሻና ጤዛ በሸፈነው መጋዘን ውስጥ በቆሸሸ የቤት ልብስ ተጠቅልሎ፣ በብርድ እየተንቀጠቀጠ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ በሁለቱ ከንፈሮቹ መካከል ሾልኮ የሚወጣው ትንፋሹ እንፋሎት ይተፋል፡፡ በግንድ ጉማጅ ላይ ተቀምጦ፣ ትንፋሹ ከአፉ ሲወጣ እያየ በመደነቅ ጊዜ ለማሳለፍ ሞክሯል፤ ነገር ግን በጣም ርቦታል፡፡ እንደ ወረቀት የሳሳ፣ የነተበ ብርድ ልብስ ደርባና ጭንቅላቷን ቡትቶ ጨርቅ አንተርሳ ወደተኛችው እናቱ፣ ከጠዋት ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተመላልሷል፡፡
እንዴት ወደዚህ ልትመጣ ቻለች? ምናልባት ሩቅ ከሆነ ከተማ ይሆናል የመጣችው፡፡ የዚህ የተጎሳቆለ ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት ባለቤት የሆነችው ሴት፣ ከሁለት ቀናት በፊት ተይዛ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳለች፡፡ ዛሬ ዓመት በዓል ነው፡፡ ሌሎች ተከራይ ጭሰኞች ወጥተው ሄደዋል፤ ከነዚህ ጭሰኞች መካከል አንደኛው ዓመት በዓልን ሳይጠብቅ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ አልጋ ላይ ከተዘረረ ሃያ አራት ሰዓት አልፎታል። አንደኛው ጥግ ላይ ሪህ ይዟት የተኛችው የሰማንያ ዓመት አሮጊት የምታቀርበው ቅሬታ ይሰማል፡፡ ይቺ አሮጊት ቀደም ሲል የሆነ ቦታ የህፃናት ሞግዚት የነበረች ቢሆንም አሁን ግን ብቻዋን ቀርታ እየሞተች ነው፡፡ ልጁ፤ ጉሮሮዋ ላይ ሞት እያፏጨ በእሱ ላይ ወደምታማርረው፣ ወደምትጮኸውና ወደምትቆጣው አሮጊት ለመጠጋት ፈርቷል፡፡ በአዳራሹ መተላለፊያ ላይ የሆነ የሚጠጣ ነገር አገኘ፣ በቁራሽ ዳቦው ላይ ግን እጁን ለማሳረፍ በፍርሃት አመነታ፡፡ አሁን እናቱን ለመቀስቀስ ሲመጣ አስረኛ ጊዜው ነበር፡፡ በመጨረሻም በጨለማ ለመውጣት ፈራ፡፡
ከጨለመ ቆይቷል፣ እሳት ለማያያዝ ማንም አልመጣም፡፡ የእናቱን ፊት በዳበሳ አገኘው፤ መንቀሳቀስ ባለመቻሏና እንደ ግድግዳው ቀዝቅዛ ስላገኛት ተገርሟል፡፡
“በጣም ቀዝቅዟል!” ሲል አሰበ፡፡
ለተወሰነ ሰዓት እጆቹን በእናቱ በድን ትከሻ ላይ አሳርፎ ሳይንቀሳቀስ ቆየ፡፡ ከዚያም በጣቶቹ ላይ ተነፈሰ፡፡ ትንሹን ኮፍያውን አልጋው ላይ አገኘው። ቀስ ብሎ እየዳሰሰ በሩን ፈልጎ አገኘና ምድር ቤት ከሚገኘው ጊዜያዊ ማረፊያ ቤት ውስጥ ወጣ፡፡ ጎረቤታቸው በር ላይ ቀኑን ሙሉ ሲጮህ የዋለውን ትልቅ ውሻ ባይፈራ ኖሮ ቀደም ብሎ ይወጣ ነበር፡፡
ኦ! ምን አይነት ከተማ ነው! ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ነገር ፍጹም አይቶ አያውቅም፡፡ እሱ ከመጣበት ሩቅ ቦታ ምሽቶቹ ጨለማ ናቸው። በአጠቃላይ ለአንድ መንገድ አንድ የመንገድ መብራት ብቻ ነው ያለው፤ ትንንሽና ዝቅተኛ የሆኑ የእንጨት ቤቶች ብቻ ነበሩባቸው፡፡ ከጨለመ በኋላ ማንም ሰው መንገድ ላይ አይታይም፡፡ ሁሉም ሰው ቤቱን ዘግቶ ይቀመጣል፡፡ መቶ፣ አንዳንዴም ሺ የሚደርሱ የተሰበሰቡ ውሾች ብቻ ሌሊቱን ሙሉ ሲጮሁና ሲያላዝኑ ይሰማል፡፡ ነገር ግን እዚያ ይሞቃል፡፡ የሆነ የሚበላ ነገርም ያገኝ ነበር፡፡ እህ! እዚህም አንድ የሚበላ ነገር ቢያገኝ እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ የምን ድምጽ ነው! የምን ጩኸት ነው! ምን ዓይነት ከፍተኛ ብርሃን ነው! የምን የሰዎች ስብስብ ነው! የምን ፈረሶች ናቸው! የምን ሰረገላዎች ናቸው! በዚያ ላይ ብርዱ!
