Monday, 02 January 2017 07:34

የኢሠማኮ የስፖርት ውድድሮች በፌስቲቫል ደረጃ ማደግ አለባቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የሚያዘጋጀው ዓመታዊ የበጋ ወራት ስፖርት ውድድር ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድዬም ተጀምሯል፡፡ የመንግስትና የግል ተቋማት ሠራተኞች ቡድኖችን የሚያሳትፈው ውድድሩ ለሚቀጥሉት 3 ወራት የሚካሄድ ይሆናል። በኢሰማኮ የበጋ ወራት የስፖርት ውድድሩ ላይ አርባ ሦስት ማህበራት ፤ በአስር የስፖርት ዓይነቶች ሲካፈሉ በአጠቃላይ 17500 ስፖርተኛ ሰራተኞች እንደሚሳተፉ 320 ሴቶች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የበጋ ወራት የስፖርት ውድድሩ ኢሠማኮ በዓመት ውስጥ ከሚያደርጋቸው  ዝግጅቶች አንዱ ቢሆንም በተለይ የክረምት ወቅትን ጠብቆ በሠራተኛው የሚደረገው አገር አቀፍ ውድድር ዋነኛው እንደሆነ ይገልፃል፡፡ አስተያየት ሰጭዎች ውድድሮቹ በየዓመቱ ሲካሄዱ በፌስቲቫል ደረጃ ሰፋ ያለ ነዝግጅት ኖሯቸው፤ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በስፋት ትኩረት ሰጥተውበት እነደ ክብረ በዓል በደመቀ ሁኔታ መካሄድ እንደሚኖርበት ይመክራሉ፡፡
ሠራተኛውን ለማገናኘትና ለማቀራረብ በኮንፌደሬሽኑ የሚደረጉ ውድድሮች ብዙም ትኩረት እያገኙ አለመሆናቸው መለወጥ እንደሚገባውም ይገለፃል፡፡ በኢትዮጵያ የስፖርት እንቅስቃሴ ታሪካዊ ዳራ የነበራቸው ውድድሮቹን ለማጠናከር ኢሠማኮም ይፈልጋል፡፡ ጨዋታዎችን በየዓመቱ በኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አዘጋጅነት ዕድሜ ጠገብ የሠራተኞች ዓመታዊ የስፖርት ዝግጅቶች ብዙ ታሪክ የተሰራባቸውም እንደነበሩየሚናገሩት የኢሠማኮ የማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሥሐጽዮን ቢያድግልኝ ‹‹በማኅበራት መካከል ያለውን  ግንኙነት ለማጠናከርና የሠራተኞችን ውጤታማነት ለማጎልበት አመቺ መድረክ ናቸው፡፡››ይላሉ፡፡
በርግጥም ከኢሠማኮ ቀደምት የስፖርት ውድድሮች የአገራችን ታላላቅ ስፖርተኞች ወጥተዋል፡፡ ብዙዎቹ የተለያዩ ፋብሪካዎች ሰራተኞች የነበሩ ናቸው፡፡ ከእነሱም መካከል ታላላቅ አሰልጣኞች የሆኑት ስዩም አባተ፣ አስራት ኃይሌ እና አብዶ ከድር እንዲሁም ታዋቂው ግብ ጠባቂ ጌታቸው ዱላ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከኢሠማኮ የስፖርት ውድድር የወጡ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከብሄራዊ ቡድን ተሰላፊዎች 90 በመቶ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በቦክስ፣ በአትሌቲክስ እና በሌሎች የስፖርት ውድድሮች ውጤታማ ስፖርተኞች ተገኝተውበታል፡፡
በአጠቃላይ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ የሆኑ ስፖርተኞችን አፍርቷል፡፡ የስፖርት ውድድሩ አገር አቀፍ የሰራተኞች ማህበራት መኢሠማ እና ኢሠማ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ የሚከናወንም ነበር፡፡ ከታላላቅ ስፖርተኞች ውጭ በእግር ኳስ ወደ ከፍተኛ የክለብ ውድድሮች በማደግ የተሳካላቸውም ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኦርቢስ፤ ሲሚንቶ እና ሌሎችም ናቸው፡፡
