Sunday, 25 December 2016 00:00

ስታድዬሞቻችን ያዋጣሉ?!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • የመሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድዬም ጥር 6 በወልዲያ ከተማ ይመረቃል፡፡
                  • በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ስታድዬሞች ይገነባሉ፡፡ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ

       በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሸራተን አዲስ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤክዚዮከቲቭ አፊሰር ዶክተር አረጋ ይርዳው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ መግለጫው በክቡር ዶክተር ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ የገንዘብ ወጭ ግንባታው ተጠናቅቆ፣ በጥር 6 በወልዲያ ከተማ የሚመረቀውን አዲስ ስታድዬም ይመለከታል፡፡ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም እና የስፖርት ማዕከል ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ዶ/ር አረጋ ይርዳው እንደገለፁት ስታድየሙ ስያሜውን ያገኘው በከተማው ህዝብ ውሳኔ ነው፡፡  ስታድዬሙ በጥር 6 /2009 ዓ.ም በይፋ ከመመረቁ በፊት በአጠቃላይ 567 ሚሊየን ብር ወጭ ሆኖበታል፡፡ በወጭው ከፍተኛነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ የሚጠቀስ ይሆናል። ‹‹ስታድዬሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት  ነው›› ያሉት ዶ/ር አረጋ፤ ‹‹ለዞኑ፣ እና ለከተማው መስተዳድር በኃላፊነት የሚሰጥ፣ የህዝብ ንብረት  ይሆናል›› ብለዋል፡፡  ወልዲያ ከአዲስ አበባ 520 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡  በተራራ የተከበበች ውብና የደጎች ከተማ ይሏታል፡፡  የወልዲያ ህዝብ ለስፖርት ያለው ፍቅር የእህል ውሃ ያህል ነው፡፡ ስታድዬሙ ሊሠራ የቻለው በከተማው ህዝብ በተቆሰቀሰ ፍላጎት ነበር። በመጀመርያ በተደረገው እንቅስቃሴ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተድርጎ እስከ 30 ሚሊዮን ብር  ተሰባስቧል፡፡ ይህ ገንዘብ በቂ አልነበረም፡፡ እናም በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አማካኝነት በሸራተን አዲስ ሌላ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጀ፡፡  ‹‹የወልዲያ ልጆች ስታድዬሙን እኔ እገነባለሁ። ለዶ/ር አረጋ ደግሞ ኃላፊነቱን ሰጥቸዋለሁ፡፡›› በማለት ሼህ መሀመድ 100 በመቶ ወጭውን በመሸፈን እንደሚያሰሩ ቃል ገቡ፡፡ ከዚያም የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ፕሮጀክቱን የመነሻ ዲዛይኑን በመቀየር በዕጥፍ ዋጋ በፊፋ መስፈርቶች የተቀረፀ ዲዛይን  በድጋሚ አሠራ፡፡
ኦርጋኒኩ፤ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድዬም
የመሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም በወልዲያ ከተማ መቻሬ ሜዳ በተባለው ቦታ 177 ሺ ካ.ሜ  ላይ ተቀምጧል፡፡ ከባህር ወለል በላይ 2000 ሜት ከፍታ ላይ የተገነባው ስታድዬሙ በዘመኑ ቴክኖሎጂ የታነፀ ሲሆን ከበጋ እስከ ክረምት ውድድሮችን ማስተናገድ ይችላል። 