Saturday, 17 March 2012 09:10

ሙስና ሲንሰራፋ መልካም አስተዳደር አዲዮስ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የመንግስት ቁርጠኝነት ምን ያህል ነው?

ከጥቂት ወራት በፊት በሀገራችን ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ በመሆን የፖለቲካ መድረኩን የተቆጣጠረው አብይ ጉዳይ ሽብርተኝነትና የሽብርተኝነት አደጋ ነበር፡፡  በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፤ የመንግስታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ለሀገሪቱና ለመንግስታቸውም ጭምር ከፊታቸው የተደቀነው ዋነኛና አስከፊው አደጋ ሽብርተኝነት ሳይሆን ሙስና መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ ከዚያ ጊዜ አንስቶም ሙስና ሽብርተኝነትን ተክቶ የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረክ ተቆጣጠረ፡፡

መንግስቱን ከሚመራው ከኢህአዴግ ጀምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለፃ ተከትለው፣ ሙስና የሥርዓቱ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡ ከተቃዋሚዎች የሚሰማው ጩኸት ተገቢ መሆኑ ባይካድም እምብዛም እንግዳ ጉዳይ ባለመሆኑ እንደ አዘቦት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚቆጠር ነው፡፡ የተቃዋሚዎቹ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆን ያለበትም ይመስለኛል፡፡ ከሌላው ጊዜ የተለየና እንደ አዲስ ነገር የሚቆጠር አንድ ጉዳይ ግን አለ፡፡ ይኼውም ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ከምናውቀው ለየት ባለ መልኩ፣ ሙስና  የስርአቱና የመንግስቱም አደጋ መሆኑን በይፋ መናገሩና ችግሩን ለማስወገድ የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት ማጣቱን መግለፁ ነው - ያውም በአንዳንድ የፓርቲው አንጋፋ መስራች አባሎቹና ከፍተኛ ባለስልጣኖቹ፡፡ በዚያ ላይ ይሄን ግለ - ሂስ ያደረገው በፓርቲው ውስጥ የመሰንጠቅ ችግር በሌለበት በሰላሙ ጊዜ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

በእርግጥ ይሄን ዓይነቱን ግለ-ሂስ እስከዛሬ ከምናውቀው ኢህአዴግ የምንጠብቀው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እኛ የምናውቀው ኢህአዴግ ከሞላ ጐደል በሁሉም መስክ “የተሳካልኝ ነኝ” የሚልና ችግሮቹንና ድክመቶቹን ከቻለ በሌሎች አላክኮ፣ ካልቻለ ደግሞ አቃሎና አድበስብሶ የሚያልፍ በመሆኑ ነበር፡፡ አሁን ይሄ የተለወጠ ይመስላል፡፡ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን አንስቶ እስከታችኛው ካድሬ ድረስ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ያለ ይመስላል - ከመንግስት ሚዲያዎች መከታተል እንደሚቻለው፡፡

የተለያዩ የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎችና አለምአቀፋዊ ተቋማት ባደረጓቸው ልዩ ልዩ ጥናቶች፤ ሙስና ጠንቁ አደገኛ ዳፋውም ልጅ አዋቂ ሳይለይ ሁሉንም የሚያዳፋ ክፉ ማህበራዊ ደዌ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተጠቁሟል፡፡

በሙስና በተጠቁ የተለያዩ የአለማችን ሀገራት በግልጽ እንደታየው፤ ሙስና በእርግጥም አንዲት ሀገርና ህዝቦቿ ለዘመናት ተሳስረው የቆሙበትን ሁለንተናዊ የአንድነት ገመድ ያለአንዳች ኮሽታ ቀስ በቀስ እየበላ፣ በጣጥሶ የሚጥል ማህበራዊ ብል ነው፡፡