ከደከሙት የፈረሶቹ ሰውነቶች ላይ ጭስ ይወጣል፣ የሚነደው አፍንጫቸውም ነጭ ደመና ይተፋ ነበር፣ ጫማዎቻቸው በእግረኞች መንገድ በፈሰሰው ስስ በረዶ ላይ ይንቀጫቀጫል፡፡ ሁሉም ሰው፣ ሌላው ሰው በሙሉ እንዴት ይረሳል፡፡ “እህ! ትንሽ የሚበላ ነገር ባገኝ እንዴት ደስ ባለኝ፡፡ ለዚህ ነው ጣቶቼን በጣም ያመመኝ!”
አንድ ፖሊስ በአጠገቡ አለፈ፣ ልክ ህፃኑን ላለማየት የፈለገ ይመስል፣ ጭንቅላቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዞረ፡፡
‹‹ይሄ ሌላ መንገድ ነው ..እህ! ምን አይነት ሰፊ መንገድ ነው፤ እዚህ ላይ ብውድቅ እንደምሞት አውቃለሁ፡፡ ሁሉም እንዴት ነው የሚጮኹት፣ እንዴት ነው የሚሮጡት፣ እንዴት ነው የሚያሽከረክሩት፡፡ እናም መብራቱ፣ አዎ መብራቱ! ያ ነገር ደግሞ ምንድ ነው? እንዴት አይነት ትልቅ መስታወት ያለው መስኮት ነው! ከመስኮቱ ጀርባ ደግሞ ክፍል አለ፤ ክፍል ውስጥ ደግሞ ኮርኒሱ ላይ የሚደርስ የገና ዛፍ አለ፡፡ እናም ከዛፉ ስር ያሉት መብራቶችስ ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት የወርቅ ወረቀቶችና አፕሎች ናቸው፡፡ እናም ዙሪያውን በሙሉ ደግሞ አሻንጉሊቶችና የመጫወቻ ፈረሶች። ዘናጭ፣ ንጹህ ልብሶች የለበሱ ትንንሽ ልጆች አሉ፡፡ እየሳቁና እየተጫወቱ፣ የሆኑ ነገሮች እየበሉና እየጠጡ ነበር፡፡ ከአንድ ትንሽ ልጅ ጋር መደነስ የምትፈልግ ሌላ ትንሽ ልጅ ነበረች፡፡ እንዴት ታምራለች! ሙዚቃም አለ፤ በመስኮቱ አልፎ ይሰማኛል፡፡
ሕፃኑ ልጅ ተመለከተ፣ ተደነቀ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀደም ሲል በጣቶቹና በእግሮቹ ላይ ሲሰማው የነበረው ህመም ቆመ፡፡ የእጆቹ ጣቶች በሙሉ ቀሉ፣ ጣቶቹን ማጠፍ አልቻለም፡፡ ሲያንቀሳቅሳቸው ወዲያውኑ ሕመም ተሰማው፣ ማልቀስ ጀመረና ሄደ፡፡ በሌላ መስኮት ውስጥ ሌላ ክፍል አየ፡፡ እናም እንደገና ዛፎች፣ ጠረጴዛ ላይ የተደረደሩ ሁሉም አይነት ኬኮች፣ ቀይና ቢጫ ለውዞች፡፡ በጠረጴዛው ዙሪያ አራት ቆንጆ ሴቶች ተቀምጠዋል፤ የሆነ ሰው ሲመጣም የተወሰነ ኬክ ይሰጠዋል፤ በሩን ከፍቶ ገባ፡፡ ኦህ! እሱን ሲያዩ እንዴት እንደጮሁ! እንዴት ግራ እንደተጋቡ! ወዲያው አንዲት ሴት ተነስታ እጁ ላይ አንድ ኮፔክ አስቀመጠችለትና ወደ መንገድ የሚያስወጣውን በር ከፈተችለት፡፡ አቤት እንዴት እንደፈራ!
