Monday, 09 January 2017 00:00

“ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል” - ሼክስፒር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ባልና ሚስት የገና በዓል ፌሽታ ወዳለበት አንድ አደባባይ በመኪና ይሄዳሉ፡፡
“የዘንድሮን ገና በደመቀ ሁኔታ ነው የምናከብረው” አለ ባል፡፡
“እንደሱ እንዳናደርግ እኔ ትላንት የገና ወጪ ስጠኝ ብልህ፣ እንደልማድህ ‹እሱን ለእኔ ተይው› አልከኝ” አለች ሚስት፡፡
“የልጆቹን ፍላጎት አንተ አታውቅም” ብልህ፣ “እንዴት? አባታቸው አይደለሁም?!” ብለህ ትቆጣለህ፡፡ አሁንም የገበያውን ነገር ካወቅኸው ገላገልከኝ”
ጥቂት መንገድ እንደሄዱ፣ አንድ የትራፊክ መብራት ጋ ይደርሳሉ፡፡ ባል ቀይ መብራቱን ጥሶ ይሄዳል፡፡
ትራፊክ ፊሽካ ይነፋል፡፡
ሹፌር ያቆማል፡፡
ለሚስቱ፤
“የዓመት ባል ገንዘብ ፈልጎ ነው እንጂ እኔ ምንም አላጠፋሁም!” ይላታል፡፡
“ቀይ መብራት ዘለህ መጥተህ፣‹እንዴት አላጠፋሁም› ትላለህ?”
“የአንቺን አላምንም፤ትራፊኩ የሚለኝን ልስማ!”
ትራፊኩ መጣ፡፡ ሹፌር መስተዋቱን ዝቅ አደረገ፡፡
ትራፊክ - “መንጃ ፍቃድ?”
መንጃ ፍቃዱን ጠየቀ፡፡
ሹፌር አሳየውና፤ “ምን አጠፋሁ ጌታዬ”
ትራፊክ፤ “ቀይ መብራት ጥሰዋል”
ሹፌር ፤“በጭራሽ አልጣስኩም!”
በመካከል ሚስት ትገባና፤
“እኔ ተው እያልኩት ነው የጣሰው፡፡ ግን ችግሩ እዚህ አገር፣ሰዎች ዶክተር ስለሆኑ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡
ባል፤“ዝም በይ! አፍሽን ዝጊ! … እሺ ትራፊክ ይቅርታ አድርግልኝ”
ትራፊክ፤ “ጥፋትዎ ያ ብቻ አልነበረም፡፡ 30 ኪ.ሜ በሰዓት በሚነዳበት መንገድ፣50 ኪ.ሜ በሰዓት በመንዳትዎ ይጠየቃሉ፡፡”
ሚስት፤
“እኔ ቀስ ብለህ ንዳ ብዬው እምቢ ብሎኝ ነው - ነግሬዋለሁ!”
ባል፤ “አንቺ ሴትዮ፤አፍሺን ዝጊ ብያለሁ!!”
ትራፊኩም፤ “እመቤት፤ሁልጊዜ እንደዚህ ነው የምትወያዩት?”
ሚስት፤
“ኧረ ጌታዬ፤ሌላ ጊዜ ጨዋ ነው፡፡ እንዲህ ሲጠጣ ብቻ ነው እንደዚህ የሚናገረኝ!”
ትራፊክ፤
“አሃ!!”
*   *   *
 አውቃለሁ፣ በቅቻለሁ ብሎ ሁሉ እኔ እንዳልኩት መሆን አለበት የማለት ግትርነት ደግ አይደለም፡፡ የየትኛውም ሙያ ባለቤት እንሁን፡፡ ከህግ በላይ አይደለንም፡፡ በሙያ ክህሎት አገኘን ማለት ከሀገርና ከሀገሬው በላይ ሆንን ማለት አይደለም፡፡ ዝርዝር ጉዳዮች ለዐቢዩ ህግ ተገዢ መሆናቸውን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ የትራፊክ ህግን ማክበር ከሙያችን በላይ የሆነውን ያህል፤ ለትራፊኩ የእኛን ሙያ ማክበር፣ ከሙያው በላይ መከበር እንዳለበት፣ አሊያም እኩል የሙያ አክብሮት ሊኖር እንደሚገባው መገንዘብ እንዳለበት ሊያስተውል ተገቢ ነው፡፡
በቤተሰብ ህግም የባል ሙያ መከበሩ እንዳለ ሆኖ፣ ሚስት የምትለውን አለማዳመጥ ወይም መናቅ ኪሳራ ነው!!
