Print this page
Sunday, 08 January 2017 00:00

እንኳን ለገና አደረሰን

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(4 votes)

የፈረንጅ ገና ዋዜማ ለት በሆንኩት ልጀምር። ሁለት ወዳጆቼ፤ አንደኛው ከዚሁ ከቨርጂኒያ፤ ሌላው ከሳሳከችዋን፤ ካናዳ ደውሎ ስለ በአሉ ትንሽ ተነጋገርን። እነሱም የሚሰማቸውን እኔም የሚሰማኝን ያዝ ለቀቅ አደረግነው። “ዞር ዞሮ ከቤት!” እንዲሉ ያው ሁሌም  ሚዛኑ የኢትዮጵያ አመት በአላት ናቸው። “ባሻ አሸብር ባሜሪካ” መሆናችን መሰለኝ።
ከካናዳ የደወለው የቁጫ ልጅ ነው። ቆጫ ጋሞ ውስጥ አንድ ወረዳ ነው። እኔ እስከማውቀው ዝነኛነቱ በቅቤ ነበር። አሁን፤ በዚህ “ዙሪያችሁን አጥር እጠሩና ተካለሉ” በተባለው መሠረት ይመስለኛል “እኛ ቁጫ እንጅ ጋሞ አይደለንም!” አሉ ተባለ። ያ እንደፍጥርጥሩ! እኔ የገረመኝ አምና ይሁን ሀች አምና፤ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ቁጫ የራሱን እድል የመወሰን መብቱ መከበር አለበት!” የሚል ጽሁፍ አንድ ሁለት ይሁን ሶስት ጊዜ ያነበብኩ ይመስለኛል። የጽሁፉ አቅራቢ ደግሞ “አገር አቀፍ ፓርቲ” በሚል  ከተመዘገቡትና ተቃዋሚ ድርጅቶች ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነበር። ተለዋጭ አስተያየት አልተሰጠበትምና የሚቃወሙት ያው ወያኔን ነው ብዬ አስባለሁ። አገር አቀፍ ፓርቲ ይህንን ሲደግፍ ደግሞ  ነገር አለሙ አልገባኝ ይሆን? ወደማለት ወሰደኝ። ምኑን እንደሚደግፉ፤ ምኑንስ እንደሚቃወሙ አልገባኝም ለማለት ነው። በዚህ አጋጣሚ አስታወሰኩት።
ከነሱ ጋር ዝርዝር ውስጥ አልገባንም እንጂ እኔ ይህንን የፈረንጅ በአላት፤ በተለይም ሐይማኖት ነክ የሆኑትን መንፈሴ አልተላበሰውም:: ሙሉ ለሙሉ አልተላበሰውም ማለት ይሻላል። ምራቄን አጣጥሜ ከዋጥኩ በኋላ ከአገሬ ስለወጣሁ፣ አዲስ ስር ማቆጥቆጥ አልቻልኩምና ሊሆን ይችላል። ይህ አንደኛው ምክንያት ቢሆንም ሌሎችም የሚያጣ አይመስለኝም። ለምሳሌ ያክል ይህንን የገና በዓል እንውሰድ።  ፈረንጅና ተከታዮቹ የሱስ፤ እስልምና ተከታዮች ኢሳ፤ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ እየሱስ የሚሉት  ልደት ነው። በየትኛውም ቅላጼ ይጠራ እየሱስ እናት አለው ማለት ነው። ልደት የተባለው “ተወለደ!” ለማለት ነውና! እናቱ ደግሞ ማርያም ነች። ኦርቶዶክሶቹ “ድንግል በሕሊናክ ወድንግል በሥስጋኪ!” ይሏታል። ሐዋሪያው ሉቃስም  በወንጌሉ ምዕራፍ አንድን ለማርያም ብቻ ያደርገዋል።  ተራ-ተርታው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተከታይ(The average laity) ማርያምን እንደ ቤተሰብም፤ እንደ ጎረቤትም፣ ሲበዛም በግል እንደሚያውቋት አስመለው ሲጠሯትና ሲያሞካሽዋት ማየትና መስማት የተለመደ ነው። በዚህ ውስጥ ያደገው አሌክስ፤ “ደብዳቤ ለእግዜር!” በሚለው ግጥሙ መደምደሚያ  ላይ :-
“ኧረ እግዜር በናትህ በጭንቅ አማላጇ
ባዘለህ ጀርባዋ ባቀፉህ እጆቿ
ወይ ዝናብ ላክልን ወይ ዝናብ ሁነህ ና
ሙቀት ገደለና!”--- ይላል።
አባ ህርያቆስ የሚባሉ መንኩሴ ደግሞ “ጎሣ ልብዬ ቃለ ሠናዬ!” የሚል የማርያም ቅዳሴ ደርሰዋል። ቅዳሴ ምስጋና ማለት ነው። ቀደሰ አመሰገነ ነውና! ሶርያዊ ሳይሆኑ አይቀሩም። እኔ አልፎ አልፎ “ጎሣ ልብዬ”ን አዳምጠዋለሁ። የድርሰቱ ጥልቀትና ምጥቀት ይገርመኛል!
