Print this page
Sunday, 25 December 2016 00:00

አሮጌት ሚስቱ ጥቀር ፀጉሩን ስትነቅል ወጣት ሚስቱ ነጭ ፀጉሩን ስትነቅል መላጣ ሆነና አረፈው!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ንሥርና አንዲት ቀበሮ እጅግ የሚዋደዱ ጓደኞች ይሆናሉ፡፡ አንዳችን ላንዳችን የምናስብ፣ በቅርብ የምንተጋገዝ ወዳጆች መሆን አለብን ተባብለው በአንድ ዛፍ ዙሪያ መኖር ይጀምራሉ፡፡ እርስ በርሳቸው በቅርብ በተያዩ ቁጥር የበለጠ ጓደኛሞች እንሆናለን ብለው አሰቡ፡፡
ንሥር፤
‹‹አደራ ቀበሮ፤ እኔ በሌለሁ ጊዜ ልጆቼን ላንቺ ነው ጥዬልሽ የምሄደው፡፡ አንቺም ራቅ ያለ ቦታ የመሄድ አጋጣሚ ቢመጣብሽ ላንቺ ልጆች እኔ አለሁልሽ›› አለች፡፡
ቀበሮም፤
‹‹አይዞሽ፤ እኔም አንቺ ምንም ነገር አጋጥሞሽ ልጆችሽን መጠበቅ ቢያስፈልግ ምንጊዜም ከጎንሽ ነኝ፡፡›› አለቻት፡፡
ስምምነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ንሥር በረዥሙ ዛፍ ጫፍ ላይ ጎጆዋን ሠራች፡፡ በአንፃሩ ቀበሮ ከዛፉ ግርጌ ችፍግ ባለው ቁጥቋጦ ማህል ሠፈረች፡፡ እዚያም ግልገሎችን ፈለፈለች፡፡ ብዙ ጊዜ ከንሥር ጋር በጎረቤትነት አብረው ኖሩ፡፡
አንድ ቀን፤ ቀበሮ ለግልገሎቿ ምግብ ፍለጋ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደች፡፡
ይህን ያስተዋለችው ንሥር፤ ወደ ዛፉ ግርጌ በርራ ወርዳ፡- እሷም ለጫጩቶቿና ለራሷ ምግብ ያሻታልና፤ የቀበሮን ግልገሎች አንጠልጥላ ወደ ዛፉ ጫፍ ወጣች፡፡
ቀበሮ ተመልሳ የሆነውን ሁሉ አየች! ሆኖም ዛፉ ጫፍ ላይ መውጣት እንደማትችል ስትገነዘብና በምንም መንገድ መበቀል እንደማይሆንላት ስታስብ ከልቧ አዝና ተቀመጠች፡፡ በየጊዜው ቀና ብላ መራገሟን ግን ቀጠለች፡፡
ንሥርም፤
‹‹እመት ቀበሮ፤ ምን ሆነሽ ነው የእርግማን መዓት የምታወርጂው?›› ስትል ጠየቀቻት። እንዳልገባት ሆና ለነገሩ እንግዳ ለመምሰል ነው፡፡
ቀበሮም፤
‹‹አይዞሽ ምንም ካላረግሽ እርግማኔ ሊያስፈራሽ አይገባም፡፡ እኔ እማምነው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡››
ንሥር፤
‹‹ምን?›› ብላ በችኮላ ጠየቀች፡፡
‹‹አለመታመንን የሚያጠብቅ ወንጀለኛ፤ ከሰው ልጅ ቅጣት ሊያመልጥ ይችላል፡፡ የአምላክን ቅጣት ግን ፈፅሞ ለማምለጥ አይችለም!›› አለቻት፡፡
እመት ቀበሮ ገና ይሄን ብላ ከመጨረሷ፤ የሆኑ ሰዎች አንዲት ፍየል ወደ ዛፉ አቅራቢያ እየነዱ መጡ፡፡ ፍየሏን በማረድ ለመስዋዕትነት ሊያቀርቡ ነው ዓላማቸው፡፡ አረዷትና ሥጋዋን መጥበስ ጀመሩ፡፡ ንሥር ዛፍ ላይ ሆና የሚሆነውን ስታይ ቆይታ፣ ቁልቁል በርራ አንዱን ሙዳ ከነእሳቱ መንትፋ ወደ ጫጩቶቿ በርራ ገባች፡፡ ይሄኔ አንድ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ከባድ አውሎ ንፋስ ተነሳ፡፡ ከሳር የተሰራው የንስሯና የቤተሰቧ ጎጆ በእሳት ተያያዘ፡፡ የንስሯ ትናንሽ ጫጩቶች ግማሽ በግማሽ በእሳት ተጠብሰው፣ ከዛፉ ላይ ወድቀው ቀበሮዋ ፊት አረፉ፡፡ እመት ቀበሮም፤ ንስሯ ዐይኗ እያየ፤ ተጠብሰው የመጡላትን ጫጩቶች ቅርጥፍ አድርጋ በላቻቸው!!
*         *       *