ኮፔኩ ከእጁ አምልጦ ደረጃዎቹ ላይ ወድቆ አቃጨለ፡፡ ሳንቲሙን ለመያዝ እጆቹን መጨበጥ አልቻለም፡፡ ሕጻኑ እየሮጠ ወጥቶ፣ ፈጠን ፈጠን እያለ ተራመደ፡፡ ወዴት ነው የሚሄደው? አላወቀም። እናም ሲሮጥ ሲሮጥ ቆየና እጆቹ ላይ ተነፈሰ፡፡ ቸግሮታል፣ በጣም ብቸኝነት ተሰማው፤በጣም ፈርቷል፤ እናም ድንገት፣ ይሄ ምንድን ነው! የተሰበሰቡ ሰዎች፡፡ ቆመና ተገረመ፡፡
መስኮት! ከመስኮቱ ኋላ ቀይና ቢጫ የለበሱ ደስ የሚሉና በሕይወት ያሉ የሚመስሉ ሶስት አሻንጉሊቶች፡፡ ዋሽንት የሚነፋ የሚመስል፣ የተቀመጠ ትንሽ ሽማግሌ ሰው፣ ሌሎች ሁለት ደግሞ ነበሩ፣ ቆመው ትንንሽ ቫዮሊኖች የሚጫወቱ፣ በጭንቅላታቸው ሰዓት እየጠበቁ ሙዚቃ ይጫወታሉ፡፡ እርስ በርስ እየተያዩ ከንፈራቸውን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ የምር ይናገራሉ? ብቻ ድምጻቸው በመስታወቱ አልፎ ሊሰማው አልቻለም፡፡
መጀመሪያ ሕፃኑ በሕይወት እንዳሉ አሰበ፤ ከዚያም አሻንጉሊት ብቻ እንደሆኑ ሲረዳ መሳቅ ጀመረ፡፡ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት አሻንጉሊቶች በፍጹም አይቶ አያውቅም፣ እንዲህ አይነት አሻንጉሊቶች ስለመኖራቸውም እንኳ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡  
ድንገት ኮቱ እንደተያዘ ተሰማው፤ ጭንቅላቱን በቡጢ የነረተውና ኮፍያውን ቀምቶ ያንጠለጠለው ትልቅ ባለጌ ልጅ ከጎኑ ቆሟል፡፡ ሕፃኑ ልጅ ወደቀ። በዚህ ቅጽበት ጩኸት ተሰማ፤ለአፍታ ሽባ ሆነ፤ ከዚያም ተስፈንጥሮ ተነሳ፤ ሲሮጥ፣ ሲሮጥ፣ አንድ የሆነ መግቢያ ነገር አገኘ፣ ሾልኮ ገባና የሆነ ሜዳ ላይ የተከመረ ግንድ ጀርባ ተደበቀ፡፡ በፍርሃት ተወሽቆ ተንቀጠቀጠ፤ መተንፈስ አቃተው፡፡
እናም ድንገት ምቾት ተሰማው፡፡ ትንንሽ እጆቹና እግሮቹ ማመማቸውን አቁመዋል፡፡ ልክ ወደ ምድጃ እንደተጠጋ ሁሉ ሞቀውና መላ ሰውነቱ ተንዘፈዘፈ፡፡
ትንሹ ልጅ፤ “ኦህ! መተኛቴ ነው፡፡ መተኛት እንዴት ጥሩ ነው፡፡ ትንሽ እተኛና አሻንጉሊቶቹን እንደገና ሄጄ አያቸዋለሁ!” ሲል አሰበ፡፡ አሻንጉሊቶቹን አስታውሶ ፈገግ አለ፤ልክ በሕይወት ያሉ ይመስላሉ! ከዚያም እናቱ የምትዘምርለትን መዝሙር ሰማ፡፡ ‹‹ማማ! መተኛቴ ነው፤ ኦህ! ይህ ቦታ ለመተኛት ምን አይነት ጥሩ ቦታ ነው!››
‹‹ትንሹ ልጅ፤ የገናውን ዛፍ ለማየት ከፈለክ ወደ እኔ ቤት ና” አንድ ዝቅ ያለ ድምጽ ተናገረ፡፡ መጀመሪያ ላይ እናቱ የምትጠራው መስሎት ነበር፤ ነገር ግን የጠራችው እሷ አልነበረችም፡፡ ታዲያ ማን ነው የሚጠራው? የሚጠራውን ሰው አላየም፤ ነገር ግን በጨለማው ውስጥ የሆነ ሰው ጎንበስ አለና፣ በሁለት እጆቹ አቅፎ ያዘው፤እሱም ወዲያው ሁለት እጆቹን ዘረጋ፡፡ ምን ዓይነት ብርሃን ነው! ምን ዓይነት የገና ዛፍ ነው! አይ፣ ይሄ የገና ዛፍ አይደለም፡፡ ይሄን የሚመስል የገና ዛፍ በፍፁም አይቶ አያውቅም!
