Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 March 2012 09:18

ስትታጭ ያጣላች፤ በሠርጓ ታጋድላለች!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንዳንድ ዕውነተኛ ታሪክ ሲቆይ እንደ ተረት ይወራል፡፡ አንድ ከረዥም ጊዜ የሥራ ልምድ በመነሳት ታዋቂ ጠበቃ የሆኑ ሰው ደምበኞች ወይም ባለጉዳዮች ይዘው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ጠበቃዎች “የልምድ-አዋላጅ” ይባላሉ፡፡  የልምድ- አዋላጅ የተባሉበት ምክንያት ሙያውን በት/ቤት ወይም በኮሌጅ ተምረው አውቀውት ሳይሆን፤ እንደው በዘልማድ በትንሽ ደረጃ ጥብቅና በመቆም ጀምረው ለከፍተኛው ፍርድ ቤትም ጠበቃ እስከመሆን የደረሱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት የልምድ - አዋላጅ ደግሞ በራፐር - ፀሐፊነት ወይም ማመልከቻ ከመፃፍ ተነስተው ቀስ በቀስ አንቀፆቹን ያወቋቸውና ወደ ጥብቅናው ሥራ የሚገቡት ናቸው፡፡ ከተራ ጉዳይ አስፈፃሚነት ወደ ጥብቅና የሚሸጋገሩም አልፎ አልፎ ይገኛሉ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን የልምድ - አዋላጁ ጠበቃ የያዟቸውን ደንበኞች፣ አፈ-ጮማው ራፖር-ፀሐፊ ይነጥቃቸዋል፡፡ የልምድ - አዋላጁ ማን እንደነጠቃቸውም ሆነ ለምን ደምበኞቻቸው እንደተውአቸው አላወቁም፡፡ ስለዚህ በፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ቀን ልደታ አካባቢ አድፍጠው ይጠብቃሉ፡፡

ለብቻቸው ቆመው እንዲህ ብለው ያስባሉ፡-

“ይህን ደመኛ ጠላቴን ብቻ ልወቀው፡፡ እኔ በስንት ትውውቅ ያፈራሁዋቸውን ደንበኞች ነጥቆኝማ እዚች አገር ላይ አይኖራትም! አሳያዋለሁ፡፡ የእኔም እንጀራዬ ነው የእሱም እንጀራው ነው! ግን እንጀራውን የሚጋግረው የእኔን እንጀራ አሳርሮ መሆን የለበትም!

ደምበኞቼስ ቢሆኑ ምን አጉድዬባቸው ነው ወደሱ የታጠፉት? መቼም ህጉን አውቀው እኔን አያውቅም ብለው አይደለም፡፡ አታሏቸው ነው! አዎ የጠበቃ ምላስ መንታ ነው፡፡ የሆነ ያልሆነውን ቀበጣጥሮ አሳምኗቸው፤ አጭበርብሯቸው ነው! ይሄ ቀጣፊ!” ይህን እያሉ በትዕግሥት አድፍጠው መጠበቃቸውን ቀጠሉ፡፡

በቀጠሮው ሰዓት ራፖር ፀሐፊው ጠበቃ ከልምድ አዋላጁ የነጠቃቸውን ደንበኞች አስከትሎ ይመጣል፡፡ ራፖር - ፀሐፊው ጠለቅ ያለ የጥብቅና ዕውቀት ስለሌለው ከደምበኞቹ ጋር የህግ ዝርዝር አያወራም፡፡ ለዚህም የሚጠቀምበት ዘዴ በአንድ በሁለት ሜትር ርቀት ከደምበኞቹ ፊት ፊት ቶሎ ቶሎ መሮጥ ነው፡፡ ደምበኞቹ ከሱ እኩል ለመራመድ በፍጥነት ከኋላ ኋላው ኩስኩስ ይላሉ፡፡ የልምድ-አዋላጁ ጠበቃ በዕድሜ ገፋ-ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ተከትለው ሲደርሱባቸው ከኋላ ከኋላ ብዙ ይጣጣራሉ፡፡ ሆኖም የራፖር - ፀሀፊውን ፈጣን እርምጃና የደምበኞቹን እሱን ተከትሎ መሮጥ፣ በጭራሽ ሊደርሱበት የሚችሉት አልሆነም፡፡ ስለዚህም ተስፋ-ቆርጠው ቆሙ፡፡ ከዚያም፤ “የው በዚህ ዓይነት ፍርድ ቤቱን ታልፉታላችሁ!” አሉ፡፡ ወይኗን ለመብላት ዘላ ዘላ መድረስ ያቃታት ቀበሮ “እቺ ወይን’ኮ ገና ጥሬ ናት” እንዳለችውና ጥላ እንደሄደችው መሆኑ ነው!