በመተማመን ላይ የተመሰረተን የቆየ ወዳጅነት ማፍረስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከሰው ባይገኝ ከመለኮት በቀሉ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ የሚለው ተረት የዋዛ አይደለም። ለምናደርገው ነገር ሁሉ ምክንያታዊ መሆን ብቻ ሳይሆን ቀና ልቦና ልንጨምርበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የምንፈጥረው ሰበብ ምንም ዓይት አመክኖአዊ ስሌት ይኑረውና ያሳምን፤ ውስጡ ተንኮል ሊኖርበት ይችላልና ነው፡፡ ተንኮል ያለበት ነገር ቢያንስ ውሎ አድሮ ህሊናን ይወጋል፡፡ ቃልን አለማክበር የሀገራችን አባዜ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አብዛኞቹ ጥያቄዎቻችን እምንመልሰው ለጊዜው ከውጥረት ለመገላገል ከሆነ፣ ስር የሰደደው ችግር ሳይነቀል ይቀራል። መፍትሄአችን ዋናው መንገድ ሲበላሽ መተንፈሻ ተብሎ እንደሚሰራው መጋቢ መንገድ ብቻ ሊሆን አይገባውም። ምነው ቢሉ፤ መተንፈሻ ብለን የሰራነው መንገድ ዋና ሆኖ ሊቀር ይችላልና! ከዚያ ወዲያ አውራ ጎዳናውን እንረሳዋለን፡፡
የዚህ አይነቱ አሰራር በየቦታው ሲከሰትና ሲጠራቀም አገር - ሙሉ የመንገድ ችግር ያጥለቀልቀናል፡፡ ስለዚህ የዋናና የማስተንፈሻ መፍትሄዎቻችንን ባህሪ መመርመር ትልቅ ቁም ነገር መሆኑን እንገንዘብ፡፡
ችግሮቻችንን ለማስወገድ ጥረትና ትግል የማስፈለጉን ያህል፣ ውስጣዊ ዲሞክራሲን ያለ አንዳች ሽንገላና ይስሙላ መገንባት አማራጭ የለውም፡፡ አለበለዚያ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ በማናቸውም ጠንካራ የትግል እንቅስቃሴ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁለት መሰረታዊ አካሄዶች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህም ውስጠ ፓርቲ ትግልና በፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ትግሎች ናቸው፡፡ እነዚህን በድርጅቶችም አናፅሮ ማየት አይከብድም፡፡ (ፈረንጆቹ፣ በተለይም የጥንት አበው ፖለቲከኞች፤ Inter - party and Intra - party struggle የሚሉት መሆኑ ነው፡፡)
ስም ተግባር አይሆንም፡፡ ራስን ማየትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ it is all nomenclature, but it is practice that matters - ከስሙ ምን አለህ፤ ዋናው ተግባር ነው እንደማለት ነው፡፡ “ግምገማ”፣ “ውይይት”፣ “ተሀድሶ”፣ “ጥልቅ - ተሃድሶ” … ወዘተ ስሞችና የስም ማሻሻያዎች ብቻ እንዳይሆኑ ተግባራቸውን እንፈትሽ! ከአንደበት ወጥተን ድርጊትን እናድምቅ፡፡ የሀገራችን ፍቱን ጉዳይ የሀብትና የስልጣን ፍትሃዊ ድልድል ነው! መፍትሄዎችን ለነገ አንበል (Procrastination):: የእኔ ጥፋት አይደለም፤ የውጪ ኃይሎች ነው አንበል (No externalization) በሌሎች አናሳብ (No blame - shifting) በአዲሱ የወጣቱ ትውልድ እንመን (The new is invincible) የመንግስት ባለስልጣናት ንግድ  ውስጥ እንዳይገቡ እንታገል (fight bureaucratic capitalism)፡፡ የሁሉም መጠቅለያ ግን ህዝብን የሚያሳትፍ ዲሞክራሲን ዕውን ማድረግ ነው!! አሮጌውን ሥርዓት መታገል ግድ ነው፡፡ አዲሱ እንዲፈልቅ መሳል ተገቢ ነው፡፡ (Fight conservatism Accept the invincibility of the new) ዋናው አገር የሚያድን ይሄ ነው፡፡ ‹‹ሁለት ባላ ትከል፣ አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል›› ዛሬ አያዋጣም፡፡ ያ ከሆነ፤ ‹‹አሮጊት ሚስቱ ጥቁር ፀጉን ስትነቅል፣ ወጣት ሚስቱ ነጭ ፀጉሩን ስትነቅል፤ መላጣ ሆነና አረፈው!›› የሚለው ተረት ዕውን ይሆናል፡፡ በወጉ እንጓዝ! አገር በወጉ እንድትለወጥ መላ እንምንታ!

Read 5522 times
Administrator

Latest from Administrator