Monday, 12 December 2016 12:17

የኪስ ቀበኛው

Written by  ዮናስ ነማሪያም
Rate this item
(12 votes)

… መሃል ጣሊያን ሰፈር የሚገኝ ጨለም ያለ ቡና ቤት። … በጣት የሚቆጠሩ ጠጪዎች እንደ ፍላጎትና ኪሳቸው ብራንዲ - ጂን - ኡዞ - ቢራ … ይዘዋል። አሳላፊዎቹ ላይ ታች ይባትላሉ … ቅርፃቸው፤ እድሜያቸው የተለየ ሴቶች … ሁለመናዋ ከተድበለበለው ቲጂ እስከ ሲኪኒዋ አልሚ … 16 ዓመቷ ከሆነው ሰኒ እስከ 40 ዓመቷ ዝናሽ። …
ካሸሪም ተቆጣጣሪም ዝናሽ ነች። 40ኛ ዓመት የዕድሜ ጠርዝ ላይ እንደ ዘበት ደርሳለች። በአፍላ የኮረዳነት ዘመኗ አንፀባራቂ ውበት ነበራት … በሴትነቷ ዙሪያ የብረት አጥር አጥራ ማንንም ወንድ የማታስጠጋ አራስ ነብር። ዛሬስ?
ሰዓቱ እየሄደ ነው … ሴቶቹ መውጫ እየቆረጡ ከወንዱ ጋር ወጡ። ሁሉም ጠጪዎች ወጥተው አንድ ልጅ ብቻ ቀርቷል … እድሜው በ20ዎቹ መጀመሪያ ይገመታል … የመጨረሻዋን የቢራ ጭላጭ ጨልጦ ሊወጣ ሲነሳ ዝናሽ “… በቃ መሄድህ ነው፤ ጨክነህ …” አለችው በሚያማልል ድምፅ። በአግራሞት አፈጠጠባት። አይኗ ውስጥ የፍትወት ስሜትን የሚያጭር አማላይ ድባብ አየ። የዝናሽ ሞንዳላ ገላ ልጁን በወሲብ ጥማት አንሰፈሰፈው። … ለመውጣት የነበረውን ሃሳብ እርግፍ አድርጎ ደብል-ብራንዲ አዘዘ - ለሷም። … ደገሙ … ደጋገሙ። ዝናሽ በፍጥነት ነበር የምትጠጣው - ግን አንዳችም ሞቅታ አይታይባትም … ልጁ ግን ጢው ብሎ ሰከረ … አብሯት ለማደር እንደሚፈልግ እየተለፋደደ ነገራት … የደንቡን ተነጋገሩ - ለአዳር …
“ለመሆኑ ኮንዶም ይዘሃል?”
አለመያዙን አንገቱን በመነቅነቅ ገለፀላት …
“የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ አሉ .. በል ፈጠን ብለህ ገዝተህ ተመለስ።” ወጣ ብሎ አንድ ፓኬት ገዝቶ መለስ አለ። … “አንድ ፓኬት ብቻ ነው እንዴ የገዛኸው፤ ሶስት ብቻ እኮ ነው የሚይዘው በል ሌላ ጨምር … ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም አሉ …”
ልጁ የዝናሽን አሽሟጣጭ ተረት ላለመስማት በፍጥነት ወጣ ብሎ ሁለት ፓኬት ተጨማሪ ገዛ …
ወዴት መሄድ እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ኮንዶሙን በእጁ እንደያዘ ተገትሮ ቀረ …
“ምን እንደ ከረሜላ እጅህ ላይ ታንከረፍፋለህ ወደ ኪስህ …” የሚል መመሪያ ሰጥታው ወደ ክፍሏ ይዛው ገባች …
