Saturday, 31 December 2016 11:09

የእህል በረንዳ ሰራተኞች፤ከወረዳው ጋር እየተወዛገቡ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    ከ30 ዓመታት በላይ በእህል በረንዳ በጫኝና አውራጅነት ስራ ሲተዳደሩ የቆዩ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ሰራተኞች፤ ከኮልፌ ቀራንዮ፣ ወረዳ 4 መስተዳድር ጋር እየተወዛገቡ ነው፡፡ የውዝግቡ መነሻ ወረዳው 87 አዳዲስ ወጣቶችን ወደ እነሱ ስራ በማስገባቱ እንደሆነ ነባሮቹ ሰራተኞች ተናግረዋል። የወረዳው መስተዳድር በበኩሉ፤ በእህል በረንዳ የሚታየውን ህገ - ወጥ አሰራር ስርዓት ለማስያዝ ወጣቶቹን ማደራጀቱን ይገልፃል፡፡
ከ3 አስርት ዓመታት በላይ የተለያዩ ጭነቶችን በመጫንና በማውረድ ኑሯቸውን ሲገፉ እንደነበር የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በስራቸው እስከ 60 ሺህ ቤተሰብ የሚተዳደርበት ስራ ተወስዶ፣ ለ87 ወጣቶች መሰጠቱ ፍትሀዊነት የጎደለው አሰራር ነው ብለዋል፡፡  የወረዳ 4 ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳሙኤል አባዲ በበኩላቸው፣ 87ቱ ወጣቶች በሱስ በወንጀልና መሰል ጥፋቶች ማረሚያ ቤት የቆዩ የህግ ታራሚዎች ወደ ቀደመ ጥፋታቸው እንዳይመለሱና ከማህበረሰቡ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀው፤  ሆኖም ማለት ከዚህ ቀደም የነበሩት ሰራተኞች አይሰሩም ማለት እንዳልሆነና በማህበር ተደራጅተው በህጋዊ መንገድ እየሰሩ መንግስትም ሆነ ራሳቸው ሰራተኞቹ ማግኘት የሚገባቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ረፋድ ላይ የወረዳው መስተዳደርና ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ለመነጋገር በወረዳ 1 ወጣት ማዕከል አዳራሽ በተሰበሰቡበት ወቅት፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ “እስከዛሬ ሁብት አካብታችኋል፤ ለቃችሁ ውጡ” መባላቸውን ገልፀው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ለመደራጀት እንደሞከሩና መንግስት ጥያቄውን ሳይቀበል በመቅረቱ፣ ቀድሞ ይሰሩበት በነበረው መንገድ መቀጠላቸው ተናግረዋል፡፡ የወረዳው ም/ስራ አስፈፃሚ፤ ሰራተኞቹ እንደራጅ ሲሉ መንግስት ችላ ብሎ መቆየቱ የመስተዳድሩ ችግር መሆኑን ያመኑት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ “እንደራጅ” ብለው ለሚመጡ ሁሉ የወረዳው በር ክፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፤ 87ቱ ወጣቶች በመንግስት መደራጀታቸውን ከለላ በማድረግ፣ ከ20 ሺህ በላይ የሆነውን ጫኝና አውራጅ፣ “በእኛ ስር ትሰራላችሁ” ማለታቸውን እንደማይቀበሉት ገልፀዋል፣ መንግስት በነበሩበት ስራቸው እንዲቀጥሉ እንዲፈቅድላቸው የጠየቁት ነባር ሰራተኞቹ፤ እነሱም ሆነ መንግስት ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ለማስከበር የተለየ ዘዴ በጋራ መፈለግ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የወረዳው ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ በጉዳዩ ላይ 350 ከሚሆኑ የአካባቢው ነጋዴዎች ጋር ለመወያየትና ለችግሩ እልባት ለመስጠት፣ ባለፈው ማክሰኞ ቀጠሮ ይዞ የነበረ ሲሆን በውይይቱ ላይ የተገኙት ነጋዴዎች ቁጥር ከ40 አይበልጥም ነበር ተብሏል፡፡ የወረዳው ኃላፊዎች፤ 87ቱ ወጣቶች ወደ ስራው ቢገቡ ነጋዴዎቹ አብረዋቸው ይሰሩ እንደሆነ ጥያቄ ቢያቀርቡም እምቢም እሺም ሳይሉ ዝምታን በመምረጣቸው፤ ወጣቶቹ ተወደደም ተጠላም አርብ ጠዋት ስራ እንዲጀምሩ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የወረዳውን ውሳኔ ተከትሎ፣ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፣ ወረዳው 20 ሺ የአካባቢውን ጫኝና አውራጆች ቅሬታ ችላ ብሎ፣ 87ቱን ወደ ስራው እንዲገቡ በመፍቀዱ፣ የተሰማቸውን ቅሬታ የገለፁ ቢሆንም ወጣቶቹ በትላንትናው እለት ወደ ስራ እንደገቡና በስራው ልምድ የሌላቸው በመሆኑ፣ ስራው እንደከበዳቸው ምንጮች ገልፀው፤ 87 ወጣቶች መንግስትን የጠየቁት በጫኝና አውራጅነት እንዲያሰራቸው ሳይሆን በፅዳትና በፓርኪንግ ስራ እንደነበር ገልፀዋል፡፡  




Read 3645 times