Print this page
Monday, 12 December 2016 11:59

ተሃድሶ፣ ግምገማና የሥልጣን ሹም ሽር

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(31 votes)

የኢህአዴግ ተሃድሶ፣ ግምገማና ሹም ሽር ቀጥሏል፡፡ ሰሞኑን የትግራይ ክልላዊ መንግስት በዶክተር ምሁራን የተሞላ አዲስ ካቢኔ ይፋ አድርጓል፡፡ ተቃዋሚዎችና የግል ፖለቲከኞች ግን ሁሉም አልተዋጠላቸውም፡፡ ከወትሮው የኢህአዴግ አካሄድ የተለየ ነገር አላየንም ባይ ናቸው -ተቃዋሚዎች፡፡ በሁሉም ዘንድ ጎልቶ የሚስተጋባው ትችት ደግሞ ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ አይደለም የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን ይሄን አይቀበልም፡፡ እኛ አስተያየት ማስተናገዳችንን፣ ሃሳብ ማንሸራሸራችንን እንቀጥላለን፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ሁልጊዜም ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡ ዛሬም የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በኢህአዴግ ተሃድሶ፣ ግምገማና የሥልጣን ሹም ሽር ዙሪያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


“ህዝቡ ታደሱልኝ ሲል አልሰማንም”

የተከበሩ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም  (የቀድሞው የፓርላማ አባልና የመድረክ አመራር)
ኢህአዴግ በጥልቀት እታደሳለሁ የሚለው ሁሌም የተለመደ ነው፡፡ መታደሱን እንግዲህ በተግባር የምናየው ይሆናል፡፡ አሁን እያየነው ያለው አንዱ የተሃድሶው አካል የተባለው የምሁራን ካቢኔዎችን መገንባት ነው፡፡ የቀለም (አካዳሚ) ሰዎች ቢሮክራሲውንና መሬት ላይ ያለውን ችግር አውቀውት ይሰራሉ ወይ የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ምክንያቱም በህዝብ ሲነሳ የነበረው ጥያቄ፣መሰረታዊ ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎችን ያካተተ ነው፡፡
ስለዚህ የአካዳሚክ ሰዎች ይሄን እንዴት ይፈቱታል? የሚለውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል። በኮሚኒስት ሀገሮች እንደተለመደው ሚኒስትሩን ምሁር አድርገው፣ ከስር ያለው ካድሬ እንዲዘውረው ይደረጋል፡፡ ሚኒስትሮቹ ምሁራን ናቸው ቢባልም ዞሮ ዞሮ የኢህአዴግን ፖሊሲ ማስፈፀምና ማስረፅ ነው ኃላፊነታቸው፡፡ ሌላ አስተሳሰብ ማራመድ አይችሉም፡፡
አንዳንዶቹም ወትሮም ቢሆን በኢህአዴግ ካድሬነት የሚታሙ ነበሩ፡፡ አሁን በጥልቀት እታደሳለሁ የሚለው ምን ያህል ሜትር ጥልቀት እንደሚኖረው አይታወቅም፡፡ ጉዳዩም ግልፅ አይደለም፡፡ ህዝቡ “የመሰብሰብ፣ የመናገር፣ የመደራጀት ነፃነቶች ሳይሸራረፍ ይከበሩልኝ” አለ እንጂ “ኢህአዴግ ሆይ ታደስልን” ሲል አልሰማንም፡፡
 ግምገማዎቹን ስንመለከት ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ እንደሚባለው ነው፡፡ መጀመሪያ ህዝቡን አነጋግሮና ችግሮቹን ተረድቶ፤ “ምንድን ነው ከህገ መንግስቱ ውስጥ ያጎደልንብህ?” ብሎ ጠይቆና መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን አንጥሮ አውጥቶ ነው ወደ ራስ ግምገማ መገባት የነበረበት፡፡
ካድሬዎቻቸውንም “ይሄው ህዝቡ እንዲህ ብሏችኋል? ምን ትላላችሁ?” ተብለው ተጠይቀው ነው መገምገም ያለባቸው። በሌላ በኩል ግምገማቸው ወጥነት የለውም፡፡ ብአዴን የሚያካሂደውና ህውሓት የሚያካሂደው እንዲሁም ኦህዴድና ደኢህዴን የሚያካሂዱት ግምገማ የተለያዩ ናቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ህዝቡ ተገማገሙልኝ ወይም ታደሱልኝ ሲል አልሰማንም፡፡
ይህቺ ሀገር ሰፊ ብዝሀነት ያለባት ሀገር ነች። ስለዚህ “ሰነፍ እረኛ ከብቶቹ ከራቁ በኋላ ነው ለመመለስ የሚነሳው” እንደሚባለው እንዳይሆን በተደጋጋሚ ችግሮቹ እንዲህ ያለ ደረጃ ሳይደርሱ እንዲፈቱ ለሁሉም አካላት ስናሳስብ ነበር፤ጆሮ የሚሰጠን አጣን እንጂ፡፡ “እባካችሁ እንነጋገር” እያልናቸው ነበር፤ “እኛ ብቻ አዋቂዎች ነን አትበሉ” ብለን ለመምከር ሞክረናል፤ ግን ተቀባይነት አላገኘንም፡፡ አሁንም በጠረጴዛ ዙሪያ ሁላችንም ተነጋግረን፣ ሀገራዊ መግባባት መፈጠር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡


================================

“ፖለቲካዊ ጥያቄዎችስ እንዴት ይፈቱ?”
ዋሲሁን ተስፋዬ (የኢዴፓ አመራር)
 ግምገማ፣ በጥልቀት መታደስና ሹም ሽረቶችን በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ባለፈው አንድ ዓመት በሀገሪቱ የተፈጠረው ጉዳይ ነው። ይሄ ጉዳይ ለምንድነው የተነሳው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዋናነት የተነሱት ጉዳዮች የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ራሱንና ድርጅታዊ መዋቅሩን ማጠናከሩ ክፋት የለውም። አገርን የሚያስተዳድር መንግስት እንደመሆኑ ራሱን ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ግን እራሱን ብቻ አጠናክሮ ችግሩን ይፈታዋል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ ጥያቄዎች ናቸው፡- ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ውስጥን በማደስ ብቻ መፍታት አይቻልም፡፡ ከመስከረም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ኢህአዴግ የችግሩን ምንጭ በደንብ አጥርቶ ለማየትና ምንጩን ለመንካት ጥረት ሲያደርግ አላየንም፡፡ ጥያቄዎቹን ሁሉ የመልካም አስተዳደርና የቢሮክራሲ ጥያቄ አድርጎ ነው የተመለከተው፡፡ ዋናው የችግሩ ምንጭ ጋ ለመድረስ አልሞከረም፡፡
የህዝብ ጥያቄ ሚኒስትሮችን የመቀየር ጥያቄ አይደለም፤ በአንድ በኩል የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነዚያን ለመፍታት አመራሩን ማጠናከር ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ፖለቲካዊ ጥያቄዎችስ እንዴት ይፈቱ? የሚለው ነው፡፡
የግምገማ ልምዳቸውን ስንመለከት፣ሁልጊዜ ከላይ ወደ ታች ነው የሚወርዱት፡፡ ከታች ከህብረተሰቡ ጀምሮ ችግሩን ተረድቶ፣ ወደ ላይ ለመሄድ ጥረት ሲደረግ አይስተዋልም፡፡ “ችግሮቹን እኛ እናውቃለን፤ እኛው እንፈታለን” የሚል አመለካከት ነው ያለው፡፡ አዲስ በተበወዘው አመራር ህዝቡ ካልተደሰተ እንደገና ሊበውዙ ነው ማለት ነው? ይሄ ደግሞ ባለፉት 25 ዓመታት ሲከተሉት የነበረው አካሄድ ነው፡፡  
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምናልባት ሀገሪቱ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆና ለውይይት እድል ሊከፍት ይችላል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። “አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መፍትሄ አምጥቷል፤ ስለዚህ በተለመደው መልኩ እንቀጥላለን” የሚለው አያዋጣም፡፡ መታወቅ ያለበት ቁምነገር፣ የሀገሪቱ ፖለቲካ ባለፉት 25 ዓመታት በሄደበት መንገድ እንኳን ሊቀጥል የሚችልበት መንገድ እየጠበበ መምጣቱ ነው፡፡
ችግሮችን ለመፍታት ውይይቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ በተለይ የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ አካላት ጋር ሁሉ ትክክለኛ ውይይት ሊደረግ ይገባል፡፡ ችግሮቹ የማይፈቱ አይደሉም። መንግስት መፍታት የሚችልበትን መንገድ ግን ማወቅ አለበት፡፡ በተደጋጋሚ “ከተቃዋሚዎች ጋር እንወያያለን” ቢባልም እስካሁን ምንም የውይይት ፍንጭ አልታየም፡፡ እኛን ማንም  እንነጋገር ብሎ የጠየቀን የለም፡፡ እኛ ችግሩ በውይይት እንደሚፈታ ስለሚገባን፣ በማንኛውም ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን፡፡    

============================

“የግምገማዎቹ አካሄድ ትክክል አይደለም”