አሁን የት ነው ያለው? ሁሉም ነገር ያንጸባርቃል! ሁሉም ነገር ብርሃን ይረጫል፡፡ በዙሪያውም አሻንጉሊቶች አሉ፤ ነገር ግን አሻንጉሊቶች አይደሉም፤ ትንንሽ ወንድና ሴት ህፃናት ናቸው፤ ብቻ በጣም ያበራሉ፡፡ ሁሉም እየበረሩ ዙሪያውን ከበቡት፤ ያዙትና ወሰዱት፤ እሱም አብሯቸው መብረር ጀመረ፡፡ እናቱ እሱን እየተመለከተች በደስታ ስትስቅ አያት፡፡
“እማማ፣ እማማ! እዚህ መሆን እንዴት ደስ ይላል!” ትንሹ ልጅ ገለጸላት፡፡
እናም እንደገና ልጆቹን አቀፋቸውና፣ ከመስኮቱ ኋላ ስላሉት አሻንጉሊቶች ሊነግራቸው ወደደ፡፡ “እናንተ ትንንሽ ሴት ልጆች፤ እነማን ናችሁ?” ሲል ጠየቃቸውና እየሳቀ ዳሰሳቸው፡፡
ይሄ በኢየሱስ ቤት ያለ የገና ዛፍ ነው፡፡
በዛ ቀን በኢየሱስ ቤት ውስጥ የራሳቸው የገና ዛፍ የሌላቸው ህፃናት የገና ዛፍ ይኖራቸዋል፡፡ እናም እነዚህ ሁሉ ትንንሽ ወንድና ሴት ህፃናት፣ ልክ እንደሱ የሞቱ ልጆች መሆናቸው ገባው፡፡ የተወሰኑት ፒተርስበርግ ውስጥ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች በር ላይ በዘንቢል ተጥለው፣ በቅዝቃዜ ምክንያት የሞቱ ናቸው፡፡ ሌሎች መናኛ በሆኑት የቸካንስ ደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ እንክብካቤ በሚደረግላቸው ወቅት በተፈጠረ ስህተት የሞቱ ናቸው፡፡ ሌሎች በቸነፈሩ ጊዜ የእናቶቻቸው ጡት በመንጠፉ ምክንያት በረሃብ የሞቱ ናቸው፡፡ አሁን ሁሉም እዚህ ናቸው። ሁሉም ትንንሽ መላእክት ሆነዋል፣ ከኢየሱስ ጋር ናቸው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ነበር፤ እጆቹን በላያቸው ላይ አድርጎ፣ እነሱንና ሃጢያተኛ እናቶቻቸውን እየባረካቸው ነው፡፡
እናም የእነዚህ ህፃናት እናቶች፣ ከልጆቻቸው ተነጥለው፣ የየራሳቸውን ወንድ ወይም ሴት ልጆች እያዩ ተቀምጠው ያለቅሳሉ፤ ልጆቻቸውም ወደ እነሱ እየበረሩ በመሄድ፣ በትንንሽ እጆቻቸው እንባዎቻቸውን በማበስ፣ እንዳያለቅሱ አቅፈው ይለምኗቸዋል፡፡ ጠዋት ላይ የቤቱ ተቆጣጣሪ፤ ጓሮ ተጠልሎ የነበረውን የትንሹን ህፃን አስከሬን፣ ከተከመረው እንጨት ጀርባ ፣መሬት ላይ ደርቆና ቀዝቅዞ ወድቆ አገኘው፡፡ ከእሱ በፊት የሞተችው እናቱ አስከሬንም እንዲሁ ተገኘ፡፡ ሁለቱ በሰማይ፣ በጌታ ቤት ውስጥ እንደገና ተገናኙ፡፡

Read 3687 times