Saturday, 31 December 2016 11:39

“ድንጋይ እንዳይወረወር----- ሃሳብ መወርወርያ-----መድረክ!!”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(5 votes)

የፖለቲካ ፓርቲዎች ----የትም አገር የሚቋቋሙት----- ሰማይ ቤት ጽድቅ አይደለም---ለምድር ሥልጣን ነው። በምርጫ ተፎካክረው፣ አማራጭ ፖሊሲ አቅርበው! (ሲኖር ነው ታዲያ!) ህዝብን አሳምነው------አማልለው ወይም “አታለው” ----- ሥልጣን ለመያዝ ነው፡፡ አገር  ለማስተዳደር ----- መንግስት ለመሆን!! (ህገ መንግስታዊ መብት ነው!!)
የሚቀድም ሃሳብ ግን  እነሆ!! ------ በምንወዳትና በምትወደን አገራችን ስንኖር ------ (አለመውደድ አያሰቅልም!!) ------ ሁልጊዜም ከዛሬ ነገ የተሻለ ህይወት ለመምራት መትጋት አለብን----ኢህአዴግ ስለፈለገ ወይም ተቃዋሚዎች ስላልፈለጉ አይደለም-----እኛ ዜጎች በየቀኑ ወደ ላይ ማደግ መመንደግ ---- እንጂ ወደ ታች ማሽቆልቆልም ሆነ ----- ወደ ጎን መገፍተር ስለሌለብን ነው----ጨርሶ መፍቀድም የለብንም----እምቢተኝነት ወይም አመጽ አሊያም አብዮት አይደለም!! -----(አቤት አብዮት ስጠላ!!)
የተፈጠርነው ለክብር ነው ---የተፈጠርነው ለስኬት ነው----የተፈጠርነው ለሳይንስና ፈጠራ ነው----የተፈጠርነው ለእድገትና ብልጽግና ነው--- የተፈጠርነው ለተሻለ ህይወት ነው-----ስለዚህ ሁሌም ከዛሬ ነገ የተሻለ ህይወት መመኘታችን ትክክል ነው፡፡ እናም ---- የትላንት ህይወታችን ፈትሸን-----ልምዳችንን ጨምቀን-----መንግስትን በ”ጥልቀት” ገምግመን-----ራሳችንን አድሰን -----ሃቁን በህሊናችን መዝነን----የተሻለ ነገን ለየራሳችን መፍጠር የተፈጠርንበት ዓላማ ነው፡፡
እናላችሁ-----ተቃዋሚዎች ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርጉት ሰላማዊ ፉክክር ሁሉ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ስለዚህ እየዞሩ ለህዝብ ሃሳባቸውን ---- መንገር----ፖሊሲያቸውን ማስተዋወቅ…ከሥልጣን ተፎካካሪያቸው ከኢህአዴግ የሚሻሉባቸውን ነጥቦች ዘርዝረው ማስረዳት--- (ትረምፕ ከአሜሪካ የፖለቲካ ልሂቃን ተሽለው ተመርጠዋል!) በአጠቃላይ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች------የምርጫ ሰሞን ብቻ ሳይሆን (ህዝብ እኮ ሁሌ አለ!)---- በአዘቦቱም ቀን ጭምር፣ ራሳቸውንና ፓርቲያቸውን ለህዝቡ መሸጥ------ማስተዋወቅ------መወያየት---መግባባት------አለባቸው፡፡ (ልብ ለልብ!!) በነገራችን ላይ እንኳንስ “ነገ እንመራዋለን” የሚሉትን ህዝብ ------ ኢህአዴግንም ጭምር በጥልቀት ማወቅ---- መረዳት---- መገንዘብ ---- አለባቸው ---- የሥልጣን ተፎካካሪያቸውን!! (ያለዚያ ማሸነፍ ህልም ይሆናል) ቢቻል የመረረ ጥላቻ አለማዳበር ይመረጣል፡፡ (“ኢህአዴግን ውደዱት”---አልወጣኝም!!) ፍቅር ትዕዛዝም ሆነ ፕሮፓጋንዳ አይሰማም፡፡ (ፖለቲከኛ አይደለማ!)
