Print this page
Sunday, 08 January 2017 00:00

‘ማን ከማን ያንሳል!’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

  “---ዘንድሮ ‘ከኑሯችን ቀድመን እኛ ፎቅ ላይ ወጣንና’… የበግና የዶሮ መፎካከሪያችንን ተነጠቅን፡፡ ልክ ነዋ… ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ መቶ ምናምን በግ ሲጮህ፣ የቱ የማን እንደሆነ ስለማይታወቅ ----- ‘ሰው አፍ’ የሚገባ ላይኖር ይችላል፡፡----”
           

       እንዴት ሰነበታችሁሳ!    እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁማ!
ስሙኝማ…እንደ ባንኮች የመሰሉ ድርጅቶች ብልጥ ሆኑ አይደል፡ ልክ ነዋ…በፊት አንድ በዓል ሲመጣ በዓሉን ጠቅሰው ነበር እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት …የሚሰቅሉት
“እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!”
“እንኳን ለመውሊድ አደረሳችሁ!”----
አይነት መልካም ምኞት መግለጫዎች ይሰቅሉ ነበር፡፡ (‘በደጉ ጊዜ’ ማለት ክፋት አይኖረውም…)
እናላችሁ…ዘንድሮ ግን የሚሰቀለው ምን የሚል መሰላችሁ… ‘እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ!’ ሌጣውን! እያንዳንዱ ክብረ በዓል፤ የራሱ መለያ አሻራ ምናምን ነገር አለዋ! ነገርዬው ወጪ ቁጠባ ምናምን ይመስላል። ለብጣሽ ጨርቅ!
እናማ ባንኮች ምናምን ----- ያንን ሁሉ ሚሊዮን ብታተርፉ ምን ይገርማል፡፡ ሚያዝያ 27ም በዓል፣ ’ቫለንታይንስ ዴይ’ም በዓል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
‘ማን ከማን ያንሳል!’
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘ታንክስ ጊቪንግ’ የሚሉት የ‘አሳዳሪዎቻችን’ በዓል… አለ አይደል…  የ‘ቫለንታይንስ ዴይ’ን ያህል የሚከበረው መቼ እንደሆነ ይነገረንማ፡፡ ፈራ ተባ እያልን እንዳንሳቀቅ፣ አንደኛውን ‘ቢለይልን’ ይሻላላ! (‘የተረት አባት’ ምን እንደሆነ የማያውቁ፣ ስለ ‘ገና አባት’ ግን ሲያወሩ ሊውሉና ሊያመሹ የሚችሉ ልጆች በበዙበት ዘመን፣ በዓላትንም ‘እንዋስ’ እንጂ!)
‘ማን ከማን ያንሳል!’
ሀሳብ አለን…  እንደውም ‘ጁላይ ፎር’ም ይጨመር። አሀ… እኚህ አዲሱ ‘የአማሪካን ገዢ’ ደስ ብሏቸው፣ የእኛን ልጆች ‘አላየሁም፣ አልሰማሁም’ ብለው ሊተዉአቸው ይችላሉ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ ሰሞን ‘የገና ዛፍ የእኛ ባህል አይደለም’ …የባህል ወረራ ምናምን እያልን ብንጮህ፣ እሪ ብንል የማይሆን ሲሆን ጊዜ በ‘ማን ከማን ያንሳል!’ አይነት ፉክክር… አሁን የገና ዛፍ በብዙዎቻችን ቤት ገብቷል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…ቤቱ ውስጥ ያሉን ሁለት ቢላዋዎች አንዱ ደንዞ፣ አንደኛው ተሰብሮ አይደለም ሥጋ… “ጎመኑስ በየትኛው ቢላዋ ሊቀረደድ ነው…” እያሰኘ…የገና ዛፍ ‘ቅድሚያ’ ሲያገኝ…አለ አይደል…የሆነ ነገር እንደተሳሳተ ይሰማችኋል፡፡
ነገርዬው ምን መሰላችሁ… ሁሉም ሰው የገና ዛፍ እየገዛ ነዋ! ሁሉም ሰው ‘ዲኮሬሽን’ እየገዛ ነዋ!…ሁሉም ሰው በፕላስቲክ የተሠራ ‘የገና አባት’ እየገዛ ነዋ! እናማ… ‘ሳንታ ክላውስ’ ማን ቤት ገብቶ ማን ቤት ሊቀር ነው!
