Saturday, 10 March 2012 12:12

የራስን ግምት እየሰጡ ከመጨነቅ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

የስነተዋልዶ ጤና አካላት ከሚባሉት መካከል አንዱ ጡት ነው፡፡ የጡትን ጤናማነት በተመለከተ የተለያየ ባርይ ያለው ህመም ሊከሰት የሚችል ሲሆን ካንሰር ግን አስከፊው ነው፡፡ በጡት ካንሰር ከመያዝ አስቀድሞ ሰዎች በፍጥነት እርምጃ መውሰድ ካልቻሉ እና የንንሰር ህመሙ ከተስፋፋ እስከሕልፈት የሚያደርስ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የጡት ካንሰርን በተመለከተ ብዙዎች የተሳሳተ አመለካከት እንደሚኖራቸው ከአንድ መረጃ ያገኘናቸው ጥርጣሬ አዘል ጥያቄዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህ እትም እነዚህን በጥርጣሬ የተሞሉ ጥያቄዎች ለመመለስ ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስን ጋብዘናል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ መምህርና በአዲስ ሕይወት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡

ጥያቄ፡ የጡት ካንሰር በአብዛኛው የሚተላለፈው በዘር ነውን?

ዶ/ር ይህ ጥያቄ ትክክል ነው ፡፡ የጡት ካንሰር ከዘር ሀረግ ጋር ይገናኛል ፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ታማሚ የሆነ ሰው ካለ በዘር የመውረስ እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የጡት ካንሰር በአንድ ሰው ላይ ሲከሰት የአንጀት ካንሰር እንዲሁም የዘር ማፍለቂያ ኦቫሪ ካንሰርም ከጡት ካንሰር ጋር የተቆራኙ ስለሆኑ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የጡት ካንሰር በዘር ይተላለፋል፡፡

ጥያቄ፡ በጣም ቀጭን የሆኑ እና በደረታቸው ላይም ጡት የላቸውም የሚባሉ ሴቶች ካንሰር ሊይዛቸው ይችላልን ?

ዶ/ር አንድ ሰው ቢወፍርም ቢቀጥንም የጡት ካንሰር ሊይዘው ይችላል፡፡ መወፈር መቅጠን የካንሰር በሽታ ያስይዛል ወይንም አያስይዝም የሚል ሀሳብ ሊነሳ አይገባም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሊታወቅ የሚገባው ነገር የጡት ካንሰር የሚይዛቸው ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡

ጥያቄ፡ የጡት ካንሰር ይዞኛል ወይንም አልያዘኝም ማለት የሚቻለው እባጭ በጡት ላይ ሲገኝ ነውን?

ዶ/ር በእርግጥ የጡት ካንሰር በአብዛኛው በእባጭ መልክ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዳንዴ ግን ቧምቧዎቹ ላይ ሕመሙ የሚከሰት ከሆነ እባጭ ሳያሳይ ሊፈጠር ይችላል፡፡ እንደዚሁም የካንሰሩ ምልክት በጣም ትንንሽ የሆኑ እባጮች 2 ሳ.ሜ መጠን ያለው ከሆነ ደግሞ እንኩዋንስ ታማሚው ሐኪሙም በዳሰሳ ላያገኘው ስለሚችል እባጭ አለው የለውም ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ በእጅ የሚዳሰስና የሚታወቅ እባጭ ስለሌለብኝ በሽታው የለብኝም ማለት አይቻልም፡፡ ከውስጥ ተቀብሮ የሚገኝ በእጅ የማይዳሰስና የማይጨበጥ እባጭ ሊኖር የሚችል ሲሆን ይህ  ሊታወቅ የሚችለው በህክምና ምርመራ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምንም እባጭ ሳይኖርም የካንሰር በሽታ ሊኖር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም እባጭ የካንሰር ምልክት ነው ለማለት አያስደፍርም ፡፡ ሌሎች ሕመሞችም በእባጭ መልክ ጡት ላይ ሊገኙ ይቻላሉ፡፡

ጥያቄ፡ Mammogram  የተሰኘው የጡት መመርመሪያ መሳሪያ ለጡት ካንሰር መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላልን?

ዶ/ር ይህ የጡት የራጅ ምርመራ ማሞግራፊ ወይም ማሞግራም የሚባለው መሳሪያ በእጅ የማይዳሰስና የማይታይ ትንንሽ እባጭ በጡት ላይ ሲከሰት ሳያድግ እንዲታወቅ የሚረዳ በሽታው መከሰት አለመከሰቱን የሚያሳይ የህክምና መሳሪያ ነው፡፡ ይህ የህክምና መሳሪያ በሽታው ገና በጅምር ደረጃ ላይ እያለ ለማወቅ የሚረዳ እንጂ በምንም አይነት ካንሰር ያመጣል ወይንም አያመጣም የሚል እምነት ሊኖር አይገባም፡፡

ጥያቄ፡ ያልተፈለግ እርግዝናን ለመከላከል የሚወሰደው ኪኒን ለጡት ካንሰር ይዳርጋልን?