እውነቱን ለመናገር በተቃዋሚዎችም አልፈርድም። “ለምን አውራውን ፓርቲ ትጠምዱታላችሁ?” ብዬ ለመናገር ወኔ ይከዳኛል፡፡ እንኳን እኔ ራሳቸውም ወኔ የሚከዳቸው ይመስለኛል፡፡ (ወኔና ፍቅር ሃቀኛ ናቸው!) ይታያችሁ --- ያለፉትን 25 ዓመታት የፖለቲካ ፓርቲ መስርተው ---- ተቃዋሚነታቸውን በአደባባይ አውጀው ---- ደጋፊዎቻቸውን ለማግኘት ከሸገር ወጣ ሲሉ ---- ከወረዳና ከዞን የኢህአዴግ ተመራጮች ጋ ግብግብ ገጥመው!! በየ5 ዓመቱ ምርጫ ሲመጣም ---- አሸንፈው ፓርላማ ከመግባት ይልቅ---- ወህኒ እንደሚገቡ እርግጠኛ ይሆኑ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ነፍሴ ደግሞ ---- ጎረቤታችን ኬንያና ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የሞከሩትን “ስልጣን ማጋራት” (power sharing) እንኳን ሊሞክረው----ድንገት ቢሰማው፣” ኤሌክትሪክ ካልጨበጥኩ” ነው የሚለው፡፡ (የተማሪዎች “cost sharing”! ነው የሚያውቀው!)  
አያድርስና----አንድ ተቃዋሚ የ7 ወር ነፍሰጡር፣ ድንገት ተነስታ---፣” ሥልጣን አማረኝ፤ ውለዱ!” ብትልስ፣ ምን ይኮናል!!! ሰላማዊ ሰልፍ ባልተጸፈ ህግ በተከለከለበት የ97 ምርጫ ማግስት፣ ያየሁት ኮሜዲ ትዝ አለኝ።  አንዷ እርጉዝ፤ ”ሰላማዊ ሰልፍ አማረኝ!!” ብላ ባሏን ታፋጥጠዋለች፡፡ እናላችሁ----ተቃዋሚዎች ለሩብ ክ/ዘመን ሥልጣን ቢመኙም ጨርሶ አላገኙም፤መንግስት ሆነው አያውቁም፡፡ እንኳንስ አንድ ሙሉ መንግስት፣ሩብም አልደረሳቸውም፡፡ (“የስጋና የሥልጣን ሩብ የለውም!) ተቃዋሚዎች ከታሪካዊው የ97 ምርጫ በኋላ ከመንግስት ሥልጣን በእጅጉ ርቀዋል፡፡ (“አሳይተህ ነሳኸን” ቢሉ ይፈረድባቸዋል?!) በጣም በቅርቡ ቢሆንም ኢህአዴግ የመንግስት ሥልጣኑን ብቻ ሳይሆን የፓርላማውን መቀመጫ ጭምር ጠቅልሎ መውሰዱ ግን የሚያስኬድ እንዳልሆነ ---- (“ህዝብ መርጦኝ ነው” ቢልም!) አንዳንድ የኢህአዴግ አንጋፋ አመራሮች በድፍረት ሲናገሩ ሰምተናል፤ በቴሌቪዥን መስኮት፡፡ (ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ አሁንም የህዝብና የመንግስት ንብረት ናቸው??)
