Monday, 12 December 2016 12:04

‘ልፋ ያለው አንድ እንጨት…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የሰሞኑ ነፋስ ጠበሰንሳ! የምር ግን… “ክብደት ቀንሱ” ምናምን የሚባለው ምክር… አለ አይደል… “አንዳንድ ጊዜ ግን ክብደት ሊጠቅም ይችላል…” ምናምን የሚል ሀረግ ይቀጠልበትማ! አሀ… እኛ በግዴታ በ‘ዳየቱም’ በምኑም እየመነመንን በዚቹ ‘ኪሏችን’ የሰሞኑ ነፋስ የት ወስዶ እንደሚጥለን አይታወቅማ! (ስሙኝማ…“ዳይት ላይ ነኝ…” ምናምን የምትለዋ ነገር አሪፍ ነች፡፡ ልክ ነዋ… “ኑሮ ተወዶ የምግብ ፍጆታዬ ቀንሷል…” ከማለት ይልቅ “ዳየት ላይ ነኝ…” ብሎ ‘ስልጡኖቹን’ መቀላቀል ነዋ!)
እኔ የምለው…የት ቦታ ምን ማለት እንዳለብንና እንደሌለብን አለማወቁ እንዴት አስቸጋሪ መሰላችሁ! ይሄ የሆነ ነገር ነው፡፡ ወጣቶቹ የአንድ ሰው ሙት ዓመት የሚከበርበት ቤት ይገባሉ፡፡ እናም የቀረበውን ጸበል ጸዲቅ በልተው፣ ጠጥተው ከበቃቸው በኋላ ሊሄዱ ሲነሱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው..
“ዓመት ዓመት ያድርስልን!”
ልጆቹ ለመቀለድ ፈልገው ሳይሆን ትክክለኛው መሰናበቻ ስለመሰላቸው ነው፡፡
ምን ይደረግ ነገራችን… ‘ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል’ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡
የሆነ ሰው የጤና ችግር ገጥሞት ይተኛል፡፡ እናም የቅርብም፣ የሩቅም ጠያቂዎች ይመጣሉ፡፡ (በነገራችን ላይ ሆስፒታል የታመመ ለመጠየቅ የሚሄዱ ሰዎች አጥሚት በፔርሙስ፣ የዶሮ ፍትፍት በሳህን ይዘው መሄድ ትተዋል የሚባለው ነገር ይጣራልንማ! የኢት ፍሩት ብርቱካን ሚናም ይለይማ!…)
“አሁን እንዴት ነህ፣ ሻል ብሎሀል?” ይላል ጠያቂ፡፡
“እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነኝ…”
በነገራችን ላይ ጠያቂዎች ከንፈር መምጠጥ የሚጀመሩት ገና ሰውየው የተኛበትን ክፍል በር አልፈው መግባት ሲጀምሩ ነው፡፡ እና ሰውየው ደህና ነኝ… ሲል ከንፈር መጠጣው እንደመቀነስ ይጨምራል፡፡
“ምንህን ነው የሚያምህ!”
የምር ግን… ይሄ ጥያቄ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ምናምን መባል አለበት፡፡ በሽተኛውን ይበልጥ ማስቸገር ነዋ!
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ብዙዎቻችን የሆነ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች የወዳጅነት ሳይሆኑ… አለ አይደል… የሆነ ‘ኢንተሮጌሽን’ ምናምን ይመስላሉ፡፡
“አሁን፣ የት ነው የምትሠራው?”
“እንትን ፋብሪካ…”
“ጥሩ ቦታ ገብተሀላ!…ለመሆኑ ስንት ይከፍሉሀል?”  ኸረ እየተስተዋለ! ልክ ነዋ… ሚስቶች እንኳን እውነተኛውን የባሎቻቸውን ደሞዝ በማያውቁበት ዘመን የምን አውጫጪኝ ነው፡፡
“ምንም አይል፣ ደህና ይሰጡኛል…”
“እንደው አንድ አምስት ሺህ ብር አይከፍሉህም…”
እናላችሁ…እዚህ ላይ ብልጥ ሆኖ ‘ኖ ኮሜንት’ አይነት ዝምታ ተረስቶ ቁጥር ከተጠቀሰ …አለቀ፣ ያንኑ ቀን ታሪክ ተፈጥሮ ያድራል፡፡
“ስማ ያ እንትና…ስንት እንደሚያገኝ ታውቃለህ? ሰምቼ ገርሞኝ፣ ገርሞኝ…”
“ስንት ያገኛል?”
“አምስት ሺህ! ታምናለህ፣ አምስት ሺህ ያገኛል!”
“አትለኝም! አምስት ሺህ ብር እያገኘ ነው እንዲህ ቆንቋና የሆነው!”
