Saturday, 31 December 2016 11:14

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላስ??!!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“ሃሳቦች አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው”

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ፣በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በተቃውሞና በቀውሱ ሰዓት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር ከዋሉ
ከ24ሺ በላይ ግለሰቦች መካከል 9ሺ ገደማው ባለፈው ሳምንት ስልጠና ተሰጥቷቸው መለቀቃቸው አይዘነጋም፡፡ ከ2ሺ በላይ የሚሆኑትም ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሏል፡፡
በቀሪዎቹ 12ሺ ግለሰቦች ላይም ማጣራት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፋይዳ፣ከህዝብ ጋ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ ስለሚኖረው ሁኔታ
(ተስፋዎችና ፈተናዎች) ----- የፓርቲ አመራሮችንና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ አስተያየታቸውን አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡


“በኮማንድ ፖስቱ ብቻ የትም ሊደረስ አይችልም”

አቶ ወንድወሰን ተሾመ  (የኢዴፓ አመራር)

መጀመሪያ በህዝቡ የተነሳው ጥያቄ፡- የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብትና ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው። የተወሰደው እርምጃ ግን ጥያቄ አቅራቢውን የማሸማቀቅ እርምጃ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ስርአት ያለመስፈን ትልቁ ተጠያቂዎች እነዚህ የታሰሩ ሰዎች አይደሉም፡፡ ትልቁ ተጠያቂ መንግስት ነው። ተለቀቁ ከተባሉ ሰዎች የተወሰኑትን አነጋግረናቸው ነበር፡፡ መሸማቀቃቸውን ነው የሚገልፁት፡፡ “እኔ ከዚህ በኋላ ምን አገባኝ፤አርፌ ነው የምቀመጠው” ነው የሚሉት፡፡ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ከፖለቲካ ስርአቱና ከዲሞክራሲያዊ ሚናው ውጭ እንዲሆንና፣ ቁጭ ብሎ ተመልካችና መብቱን የማይጠይቅ አድርጎ ከጫወታው ማውጣት ተገቢ አይደለም። ይሄ የበለጠ መታመቅ ነው የሚፈጥረው። ይህ ደግሞ የበለጠ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ አሁን የተወሰደው እርምጃ እንዲህ አይነቱን ውጤት ሊያመጣ የሚችል ነው፡፡ እንደ ትልቅ ለውጥ እየተወራ ያለው ተሃድሶ ነው፤ ያ ብቻውን ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። የዲሞክራሲ ተቋማትን የመገንባት ምልክትም አይደለም፡፡ ፈረሱ ከጋሪው ቀደመ ነው የሆነው። መጀመሪያ ህዝብ እንዲወያይ ሳይደረግ፣አስሮ መፍታቱ ትርፉ ማሸማቀቅ ብቻ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪቱ አደጋ ላይ በነበረችበት ጊዜ የታወጀ መሆኑን አይቶ መቀበል ይቻል ይሆናል። ግን ከዚያ በኋላ “አዋጁ ሀገሪቷን አረጋግቷል ተብሎ ከታመነ”፣ ሊመለሱ የሚገባቸው የህዝብ ጥያቄዎች አግባብ በሆነ መልኩ ካልተመለሱ አደጋ ነው፡፡ ለምሳሌ የሚፈለጉ ውይይቶች እየተደረገ አይደሉም፤የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ውይይት እስካልተደረገ ድረስ ከጥቂቶች ጋር መወያየት ጠቃሚ አይደለም፡፡ መርፌ ላይ እንደ መቆም ነው የሚቆጠረው፡፡
ውይይት ሲደረግ ከማን ጋር ነው መነጋገር ያለብኝ፤ ብሎ መንግስት ማሰብ አለበት፡፡ አሁን መገናኛ ብዙኀኑ አሰልቺ አቀራረባቸን ቀይረው፣ ሰፊ ሀሳብ እንዲያስተናግዱ ካልተደረገና ሰፊ የውይይት ሂደቶች እስካልተደረጉ ድረስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካበቃ በኋላ የሚፈጠረው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ወደ ነበረበት ሁኔታ እንዳይመለስ ብዙ መሰራት አለበት፡፡ አሁን ያለው ዝምታ፣ “አርፌ ልቀመጥ፣ የለሁበትም” አይነት ነገር ነው፤ይሄ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡ ሰዎች በየመድረኩ ካልተነጋገሩና ሀሳቦች ካልተፋጩ፣ አንድ አስተሳሰብ ብቻውን መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኋላ በኢኮኖሚና በንብረት ተቋማት ላይ የሚደርሰው ውድመት መቆሙ መልካም ውጤት ነው፡፡ ግን ደግሞ በኮማንድ ፖስት ሀገርን ማስተዳደር፣ ወታደራዊ አገዛዝን ማስፈን ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ለህዝቡ ምላሽ በመስጠት፣ የኮማንድ ፖስቱን እድሜ ማሳጠር አለበት፡፡ ኮማንድ ፖስቱን በመተማመን፣በእመቃ የትም ሊደረስ አይችልም፡፡