25115 ወንበሮች ላይ ተመልካቾች የሚይዝ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ የተሰሩት በአገር ውስጥ ነው፡፡  በኢትዮጵያ ዙሪያ ገጠም የሆነ ጥላ ፎቅ የተሰራለት የመጀመርያው ስታድዬምም ሆኗል፡፡ በሚያስፈልግ መጠን ብርሃን ሙቀት የሚሰጥና የሚቀንስ  ነው፡፡  በዙርያው ከ156 በላይ ፓውዛ መብራቶች ተገጥመውበታል፡፡ የፊፋን መስፈርት ሙሉ ለሙሉ ያሟላ ነው፡፡ የመሮጫ ትራክም ያለው ሲሆን በዘመናዊ ደረጃ የተዘጋጀው ይህ የአትሌቲክስ ትራክ በመሙ እስከ 8 አትሌቶችን በአንድ የልምምድ መርሃ ግብር ሊያስተናግድ የሚችል ነው፡፡ ዘመናዊ ሜዳ በአንድ ጊዜ አራት ቡድኖች ያስተናግዳል፡፡ ጨዋታዎች በተከታታይ ሊደረጉበት ይችላሉ፡፡ አራት የመልበሻ ክፍሎች እና ሁለት የማሟሟቂያ ሜዳዎች ተሰርተውለታል፡፡ በተጨማሪ ልዩነት የሜዳው ሣር ነው፡፡ ከው ዘርያ ጋር የተዳቀለ የሳር ተከላ ተደርጎለታል። ከሣሩ ስር ባንቧዎች ተቀብረዋል፡፡ ውሃ የሚቋጥር ሜዳ አይሆንም፡፡ በስታዲየሙ ውስጠኛ ክፍል ሁለት ግዙፍ ስክሪኖች ተገጥመዋል፡፡ ሁለት የልዩ እንግዶች (ቪአይፒ) ቦታዎች ተዘጋጅተውለታል፡፡ አንደኛው በመስታውት የተከለለና ለደህንነት አስተማማኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ መስታውት የሌለው የቪአይፒ መቀመጫዎች ስፍራ ነው፡፡8 ሳውንድ ፕሩፍ ስቱድዮች ያሉት  ሚዲያ ትሪቢዮን አለው። በውስጡ ከ300 በላይ መኪኖች ያቆማል፡፡ የመብረቅ መከላከያ ተገጥሞለታል፡፡  10 በሮች አሉት፡፡ 7 አምቡላንስ ያስገባሉ የአካባቢውን ባህል፣ አኗኗር ታሪክ ለመግለፅ እንዲያመች በሮቹ ስም ተሰጥቶቸዋል፡፡ ለምሳሌ ዳና፣ ላሊበላ…  እንደማዕከልም የመቀጠል ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ስላሟላ ነው።  በውጭኛው ስታድየም ክፍል የዋና ገንዳ፣ የቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስ እና የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎች እንዲሁም ለ34 ሰዎች የሚሆን የእንግዳ ማረፍያ አካቷል፡፡ በዙርያው ከመቶ በላይ የንግድ ሱቆች የተዘጋጀለትም ነው፡፡ ስታድየም የሄሊኮፕተር ማረፍያ፣ በቂ የመኪና ማቆምያ እና ውብ አረንጓዴ ቦታዎች አሟልቷል፡፡ በ2009 ዓም ፕሪሚዬር ሊግን የተቀላቀለው ወልድያ ስፖርት ክለብ በዚሁ ዘመናዊ ስታድየም የሚጫወት ሲሆን ከባህርዳር ስታድዬም ቀጥሎ በክልሉ ሁለተኛው ስታድዬም ሆኖ ይመዘገባል፡፡የወልዲያ ስፖርት ክለብ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ይደገፋል፡፡ ስታድዬሙ ከማለቁ በፊት በመልካ ቆሬ ስታድዬም ይጫወት ነበር፡፡ ወደ ፕሪሜርሊጉ ማለፉን ተከትሎም በሚድሮክ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እየተሰጠ ነው፡፡  የመሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድዬም በጥር 6 ተመርቆ ስራውን ከጀመረ በኋላ ክለቡ ሜዳው አድርጎ ይጫወትበታል፡፡ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ የክለቡን ሎጎ አሰርቷል፡፡ የስፖርት ትጥቅ፣ የመጓጓዣ አውቶብስ  ድጋፎች ከማረጉም በላይ በአዲስ አበባ የተጨዋቾች ካምፕ አዘጋጅቶ አደራጅቶታል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድዬም ኦርጋኒክ ነው በማለት ዶ/ር አረጋ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ ስታድዬሙ በስፖርት መሠረት ልማት ተምሳሌት የሚሆንበት ብዙ ውጤቶች ማስመዝገቡን ሲያብራሩ እንጅ ኦርጋኒክ ያሉት ያለምክንያት አልነበረም። በኢትዮጵያ አቅም የተገነባ ስለሆነ ነው፡፡ ከ95 በመቶ በላይ በስታድዬሙ ግንባታ ላይ የሠሩት መሃንዲሶች እና ሌሎች ባለሙያዎች፣ 90 በመቶ  የግንባታ ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች በአገር ውስጥ በመመረታቸው ነበር፡፡ ለኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የተሰራ በመሆኑ ስታድዬሙ ኦርጋኒክ ነው የሚሉት ዶክተር አረጋ ይርዳው  የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ከሆኑ 25 ኩባንያዎች፤ በተለይም 10 ያህሉ በአጋርነት ተሰልፈው ፕሮጀክቱን በ4 ዓመታት ውስጥ በማከናወን ስታድዬሙ  ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ሊያበቃ መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ሼህ አላሙዲ ገንዘብ መድበዋል። ሁዳ ሪል ስቴት ዋናው የኮንስትራክሽኑ ስራ ተቋራጭ ነበር።  