ይህ ነገር በበዓል ሰሞን በጣም ግዘፍ ይነሳል! መደማመጥ በበዓል ሰሞን ምንዛሪው ብዙ ነው። በአንድ ወገን ባህል አለ፡፡ በሌላ ወገን ዘመናዊ ስሜት አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በአውሮፓውያን የልደት ዛፍ (X-mas Tree) እና በእኛ ቄጤማና ነጭ አረቄ ስሜት መካከል እንደምንገነዘበው፡፡ በልጆቻችን ላይ የሚፈጠረው ስሜት፣ በወላጆቻችን ላይ የሚደረተው ስሜት፣ ማንም ስለ ምንም ማብራሪ ሳይሰጥ፣ በዘፈቀደ መከበሩና እንደፈረደብን ሳንወያይበት፣ በተድላና በደስታ ማለፋችን፤ የአልፋ - ኦሜጋ ሕግ መሆኑ ግራ ያጋባል፡፡
ባህልን መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ባህልን መከለስ ምርጫ ነው፡፡ የሁለቱን ልዩነት ማወቅና ማስተዋል፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ግዴታ ነው!
የገና በዓልን ስናስብ የክርስቶስን ልደት እናስብ፡፡ የእኛን “ልደት”ን ግን በፍፁም፣ መርሳት የለብንም። በየቀኑ መወለድ፣ በየዕለቱ ማደግ መቼም ያስተዋልነው ጉዳይ ነው፡፡ የየዕለት ውልደታችን ውጤት እገና ዘንድ እሚደርሰው፣ የዓመት ውሎአችንን ጠቅልሎ ነው፡፡ ስለዚህም ከተወለድን አይቀር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መንፈሱ የተሟላ ልደት ይሆንልን ዘንድ እንመኝ! “ከሰማያተ - ሰማያት ወርጄ፣ ከድንግል ማሪያም ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለውን አስታውሶ፣ በስፋት መጠቀም ነው፡፡ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው!” ማለትም ያባት ነው፡፡
በየወቅቱ መወለድ የአዳጊ ልጅ ባህሪ ነው፡፡ እያንዳንዷን እድገት ሳይታክቱ መመርመር ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ለመወለድ ሰብዓ ሰገሎችን ሳንጠብቅ፣ ለየራሳችን ስራ፣ ጥረት፣ ትግል፣ ዕምነት ቦታ መስጠት አገርንና ህዝብን ያሳብባል፡፡ በየዕለቱ ሁላችንም አራስ ነን፡፡ ነገ ግን ወጣት፣ ጎልማሳና አዋቂ እንሆናለን፡፡ በሁሉም ገፅታችን አገራችን ትፈልገናለች!!
የለውጥ አቅም ከለመድነው መፋታት ነው፡፡ ከለመድነው መላቀቅ፣ የአዲስ አዕምሮ ቅያስ ይፈልጋል፡፡ ቅያሱ መንገድ የት እንደሚያደርሰን ለማወቅ፣ የእንቅፋቶቹን ምንነት፣ የእኛን ምርጫና ግባችንን ማወቅ፣ የእኛን ቀጣይ - ዘዴ መቀየስ፤ የለውጥ ሙከራ ባይሳካ ደግሞ መዘጋጀት ዋና መሆኑን … ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ ያም ሲለመድ ደግሞ እንደ ህይወት ይኖራል፡፡ “ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል” የሚለው አባባል ግንዛቤ ውስጥ ይገባል የሚባለው ይሄኔ ነው!! ሁሉንም በቀናው ሂደት ይባርክልን፡፡ ራሳችንን ከአደጋ እንጠብቅ!
መልካም የገና በዓል
 ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች!!

Read 6237 times