Print this page
Sunday, 08 January 2017 00:00

የገና በዓል ገበያ እንዴት ዋለ?

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(10 votes)

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

በዘንድሮ የገና በአል ገበያ ሸቀጦች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን በተለይ የበግና የበሬ ዋጋ ከዓምና ተመሳሳይ የበአል ወቅት በእጅጉ መጨመሩን ነጋዴዎችና ሸማቾች ገልፀዋል፡፡
አቃቂ በሚገኘው የእርድ ከብቶች ገበያ፣ ባለፈው አመት የገና በአል የቅልብ ሰንጋ በሬ ዋጋ 22 ሺ ብር ገደማ የነበረ ሲሆን፤ በዘንድሮው በዓል እስከ 31 ሺህ ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡
የበሬ ዋጋ ሊጨምር የቻለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመኖ ዋጋ በመናሩ ነው ብለዋል የበሬ ነጋዴው አቶ ይማም ሽኩር፡፡ አምና፤ አንድን ከሲታ በሬ አድልቦ ለገበያ ማቅረብ እስከ 5 ወር ገደማ እንደሚፈጅ የገለፁት ነጋዴው፤ ከአርሶ አደሮች ከሲታውን በሬ እስከ 10 ሺ ብር ገደማ እንደሚገዙና ለማድለብ በሚደረገው ጥረት ቢያንስ አንድ በሬ እስከ 15 ሺህ ብር የመኖ ወጪ እንደሚያስወጣ አስረድተዋል፡፡ “በዚህ ምክንያት የደለበ ወይፈን እስከ 10 ሺህ ብር፣ መካከለኛ እስከ 20 ሺህ ብር፣ ሠንጋው ደግሞ እስከ 31 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው” ብለዋል፡፡
በዚሁ ገበያ የበግ ዋጋም ካለፈው አመት መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ያሣየ ሲሆን፤ የበግ ዋጋ ትንሹ 700 ብር ሙክት 5 ሺህ ብር ይገኝ የነበረ ሲሆን፤ በዘንድሮ በአል ከ1200 እስከ 7 ሺህ ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ ፍየል ከ800 ብር እስከ 8500 ብር ባለው ይገኛል፡፡
በአቃቂና በሣሪስ ገበያዎች ዶሮ አነስተኛው 150 ብር ሲሸጥ ትልቁ 400 እየተሸጠ የሰነበተ ሲሆን የዶሮ ገበያ በተለይ በዋዜማው ገበያው እንደሚሟሟቅ የጠቆሙት የዶሮ ነጋዴዎች፤ ዋጋው ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ከልምዳቸው ተናግረዋል፡፡
በመገናኛ ሾላ በአትክልት ተራና በሰሜን ማዘጋጃ ሾላ ገበያዎችም የዓውዳ አመት ገበያው ምን እንደሚመስል የአዲስ አድማስ ሪፖርተሮች የቃኙ ሲሆን፤ በአትክልት ተራ 1ኛ ደረጃ ቀይ ሽንኩርት፡- 9 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 40 ብር፤ ሲሸጥ ሰንብተዋል፡፡
በመገናኛ ሾላ ገበያ፡- ዶሮ አነስተኛው 180 ብር፣ ደህና ስጋ ያለው 300 ብር ተሸጧል፡፡ የፈረንጅ እንቁላል (አንዱ) በ3ብር ከ50፣ የሀበሻ እንቁላል ደግሞ በ3 ብር ከ75 ይሸጣል፡፡ በሾላ ገበያ አንድ ኪሎ ቂቤ ለጋው 250 ብር፣ መካከለኛው ከ190- 200 ብር፣ የበሰለው 160 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ሪፖርተሮች ያነጋገሯቸው ነጋዴዎች ገልፀዋል፡፡
በዚሁ ገበያ በግ፡- ከ1 ሺህ 400 እስከ 3 ሺህ 200 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ለቅርጫ  የሚሆን በሬ የገዙ ሰዎችን እንደገለፁልን ከ 9 ሺህ ብር መእስከ 16 ሺህ ብር ባለው ዋጋ መካከለኛ ከሚባለው እስከ ከፍ ያለው በሬ መግዛት ይቻላል፡፡
የዘንድሮን የገና ገበያ ለየት የሚያደርገው ባልተለመደ ሁኔታ የገና ዛፍ ገበያ መድራቱ ነው፡፡ 150 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያለው የገና ዛፍ - 700 ብር፣ ባለ 180 ሴንቲ ሜትር - 1200 ብር ሲሸጡ ከዚያም ከፍ ያለው ደግሞ እስከ 2 ሺህ ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሀበሻ ጥድን ይወክላል የተባለው ሰው ሰራሽ የገና ዛፍ እንደየመጠኑ ከ250 ብር እስከ 800 ብር ይሸጣል፡፡ የገና ዛፎቹን ለማስዋብ ጌጣጌጦችና መብራቶች ያስፈልጋሉ፡፡ በዛፉ ላይ ላይ የሚንጠለጠሉ አብረቅራቂ ኳሶች 12 ፍሬ የሚይዘው 1 ደርዘን 120 ብር ሲሸጥ፤ በዛፉ ዙሪያ በራ የሚለው መብራት 95 ብር፣ ከብልጭልጭ ወረቀት የሚሰራው የዛፍ ማስጌጫ እያንዳንዱ ከ30-45 ብር ይሸጣል። ፖስት ካርድ ከ6 ብር ጀምሮ የሚገኝ ሲሆን፤ ባለመብራቱ ፖስታ ካርድ ከ35-40 ብር ይሸጣል፡፡ ባለው ዋጋ ይገኛል፡፡ በቀይና ነጭ ቀለም ያሸበረቁ የገና ኮፍያዎችም ከ100 እስከ 130 ብር እንደሚሸጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የገና ዛፍ ገበያ የደራበትን ምክንያት የጠየቅናቸው ነጋዴዎች፤ ምክንያቱ ለእነሱም ግልፅ እንዳልሆነ ጠቁመው የገና ዛፍ ፈላጊው በመጨመሩ ዛፉን በብዛት እየሸጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች፤ የገና ዛፍ በእኛ ባህል ውስጥ የማይታወቅ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ አብዛኛው ሰው ዛፉን እንዲሁ ይገዛል እንጂ ትርጉሙን አያውቁም፡፡ “የገና ዛፍ ይህ የባህል ወረራን የሚያሳይ ግሎባላይዜሽን ያመጣብን ጣጣ ነው” ብሏል አንድ፤ አስተያየት ሰጭ፡፡

Read 4176 times