***

ከልምድ - አዋላጅ ፓርቲ ይሰውረን፡፡ ከሜካኒካል አስተሳሰብ ያድነን! በአፈ - ጮማነት እንጀራ ከሚቀማም ሆነ ጉሮሮ ከሚዘጋ ይሠውረን፡፡ እንደ ልምድ - አዋላጁ ጠበቃም ሆነ እንደቀበሮዋ ተስፋ ቆርጠው The grapes are sour (ወይኗ ጥሬኮ ናት!) ከሚሉ ሰዎች ዛቻ ያውጣን፡፡ መጀመሪያ የሚፎክሩ፣ መፈክር እንደ በቅሎ የሚያሰግሩ፣አንዱ ያለውን እየደገሙ ያወቁ የሚመስላቸው፤ አያሌ ፖለቲከኞች በሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ከትላንት እስከዛሬ እንደታዩ ናቸው፡፡ ንግግራቸውን ጨርሰው፤ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ!” እስኪሉ፤ ብዙ  ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ “ሰው በአንደበቱ፤ ውሻ በጅራቱ” ከሚል መርህ የማይወጡት እኒህ ፖለቲከኞች፣ እንኳንስ ዕውነት ተናግረው ሊያሳምኑ፤ ራሳቸው ለራሳቸው ዕውነት መሆናቸውን ያሳመኑ አይደሉም፡፡ ይልቁንም እኔ የማምነውን ያላመነ “ውጉዝ ከመዓርዮስ” ነው፤ ብለው ስም ለጥፈው፣ ቅፅል ቀፅለው መወንጀልን የሚመርጡ ይሆናሉ፡፡ በራስ - የአለመተማመን በሽታ ሌሎች ዕምነት የላቸውም ውንጀላ ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ በአቅም - ማነስ ተገምግመው እስኪገላገሉ ድረስ አቅም አለኝ እያሉ መፎከር የዘመኑ ፋሽን የሆነ ይመስላል፡፡ ሁሌ የሚታያቸው ሹመት ነው፡፡ መሰላል ሁሉ ወደላይ መውጫ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ በመጨረሻ ግን መሰላሉ መውረጃም እንደሆነ ሲነግሩዋቸው ምድር ሰማይ ይዞርባቸዋል፡፡ በቃለ - ኑዛዜያቸውም፤ “በለጠች እንዲሉኝ አክሱም ፅዮን ቅበሩኝ” ማለት ይሆናል ዕጣ - ፈንታቸው፡፡ አፈ ቀላጤ፣ አፈ-ጮማ፣ አፈ-ቅቤ፣ አፈ-ጩቤ፣ አፈ-ንጉሥ፣ አፈ-ክልስ … ሁሉም የአፍ እንጂ የልብ ሰዎች አይደሉም፡፡ የአጣቢ-ልጅ አለቅላቂ ነው እንደሚሉት ነው አበው፡፡ ልሣን እንጂ ልቡና የላቸውም፡፡ “ቀናቸው ደርሶ እስከሚፋቱ ይባላሉ አንቱ”  እንደሚለን ነው ገጣሚው፡፡ ለሰው ከመገዛት ለህሊና መገዛት ቀዳሚ ሊሆን ይገባዋል፡፡ “አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽም” ለሚክዱ ትምህርት ነው፡፡ የህዝቡ ጥቅም የት ጋ ነው? እስካሁን ከራሴ ጥቅም ይልቅ ለአገር ምን ፈየድኩ የሚል ጥያቄ በህሊናችን መመላለስ ካቆመ “አንድም ለንግሥ፣ አንድም ለኪስ” ካልሆነ በቀረ ሌላ አጀንዳ አይኖረንም፡፡ አድር-ባይነት የሙስና ቡጥ ነው - በተለይ ዛሬ!

ሶረን ኪርክጋርድ የተባለ ፀሐፊ “አድናቂነት ተደስቶ እጅ መስጠት ነው፡፡ ቅናት ደግሞ ተከፍቶ ራስን ማጨት /እኔ እሻላለሁ ማለት ነው” ይላል፡፡ ተደስቶ እጅ - ከመስጠትም፣ ስለተከፋን ብቻ ዘራፍ እኔ እሻላለሁ ከማለትም፤ ይሠውረን! የህዝብ አስተማሪ፣ አንቂ እና አሳዋቂ ነኝ የሚል አካል ወይም ግለሰብ የመጀመሪያ ትምህርቱ መሆን ያለበት አለመታበይ ነው፡፡ አለመገበዝ ነው፡፡ ትህትና - አዘል ስብዕና ነው፡፡ ቢያንስ፤ “ራሱን ዝቅ ዝቅ ያደረገ ከፍ ከፍ ይላል” የሚለውን የመፅሀፍ ቃል ያስታውሳል! ከሙስና እጁን ያልሰበሰበ ስለ ሙስና ሊያስተምር እንደምን ይቻለዋል? የውስጥ ሌቦችና የውጪ ሌቦች እያልንስ እንደምን ንፁህ ለውጥ ለማካሄድ እንችላለን? አንዱ የአገራችን ገጣሚ፤

“… ዘመንና ዘመን እየተባረረ

ይሄው ጅምሩ አልቆ ማለቂያው ጀመረ …” ያለው እንዳይፈፀም፤ ገጣሚ ነቢይነት አለውና፤ እንጠንቀቅ፡፡ ካድሬነትን እንደርስተ-ጉልት የያዙም ሆኑ፣ ሰሞነኛ ሹመኞች፤ መሥራች ነን የሚሉም ሆኑ አዲስ - ትክል ህሩያን፤ አሊያም ባለከዘራ አንጋፋዎችና በተስኪያን በመሳሚያቸው ሰዓት በፓርቲ ቤተ መቅደስ ካልቀደስን የሚሉ ሁሉ፣ ከሙስና ካልፀዱና መልካም ስብዕና ካላፈሩ ለውጥ እርም ናት!

ታዋቂው የአገራችን ፀሀፌ-ተውኔት በአንደኛው ቴያትሩ ላይ “ካድሬ ማለት ልክ እንደፍራንኩ ገፅ ነው፤ በአንድ በኩል ሰው፣ በአንድ በኩል አውሬ! ሥልጣን በሸተተው ማግሥት አካሄዱ፤ አረማመዱ ሁሉ እንደድመት ኮርማ ይሆናል?” ይለናል፡፡ ይህን በሀገራዊ ተረት ብንገልፀው “ስትታጭ ያጣላች፤ በሠርጓ ታጋድላለች” እንደ ማለት ነው፡፡

 

 

Read 4121 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:23