… ግብ ግብ … ትንቅንቅ … እንደ እሳት ጭድ መንደድ … ግን አመድ የማይታይበት የወሲብ ጦርነት። …
…ማለዳ ከእንቅልፉ ነቃ። ልብሱን መለባበስ ጀመረ። ቅዝቃዜው ያንዘፈዝፋል። በዚያ ላይ ረሃብ እያከከው ነው። ኪሱ ውስጥ ድንቡሎ የለም። የጫማውን ክር እያሰረ ቀና ሲል የዝናሽ ቀይ ፓንት እንደ ባለጌ ልጅ ምላስ ከፍራሹ ከንፈር ተንዘላዝሎ … የመቶ ብር ኖት ጫፍ ለአመል ያህል ከፍራሹ አፈንግጦ አየ። ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያውጠነጥን መልካም አጋጣሚ ተፈጠረለት። ዝናሽ ፖፖውን ይዛ ወጣች። ልጁ በፍጥነት እጁን ወደ ፍራሹ - ወደ ብሩ ኖት በዘረጋበት ቅፅበት ዝናሽ መለስ አለች … ብሩን እንደያዘ - እጅ ከፍንጅ! … እጁን ጠምዝዛ ብሩን መነጨቀችው … በቃሪያ ጥፊ ስታጮለው በቆመበት ተንገዳገደ … “ውጣ! አይንህ ይውጣና!” ስትል እንደ ብራቅ ጮኸችበት።
ልጁ ሹክክ ብሎ ወጣ። የወራዳነት፣ የልክስክስነት ስሜት አበጠረው። … በውስጥ ለውስጥ መንገድ ወደ መርካቶ አቀና … አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጋ  ሲደርስ አረፍ አለ … “ልክስክስ … ቅሌታም … ያውም የኪስ ቀበኛ መንታፊ …” ሲል ራሱን ወቀሰ … ልጁ እሳት የላሰ መንታፊ ኪስ አውላቂ  ነው … አለንጋ ጣቶች፤ ለኪስ አውላቂነት የሰጡ - ባለመንጠቆ ጣቶች። ጥርት ያለ ሰልካካ የልጅነት ዛላው … ማንም በኪስ አውላቂነት አይጠረጥረውም። እንደ እርግብ የዋህ የሚመስል ገፅታ ቢላበስም ልጁ እባብ ነበር።
… ከሰባተኛ ወደ አውቶቢስ ተራ እንደ ውሃ ቀጂ እየተመላለሰ የስንቱን ኪስ ያራቆተ … ስንቱን የደም እንባ ያስለቀሰ የኪስ ቀበኛ። ገንዘቡ ግን ኪሱ አይቀመጥም። በመጣበት ፍጥነት ይሄዳል … ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ … እየፈጩ ጥሬ። ጥሬ ብር መያዝ አልቻለም። መጠጥ፣ ጫት፣ ሴት … ያለዕድሜው የተዘፈቀባቸው የወጪ ቀዳዳዎች ናቸው። ብር ከሱ ውስጥ የመቆየት አንዳችም ፍላጎት የለውም። ከብር ጋር ሆድና ጀርባ እንደሆነ፤ ሁሌም እንደጠረረበት ነው። ልክ እንደዛሬው ህይወትን የሚጀምረው በዜሮ ነው። ዛሬ ማለዳ ከሰው ኪስ ሳይሆን ከፍራሽ ስር ሊመነትፍ ቢሞክርም አልተሳካለትም … ያቺ እንደ አይጥ አደጋ የማሽተት ችሎታ ያላት ሸርሙጣ እጅ ከፍንጅ ያዘችው! በቃሪያ ጥፊም አጮለችው … በጥፊ የተመታበትን ጉንጩን በማሸት ላይ ሳለ፣ አይኖቹ አንድ አዛውንት ላይ አረፉ።
ሎተሪ ለመግዛት ካወጡት ዳጎስ ያለ የኪስ ቦርሳ ጋር አይኖቹ ተጋጩ። የግጭቱ እምቅ ግፊት እንደማግኔት ወደ አዛውንቱ ሳበው …