የሀገራችንን የሙስና ሁኔታ በተመለከተም፣ በተለያዩ የመስኩ ባለሙያዎችና አለምአቀፍ ተቋማት በየጊዜው የተሠሩ ጥናቶች የችግሩን መጠንና ስፋት አሳይተዋል፡፡ ለምሳሌ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው አለም አቀፍ የፀረ ሙስና ተቋም በየአመቱ በሚያወጣው ጥናት፤ ሙስና ከአመት አመት የሀገሪቱ ዋነኛ ችግር እየሆነ እንደመጣ ሲያሳይ፤ በቅርቡ ደግሞ ኪሊማንጀሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን የተባለ ድርጅት፤ ከአለም ባንክ በእርዳታ የተገኘ ጠቀም ያለ ዶላር ተከፍሎት ባካሄደው ጥናት፤ በሀገራችን ያለው የሙስና መጠን ከሌላው ጊዜ እየተሻሻለ እንደመጣ ጠቅሶ፤ ችግሩ ከትላልቆቹ ይልቅ በትናንሾቹ ላይ የበዛ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡

የጥናት ድርጅቱ በሀገራችን ያለው የሙስና ችግር በትላልቅ የገንዘብ መጠን ሳይሆን በሀምሳና በአምስት መቶ ብር ደረጃ የሚካሄድ፣ እዚህ ግባ የማይባል አነስተኛ የጉቦ ቅብብሎሽ ነው በሚል ያቀረበውን ድምዳሜ፣ ናይጀሪያውያን ቢሰሙት የእድሜ ዘመናቸውን “ታላቅ ሳቅ” እንደሚስቁ ጨርሶ አይጠረጠርም፡፡ በእነሱ ዘንድ ሠላሳና አርባ ዶላር፣ በሬስቶራንት ወይም በመሸታ ቤት ውስጥ ላስተናገዳቸው አስተናጋጅ አሊያም በሱፐር ማርኬት ዘንቢላቸውን ላቀበላቸው “ከተፎ” ሠራተኛ የሚሠጡት ጉርሻ ወይም ቲፕ እንጂ ለጉቦነት ይበቃል ብለው እንኳን ዛሬ በመቶ አመትም ሊያስቡት አይችሉም፡፡

የድርጅቱ የጥናት ድምዳሜ ምናልባት ለመንግስት ወይም ለኢህአዴግ ካልሆነ በቀር ለእኛ ፈፅሞ ውሃ የማይቋጥር ነው፡፡

ድርጅቱ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው መጠይቅ በትኖ በሰበሰበው ምላሽ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ እንግዲህ በአገራችን ያለውን መረጃን በነፃነት የመስጠት ባህልና ልምድ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳዩን ስንመረምር፣ ለምሳሌ ምን ያህሉ መላሽ “ከ10ሺ ብር በላይ ጉቦ ሰጥቻለሁ” ብሎ ሊመልስ ይደፍራል? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፡፡ የትኛውም መላሽ ቢሆን ይሄን ዓይነት ምላሽ ከመስጠቱ በፊት ይሄ ምላሹ ለከርቸሌ እንደማይዳርገው በእርግጠኝነት ማወቅ ይሻል፡፡ ይሄን የሚያረጋግጥለት ካላገኘ ግን “ከነገሩ ጦም ይደሩ” በሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል መሰረት፣ ለአደጋ የማያጋልጥ ምላሽ እንደሚሰጥ አያጠራጥርም፡፡

አንዳንድ የሙስና ችግር ተጠቂ ዜጐች በሹክሹክታ ሲናገሩ እንደምንሠማው፤ አሁን አሁን ሃምሳ ብርና አምስት መቶ ብር ከጉቦ ተራ ቀስ በቀስ እየወጡና ሠጪም ሠጠሁ፣ ተቀባይም ተቀበልኩ እማይልበት ደረጃ መድረሱን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኮርፖሬሽኑን  ድምዳሜ አምኖ ለመቀበል ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ የግድ ተቀበሉት ከተባለ ግን በሚከተለው ዓይነት ግንዛቤ ልንቀበለው እንችላለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ ምናልባት ሀምሳ ብርና አምስት መቶ ብር ጉቦ የሚከፈለው፣ አንድ መስሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ለመግባት ለሚፈቅደው ዘበኛና ፋይል ከመዝገብ ቤት ለሚያወጡት  ሠራተኞች ወይም ተላላኪዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናውን ጉዳይ የሚያስፈጽመውንና የመጨረሻውን ውሳኔ የሚወስነውን ባለስልጣን ግን በሃምሳና በአምስት መቶ ብር ጉቦ መገላገል ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡

የሆኖ ሆኖ ድርጅቱ በሀገራችን ያለው ሙስና መቀነሱን ጠቅሶ ያወጣው ሪፖርት ለእኛ ብዙም ችግር አያመጣብን ይሆናል፡፡ እውነቱን አሳምረን እናውቀዋለንና፡፡ ሁሌም ችግሮቹን የመሸፋፈንና የማድበስበስ የዳበረ ባህልና ልምድ ላለው መንግስታችን ግን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜና አቋም የሚወስድ ነውና ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የሁሉም ተቋማት ሪፖርቶች የሚያረጋገጡት አንድ መሠረታዊ እውነት ቢኖር፣ ሙስና በሀገራችን የተንሰራፋ ትልቅ ችግር መሆኑን ነው፡፡

ትልቅም ይሁን ትንሽ ሙስና ያው ሙስና ነው፡፡ ችግሩና መዘዙም እንዲህ በቀላሉ የሚለቀን አይደለም፡፡ ትክክለኛው መረጃ ስለሌለን ወይም ደግሞ አንድ ሰው ሊዘርፈው የሚችለው በመቶ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሀብት ሀገራችን ስለሌላት፣  ምናልባት  ናይጀሪያና አንጐላን በመሳሰሉት ሀገራት እንደምናያቸው አይነት ትጉህ ሙሰኞችን ማየት አልቻልን ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባለ፣ በቀን ሁለት ጊዜ ለመመገብ እጅግ ፈተና በሆነበትና የአለምአቀፍ ለጋሾችን እርዳታ የሚጠብቅ በርካታ ህዝብ ባለበት ሀገር፣ የሃምሳና የአምስት መቶ ብርንም ጉቦ ቢሆን እንደ ቀላል ነገር አድርጐ መገመት፣ የችግሩን አሳሳቢነት በወጉ አለመረዳት ነው፡፡ እንዴት ቢባል? በእኛው አቅምና የሀብት ልክ የተሰፉ የእኛው አይነት ትጉህ ዘራፊዎች  እንዳሉን በደንብ እናውቃለን፡፡

ኪሊማንጀሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን፣ በሪፖርቱ ካወጣው ድምዳሜ ይልቅ ሙስና የተንሰራፋባቸውን መንግስታዊ ተቋማት በተመለከተ ያቀረበው መረጃ ከሁሉም የላቀ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሙስና የተንሰራፋባቸውና የህዝብ አመኔታ ያጡ በሚል ካቀረባቸው መንግስታዊ ድርጅቶች ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር ቢሮዎች ናቸው፡፡

የአንድ ሀገር የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ለሀገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለህዝቦች መሠረታዊ የሠብአዊ መብት አያያዝና ጥበቃ የሚጫወተውን ምትክ የለሽ ሚና መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የመልካም አስተዳደር ዋነኛ ምሰሶ ናቸው የሚባሉት ፍርድ ቤት፣ ፖሊስና የተለያዩ የአስተዳደር ተቋማት የሙስና ሰለባ መሆናቸውን ስትሰሙ የቱን ያህል ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ልትረዱ ትችላላችሁ፡፡

በሌላ አነጋገር ከፍርድ ቤቶች፣ ከፖሊስና ከአስተዳደር መስሪያ ቤቶች ውጪ መልካም አስተዳደርን ማሠብ ወይም ስለ መልካም አስተዳደር ማውራት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሙስና ተንሠራፍቷል ማለት መልካም አስተዳደር የለም ማለት ነው፡፡ መልካም አስተዳደር በሌለበት ስርአት ውስጥ ደግሞ ስለ ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊነት ፈፅሞ መነጋገር አይቻልም፡፡

መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ ሙስና በሀገሪቱ ላይ ያንዣበበ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን ማመናቸው አንድ በጐ ነገር ነው፡፡ የሙስና ችግር የሚፈልገው ግን ማመን ብቻ ወይም ስለ ችግሩ በአደባባይ መናገር ብቻ አይደለም፡፡ ከንግግር በላይም ተጨባጭ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ በወሬና በጫጫታ የሚፈርስ የሙስና “የኢያሪኮ ግንብ” የለም፡፡ ነገም ሆነ ከነገ ወዲያም ቢሆን አይመጣም፡፡ ዋናው ጉዳይ ችግሩን ለማስወገድ የሚወሰደው ተጨባጭ እርምጃ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ደግሞ እስካሁን መንግስትም ሆነ መንግስቱን የሚመራው ኢህአዴግ፣  ከንግግር ባለፈ ያሳየን ተጨባጭ እርምጃ እዚህ ግባ የማይባል ከመሆኑም በላይ ግንዱን ትቶ የቅርንጫፎቹን ቅጠሎች በማራገፍ ላይ ብቻ ያተኮረ የሚመስል ነው፡፡ መንግስት ሙስናን በመዋጋት ረገድ እያሳየ ያለው ፍላጐት፣ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳበት ነው፡፡

መንግስት በተደጋጋሚ በሀገሪቱና በስርአቱ ላይ የተጋረጠው ትልቅ አደጋ ሙስና መሆኑ ይናገር እንጂ ተጨባጭ እርምጃ ባለመውሰዱ ችግሩ እየተስፋፋ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡ ዛሬም ቢሆን ትንሽ ቆሎአቸዉን ይዘው ወደ ትልቁ የመንግስት አሻሮ የተጠጉ ሞልተዋል፡፡ የመንግስትን መዘውር ከያዙት ጥቂት ምርጦች ጋር በፈጠሩት ወዳጅነትና ታዛዥነት፣ በብርሀን ፍጥነት ከተራ የሲጋራ “ቀፋይነት” ወደ ሚሊዬነርነት፤ ከተራ ቡቲክ ነጋዴነት ወደ ታላቅ የፋብሪካ፣ የቢዝነስና የሪል እስቴት ወዘተ ባለቤትነት አይናችን ስር የተቀየሩ፤ ከላይኛው የመዘውሩ ጫፍ የቋጠሯት ገመድ ያለ አንዳች ድካምና ወጪ፣ ወደ ከፍተኛው የሀገሪቱ የሀብት መንደር ያደረሳቸው፣ የግልም የመንግስትም ትጉህ ሙሠኞች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ባላቸው የትምህርት ደረጃና የስራ ልምድ ሊያገኙት የማይችሉትን የስራ መደብና ሀላፊነት፤ የደመወዝ ጭማሪ፣ የትምህርትና የስልጠና እድል፣ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ቤት መሬት ወዘተ .. የመሳሠሉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የሀገሪቱን የአመራር መዘውር ከያዙ ጥቂት ምርጦች ጋር በመሠረቱት ወይም ባላቸው የፓርቲ፣ የዘር፣  የቡድን ወዘተ ገመድ ብቻ፣ ከህግ አግባብ ውጪ በቅድሚያና በአድልኦ እንዲያገኙ ሲደረግላቸውና ሲያደርጉላቸው በይፋም በምስጢርም መታዘባችን አልቀረም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዜግነታቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ከነዚያ “የምርጦች ጐራ” የሚያስጠጋቸው በማጣታቸው የተነሳ ብቻ ለማግኘት ያልታደሉና የእጦታቸው ችግር የፈጠረባቸውን ፈተናና ፍዳ እያስታመሙ የድረሱልን እንባ ለአመታት እያነቡ ያሉ፣ መንግስታቸውን ሳይሆን አምላካቸውን ሌት ተቀን “ኤሎሄ” እያሉ የሚማፀኑ ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

እነዚህን የትየለሌ የሙስና ችግሮች በአንድ ላይ ጨምቀን፣ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ሥር እናጠቃልላቸው ብንል እነዚህን እናገኛለን፡፡ አንደኛው ግንባር ቀደም የሙስና አደጋ፣ ህዝቡ በሀገሩና በሚመራው መንግስት እምነት እንዲያጣና ተስፋ እንዲቆርጥ ማድረጉ ነው፡፡

በዜጐቿ ተስፋ የተቆረጠባት ሀገር፣ የወደፊት እድገቷ ብቻ ሳይሆን ህልውናዋም ጭምር ለከፍተኛ አደጋ እንደሚጋለጥ የአለማችን የሀገራት ታሪክ  የምንጊዜም እማኝ ነው፡፡