‘ማን ከማን ያንሳል!’
እናላችሁ…በፊት “ማን ከማን ያንሳል…” ፉክክር በግና ዶሮ ላይ ነበር፡፡ በበር ቀዳዳ አጮልጎ አይቶ… ፤ የእነ ጩኒ አባት የገዙትን በግ ብታይ ምን እንደሚያክል!” ብሎ የመጀመሪያውን ጥይት የሚተኩስ ልጅ አይጠፋም፡፡ ለቀሪው ፍልሚያ ደግሞ እናት አለች…
“የአንተ አባትማ---እንዲህ የሰው መዘባበቻ ያድርገን እንጂ! ልጄ የሰዉ ባል ምን የመሳሰለውን ሙክት ያስጎትታል…”  እያለ ይቀጥላል፡፡
ዘንድሮ ‘ከኑሯችን ቀድመን እኛ ፎቅ ላይ ወጣንና’… የበግና የዶሮ መፎካከሪያችንን ተነጠቅን። ልክ ነዋ…  ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ መቶ ምናምን በግ ሲጮህ፣ የቱ የማን እንደሆነ ስለማይታወቅ ‘ሰው አፍ’ የሚገባ ላይኖር ይችላል፡፡ እናማ…ባዶ ቦታ ተገኘና እነ ‘ክሪስተማስ ትሪ’ ሹልክ ብለው ገብተው የ“ማን ከማን ያንሳል!” መፎካከሪያችንን ለወጡት፡፡ አሀ…በር ሲከፈትና ሲዘጋ ሳሎኑ ‘ብልጭ’ ይላላ! ቂ…ቂ...ቂ…
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ኮንዶሚኒየምን ሳነሳ፣ አንድ ወዳጄ የነገረኝ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ እንግዲህ በፊት ባል ፊልድ ሲሄድ…አለ አይደል… ወይ በጓሮ በኩል በተሸነቆረ አጥር ሾልኮ፣ ወይ በማድ ቤቱ አጠገብ ባለው መስኮት በኩል ዘሎ ምናምን ይገባ ነበር። ያውም ከአሁን አሁን ጎረቤት አንኳኳ፣ ቀበሌ “ጽዳት ዘመቻ ውጡ” አለ…ምናምን እየተባለ እየተሳቀቁ!
እናማ ኮንዶሚኒየም እነኚህን ሁሉ ስጋቶች በአስተማማኝ እንደፈታቸው መግለጽ እንወዳለን። ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…ልክ ነዋ! “እስቲ አንድ ጣሳ ሹሮ አበድሪኝ…” ብሎ የሚያንኳኳ የለ፣ “እማማ ቡና ጠጡ ብላለች…” ብሎ በር የሚቆረቁር ልጅ የለ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ጽድት ያለች ሸሚዝ በለበሳችሁ ቁጥር…
“ሁልጊዜ እንዳማረብህ፣ አሮጌ አርመን ዘረፍክ እንዴ!” ምናመን የሚል ሰው የለ!
ጫማዋ ተወልውላ ባብረቀረቀች ጊዜ…
“አጅሬው፣ ዘንድሮ እንዳንተ የተመቸው የለም፣ ምን ተገኘ!” የሚል የለ!
ደግሞላችሁ…. ኮንዶሚነየም ቢያንስ ቢያንስ፣ ባለመኪናው ስለሚለይ ለመሸወድ ያስቸግራል፡ ልክ ነዋ…በፊት እኮ… “አንዲት ፊያት መቶ ሀያ ሰባት አለችኝ፣ ጋራዥ ገብታ ነው፣ ቀስቷን ደግሞ አንድ ጓኛዬ ሰርግ ላጅብበት ብሎ ወስዷት ነው...  ምናምን እያሉ መሸለል ይቻል ነበር፡፡ አሀ…እንትናዬዎቹ…
“ተጨባጭ ማስረጃ አቅርብ…”
“ሦስት ምስክር አምጣ…”
“ይሄ ጨለማ አይንጋልኝ ብለህ ማልልኝ…”
ምናምን አይሉም ነበራ!  (‘በደጉ ጊዜ’ ማለት ክፋት አይኖረውም…) እሱዬው እኮ አይደለም እግሩ ፊያት መቶ ሀያ ሰባት ፍሬን ላይ ሊያርፍ ቀርቶ፡ የመቶ ሀያ ሰባት ብር ጫማ አድርጎ አያውቅም፡፡ ለነገሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት የመቶ ብር ጫማ እንኳን ማድረግ… “አንተማ ደልቶህ መቶ ብር እየረገጥክ ትሄዳለህ…” ምናምን የሚያስብል ነበር፡፡  ቂ…ቂ…ቂ…
እኔ የምለው…ብዙ ሰው የእንኳን አደረሰህ/አደረሰሽ ካርድ መላክም ለመደ አይደል!