የህዝባዊ አመፁ ሰሞን በኢህአዴግና በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ግምገማ ሲሰጡ ከነበሩ አንጋፋ ታጋዮች አንዱ  አቶ በረከት ስምኦን፤ ‹‹ኢትዮጵያን የሚያህል ትልቅ አገር በኢህአዴግ ብቻ ሊወከል አይችልም›› ያሉ መሰለኝ። (ቃል በቃል ሳይሆን ሃሳቡን ነው!) ፓርላማው ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በኢህአዴግ ብቻ መሞላቱንም እንደ ችግር ገምግመውታል፡፡ (‹‹በእርግጥ ህዝብ መርጦን ነው!›› ማለቱን አልዘነጉትም- እንዳይረሳ!) ኢህአዴግ 100 ፐርሰንት አሸንፏል በተባለበት የ2007 ምርጫም ቢሆን እንኳን ተቃዋሚዎችን የመረጠ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን አስረግጠው ተናግረዋል - ይሄ እውነታ ለማይዋጥላቸው የፓርቲያቸው ካድሬዎች ጭምር በሚመስል ቅላፄ! የምርጫ ሥርዓታችን ግን ‹‹ያሸነፈ ይጠቀልላል!” የሚል በመሆኑ አንድም ተቃዋሚ እንኳ ፓርላማ መግባት አልቻለም ብለዋል፤ አቶ በረከት። (ያልገቡበትን ምክንያት እንጂ አለመግባታቸውንማ ዓለምም ያውቀዋል!) ለእዚህ መፍትሄው የምርጫ ሥርዓቱን ማሻሻል ነው ብለዋል (ተመስጌን ነው!) ለቀጣዩ ምርጫ ይደርስ ይሆን? እንዴታ! (‹‹ካልታዘልኩ አላምንም!›› ማለት መብታችሁ ነው!!)
በነገራችን ላይ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች… “ኢህአዴግ ያልተጠየቀውን ይመልሳል” ሲሉ ይወቅሳሉ። (እስኪጠየቅ መጠበቅ አለበት እንዴ?) በእርግጥ እነሱ ሊሉ የፈለጉት አልጠፋኝም፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤” ዋና ችግሩ የምርጫ ሥርዓቱ አይደለም›› ይላሉ፡፡ (ታዲያ ምንድን ነው?) ሲባሉ… ‹‹የምርጫ ሂደቱ!›› ባይ ናቸው፡፡ ‹‹የምርጫው… ነፃ…ፍትሃዊና…ዲሞክራሲያዊ… አለመሆን ነው ችግሩ›› በዚህ ብቻ ግን አያበቁም። ምርጫ በመጣ ቁጥር ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥርጣሬ ወደሚያዩት የምርጫ መ/ቤት ጣታቸውን ይሰነዝራሉ - ወደ ምርጫ ቦርድ!! ‹‹የቦርዱ ገለልተኛነት ተረጋግጦ ሁሉም ወገን እኩል የሚተማመንበት የምርጫ አስፈፃሚ እስካልተፈጠረ ድረስ … ሺ ጊዜ የምርጫ ሥርዓቱ ቢሻሻል ዋጋ የለውም›› ባይ ናቸው፤ ተቃዋሚዎች፡፡ ሌሎች ተቃዋሚዎችስ ምንድን ነው ሃሳባቸው? ኢህአዴግ ነፍሴስ? ምሁራንስ? የንግዱ ማህበረሰብስ? ጋዜጠኞችስ? የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ  ይናገር… ይተንፍስ…ሃሳብ ያዋጣ… (ህዝብ ሲታፈን ---- የሚያስከትለውን ጣጣ  አይተነዋል?!)
እኔና ኢህአዴግ ነፍሴ ሃሳባችን ለየቅል ነው እንጂ ---- ዜጎች ሃሳባቸውን እንደ ልብ የሚተነፍሱበት መድረክ በብዛት መፈጠር ያለበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ኢህአዴግን ብሆን ኖሮ ምን እንደማደርግ ታውቃላችሁ?… ያንን የህዝብ አመፅና ቁጣ (ብሶት…በደል…መታፈን…የመብት ጥሰት… ድህነት… የኑሮ ውድነት.. የነፃነት ምህዳር መጥበብ… ወዘተ…) ካየሁ በኋላ፣ ተርፎ ከሞላው ኤፍኤም ሬዲዮ… ቴሌቪዥን ጣቢያ----አንዱን ለህዝብ ብሶት መተንፈሽያ አደርገው ነበር፡፡ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን ቅሬታ…ትችት…. ያለ ገደብ በነፃነት የሚያሰማበት! (አቶ በረከት፤ “ዲሞክራሲያዊ ህዝብ አልፈጠርንም!” ብለው ነበር) እናም-----ይህንን ሚዲያ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ድምፅ!›› እለዋለሁ፡፡ ትክክለኛው ‹‹የህዝብ ድምፅ›› ይስተጋባበታላ!