ኩባንያዎቹ በየዘርፉ የኮንትራት ስራ እየተሰጣቸው ገንብተውታል፡፡ የስራ ልማዳቸውን አሳድገውታል፡፡፡ የሙያተኞች ብቃት ተሻሽሏል፡፡ በአገር በቀል መሀንዲሶች ለስታድዬም እና ሌሎች የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎች ኢትዮጵያዊ አቅም ተፈጥሯል፡፡ ከወልዲያው ስታድዬም ግንባታ በኋላ ሚድሮክ ሌላ ግንባታ ኮንትራት ለማግኘት ፈልጎ አልተሳካለትም፡፡ ወደፊት ዕድሎች እንደሚፈጥሩ እምነት ግን አለ በስታዲዬም ግንባታ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ፍላጎት አለን ብለዋል፡፡ ቺፍ ኤክሲኪዩቲቭ ኦፊሰሩ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን 50 እና 60 ሺ ተመልካች የሚይዙ ስታዬሞች መገንባት ይቻላል፤ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከአዲስ አድማስ ለሚድሮክ ቴክኖሎጁ ግሩፕ ኤክስኪዩቲቭ  ኦፊሰር ዶ/ር አረጋ ይርዳው  የቀረቡ 3 ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፡፡  ስታዲየሞች በብዛት ያስፈልጋሉ ወይ፣ ከሆነስ በየትኞቹ ከተሞችና ክልሎች የሚለው የመጀመርያ ነበር..፡፡  ዶ/ር አረጋ ምላሽ ሲሰጡ “መቼ ነካውና፡፡ አገሪቷ ውስጥ ምን ስታድዬም አለና፡፡ 100 ሚሊዮን ህዝብ ያለባት - 70 በመቶ ወጣት ለሆነበት አገር። ስታድዬም ብዙ ነው የሚያስፈልገን፣ ለጊዜው ተጫዋች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ በየምሽቱ እንደምናየው የማንቸስተር፣ የአርሰናል ስታድዬም አይሟላ ይሆናል፡፡ የአቅም ጉዳይ፣ የስፖርቱ እድገት፣ የተመልካችነት ባህል መጨመር እነዚህን ሁሉ የሚጀምር ነው፡፡ እስከመቼ ድረስ ነው፡፡ በቴሌቪዥን ብቻ የሌላውን አገር ጨዋታ እያየን የምንዘልቀው።  ስታድዬሞች የት ይገንቡ፤ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥናት ተደርጎበታል፡፡  በእያንዳንዱ ክልልና ከተማ ልክ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳሉ ስታዲዬሞች መኖር አለባቸው።››
የወልዲያ ከተማ አየር ሁኔታን በተመለከተ እና መቼ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ሊያስተናግድ ይችላል የሚሉት ሌሎቹ ከአዲስ አድማስ የቀረቡ  ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ዶ/ር አረጋ በመጀመርያ ምላሻቸው ስለአየር ሁኔታው ‹‹የኢትዮጵያ አየር ለማንም ስፖርተኛ መጠናት የሚያስፈልገው አይደለም።  ከወደ በረሃ ለሚመጡ ቡድኖች  አስፈላጊ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ከፍ ያለች ከተማ ነች ወልዲያ … ተጋጣሚ ቡድኖችን እያስተናግደን ቶሎ ቶሎ ብናሸንፍ ጥሩ ነው፡፡›› ብለው ለመጨረሻው ጥያቄ “ስታድዬሙ የተረከበው አካል ይህን በቶሎ ቢያደርግ ማየት ደስ ይለኛል፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የስታዲየሙን ፋይዳ አስመልክቶ ዶ/ር አረጋ ሲናገሩ ወልዲያ ለላሊበላ ቅርብ በመሆኗ፣ ባቡር በከተማው ስለሚያልፍ፤ ለመቀሌ፣ ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለደብረ ማርቆስ አዋሳኝ ከተማ በመሆኗ የቱሪዝም መስህብነቷን እንደሚጨምር በመጥቀስ ነው፡፡ በከተማው ስፖርትን ለማነቃቃት ከፍተኛ አቅም በስታድየሙ መኖር ይገኛል በማለትም አብራርተዋል፡፡