“አይገርምህም! ለአንድ ሻይ የከፈለልህ እንደሆነ እኮ ልክ ቶዮታ ያሪስ የገዛልህ ይመስል እንዴት እንደሚያደርገው ብታይ…
“ለእኔ ነው የምትነግረኝ፣ አብጠርጥሬ አውቀዋለሁ። ገንዘብ ስጠኝ ከምትለው፣ ደም ስጠኝ ብትለው ይሻለዋል።”
ምን ይደረግ፣ ነገራችን… ‘ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል’ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡
እናላችሁ… እንዲህ እየተባለ የሰውየው ግለ ታሪከ ላይ አዳዲስ ምዕራፎች ይጨመራሉ፡፡
ይቺን ሳናወራት አልቀረንም…ሀኪሙ በሽተኛውን ይመረምረውና… “የምርመራው ውጤት እንደሚያሳየው ለክፉ የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ በእርግጥ የግራ እግርህ አብጧል፡፡ ግን ይሄ እኔን ብዙም አያሳስበኝም…” ይላል። ይሄኔ በሽተኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ዶክተር የአንተ ግራ እግር ቢያብጥ ኖሮ እኔንም አያሳስበኝም ነበር፡፡”
እናላችሁ… የታመመው ሰው…
“ለመሆኑ ምንህን ነው የሚያምህ?” ይባላል፡፡
“ኩላሊትህ ላይ ጠጠር ታይቷል አሉኝ…”
ይሄኔ ነው ጨዋታ የሚመጣው፡፡ ከአምስት ጠያቂዎች አራቱ ወይ ያማትባሉ፣ ወይ ሽቅብ እጃቸውን ያርገፈግፋሉ፡፡
“አፈር በበላሁ ምን ብሎ መጣብህ! እንደው አንቺ እመ ብርሀን ምኑን ነው የምታሰሚኝ!”
“የኩላሊት ጠጠር! መጥፎ ነገር እንደምሰማ ገና ከቤት ሳልወጣ ነው ያወቅሁት…” እንትፍ፣ እንትፍ ይሉና “እሱ ይማርህ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!…”
“ምኑን አምጥቶ ከመረብህ የእኔ ጌታ!”
እንዲህ፣ እንዲህ እየተባለ ልክ ከ‘ሆረር’ ፊልም ጽሁፍ ላይ የተወሰዱ ቃለ ተውኔቶች የሚመስሉ ንግግሮች ይጎርፋሉ፡፡ ይሄኔ ታማሚው የሚሰማውን አስቡልኝ፡፡ በዚህ ቢበቃ ጥሩ! ከዛም አንዱ ጠያቂ…
“አሁንማ ሰዉ ሁሉ ኩላሊት ታማሚ ሆኗል፣ ምን አይነቱን የጉድ ዘመን አመጣብን!” ይላል፡፡ ሌላኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አሁንማ የሚሰማው ሁሉ እከሌ ኩላሊቱን ታመመ በተባለ በሦስተኛው ቀን “አረፈ!” ሲባል ነው፡፡ እዚህ “አረፈ!” ነው፣ እዚያ አረፈ ነው…”
ምን አለፋችሁ…ታሞ የተኛው ሰው ስስ ከሆነ… አለ አይደል…አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ የደረሰ ነው የሚመስለው፡፡ “እነኚህ ሰዎች እንዲህ የሚሉት የሆነ የሚያውቁት ነገር ቢኖር ነው!”
ኮሚክ እኮ ነው… ከምንም ጊዜ በላይ የሚያጽናና በሚፈልግበት ወቅት፣ ከምንም ጊዜ በላይ… “አይዞህ፣ ሁሉ ነገር ሰላም ይሆናል…” የሚል በሚፈልግበት ሰዓት፣ አሥራ ምናምን ሰው ከቦት ከንፈር ሲመጥ ሊሰማው የሚችለውን ተስፋ መቁረጥ አስቡት፡፡
ምን ይደረግ፣ ነገራችን… ‘ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል’ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡
ደግሞላችሁ…ሴቶች ነጠላ ለብሰው ከመጡ በነጠላ አፋቸውን ግጥም አድርገው ሲተክዙና ሲጉተመተሙ… ሊጠይቁ የመጡ ሳይሆን ሠልስት የሚደርሱ ይመስላሉ፡፡
እናላችሁ….ወሬው ይቀጥላል፡፡
“ለመሆኑ መድሀኒት እየወሰድክ ነው?”
“አዎ አምስት አይነት ኪኒንና በቀን ሁለት ጊዜ መርፌ ሰጥተውኛል…” ይላል፡፡ ይሄኔ…
“አይዞህ፣ አሁን ነው የሚሻልህ፣ አንተ ብቻ መድሀኒትህን አታቋርጥ…” ምናምን እንደማለት ምን ቢሉት ጥሩ ነው…
“ምን የዘንድሮ መድሀኒት እንደሁ ዱቄት ነው፡ በሶ መቃም ይሻላል፡፡”
ይሄኔ የሰውያችን ሁለመና ዱቄት ይሆንላችኋል፡፡ አንዱ ጠያቂ ከተል ያደርግና…
“ይኸው ያቺ ላይ ሰፈር የነበረችው ማን ነች፣ አንድ ቁና ሙሉ ኪኒን ሰጥተዋት እሱን ስትቅም ከርማ መች ተረፈች!” ይላል፡፡ እናላችሁ…ሊያጽናና ተስፋ ሊሰጠ የሄደ ጠያቂ፣ ተስፋ አስቆርጦ እያፏጨ ቤቱ ይገባል፡፡ ለነገሩ እኮ ብዙ ጊዜ…
“ጤንነትህ እንዴት ነው?” ስንባል…  
“ምን ጤንነት አለ ብለህ ነው!” ይባላል፡፡ እናማ “ምን ጤንነት አለ ብለህ ነው?” የሚለው ሌላ ጥያቄ አያስከትልም፡፡ ለመድነዋ!
ታዲያላችሁ… ምን ቦታ ምን እንደሚባል ነገሬ ካልተባለ ተዝካር ሄደው “ዓመት፣ ዓመት ያድርሰን…” ማለት ይመጣል፡፡
ምን ይደረግ፣ ነገራችን… ‘ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል’ ሆኖብን ተቸግረናል፡፡
ሰላምና ጤናውን እየሰፈረ ይስጥልኝማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 5528 times Last modified on Monday, 26 December 2016 10:01