ኢ/ር ዘለቀ ረዲ (ፖለቲከኛ)
ተሃድሶ የሚለው ጉዳይ “ጥልቅ” የሚለውን ጨምሮ መምጣቱ ነው እንጂ ከዚህ በፊትም ሲደረግ የነበረ ነው፡፡ አጠቃላይ ተሃድሶ ሲባል፤ የነበረውን ነገር አዲስ ማድረግ ነው፡፡ መታደስ ማለት አሮጌ የሆነውን ነገር ጥሎ በአዲስ መተካት ማለት ነው። በዚህ መንገድ ካየነው ደግሞ ዋናው የሚፈለገው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በፊት “ከላይ ነው የበሰበስኩት፤ መታደስ አለብኝ” ብሎ ብዙ ነገር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ሆኖም ተሃድሶ ባመጣው ለውጥ “ታድሰናል” ያሉ ሰዎች፣ የበለጠ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ ነው ያየናቸው። አንዳንዶቹም የራሳቸውን ሀብት ነው ያካበቱት። ተሃድሶ ከተባለ በኋላ እንደውም ባለጉዳይ አገልግሎት ማግኘት ያልቻለበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፣ ቢሮ ዘግቶ ስብሰባ ነው የተበራከተው። ተገልጋይ የሚፈልገውን ነገር ማግኘት አልቻለም። እናም ከዚህ በፊት የነበረው ተሃድሶ፣ ህዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት የማያገኝበት፣ ካድሬዎቹ ግን ራሳቸውን ያበለፀጉበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣናት ደሞዝተኛ ሆነው ሳለ ባለ መሬት ባለ ፎቅ፣ ባለ ከፍተኛ ሀብት ባለቤት ሆነው ይታያሉ፡፡ ይሄ ከተሃድሶው በኋላ የመጣ ነው፡፡
በተመሳሳይ በወረዳ ህዝብን ያማረረ ሰው፣ ታማኝ የፓርቲ አባል እስከሆነ ድረስ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጠውና ወደ ዞን እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ እኔ ያለኝ ስጋት “አሁን ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነን” ብለዋል፤ሰውም ብዙ እንዲጠብቅ እያደረጉት ነው፡፡ ከጥልቁ ተሃድሶ ሲወጡስ እንዴት ይሆናሉ? የተጠበቀውን ያህል ይሆናሉ? ይሄ አጠያያቂ ነው፡፡ ህዝቡ መቶ በመቶ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ተሃድሶው ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ይሄ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያደረገው እኮ የህዝብ ግፊት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ አቅም አለው፡፡
ይህቺ ሀገር የሁሉም ነች፤ እድገቷን ጠላቶቿ ካልሆኑ በቀር ሁሉም ይፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ከህዝብ ጋር ቅድሚያ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ የሚፈልገው መሬት ላይ የሚታይ ለውጥ እንጂ የሚኒስትሮች ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ነው ህዝብ የሚፈልገው፡፡ ይሄን ማምጣት ያስፈልጋል። ተሃድሶው ምን አይነት ለውጥ ያመጣል? የሚለው ለወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ በኔ በኩል ትልቅ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁን የህዝቡ ግንዛቤ አድጓል፡፡ የሚሆነውንና የማይሆነውን ለይቶ እያወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ህዝብ ይዞ፣ ትክክለኛ ለውጥ ሳያደርጉ በጎን በኩል አልፋለሁ የሚለው ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡
ግምገማዎቹን በተመለከተ አካሄዱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ አንድ ዛፍ ፍሬ የሚያፈራው ከታች ወደ ላይ በማደግ እንጂ ከላይ ወደ ታች በማደግ አይደለም፡፡ ግምገማውም ፍሬያማ እንዲሆን  ከታች መጀመር ነበረበት፡፡ መጀመሪያ ህዝቡን ማነጋገርና ሁሉንም ችግሮች መረዳት ነበረባቸው። አሁን ከላይ ተገማግመው ስልጣን አከፋፍለው ከጨረሱ በኋላ ወደ ህዝቡ ሲወርዱ፣ህዝብ “ይሄ ባለስልጣን ሙሰኛ ነው” ሲል “አይደለም”፤ ህዝብ “በቂ አገልግሎት እያገኘሁ አይደለም” ሲል “እያገኘህ ነው” ሊባል ነው? እንዴት ነው የሚሆነው፡፡ ወደ ህዝቡ ቢወርዱ ኖሮ የበለጠ ብዙ ነገር ሊያገኙ ይችሉ ነበር፡፡ የግምገማው አንዱ ችግር፤ “ምንድን ነው የምንገመግመው? ህዝብ ምንድን ነው ያጣው? ችግሩ ምንድን ነው?” የሚለውን ነገር አለመያዙ ነው፡፡ ከህዝብ መነሳት ጉዳዩን ያቀለው ነበር፡፡ አሁን ከላይ ወደ ታች መውረድ፣ ከወረዱ በኋላ በድጋሚ እንዴት ሊወጣ ይችላል? ከላይ ከተጨረሰ በኋላ ህዝቡ የሚወያየው ምንድን ነው? “የህዝብ ጥያቄ ነው ወይ እየተገመገመ ያለው?” የሚለው መታየት ነበረበት፡፡  