‹‹ስታድዬሙን ወልዲያ ከተማን ያስተዋወቃል በማለት በጋዜጣዊ መግለፃ ላይ የተናገሩት ዶክተር አረጋ ይርዳው፤ በካሊፎርኒያ ቤቨርሂልስ እንደሚገኘው ‹‹ሆሊውድ›› የተሰኘ ላንድ ማርክ ምልክት ቢሰራም የመሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድዬም የከተማው ምልክት ይሆናል ብለዋል፡፡ ስታድዬሙ አገር አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች በማስተናገድ  ፈርቀዳጅ እንደሚሆን የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እንደሚያምንበት ከፍተኛ የገቢ አቅም ሊፈጥር የሚችል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ስታዲየሙን የሚያስተዳድረው የከተማው አስተዳደር ነው፡፡ ስታዲየሙን በማከራየት፤ ከዩኒቨርስቲ ጋር በቅንጅት ለመስራት፣ ብዙ ፋይዳዎቹ ይኖሩታል፡፡ ሚድሮክ የስታዲየሙን የቅርብ ክትትል ያደርጋል ዕድሳቶችን በየጊዜው ያከናውናል፡፡
የስታድዬም መሰረተ ልማቶችና የውድድር መስተንግዶዎች
በኢትዮጵያ ስፖርት አንዱ ትልቁ ውጤት የስታድዬም መሰረተ ልማቶች መስፋፋት መሆኑን ባለፉት 3 ዓመታት በየክልሎቹ እና በየከተሞቹ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ማስተዋል ይቻላል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የክልል ከተሞች ሙሉ በሙሉ ስራ የሚጀምሩ ከ12 በላይ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስታድዬሞች አገሪቱ ይኖሯታል። እስከ 60ሺ የሚያስተናግደው የባህርዳር ስታድዬም ግንባታውን በቀዳሚነት አጠናቅቆ አገልግሎት በመስጠት ፈርቀዳጅ ነው፡፡ የባህርዳር ስታድዬም የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፤ ከዚያም የአፍሪካ ክለቦች ውድድሮችን እንዲሁም የብሄራዊ ቡድኑን ጨዋታዎች በማስተናገድ ስኬታማ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አምና 38ኛው የሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ያስተናገደው በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የተገነባው የሐዋሳ ስታዬም  እስከ 45ሺ ተመልካች የሚይዝ ነው፡፡ የሐዋሳ ስታድየም የሴካፋን የምድብ ጨዋታዎች በማስተናገድ በካ እውቅና እግኝቶ ከባህርዳር ስታዬም በመቀጠል ሁለተኛው ውጤታማ መሰረተልማት ሆኗል። ዋልያዎቹ 2ለ0 ሶማሊያን ያሸነፉበትን የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኢንተርናሽናል ጨዋታ ለማስተናገድ የበቃ ሲሆን ከዚያም ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከሲሸልስ ጋር የተደረገ ግጥሚያንም ያስተናገደ ነው። ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሐዋሳ እና የባህርዳር ስታድዬሞች አገልግሎት መስጠትና በካፍ እውቅና ማግኘት በመጀመርያ የፈጠሩት መነቃቃት በሌሎች ከተሞችም በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በካፍ እና በፊፋ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ ስታዬሞች ደግሞ ብዛታቸው 5 ደርሷል፡፡ የአዲስ አበባው ይድነቃቸው ተሰማ ስታድዬም፤ አበበ ቢቂላ ስታድዬም ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ ከዚያም ባለፈው ዓመት የባህርዳር ፤ የሃዋሳ ከነማ እና የድሬዳዋ ስታድዬሞች እውቅና በማግኘት አህጉራዊ ጨዋታዎችን አስተናግደዋል፡፡ በወልዲያ ከተማ የተገነባው ሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ  አላሙዲ ስታድዬም ለዓለም አቀፍ እውቅና በመድረስ 6ኛው ስታድዬም ነው፡፡