የኢሠማኮ የማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ እና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ፍስሀፅዮን ቢያድግልኝ ፤ ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት ‹‹በብሄራዊ ደረጃ የሚካሄደው የስፖርት ውድድሩ ላለፉት 15 ዓመታት መሰረቱን ጠብቆ እየተካሄደ ቢሆንም በተሻሻለ ደረጃ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ›› “ሠራተኛው በአሁኑ ወቅት ስፖርቱን የራሱ አድርጎ አለማየቱ፤ በየተቋማቱ ስፖርቱን የሚወድ አስተዳደር እየጠፋ መሆኑ ለምንፈልገው የለውጥ እና የመሻሻል እንቅስቃሴ እንቅፋቶች ናቸው” ብለውም ይናገራሉ፡፡ ዘንድሮ በሚገባ ተዘጋጅተው ወደ ውድድሩ የገቡ አዳዲስ ማህበራት ሲኖሩ ሌሎች አንጋፋ ማህበራት ወደ ውድድር መመለሳቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ ፒፒ ከረጢት ማምረቻ ከነባሮቹ ማህባር የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ ኮካ ኮላ፤ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፤ ዋልያ ቢራ፤ቴክኖ፤ ቃሊቲ ብረታብረትና ፤ ተክለብርሃን ኮንስትራክሽን በሠራተኛው ለመጀመርያ ጊዜ ከሚሳተፉት ይገኙበታል።   ስፖርቱን የሚወድ አመራር ካለ ስፖርቱ ያድጋል፣ ከሌለ ይወድቃል የሚሉት የኢሠማኮ የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢው በዘንደውሮው የበጋ ወራት የስፖርት ውድድር የተስተዋሉ ሁኔታዎች እንደምሳሌ የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ከቋሚ ተሳታፊዎች መካከል  ሙገር፤ አምቼ ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ የማይሳተፉ ሲሆን የአንዳንዶቹ ማህበራት ተሳትፎም የቀዘቀዘም ሆኗል፡፡ ‹‹በየመስሪያቤቶቹ ስፖርት የሚወዱ አመራሮች፤ እና መዋቅሮች ካሉ የኢሠማኮ የስፖርት ውድድር መጠናከር እንደሚችል ጤንነታቸው የተጠበቀ አምራች ሰራተኞችን ለማፍራት እንደሚቻል ሁሉም ተቋማት በመገንዘብ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡›› በማለት ለስፖርት አድማስ ያስረዱት አቶ ፍስሃፅዮን ቢያድግልኝ ‹‹አሁን ኢሠማኮ ትኩረቱ የራሱን የስፖርት መሰረተ ልማት በመገንባት ላይ አድርጓል፡፡ ሁሉንም ያሟላ የስፖርት ማዕከል ለመፍጠር ታቅዷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ለሚኒስተር መ/ቤቱ የመሬት ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን፣ ሰራተኛው ስፖርቱን የራሱ አድርጎ በንቃት እንዲሳተፍ፤ በስፖርት ማዕከሉ ግንባታ አስፈላጊው ግንዛቤ እንዲኖረውና በገንዘብ መዋጮ እና ድጋፍ እንዲተባበር እየሰራን ነው፡፡ ›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ የኢሠማኮ የስፖርት ውድድሮች ተቋማት አገልግሎቶቻቸውን፤ ምርቶቻቸውን፤ የአስተዳደር እና የውጤታማነት ተመክሮዎቻቸውን የሚያስተዋውቅ መድረክ መሆኑን በመገንዘብ በቀጣይ ለሚኖራቸው ተሳትፎ በቂ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አቶ ፍስሐፅዮን ቢያድግልኝ መክረዋል፡፡ በቀጣይ የኢሠማኮ ዓመታዊ የስፖርት ውድድሮችን ለማጠናከር  ከመንግስት፣ ከባለሀብቶች፣ ከሚኒስተር መ/ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለመስራት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በመግለፅም፤ ከኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌደሬሽን ጋር ያለውን የተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማዳበር በስፖርቱ የበለጠ መሻሻል ለመፍጠር ትኩረት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

Read 2246 times