========================


“ችግሮችን የሚሰሙበት ቋንቋ መቀየር አለበት”

አቶ ጎይቶም ፀጋዬ
(የአረና ፓርቲ ም/ሊቀመንበር)
በጥልቀት መታደስ የሚሉትም ሆነ ግምገማዎቹና ሹም ሽረቶቹ ግልፅነት የላቸውም። አጠቃላይ ችግሮችን በዝርዝር አስቀምጦ ዝርዝር መፍትሄዎች ለመስጠት አልተሞከረም፡፡ በዚህ ረገድ ከህዝቡ ጥያቄ ጋር የተግባቡ አልመሰለኝም። ለምሳሌ የምርጫ ሥርዓት ችግር አለ የሚል ሃሳብ ተነስቶ “ስርአቱን እናስተካክላለን፤ ህገ መንግስቱንም ጭምር አስፈላጊ ከሆነ እንቀይራለን” ተብሏል፡፡ ግን የምርጫ ችግራችን ምን ነበር? እኔ እንደሚመስለኝ፤ የምርጫው ሂደት ገለልተኝነት፣ ታማኝነትና ፍትሃዊነት ጥያቄ ነበር የሚነሳው። እኛ ተቃዋሚዎች “ይሄ ነው ችግራችን” ስንል፣ እነሱ “አይደለም ችግራችሁ የምርጫ ስርአቱ ነው” እያሉን ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የምንግባባው፡፡ እኛ የነገርናቸውን ችግር ትተው አዲስ ችግር ነው እየነገሩን ያለው፡፡
ሌላው ደግሞ የህዝብ ችግሮች በየክልሉ ምን ገፅታ ነበራቸው? ቀጥተኛ ጥያቄዎቹስ ምን ነበሩ? የሚለውን በሚገባ የተረዱት አይመስልም። እየተሾሙ ያሉት ዶክተሮች የነበረውን ችግር በሚገባ ያውቁታል? ወይንስ ዶክተሮች ስለሆኑ ብቻ መፍትሄውን ያበጃሉ? ይሄ ግራ አጋቢ ነው። የህዝቡ ጥያቄ በቀጥታ እየተመለሰ አይደለም፡፡ “ውሃ ጠማኝ” ለሚል ጥያቄ “ምግብ ነው የራበህ” የሚል መልስ ነው እየተሰጠ ያለው፡፡ ይሄ ፈፅሞ ስህተት ነው፤ ጥቅም የለውም፡፡ ጥልቅ ተሃድሶውም ቢሆን የፖሊሲ ለውጥ ያመጣል ወይስ ሰዎችን ነው የሚቀያይረው? ይሄ በግልፅ መቀመጥ አለበት። እኔ አላማውም አልገባኝም፡፡ ከህዝቡ ጋር ንግግር ሳይደረግ ራሱ ጥያቄ ፈጥሮ ራሱ መመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡
ሹም ሽረቱ ላይ ከስልጣናቸው የተነሱ ሰዎች በምን ምክንያት ተነሱ? የሚለው ግልፅ አይደለም። የነበሩ እጥረቶችን አናውቅም ወይም እንደ ህዝብ እንድናውቅ አልተደረግንም፡፡ በፖሊሲና ስትራቴጂ ለውጥ ላይ እንኳ መነጋገር አልፈለጉም፡፡ በዚህ ላይም በድፍረት መነጋገር ነበረባቸው፡፡ በዚህ ላይ ክርክር ቢያካሂዱ ኖሮ፣ችግሩን ለመፍታት ጥሩ አቅጣጫ ይዘዋል ለማለት ያስደፍር ነበር፡፡ ምሁራን መምጣታቸውን እኔ አልቃወምም፤ ግን እነዚህ ምሁራን ምን ችግር እንዲፈቱ ነው የመጡት? በሚለው ላይ መግባባት አለብን፡፡ ለኔ በጣም ያሰጋኝ ነገር እነሱ እየሰሙበት ያለው መንገድ ነው፡፡ ችግሮችን የሚሰሙበት ቋንቋ መቀየር አለበት፡፡

Read 7678 times