ኢህአዴግ ይሄን የማያባራ የህዝብ ተቃውሞና አመፅ…. በዓይኑ በብሌኑ ማየት እስከጀመረበት ዓመት ሁለት ዓመት ድረስ ያለውን አምርሬ  ልወቅሰው አይዳዳኝም፡፡ ለምን ቢሉ … ላለፉት 25 ዓመታት የሚያውቀው ህዝብ “ሁሉን ቻይ ነዋ!” እናም አምባገነንም ዲሞክራሲያዊም ሳይሆን እያጣቀሰ ሲገዛን መቆየቱን እቀበለዋለሁ፡፡ (“ኢህአዴግም እኮ አፍሪካዊ ነው!”) እናም … ከዲሞክራሲ በፊት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከነፃነት … በፊት ለሆድ ጥያቄ … ትኩረት ቢሰጥ ላያስወቅሰው ይችላል በወቅቱ! (ግን ኢህአዴግ የታገለው ለዳቦ ነው? ለነፃነት?) እውነት ለመናገር … ህዝብ እንዲህ አምርሮ የኢኮኖሚም--- የዲሞክራሲም ጥያቄ ያቀረበበት ዘመን የለም፡፡ ህዝብ የፈለገ ቢብስበት … ለዓመት የዘለቀ ተቃውሞ ያደረገበት ጊዜ የለም፡፡ (በ5 ዓመት አንዴ በየአዳራሹ አለቃቅሶ ይወጣለት ነበር!) አንድ ነገር መረዳት ያለብን -----እንኳን ኢህአዴግ የአሜሪካው ዲሞክራት ፓርቲና መሪዎቹ ቢመቻቸው፣ እልም ያለ አምባገነን ለመሆን ዝግጁ እንደሆኑ፣በምርጫው ሽንፈት ማግስት ጀምሮ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች መገንዘብ ችለናል፡፡ ግን የአሜሪካ ሲስተም ፈጽሞ አይፈቅድም!! (እኛ እኮ ሲስተም የሚባል ራሱ የለንም!) እናላችሁ----የኢህአዴግን ጉድ የማየው … ከአሁን በኋላ ነው፡፡ በቅርቡ በተዋቀረው የጠ/ሚኒስትሩ አዲስ ካቢኔ (ሹም ሽር!) ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊነታቸው የተነሱት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ በ‹‹ቀውጢው›› ሰዓት … ለአንድ የኤፍኤም ሬዲዮ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ የተናገሩት ሃሳብ ሁሌም አይረሳኝም፡፡ ‹‹አንድ ጓደኛዬ ምን አለኝ መሰለህ›› ብለው ይጀምሩለታል፤ ለጋዜጠኛው፡፡ ‹‹…ለህዝቡ የሀሳብ መወራወርያ መድረክ ብታዘጋጁለት ኖሮ… ድንጋይ አይወራወርም ነበር…›› አራምባና ቆቦ የዘለልኩበትን ጉዳይ በአንዲት ዓረፍተ ነገር ቁጭ አደረጉልኝ!! (የቀድሞው ክቡር ሚኒስትር!)
እናላችሁ… ኢህአዴግ አሁን መንቃት አለበት። በአካልም… በመንፈስም! በሌላ በኩል፤‹‹ኢትዮጵያን ማስተዳደር…. ህዝቡን ከድህነት ማውጣት… ባለ 2 ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ---ባለ መካከለኛ ገቢ አገር መፍጠር … ወዘተ የእኔ ብቸኛ ዕዳ ነው!›› ከሚል ነባር የተሳሳተ ሃሳብና እምነቱ መውጣት አለበት - ኢህአዴግ!! የኢዴፓ መስራቹና ትንታግ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀ ሰሞን በፋና ብሮድካስቲንግ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ (ጥፊ… እንኳን ይደገማል!) እንዲህ ማለታቸው ይታወሳል።
‹‹…ከዚህ በኋላ መታወቅ ያለበት … ኢትዮጵያ የኢህአዴግ ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት!›› (የኢህአዴግ ብቻ ነበረች እንዴ?) ለነገሩ እሱም እኮ አላስተባበለም!! ዋናው ቁም ነገር ግን… አገሪቱ የሁላችንም ናት ከተባለ… ዕዳውም የሁላችንም ነው ማለት ነው፡፡ እናም… በጋራ ማልማት…በጋራ መምራት…በጋራ መወሰን…በጋራ መወያየት…. በጋራ መምከር… የግድ ነው (የጋራ አገር ናታ!)