ማርያምም በዚሁ በሉቃስ ምዕራፍ አንድ ውስጥ “ከእንግዲህ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል” ትላለች። ትውልድ ስትል የሰው ዘር ሁሉ ማለት ባይሆንም ክርስቲያን የሆነውን ሁሉ ማለቱ ይመስለኛል። ከሆነም ደግሞ ፈረንጁም እዚያው ትውልድ የሚለው ውስጥ ይጠቃለላል። ካልተጠተቃለለ ደግሞ ትውልድ አይደለንም ማለታቸው  ይሆን? ወይም የሉቃስን ወንጌል ምዕራፍ አንድን አላየንም! አልሰማንም! ማለት ይሆን? ፈረንጅ በማርያም አካባቢ ድርሽ አይልም!  ካቶሊኮችን አይጨምርም። ነገሩ “ማን ይመራመር!?” ውስጥ የሚገባ መሰለኝ።
አንድ ቀን “ክርስትና በአሜሪካ!” የሚል መፃፌ የሚቀር አይመስለኝም።  ይህ ሁሉ ነገርን ነገር ያነሳዋል በሚል እንጅ እምነት ውስጥ ገብቼ ለመዘባረቅ አይደለም። ልገባ እንኳን ብፈልግ እዚያ የሚተራመሰው፤ የሚያተራምሰው ብዙ ስለሆነ ክፍት ቦታ የማገኝ አይመስለኝም።
*   *   *
ከወዳጆቼ ጋር ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ አንድ ቦታ ለመሔድ Malcom X እና Baylor Hospital  ያለው ባቡር ጣቢያ ቆሜያለሁ። የባቡሩ ጣቢያ መናፈሻም (Park) ጭምር ያለው ስለሆነ አልፎ አልፎ መናፈሻው ውስጥ ተቀምጬ አነባለሁ ወይም እቆዝማለሁ። ዛሬ ያለወትሮው ጭር ብሎ ነበር።
እንደቆምኩ SUB አንድ ትልቅ ፈረንጅ የሚነዳውና አጠገቡ የ15 አመት የሚሆነው ወጣት የተቀመጠበት ፊት ለፊት ቀጥ ብሎ ቆመ። በኔ በኩል ያለው ወጣቱ ነው። ፊቱ ላይ ፈገግታ አለው። መስኮቱን ከፍቶ እጁን ወደኔ ዘረጋ። ገርሞኝ ልጨብጠው እጄን ስዘረጋ፣ በእጁ የያዘውን ሰጠኝ። የሰው እጅ ያልነካው ሁለት ባለ $20 ነው። አልተዘጋጀሁበትምና እንኳን አደረሳችሁ (Merry Chistmas) የመሳሰለውን ስል ግዙፉ አባት ወይም አያት ወጥቶ አቅፎ፣ እንኳን ለገና አደረሰህ (Merry Chirstmas) ተባባልን። ብዙ ጊዜ አይቻቸው የማላውቀው፣ አዲስ ከፓኮ የወጡ፤የዚህ አካባቢ የማይመስሉ ፈረንጆች ነበሩ!
*   *   *
ከሰአት በኋላ ይህንን ለልጆቼ፣ ለእመቤት አሰፋና ለቡርቱካን ሚደቅሳ ነገርኳቸው። ለእመቤት ደውዬ ነው። ቡርቱካን “እንኳን አደረሰህ !”ለማለት ደውላ ነው። ሁለቱም ተቀራራቢ መልስ የሰጡኝ ይመስለኛል። “አንተ መንፈሴ አልተላበሰውም” ስትል ይኸው “ወዴት ገሽሽ  ገሽሽ !” ብሎ መልእክተኛ መጣብህ የሚል ቃና ያለው መሰለኝ። ከሆነ ደግሞ “ማን ይመራመር?” አይነት ሊሆን  ነው
“ማን ይመራመር፤ ማን ይመራመር፤
ያንተን ሥራ ያንተን ግብር፤ ማን ይመራመር?” ይላል፤ መዲናና ዘለሰኛው።
እኔም እስማማለሁ! ብቻ ይህንን “ያንተን ሥራ! ያንተን ግብር! ማን ይመራመር!?” የሚለው አንድምታም ያለው ይመስለኛል። በአንድምታው ከሔድን ደግሞ “ያንተ ሥራ!” የሚለው ፈጣሪን ማለት ሳይሆን፤ ወይም ፈጣሪን ብቻ ማለት ሳይሆን ተፈጥሮን ብሎ መተርጎም የሚቻል ይመስለኛል። ተፈጥሮ አምቃ የያዘችውን ምስጢር ለማወቅ ጥረቱ ገና በሩን በማንኳኳት ላይ ያለ ይመስላል። እና ልጆቼ ያሉትን በዚያ ትርጉም ጭምር ተቀብያለሁ ለማለት ነው።
*   *   *