በግንባታ ላይ የሚገኙት 30ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው ስታድዬም  የመቀሌ ስታድዬም ፤ ከ90 በመቶ በላይ ግንባታው የተጠናቀቀ እና 60ሺ የሚይዘው የነቀምቴ  ስታድዬም በመጨረሻ ምእራፍ ላይ በምደረሳቸው የሚጠቀሱ ይሆናል፡፡ የአዳማና ጋምቤላ ከተሞች ዘግይተው ቢጀምሩም 80ሺ እና 30ሺ ተመልካቾች የሚይዙ ስታድዬሞቻቸውን እንደ ቅደም ተከተላቸው እያስገነቡ ናቸው፡፡ የአዳማ ስታድዬም እስከ 1.7 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጭ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በሚይዘው ተመልካች ብዛት ግዙፉ ሊሆን የሚበቃ ሲሆን እስከ 80ሺ በማስተናገድ ነው። እንዲሁም የጋምቤላው ስታድዬም እስከ 380 ሚሊዮን ብር ይወጣበታል፡፡ በሚገነቡ ስታድዬሞች የዘገየው የአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡  እስከ 60ሺ ተመልካች እንደሚይዝ የሚጠበቀው አደይ አበባ የሚል ስም የወጣለት ብሄራዊ ስታድዬም ዋናው የከተማ እቅድ ነው፡፡ ይህ ስታድዬም ከጎኑ የኦሎምፒክ መንደር የሚገነባለት መዋኛ፤ የመረብ ኳስ፤ የቅርጫት ኳስ ሜዳዎች እና ሌሎች የስፖርት መሰረተልማቶች ያሉት  60ሺ ተመልካች የማስተናገድ አቅም የሚኖረው  ይሆናል፡፡ የስታድዬሙ ዲዛይን በ40 ሚሊዮን  በኤምኤች የተሰራ ሲሆን በቻይና ስቴት ኢንጅነሪንግ  ኮርፖሬሽን በሁለት ደረጃዎች የሚገነባ የግንባታ ወጭው በመጀመርያው ምዕራፍ እስከ 2.4 ቢሊዮን ብር የተተመነ ነው፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በአምስት ዞኖች እያንዳንዳቸው   ለግንባታቸው 300 ሚሊዮን ብር ወጪ  አምስት ስታድዬሞች እንደሚታነፁ የተገለፀው ከሶስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በመተሳሳይ ወቅት በ1.3 ቢሊዮን ብር በጀት 60ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የአቃቂ ቃሊቲ ስታድዬም ዲዛይኑ በዮሃንስ አባይ ኮንሰልታንሲ ተሰርቶ በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን እንደሚገነባም ተገልጿል፡፡ ሻሸመኔ፤ ድሬዳዋ፤ ሃረር፤ ጅማ ፤ ጎንደር፤ ስታድዬሞች መገንባት ያለባቸው ሌሎች ክልሎችና ከተሞች መሆናቸው ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከወር በፊት ይፋ ባደረገው የ2008 በጀት ዓመት የገቢ ዝርዝር ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ከስታድዬም ትኬት ሽያጭ የተገኘው ነው፡፡ በውድድር ዘመኑ ከብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች፤ ከሴካፋ እና ከፕሪሚዬር ሊግ ውድድሮች በተያያዘ የተገኘው ገቢ ከ13.6 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡
የስታድዬሞች መሰረተ ልማት መስፋፋት  
ኢትዮጵያ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች የሚኖራትን ንቁ ተሳትፎ የሚያነቃቃ ይሆናል፡፡ አገሪቱ ለትልልቅ የስፖርት መድረኮች በመስተንግዶው፣ በትራንስፖርት አቅርቦት፤ በፀጥታና ደህንነት ያሏትብ አቅሞች  ከስታድዬሞቹ ግንባታ ጋር የሚፋጠን ነው። በተለይ ኢትዮጵያ በ2020 እኤአ የምታስተናግደው 6ኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ቻን በስታድዬሞች መሰረተልማት በኩል ያላት ዝግጁነት የተረጋገጠ ነው።  እንደ ቻን አይነት አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድር ለማስተናገድ አምስት ደረጃውን የጠበቁ ስታድዬሞች በቂ ናቸው፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ በአማካይ 40ሺ ተመልካች የሚያስተናግዱ 4 ስታድዬሞች ከተገነቡ  ምናልባትም ኢትዮጵያ  የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግድበት እድል በሚቀጥሉት 16 ዓመታት ሊሳካ የሚችል ይመስለኛል፡፡
ከ2020 እኤአ የቻን ውድድር መስተንግዶ በኋላ ትኩረቱ የአፍሪካ ዋንጫ እንዴት ይዘጋጃል? መሆን አለበት፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ብቁ የሚላቸው አገራት በሆቴል እና መስተንግዶ፤ ቢየያንስ አራት አለም አቀፍ ደረጃ የጠበቁ ስታድዬሞች ከእነ ልምምድ ስፍራቸው፤ በቂ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ አስተማማኝ ደህንነት እና ፀጥታን በዋና መስፈርቶቹ ይመለከታል፡፡