===========================

“ጥያቄ ያነሳ ህዝብ እንዴት ነው የሚታደሰው?”
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ (የመድረክ ሊቀ መንበር)

የታሰሩ ሰዎች ተሃድሶ ስልጠና ተሰጣቸው ነው የተባለው፡፡ ምን ዓይነት ተሃድሶ ነው የተሰጣቸው? እነዚህ ሰዎች እኮ የራሳቸው አላማ ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች የታደሱት ከአላማቸው ነው? ለምንድነው የሚታደሱት? የነሱ ካድሬዎች ቢታደሱ አይደንቀንም፡፡ ጥያቄ ያነሳ የህዝብ አካል ግን እንዴት ነው የሚታደሰው? እነዚህ ሰዎች እኮ ችግር እንደሚደርስባቸው እያወቁ፣ ተቃውሞአቸውን ፊት ለፊት ያሰሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ታደሱ ሲባል፣ ተቃውሞአቸውን ጥያቄአቸውን ተዉ ማለት ነው? ይሄ ግልፅ አይደለም፡፡ “ተሃድሶ ሰጥተን ፈተናቸዋል” የሚለው ግራ አጋቢ ነው፤ ከምንድን ነው የሚታደሱት? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ የሰውን ልጅ ክብር በሚነካ መልኩ አንድ ላይ አስሮ፣ ፀጉር ላጭቶ፣ “አይደገምም” የሚል ቲ-ሸርት አልብሶ፣ አደባባይ ማቅረብ አስገራሚ ነው፡፡ …”አይደገምም” የሚለው የእያንዳንዱ ቲ-ሸርት ለባሽ ሀሳብ ነው ወይስ የጥቂቶች? የታሰረ ሰው በምንም መንገድ ይሁን ከእስር መውጣቱን ብቻ ነው ሊያስብ የሚችለው፤ ስለዚህ ቲ-ሸርቱን መልበሳቸውም የዚሁ ግልባጭ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ያነሷቸው የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው፤ ታደሱ ሲባል እነዚህ ጥያቄዎቻቸውን ትተዋል ማለት ይሆን? ለኔ ግልፅ አይደለም፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ አንስቶ ሁኔታውን ስንከታተል፣ መንግስት በስፋት እያደረገ ያለው፣ ካድሬዎቹን በመሰብሰብ መወያየት ነው፡፡ ይሄ በኔ አመለካከት ያንኑ ቡድን፣ የማይበስል  ንፍሮ ዝም ብሎ ከስሩ እሳት እንደ ማንደድ ነው፡፡ ህዝቡ የተማረረባቸው የወረዳና ዞን አስተዳደሮች፤ራሳቸው ደጋፊዎቻቸውን ሰብስው ከሚያደርጉት ውይይት ምን ይጠበቃል? ለ100 ሚሊዮን ህዝብ እነዚህ ሰዎች በቂ ወኪሎች አይደሉም፡፡ እንደኔ አሁን የተያዘው መንገድ ዝም ብሎ የበሽታውን ምልክቶች ማከም ነው፡፡ በዜናዎች ላይ ከህዝቡ ጋር ተደረጉ የተባሉ ውይይቶችን እያዳመጥኩ ነው፤ እስካሁን ምንም የተለየ ሀሳብ ሲቀርብ አላየሁም፡፡ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፣ ሚሊዮኖችን ከሚወክሉ ብቃት ካላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀምጦ መወያየት ነው፡፡ በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ይሄ ሲደረግ አላየንም፡፡ እነሱ እያሰቡ ያሉት በአዋጁና በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ብቻ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ይመለሳል ብለው ነው፤ግን ይሄ ስህተት ነው፡፡ እኛ “የፖለቲካ ምህዳሩን በጋራ እናደላድል” የሚል ጥያቄ ነው በተደጋጋሚ ያቀረብነው፡፡ ግን ለዚህ ምላሽ ሊሰጡ አይፈልጉም። በዚህ ጊዜ ውስጥ መደረግ ከነበረበት አንዱ፣ይሄ ነበር፡፡ እኛ የምንጠይቀው የችሮታ ጥያቄ አይደለም። “እኛም ለዚህች ሀገር የራሳችን መፍትሄ አለን” እያልን ነው፡፡
ኢህአዴግ የህዝቡን ቀጥተኛ ጥያቄ፣ በቀጥታ ለመመለስ እስካልደፈረና ወደ ውይይት አደባባይ እስካልመጣ ድረስ የህዝቡ ጥያቄ እንዳለ ነው ማለት ነው፡፡ ህዝቡ’ኮ በእብደት አይደለም እንደዚያ ወደ አደባባይ የወጣው፤ ጥያቄ ስላለው ነው፡፡ ያ ጥያቄው ተመልሷል ማለት ነው? እንደኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለዚህ መጠቀም ይገባ ነበር። ይሄን ለማስፈፀም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት፤ ዋነኛ የተቃዋሚ መሪዎችን ነው እያሰረ ያለው፡፡ እነዚህን አስሮ ከማን ጋር ነው መነጋገርና መደራደር የሚችሉት? እንደኔ ኢህአዴግ አሁንም ጊዜውን እያባከነ ነው፡፡ ለችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ ስራዎችን አልሰራም፡፡ ስለዚህ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ምን ይፈጠራል? የሚለውን ለወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ግን ዶ/ር መረራን የመሳሰሉ በሳል ፖለቲከኞች መታሰራቸው፣ የውይይት ተስፋን የሚጭር አይደለም፡፡