ስሙኝማ… በፊት በደብዳቤም በምንም የሆድ፣ የሆዳችንን እንባባል የነበረውን ‘ሶሻል ሚዲያ’ መጣና ጉድ አደረገን እኮ፡፡ ልክ ነዋ… ፌስቡክ ሜሴጅ ላይ… “ደብዳቤው ስር የምታዪው የደሜ ጠብታ ነው…” ምናምን ሲባል አላየንማ!
የምር ግን ደብዳቤን የመሰለ ነገር የለም ነበር… “ሼር ያደርጉታል…” የለ፣ “ላይክ ያደርጉታል…” የለ… “ሩስኪዎቹ ሀክ ያደርጉታል…” የለ! (ቂ…ቂ…ቂ…) የደብዳቤ ዘመን ይመለስልንማ!
“ይገርምሀል ከልጅነቴ ጀምሮ አንድ ቀንም ደስ ብሎኝ አያውቅም፡፡ ስስቅ የምታዩኝ ሁሉ ውሸቴን፣ ለሰው ጓዳዬን እንዳያውቁብኝ ብዬ ነው፡፡ ስጠጣ ስታየኝ ደልቶኝ እንዳይመስልህ፣ ኑሮን መርሳት ስለምፈለግ ነው… አይነት ልብ የሚሰብር ነገር መጻፍ የሚያምረው ‘ሼር’ በማይደረገው፣ ‘ላይክ’ በማይደረገው ደብዳቤ ነበር፡፡
“አንቺማ ድንገት ባዶ ቤት አስታቅፈሽኝ የሄድሽው፣ ብቻውን ሜዳ ላይ ይቀራል ብለሽ ነበር፡፡ አገሩ ላይ ያለሽው ሴት አንቺ ብቻ ትመስይ፣ ‘ጦሙን ሲያድር በአራት እግሩ እየዳኸ ይለምነኛል’ ብለሽ ነበር፡፡ ደስ አይበልሽ…ምን የመሰለችውን፣ ከአንቺ በጠባይም በመልክም መቶ ጊዜ የበለጠችውን አመጣልኝ…እስከዛሬ የተበደልኩትን እየካሰኝ ነው…” ምናምን ‘እንዳማረሽ ይቅር’ ዓይነት ነገር መጻፍ የሚያምረው ‘ሼር’ በማይደረገው፣ ‘ላይክ’ በማይደረገው ደብዳቤ ነበር፡፡
እናማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የሰሞኑን ‘ገበያ’ አይታችሁልኛል! አንዱ የመንገድ ዳር ነጋዴ አካባቢ ሦስት ሰው ከቆመ፣ በሴኮንዶች ውስጥ ሃያ ሦስት ሰዎች እንሆናለን፡፡ የምንሰበሰው እኮ የሚሸጠውን ዕቃ አይተን፣ ልባችን ወዶት ምናምን አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ተሰብስቧላ!  ያ ሁሉ ሰው እንዲህ የተሰበሰበው የሆነ ነገር ቢኖር ነዋ!  ሰዉ ገዝቶ እኛ ልንቀር!
ይቺ ‘መካከለኛ ገቢ’ የሚሏት እንቁልልጭ ጊዜ ደርሳ ጉዳችን ታይቶ! ቂ…ቂ…ቂ…
‘ማን ከማን ያንሳል!’ ከሚሉት ነገር የሚገላግል ዘመን ይምጣልንማ!
መልካም የበዓል ሰሞን ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4511 times