Saturday, 24 December 2016 13:23

ወጣቱና... ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(15 votes)

 “....እኔ የምኖረው በአዲስ አበባ ነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነው። አንድ ነገር ገርሞኝ ነው ወደእናንተ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ የተገደድኩት። ወደስራ ለመሄድ በመንገድ ላይ በምንቀሳቀስበት ጊዜ የተመለከትኩት ነገር አለ። ይኼውም አንድ ቀን ታክሲ ለመሳፈር ከወዲያ ወዲህ ስጋፋ አንዲት ሴት ልጅ ግን ዳር ይዛ ዝም ብላ ቆማለች። እኔም መኪና የምትጠብቅ ትሆን? ብዬ እራሴን ጠየቅሁና ግፊያዬን ቀጠልኩ። ለካንስ ይህ የታክሲ ሰልፍ ምን ያህል ገላግሎናል። በወቅቱ እዚያ ቦታ ሰልፍ አልነበረም። ምናልባትም ለታክሲ መነሻ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህች ልጅ ምናልባት የሚመጣላት መኪና ካለ ጠጋ ልበል እና ልለምን እንዴ ብዬ ወደእርስዋ ሄድኩ። አናገርኩዋት። መኪና የላትም። እሱዋም የምትጠብቀው ታክሲ ነው። .. እኔማ ግፊያውን ፈርቼ ነው ዳር ይዤ የቆምኩት።የምሄደው ወደሜክሲኮ ነው። ያዘልኩት ልጅ ትኩሳት ስላመመው ለሕክምና ብዬ ነው...” አለችኝ።
ታዲያ የያዝሽው ልጅ ከቤት አይቆይም ነበር? አልኩዋት። እርሱዋም:
“...ማን ሊጠብቀው? በር ዘግቼ ነው የወጣሁት... እባክህ ተጋፍተህ መቀመጫ ካገኘህ ለእኔም ቦታ ያዝልኝ...” አለችኝ።
እኔ ልለምን ሄጄ ጭርሱንም ተለማኝ ሆኜ እርፍ አልኩ። በዚህ መሀል ግን አንድ የከነከነኝ ነገር አለ። ይህች ልጅ ምናልባት በእድሜዋ ከ20-24 አመት የማያልፋት ሆና ነገር ግን እርጉዝ ነች።እንደገናም አንድ ልጅ በጀርባዋ አዝላ እና ሌላውን በእጅዋ እየጎተተች ነው ከመንገድ የቆመችው።በዚህ እድሜዋ ይህን ያህል ልጅ ከወለደች ገና ለወደፊቱ ስንት ትወልድ ይሆን? በጣም አሳሰበኝ። ገጠር እንዳይባል ያለችው አዲስ አበባ ነው። የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አታውቅም እንዳይባል ...ጠይቄአት እንደምታውቅ ነግራኛለች። ሀያ አምስት አመት ያልሞላት ልጅ ሶስተኛ ልጅ እርጉዝ ሆና ስትታይ ምንድነው የሚባለው? የላንቺና ላንተ አምድ አዘጋጆች... እስቲ ያልተፈለገ እርግዝናን በመከላከል ረገድ የደረስንበትን ደረጃ ብትጠቁሙን.....
 ተወዳጅ ካሳው ከነፋስ ስልክ ላፍቶ
አቶ ተወዳጅ ካሳው ያደረሱን ጥያቄ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በኢትዮጵያ ምን መልክ አለው የሚለውን ነገር እንድንፈትሽ አስገድዶናል። በእርግጥ በገጠሩ ክፍል ቢሆን ኖሮ ምናልባትም መረጃውን ካለማግኘት ወይንም ለነገሮች ትኩረት ካለመስጠት አንዳንድ ጊዜም የቤተሰብ ተጽእኖ በመሳሰሉት ምክንያቶች አገልግሎቱን ላያገኙ ይችላሉ ተብሎ ሊገመት ይችል ይሆናል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በጤና ኤክስንሽን ሰራተኞችና እንዲሁም እናቶች በተወሰነ ቁጥር ተቧድነው ስለጤናቸው ክትትል የሚያደርጉበት የሚማሩበት ሁኔታ ስለተመቻቸ የመረጃ እጥረት የሚባለው ነገር ብዙም የሚያሰጋ አይደለም። በገጠሩ ክፍል ምናልባት የአቅርቦት ችግር አለ ከተባለ መነጋገር ይቻላል። በከተሞች ግን ልጅ አብዝቶ የመውለድ አዝማሚያ የሚታይ ከሆነ ልጅ የመውለድ ፍላጎት ካልሆነ በስተቀር አገልግሎቱ ወይንም መረጃው ሳይኖር ቀርቶ ነው ማለት አይቻልም። ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል በመንግስትና በሌሎች የሚመለ ታቸው አካላት አገልግሎቱ በተቻለ መጠን በገጠሩም ይሁን በከተሞች ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር በስፋት ተዘርግቶ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑ እሙን ነው።
ወጣቶች ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚጠቀሙበት መከላከያ በየዘመናቱ ምን ልዩነት እንዳለውና ምን ያህል ተጠቃሚ ናቸው የሚለውን አንድ ጥናት እንደውጭው አቆጣጠር በ2015 ይፋ አድርጎታል። ይህንኑ ጥናት መሰረት በማድረግ ለአንባቢ መረጃ ይሆን ዘንድ ወደአማርኛ በመመለስ ለንባብ አቅርበነዋል። ይህ ጥናት በተለይም ያገቡ ወጣት ሴቶች ምን ያህል ዘመናዊ የወሊድ መከላከያ ይጠቀማሉ? የሚለውን ፍተሻ ያደረገ ሲሆን አጥኚዎቹም አበባው ገበየሁ ወርቁ ፣ግዛቸው አሰፋ ተሰማ እና አትንኩት አላምረው ዘለቀ ናቸው።
ዘመናዊ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በኢትዮጵያ፡-
በኢትዮጵያ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የተጀመረው በቤተሰብ መምሪያ በ1966 ዓም ነው። በሁዋላም ከ1980 ዓም ጀምሮ የጤና ጥበቃ ሚኒስር በልዩ ልዩ አጋር ድርጅቶች እገዛ በተስፋፋ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ጀመረ። ከስነሕዝብ ፖሊሲ ጋር በተጣመረ መልኩም በ1993 ዓም በርካታ የአገር ውስጥና አለምአቀፍ ተባባሪዎች የቤተሰብ ምጣኔ አገል ግሎትን ከመንግስት ጎን በመሆን ፕሮግራሙን በማስፋት ከተጠቃሚው ዘንድ እንዲደርስ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስር በ1996 ዓም በኢትዮጵያ ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚበጅ የስራ መመሪያ ያወጣ ሲሆን ይህም ስራውን ለመከታተል እንዲሁም አገልግሎቱን በጥራት እና በስፋት ለማዳረስ እንዲያስችል ሆኖአል። ከዚህም በመነሳት ከ2002 ዓም ጀምሮ በጤና ኤክስንሽን ሰራተኞች ጭምር በመታገዝ አገልግሎቱን ቤት ለቤት በሚያሰኝ ሁኔታ ለመስጠት ተገቢው ጥረት እየተደረገ ነው።
በቅርብ በተደረገው የስነሕዝብና ጤና ዳሰሳ (DHS) ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ባለፉት 10አመታት ውስጥ ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያዎችን በመጠቀም ረገድ ለውጥ ካሳዩ አገራት መካከል የምትጠቀስ ናት።በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ያገቡ ሴቶች 15-49 ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ አጠቃቀም በ2000 ዓም 8% የነበረ ሲሆን በ2011 ወደ 29% አድጎአል። ይህ ቁጥር አሁንም ዝቅተኛ ቢሆንም ግን መሻሻልን አሳይቶአል። የመከላከያው አይነት የተለያየ ቢሆንም በጥቅም ላይ የሚውለው የመከላከያ አይነት ግን በአብዛኛው በመርፌ እና በክንድ ውስጥ የሚቀበር ነው።
ወጣት ሴቶች በተለይም በታዳጊነት እድሜ ያሉት በእርግዝና እና በመውለድ ምክንያት ለሚከሰቱ ሕመሞችና አልፎም ለሞት ሊዳረጉ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። በተለይም በወጣት ሴቶች ዘንድ እርግዝናው ባልተፈለገ ሁኔታ የተከሰተ ከሆነ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። በኢትዮጵያ 28% የሚሆኑት በእድሜአቸው ታዳጊዎች ከ15-19 እና ወደ 24% የሚሆኑት ደግሞ እድሜአቸው ከ20-24 የሚሆኑት ያልተፈለገ እርግዝና አጋጥሞአቸዋል።
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በአስፈላጊው ደረጃ መገኘቱ የእናቶችን ፣የጨቅላ እና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚረዳ መረጃው በመግቢያው ጠቅሶታል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች በአይነት እየጨመረ መምጣቱም ግልጽ ነው። ይህ ጥናት የአገቡ ወጣት ሴቶች ከጊዜ ጊዜ ምንያህል ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔን ተጠቃሚ ሆነዋል የሚለውን ለመፈተሸ የተሰራ ነው። ጥናቱ በእድሜያቸው ከ15-24 የሚደርሱ ያገቡ ወጣት ሴቶችንም በዳሰሳው አሳትፎአል። በ200፣2005 እና 2011 የስነህዝብና ጤና ዳሰሳሃመ መረጃዎችን በማካተት በየአ መተምህረቱም እንደምሳሌ በ2000-1990 ሴቶች በ2005- 1877ሴቶችበ2011-2167 ሴቶች ለጥናቱ ምሳሌ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