===========================

“ጥያቄ የነበራቸው የታሰሩት ብቻ አይደሉም”

አቶ ግርማ ሰይፉ (የቀድሞ የፓርላማ አባል)

 የተወሰኑ ከእስር የተለቀቁ ልጆችን ለማነጋገር ሞክሬ ነበር፡፡ ያነጋገርኳቸው ልጆች በስልጠናው አምነውበት ወይም በስልጠናው ወቅት የሚገዳደር ጠንካራ ሀሳብ ቢያነሱ ከእስር እንደማይወጡ ስለሚያውቁ አርፈው ተቀምጠው፣የአንድ ወገንን ሀሳብ ብቻ ለመስማት ይገደዳሉ፡፡ ንብረት በማቃጠልና በማውደም ላይ የተሳተፉ ሰዎች፤መለስ ብለው ሲያዩት በስሜት ተነሳስተው ያደረጉት ስለሆነ፣ “እንደዚህ ማድረግ አልነበረብኝም” ቢሉ ስህተት አይሆንም፡፡ እነዚህ ሰዎች ያንን እንዲያደርጉ ምንድን ነው የገፋፋቸው? የሚለው ጥያቄ ግን ለነሱም አልተፈታላቸውም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ንግግር ሲያደርጉ፤ ”እናንተም “አይደገምም” እንዳላችሁት፤” እኛም ጥፋታችንን እንቀበላለን” ብለው ነበር፡፡ ግን እነሱ አሁንም ጥፋታቸውን በትክክል አምነው እንዳይደገም እየሰሩ አይደለም፡፡ ወጣቶቹ ከአሁን በኋላ “እሳት አናቃጥልም፤ ድንጋይ አንወረውርም ግን ጥያቄያችንን ስሙን” ብለዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በተነሱት ጉዳዮች፣ ጥያቄ ያላቸው የታሰሩት ብቻ ናቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ሌላው አሁንም በሚዲያዎች ስንከታተል፣ ከህዝብ ጋር የሚደረጉ የሚባሉ ውይይቶች ላይ የምናያቸው ሰዎች፣ድሮም በቴሌቪዥን የምናውቃቸው አይነት ሰዎች ናቸው። “ድሮም ያለ እናንተ ለዚህች ሀገር ማንም የለም” እያሉ የሚያሞግሷቸው ሰዎች ናቸው፤ ዛሬም ህዝብ ተብለው እየተነጋገሩ ያሉት፡፡ አዲስ ሀሳብና አስተሳሰብ ይዘው የመጡ የሉም፡፡ ስብሰባዎቹ ከላይ የመጣውን ለመንገር እንጂ የማዳመጫ ስብሰባዎች አይመስሉኝም፡፡ ከህዝቡ ሰምተው ጥያቄዎቹን ይዘው የሚሄዱበት ስብሰባ አይደለም። እነሱ ብቻ ተናግረው የሚሄዱበት ስብሰባ ነው የሚያደርጉት። ከዚህ አንፃር ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ወደ ሀገሪቱ ችግሮች መፍትሄ መውሰጃ መንገድነት እየተጠቀሙበት አይደለም የሚል ምልከታ ነው ያለኝ፡፡ እኔ ተምረዋል ልል የምችለው፣ የፖለቲካ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ሙከራ ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅሞ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ፀጥ አድርጎ ሊሆን ይችላል፤ ግን ይሄ መሰረታዊ ለውጥና መሻሻል ያመጣል ማለት አይደለም። ሀገሪቱን ወደ ትክክለኛ መስመር ለመውሰድ በመጀመሪያ ራሳቸው ጋ ያለውን መደነጋገር ለማረም መሞከር ይኖርባቸዋል፡፡ ይሄን ካስተካከሉ በኋላ ደግሞ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ሊጫወት የሚችለውን ሌላኛውን አካል ማግኘት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ፖለቲከኛ ነኝ፡፡ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ ግን ይሄን እንዳላደርግ ምህዳሩ ዝግ ነው፡፡ የታለ የተከፈተልኝ? እንደፈለግሁ እገባለሁ ብል፣ መስመር ተሻገርክ ልባል ነው፤ይሄ ማለት ታፍኛለሁ ማለት ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለዚህ ከዋለ፣ በቀጣይ ምንድን ነው ሊሆን የሚችለው? ምናልባት አሁን አዋጁ በየአቅጣጫው የሚናገሩትንና ሀሳብ የሚሰጡትን ዝም አስብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የአዋጁን