… ጎን ለጎን አብሯቸው አዘገመ … ኩርባ ላይ መንጠቆ ጣቶቹን ወደ ኪሳቸው ላከ - ቦርሳቸውን ላጥ! በብርሃን ፍጥነት! ቁልቁል ወደ አሜሪካ ግቢ ወረደ … እንደመናፍስት ከዚያ ቦታ ብን ብሎ ጠፋ … ቦርሳውን አውጥቶ ብሩን ቆጠረ …
3000 ብር …
… ወደ ፒያሳ አቀና … “ደሃብ…” ገብቶ ያለ ይሉኝታ ሁለት ለብለብ ዱለት ሲጥ አደረገ። … ከዶሮ ማነቂያ ዙርባ ጫት ገዝቶ ቁልቁል ወደ ሰራተኛ ሰፈር ወረደ። ሀሰን ሻይ ቤት … ጫቱን መቃም ጀመረ - የተለመደ የቀን አዙሪቱ ጅማሬ። … ጫቱን ከላይ! ከላይ ቀንበጥ እየመረጠ በስሱ ቃመ። የመቃም ፍላጎት የለውም - የሚቅመው መጠጥ እንዲያጣጣው ለቅድመ ዝግጅት ነው …
ወደ 11፡00 “በአካል” ገብቶ ጂን በቢራ እየፈረፈረ መጠጣት ጀመረ … ሶስት ደብል ጂን በሁለት ቢራ እንዳወራረደ ውጣ! ውጣ! የሚል ስሜት ተሰማው። … ሂሳብ ዘጋ … ወደ ዳትሰን … ወደቀለጠው መንደር ለመሄድ ልቡ ተነሳሳ።
… ታክሲ ለመያዝ ማዘጋጃ እንደደረሰ አንድ አዛውንት ላይ አይኑ እንደማስቲሽ ተጣበቀ። አዛውንቱ ፎጣ አንጥፈው “… ለህክምና ከደጀን መጥቼ ሌባ 3000 ብሬን ዘረፈኝ … ጉድ አደረገኝ …” እያሉ እንባቸውን እያዘሩ ይለምናሉ …
ረፋድ ላይ የመነተፋቸው አዛውንት ነበሩ። አውቀውኝ ያሲዙኝ ይሆን? በሚል ጥርጣሬ ተጠጋቸው - በፍፁም አላስታወሱትም … እጆቹ እየተንቀጠቀጡ ከኪሱ 500 ብር በደመነፍሱ አወጣ … ፎጣው ላይ ጣል አደረገላቸው … ሰውዬው ባለማመን ተቁለጨለጩ … ምርቃታቸውን ያዥጎደጉዱት ጀመር …
“አብዝቶ ይስጥህ! ስራህን ይባርክልህ …”
“የትኛውን ስራዬ …” አምልጦት፤ ወደ አዛውንቱ ተጠግቶ … “እንኳን ዘረፍከኝ እያሉ እየመረቁኝ እኮ ነው …” አላቸው፤ በደመነፍሱ፤ ግን ወደ ህሊናው በፍጥነት መለስ አለ - ከዚህ ቦታ እንደመናፍስት ብን ብሎ መጥፋት አለበት … ቁልቁል ወደ ጣሊያን ሰፈር ሸመጠጠ … “ያዘው ሌባ! ያዘው ሌባ!” የሚል ድምፅ እንደ ገደል ማሚቶ ጭንቅላቱ ላይ አስተጋባበት።  በውስጥ ለውስጥ መንገድ እያቆራረጠ ደብዛውን ቢያጠፋም “ያዘው ሌባ!” የሚለው ድምፅ ግን ጆሮው ላይ ማስተጋባቱን አላቆመም። ምድር ተሰንጥቃ ብትውጠው ተመኘ … ፊት ለፊቱ ወደሚገኘው ቡና ቤት ሰተት ብሎ ገባ …
ዝናሽ ከት ብላ እየሳቀች … “አንተ ሞሽላቃ ሌባ ተመልሰህ መጣህ” …  አሳላፊ ሴቶች … ጠጪዎች አፈጠጡበት … ብርክ ያዘው … ።
“የፍቅር ሌባ  - እንኳን መጣህልኝ …” ከማስካካት ጋር …

Read 5079 times