በሚመራው ህዝብ ዘንድ አመኔታውን ያጣ መንግስት ደግሞ በጉልበት ካልሆነ በቀር ራሱን በሁለት እግሮቹ እንደቆመ መንግስት ሊቆጥር ጨርሶ አይቻለውም፡፡ ጉልበቱም ቢሆን የሚታደገው ለጊዜው፣ በተለይም ህዝቡ “በቃህ” ብሎ እስኪነሳበት ድረስ ብቻ እንደሆነ በቅርቡ በአህጉራችን ያየነው ክስተት ምስክር ነው፡፡

ሁለተኛው የሙስና ታላቅ አደጋ ደግሞ ከትክክለኛውና ከህጋዊው አሠራር ይልቅ ህገወጡ እንደ ትክክለኛና ተገቢ አሠራር በህዝቡ ዘንድ መቆጠሩ ነው፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ተነሳሽነት፣ ፍላጐትና ቁርጠኝነት የሌለው መንግስት፤ የሚመራውን ሀገርና ህዝብ ለእነዚህ ሁለት ታላላቅ አደጋዎች አጋልጦ ይሰጣል፡፡

ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት፤ ሙስና በሀገሪቱ በህዝቦቿና በስርአቱ ላይ የተጋረጠ ከፍተኛ አደጋ መሆኑን መግለፁ በራሱ የሚያመጣው አንዳችም ፋይዳ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል፡፡

አንድ መንግስት ሙስና በከፍተኛ አደጋነት ከፊቴ ተደቅኖብኛል ብሎ ሲያውጅ፣ በቅድሚያ የሚቀርብለት ጥያቄ፤ ይህን አደጋ ለማስወገድ የወሠድካቸውና እየወሰድካቸው ያሉት እርምጃዎችን እንዴት ያሉ ናቸው? አደጋውን በመቋቋም ረገድ ያለህ ፍላጐት፣ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነትስ ምን ያህል ነው የሚሉት ናቸው፡፡

ከእነኝህ ጥያቄዎች አንፃር፣ ኢህአዴግንና የሚመራውን መንግስት የእስካሁን እንቅስቃሴዎች ስንመዝናቸው የምናገኘው መልስ፤ ከማናችንም አንጀት ጠብ የሚል አይደለም፡፡ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት እስካሁን የወሰዳቸው እርምጃዎች ለተራ ሪፖርት እንኳ የማይመጥኑ፣ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብቻ የተወሰዱ ይመስላሉ፡፡  በተነሳሽነት፣ በፍላጐትና በቁርጠኝነት በኩልም፣ ከንግግር ያለፈ አንዳች አይነት የተግባር ምላሽ አላሳየንም፡፡ እነዚህን ግልጽ እውነታዎች ለማስተባበል መንግስት ሀይለኛ ጡንቻ አለኝ አይልም እንጂ ካለው ሲጠቀምበት ያየነውም የሙስናውን መዘውር በሚዘውሩት ትላልቅ፣ እጅግ ቁርጠኛና ትጉህ ሙሠኞች ላይ ሳይሆን የኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን፣ ለቀልድ በሚመስል አኳኋን በሪፖርቱ በጠቀሳቸው የባለ ሀምሳ ብር ጉበኞች ላይ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት መራሹ ኢህአዴግ፤ በአንድ በኩል ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት፣ ተነሳሽነትና ፍላጐት በማጣቱ፣ በሌላ በኩል ወሰድኩ የሚላቸው እርምጃዎቹ ውጤት አልባ በመሆኑ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ ህልውናችንን ለሚፈታተን ከፍተኛ አደጋ አጋልጦ ሠጥቶናል የምንለው፡፡

ስለዚህ ሁላችንም ተያይዘን ከመውደቃችን በፊት በመንግስት በኩል ቁርጠኛ፣  ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የፀረ - ሙስና እርምጃ ያለ አድልኦና ልዩነት አሁኑኑ  ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ መቼም እንዲህ ማለቴ እንደ ክፉ ሟርት ወይም ምቀኝነት እንደማይቆጠርብኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ይወጣ!

 

 

Read 3344 times Last modified on Saturday, 17 March 2012 09:15