ጊዜ በአግባቡ እየተጠቀሙበትና ማምጣት የሚገባውን ነገር እያመጣ ነው ብዬ አላስብም፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጨማሪ ማራዘም ሳያስፈልገው ወደ መጋቢት መጨረሻ የሚነሳ ከሆነ፣ በበነጋው ሀገሪቱ በቅፅበት ችግር ውስጥ ትገባለች ወይም ሁከት ተፈጥሮ ወደ ነበረችበት ትመለሳለች የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ግን የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ በፍጥነት ይነሳሳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚህ ሂደት ስራ አጥነት የሚፈጥራቸው ድብርቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ሰው፤ “በቃ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ደከመኝ” በሚል ወደ ስደት አሊያም በሌላ መንገድ እሞክራለሁ ሊል ይችላል፡፡ ድንጋይ ልወርውር ያለም ሊወረወር ይችላል፡፡ ግን ይሄ ለምን ይሆናል? ለምን ከዚያ በፊት አስፈላጊ ናቸው የሚባሉት ዘላቂ እርምጃዎች አይወሰዱም? ኢህአዴግ አንድ የተሳሳተው ጉዳይ አለ፡፡ ህዝቡ ኢህአዴግ ስህተቱን እንዲያርም ያቀረበው ጥያቄ አድርጎ ነው እየተረጎመው ያለው፡፡ ህዝቡ ይሄን የት ቦታ ነው የጠየቀው? ህዝቡ ኢህአዴግ እንዲጠናከርለት አይደለም ሲጠይቅ የነበረው፡፡ አማራጭ ነበር ፍላጎቱ፡፡ ይሄን አማራጭ የማመቻቸት ሥራ ነው መሰራት የነበረበት፡፡
ለዚህች ሀገር መፍትሄ መሆን የሚችለው እኮ ኢህአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ 10 ቢሊዮን ብር ለስራ ፈጠራ አውላለሁ ብሏል፡፡ ይሄ ገንዘብ’ኮ የኢህአዴግ አይደለም፡፡ የህዝብ ገንዘብ ነው፡፡ ሌላው ኃይልም ስልጣን ቢይዝ ሊያደርገው የሚችለው ነው። ለምሳሌ ለአንዱ ፓርቲ እድል ቢሰጠው፤ ”ኢህአዴግ 10 ቢሊዮን ያለው አይበቃም፤ እኔ 20 ቢሊዮን እመድባለሁ” ብሎ አማራጭ ማቅረብ ይችላል፡፡ አሁን ኢህአዴግ ብቻውን “መፍትሄ እየሰጠሁ ነው፤ ከህዝቡ ጋር እየተወያየሁ ነው” የሚለው አይሰራም፡፡ ራሱን ማደሱ እንደ ፓርቲ ለመቀጠል ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡ ግን ለሌሎች የሀገሪቱ ፖለቲከኞችም የመነጋገርና አማራጭ ሀሳቦችን ለህዝቡ የመሸጥ እድሎች መመቻቸት አለባቸው፡፡ ሲቪል ሶሳይቲው መነጋገር አለበት፡፡ ህዝቡ በሚፈልገው ቋንቋ ከሁሉም መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ ሀሳብ የሚሰማበት አማራጭ መፈጠር አለበት፡፡ ሬዲዮኖቹ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እየሄደ እንደሆነ መናገር አለባቸው፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር በንቃት ካልተንቀሳቀሰ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ስር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡
ህዝቡ፤ ”የስርአት ለውጥ ይምጣ” ሲል፤ ”በነውጥም በሀይልም በጦርነትም አይደለም፤ በስርአቱ ይሁን ነው” ያለው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ “እኔ የያዝኩት እውነት ብቻ ነው የዚህች አገር መድህን” የሚለውን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣”የአገራችን ጉዳይ ያገባናል” የሚሉ ወገኖችን ሀሳብ ወደ ሰፊ መድረክ ማምጣት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ 

Read 1855 times