ሌላው የዚህ ሰሞን ዜና “ከፍተን ብናየው!  የኢሳይያስ አፈወርቂና የኦነግ መስተፋቅር” ብዬ የጻፍኩት በየድረገጹም በአዲስ አድማስም ወጥቶ ነበር። አንዱ በራዲዮም ያነበበውን በUtube ለጥፎ ነበርና ይህንን በምጽፍበት ጊዜ 148,000 ሰው አዳምጦታል ይላል። ይህ በFacebook፤ በአዲስ አድማስና በድረገጾች ያነበበውን ሰው ሳይጨምር ማለት ነው። እንደሚነገረኝ ከአንባቢዎችና አድማጮች ውስጥ ብዙ ኤርትራውያን እንዳሉበት ነው። ይህ፣ ለኔ፣ ማህበራዊ ገጽ የሚባለው የሚሰራውን ትንግርት የሚነግረኝ ነው።
አሁን ወደ ጦሴና ጥንቡሳሴ ልግባ
ፕሮፌሰር አየለ በከሪ አንድ የግእዝ ማእከል የጎበኘውን CNN ታሪካዊ ብሎ አቀረበው። እኔ፤ ያንን Utube በFacebook  ግርግዳዬ ላይ ለጠፍኩት። ብዙ ወዳጆቼ ጎበኙት! አደነቁ፤ አስተያየትም ሰጡ! ከነዚህ ውስጥ አንዱ፣ ዳግማዊ ተሾመ የተባለ “ባይሆን አርፈህ ስለ ጨንቻ ብትጽፍ አይበቃህም?” የሚል አስተያየት ሰጠ። ሁለትየጥያቄ ምልክትም አድርጓል። የFacebook ጥሩነቱ፤ “ወዳጅ Friend” መስሎ የመጣውን “ቅርብኝ  Unfriend” ለማለት ሴኮንዶች ነው የሚወስደው። በዚህ መሠረት ዳግማዊ ተሾመን “ቅርብኝ!” አልኩት።
ሳስበው ስሙ አይመስለኝም። የዚህ አዲሱ  Facebook ላይ ከተፈለፈሉት “የአማራ ነጻ አውጭ!” ነን ከሚሉት፣ወደ ዘመነ መሣፍንት ተጓዦች አንዱ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም። “ግዕዝ የኛ ነውና ለአንተ ምንህ ነው?” እንደማለት። ከ2009 እስከ 1855  ዘመነ መሣፍንት ድረስ መጓዝ አልችልምና ዳግማዊ ተሾመን፤ “እዚያ  ይሙቅህ!” ብዬ አሰናበትኩት። ቴክኖሎጂ ጥሩ ነገር! ውጣ ውረድ ይግባኝ የሌለበት!
*   *   *
ሌላው በዚህ “ከፍተን ብናየው..!” ብዬ በጻፍኩት ላይ አንዱ “ሽማግሌና ሕጻን አንድ ነው!” የሚል አስተያየት ሰጠ። “ቅርብኝ (Unfriend)” ልበለው አልበለው ስል ብዙዎች መልስ ሰጡበት። አንደኛው አረካኝ። “ልክ ነህ! ሽማግሌና ሕጻን አንድ ነው! ልክ እንደወረደ እውነቱን ይናገራል!” አለ። ይህን አይቼ “ቅርብኝ!” አላልኩትም።
*   *  *
የፈረንጅ አዲስ አመት ዋዜማ ዘወትር ቅዳሜና እሁድ እንደማደርገው ፕሌኖ(Pleno) የምትባል ከተማ ለመሔድ ባቡር ተሳፈርኩ። እዚያ ሰውም አገኛለሁ። ጋዜጦችም የማገላብጥበት፣ መጽሐፍት ቤትም ቁጭ ብዬ የማነብበት Starbucks አለ። አንድ የማነበው The Orgin of Amharic  የሚል የዶክተር ግርማ ደመቀን መጽሐፍም ይዣለሁ። ከባቡሩ ስወርድ ረስቼ ወረድኩ። ሁለት ይሁን ሶስት ወር ሙሉ አንዴ በብጫ ሌላ ጊዜ በሰማያዊ ሳቀልመው (Highlight)፣ አናቱ፣ እጎኑና ግርጌው ላይ ሁሉ ስጽፍበት የከረምኩት ጠፋ! ጠፋ!። ዶክተር ግርማ ዛሬ እልክልሃለሁ ብሏል።
ይህንና ይህንን ነው “ጦሴን ጥንቡሳሴን ይዞት ይሂድ!” ያልኩት፡፡
ማሳረጊያ
ከዚህ ከረዘመ “እንኳን አደረሰን!” ሳይሆን ንዝንዝ የሚሆን መሰለኝ! ለዘንድሮ ገና ይኸው ይብቃና!
“ገና” ላልቶ ሲነብብ “ገና!” ማለትም ነው። የተሻለ ነገም አለ ማለት ነው!
ለተሻለ ነገ ያብቃን!
ከፋፋዮችን፤ ከሐዲዎችን፤ ያትንንልልን! ያብንልን!
ኢትዮጵያ በነፃነትዋ ለዘለዓልለም ትኑር!

Read 3459 times