በአህጉራዊ ውድድር መስተንግዶ በሁሉም ከተሞች የሚገኙ ስታድዬሞች  ከአምስት በላይ ከብሄራዊ ኮሚቴው ጋር ተፈራርመው የሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ከወዲሁ ማፈላለግ እና በአጋርነት የመስራት ስምምንት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ስራ እየጀመሩ የሚገኙት እና በግንባታ ላይ ያሉት ብዙዎቹ ስታድዬሞች በአፍሪካ ደረጃ ተመጣጣኝ ጥራት ያላቸው መሆናቸው የሚያበረታታ ነው፡፡ የስታድዬሞቹ በየክልሉ መስፋፋት ታላላቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት አቅም፤ የየተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያነቃቃም ይሆናል። የስፖርቱን አስተዳደር ሁለገብ አቅም ያሳድጋል፡፡ አለም አቀፍ ትኩረት ይገኝበታል፡፡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ይሆናል፡፡ የስፖርት እድገትን ለማቀላጠፍ ያግዛል፡፡ አንድ አገር አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮችን በማስተናገድ በቂ ተመክሮ እና አቅም እየገነባ ሲሄድ እንደ ዓለም ዋንጫ ኦሎምፒክ መድረኮችን ማዘጋጀት የሚቻልበት ምእራፍ ላይ የሚደረስ ይሆናል፡፡
ዎርልድ ስታድዬም ኢንዴክስ የሚባል የዓለም አቀፍ ሪፖርት አለ፡፡ በዳንሽ ኢንስቲትዩት ነው ስፖርት ስታዲስ የተሰራ ጥናት ነው “play the game” በሚል ርዕስ በለቀቀው ሪፖርቱ በ20 አገራት በሚገኙ 75 ስታዲየሞቹ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ከአውሮፓ ዋንጫ፣ ከዓለም ዋንጫ እና ከአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶዎች ጋር በተያያዘ  በ20 አገራት ባለፉት 15 ዓመታት የተገነቡት 75 ስታድየሞች በ14.5 ሲሆን ዶላር ነው፡፡ የዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ የስታድዬም ግንባታና እድሳት በጀት እስከ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ በ2018 እ.ኤ.አ ራሽያ ለ21ኛው ዓለም ዋንጫ 3.8 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2022 እ.አ.አ ኳታር ለ22ኛው ዓለም ዋንጫ እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር በጀት የያዙት ከስታዬሞች ግንባታና ዕድሳት ጋር በተገናኘ ነው፡፡  በሌላ በኩል ደረጃውን የጠበቀ የኦሎምፒክ ሙሉ ስታዲየም እስከ 270 ሚ. ዶላር በጀት ይጠይቃል፡፡ በ2008 ዓ.ም ቤጂንግ 29ኛውን ኦሎምፒክ ያስተናደችው በ428 ሚ. ይዞር በተገነባው የወፍ ጎጆ ስታድዬም ነበር፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት አፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጁ አገራት በአማካይ ከ4-6 ስታድዬሞች እንዲገነቡ በካፍ የመስተንግዶ መስፈርት ይጠይቃሉ፡፡ ለአውሮፓ ዋንጫ መስተንግዶ 8 ስታድዬሞች ለዓለም ዋንጫ  ደግሞ ከ10-12 ስታዲዬሞች መገንባት መስፈርቱ ይጠይቃል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ስታድየሞች ከፍተኛ 45ሺ ዝቅተኛ 15 ሺ ተመልካች የሚያስተናግዱ መሆን አለባቸው፡፡ የአውሮፓ ዋንጫ ስታድዬሞች  በአማካይ ከ30-50 ሺ ተመልካች የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡  በዓለም ዋንጫ የመክፈቻና የዋንጫ ጨዋታዎች የሚያስተናግዱ ስታድዬሞች ያስፈልጋሉ፡፡ ባለፉት 5 የአፍሪካ ዋንጫዎች  አዘጋጅ አገራት በአማካይ ለመስተንግዷቸው ከ3 እስከ አምስት አዳዲስ   ስታድዬሞች ገንብተዋል፡፡ 

Read 3793 times