በውጭው አቆጣጠር በ2000 ዓም የወጣት ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ፍላጎት ወደ 6% የነበረ ሲሆን ይህ ፍላጎት በ2005 16% እና በ2011 36% ደርሶአል። ይህ ወደ 34% የሚደርስ ልዩነት የተመዘገበውም በሴቶቹ የእድሜ ፣የትምህርት ፣የእምነት እና የባልና ሚስት የጋራ ውሳኔ እንዲሁም ልጅ የመውለድ ፍላጎት ላይ መሰረት ያደረገ ነው።
የዚህ ጥናት ትኩረት ባለፉት አስር አመታት ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያን በመጠቀም ረገድ በበጎም ይሁን በአስከፊ ጎን አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች መኖር አለመኖራቸውን ለመፈተሸ ነው። በጥናቱ እንደታየውም ከ2005-2011 ወጣት ሴቶች አገልግሎቱን በማግኘት ረገድ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ተመዝግቦአል። ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ ሶስት ሀገራትማላዊና ሩዋንዳ አንዱዋ በመሆን ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን ስራ ላይ በማዋልና ተጠቃ ሚው ህብረተሰብም እንዲገለገልበት በማስቻል ፈጣን ለውጥ አስመዝግባለች። ይህም በመንግስት እና ሌሎች በሚመለከታቸው አካላት የልማት ግቡን ለማሳካት ከተወሰዱ እርምጃዎች በጤናውና የእናቶችንና የህጻናቱን ደህንነት በመጠበቅ በኩል ከፍተኛ የልማት አቅጣጫ የተመዘገበበት ነው።
ሌላው ወጣት እና ያገቡ ሴቶች ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ረገድ ለውጥ ያሳዩበት ምክንያት በግለሰቦች ዘንድ በሚታዩ የተለያዩ ገጸባህርያት ምክንያት ነው። የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኑሮ ምክንያት በመገናኘታቸው እና ልምድ መቅሰም እውቀትን ከፍ ስለሚያደርግ በዚያም ሳቢያ ያልተፈለገ እርግዝናን እንዳይከሰት ለመከላከል ወጣት እና ያገቡ ሴቶች ከትዳር ጉዋደኞቻቸው ጋር በመምከርም ይሁን በግላቸው ለአገልግሎቱ በመቅረባቸው ሁኔታውን የተሸለ አድርጎታል።
ጥናቱ በማጠቃለያው እንዳሰፈረው ከሆነ ከ200-2011 ባለው ጊዜ የተመዘገበው የዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ አጠቃቀም የተሻሻለበት ምክንያት በእድሜ ፣በትምህርት ፣በእምነት፣ የትዳር ጉዋደኛሞች ተቀራርበው መወያየታቸው እና ቤተሰቡ በቁጥር ምን ያህል ሊሆን እንደሚገባው መወሰን በመቻላቸው እንዲሁም በኑሮ የተለያዩ ሰዎች ሀሳብ በመጋራታቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የዘመናዊው የእርግዝና መከላከያ አይነት አማራጭ ባለው ሁኔታ መቅረቡም ሌላው ለተጠቃሚው ቁጥር መሻሻል ምክንያት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የጤናና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ምን መምሰል እንዳለበት ህብረተሰቡን በተለያዩ መድረኮች ማስተ ማር ፣እንዲሁም የምክር አገልግሎት መስጠት ፣በተለይም በኑሮ ዝቅተኛ ለሆኑ ላልተማሩ እና ለመሳሰሉት መስጠት ሌላው አገልግሎቱን በተሻለ ደረጃ ለመጠቀም ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል ናቸው ። በገጠሩ አካባቢ ከ2000-2011 በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል አሳይተዋል የተባሉ መስተዳ ድሮች አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው።
ለዚህ አምድ ጽሁፍ መነሻ የሆኑን ተወዳጅ ካሳው ሀሳብም ይሁን ተመሳሳይ ጥያቄ ላላቸው አንባቢዎች ይህ ጥናት መጠነኛ መረጃ ይሰጣል የሚል እምነት አለን። ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በኢትዮጵያ ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ በተሸለ ሁኔታ በመሰጠት ላይ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሞአል።
 ምንጭ -PLOS ONE journal

Read 24603 times