አይገርማችሁም…. ወጌን የጀመርኩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለስልጣን የሚያደርጉት ጥረት …. ለሩብ ክፍለ ዘመን ሳይሳካ የቀረበትን ሁኔታ ነበር፡፡ ግን ወደ ሌላ ጥልቅ ጉዳይ ሳላውቅ ገባሁ፡፡ እናም --- መንግስት የመሆን ረሃባቸው እንኳንስ በእውን-----በአፕሬንትሺፕ የቲቪ ሪያሊቲ ሾው እንኳን የሚያስታግስላቸው አላገኙም። እኔ የምለው ግን… ከ70 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ የሚባለው… እውነት ነው እንዴ? ቆይ ምን የሰራሉ? (ዩኔስኮ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይመዘግባል እንዴ?) እኒህ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኖረውም ግን … አገሪቱ ላይ ዲሞክራሲ እንኳን ሊዘንብ ---- አላካፋም፡፡ (የፓርቲዎች መብዛት ዲሞክራሲ አይወልድ!)
የአገሬን ተቃዋሚዎች ምን ታዘብኳቸው መሰላችሁ? ሲወዛገቡ እንኳን …ጊዜና ቦታ አይመርጡም፡፡ (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ረስተውታል እንዴ?) በዚያ ላይ ውዝግባቸው ራሱ የቸከና የሰለች ነው፡፡ (የውዝግብ “ክሊሼ” አለው?!) እስቲ ይታያችሁ…. በህግና በደንብ የሚመራ ታዋቂ ፓርቲ፤ በአመራር ይገባኛል ጥያቄ በውዝግብ ሲናጥ? (ያውም አገር ውጥረት ውስጥ ሆና!) አንድ ቀንማ … ግብግብ ሊገጥሙ ነበር ተባለ፡፡ እንግዲህ አሁን ሁለት ‹‹የፓርቲው አመራር ነኝ›› የሚሉ ቡድኖች፤ ቅሬታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቅርበዋል፡፡ መቼም ከሁለት አንዱ ህገወጥ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ሁለቱም ህገወጥ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ሁለቱም ግን በአንዴ ትክክል (ህጋዊ) ሊሆኑ አይችሉም። ሁልጊዜ የፓርቲዎች  የአመራር ውዝግብ ሲነሳ የማትቀረው የ‹‹ማህተም ስርቆት›› ጉዳይ ትገርመኛለች፡፡ በሰማያዊ ፓርቲማ … ሰነዶችም ተዘርፈዋል ተብሏል፡፡ (ፖሊስ ዝም ካለ የጉድ ነው?!)
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች ዋና ችግራቸው (እስከ ዛሬ እንደታዘብናቸው!) ምን መሰላችሁ? (ሁሉንም አልወጣኝም!) የሃቀኝነት ችግር! ለእውነት ዋጋ ያለመስጠት! ዋሾነት! ክህደት! አለመተማመን! ---- እንደተባለው ማህተምና ሰነዶች ተሰርቀው ከሆነ ደግሞ፣ዝርፊያና ስርቆትንም ይጨምራል፡፡ (ኩዴታውስ!) ይሄን እንኳን ምርጫ ቦርድ ይመርምረው፡፡ ግን ሁሉም አዲስ ነገር  አይደለም፡፡ በ‹‹አንድነት››፣ በ‹‹መኢአድ››… ተከስቷል፡፡ አሁን ደግሞ በ‹‹ሰማያዊ!”
እኔ የምለው… ‹‹አዲሱ የሰማያዊ ተመራጭ›› ሊቀመንበር … “የፀደቀው የሩብ ዓመት በጀት ያሉት፣ 3 ሚ ብር….” የምር ነው የፉገራ? (የዓመት በጀቱ እኮ 9 ሚ. ብር ሊሆን ነው!) በንጽህና ከሆነ --- ያድርግለት !!

Read 4027 times