ዶ/ር የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒን እና የጡት ካንሰር በምንም ምክንያት አይገናኙም፡፡ የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒን ንጥረ ነገሩ በጣም ትንሽ የሆነና የዘር ፍሬው እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም ግን የጡት ካንሰር ያላቸው ሴቶች የወሊድ መከላከያ ኪኒን እንዳይወስዱ ይመከራል፡፡ የዚህም ምክንያት ኪኒኑ ኢስትሮጂን ወይንም ፕሮጀስትሮን ያለበት ስለሆነ ካንሰሩን ሊያባብስ ስለሚችል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የወሊድ መከላከያ ኪኒን የጡት ካንሰር ያመጣል የሚባለው ግምት እስካሁን ምንም ማረጋገጫ የሌለው ነው፡፡

ጥያቄ፡ ወጣት ሴቶች የጡት ካንሰር ይይዛቸዋልን?

ዶ/ር የጡት ካንሰር በእርግጥ እድሜ እየገፋ በሄደ ቁጥር የመያዝ እድሉ እየሰፋ ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ወጣት ሴቶች እና በእድሜ የገፉ በእኩል ደረጃ ካንሰሩ ይይዛቸዋል ሊባል አይችልም ፡፡ ይህ ሲባልም ወጣት ሴቶች ካንሰሩ አይይዛቸውም ማለት አይደለም፡፡ ማንኛዋም ሴት በካንሰሩ የመያዝ እድል አላት፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም ሴቶች ሰውነታቸውን ሲታጠቡ ጡታቸውን እየነካኩ እራሳቸውን ይፈትሹ ይመርምሩ የሚለው ምክር የሚሰጠው፡፡ ወጣት ሴቶች እና በእድሜ የገፉ ማለትም 25-30 አመት በላይ ባሉትና ከዚያ በታች ባሉት በጡት ካንሰር እኩል የመያዝ እድል አይኖርም ቢባልም ወጣት ሴቶች እንደትልልቆቹ ባይሆንም በካንሰሩ የመያዝ እድሉ ግን አላቸው፡

ጥያቄ፡ ሴቶች የሚጠቀሙባቸው የብብት ጠረን መለወጫ ወይንም በልብስ ላይ የሚረጩ ሽታ ያላቸው ኬሚካሎች ለጡት ካንሰር መንስኤ ይሆናሉን?

ዶ/ር የጠረን መለወጫ ኬሚካሎች ከጡት ካንሰር ጋር ምንም የሚገናኙበት ምክንያት የለም፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ይህንን ችግር የሚያመጡ ቢሆን ኖሮ ገበያ ላይ አይውሉም ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን ተጠቃሚዎች ብዙ ጊዜ የምርትን ምንነት ለማረጋገጥ ትእግስቱ ባይኖራቸውም ይህንን ለመቆጣጠር ሓላፊነት የተሰጠው አካልና እንዲሁም ከህብረተሰቡ መካከል መረጃውን የሚያገኙ ስለሚኖሩ ኬሚካሎቹን ሰዎችም አይጠቀሙባቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ሰዎች በራሳቸው ግምት የሚፈጥሩት ስጋት እንጂ ተጨባጭ የሆነ መረጃ የሌለው ነው፡፡

ጥያቄ፡ የጡት መያዣ ለጡት ካንሰር መንስኤ ይሆናልን?

ዶ/ር የጡት መያዣዎች ከጡት ካንሰር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡

ጡት መያዣ ቢጠብ ቢሰፋ ወይንም ቢወፍር ቢሳሳ ከካንሰር ጋር ምንም

አይነት ግንኙነት የለውም፡፡

ጥያቄ፡ በፕላስቲክ ጠርሙስ ታሽገው የሚሸጡ ውሀዎች በተለይም ከአቀማመጥ የተነሳ በጸሐይ ሞቀው ለመጠጥነት ሲውሉ የጡት ካንሰር ሊያመጡ ይችላሉን?

ዶ/ር ከላስቲክ ውሀ ጋር በተያያዘ ለካንሰር ያጋልጣል የሚል ጥናት እስከአሁን ስላልተደረገ ግምቱ ትክክል ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ የወደፊቱን ባላውቅም ...እስከአሁን ድረስ ሪፖርት የተደረገ ነገር ስለሌለ ምንም መረጃ የለኝም፡

ጥያቄ፡ የጡት ካንሰርን በሚመለከት በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ በማሞግራም ከተመረመሩ ሌላ ጊዜ እንደገና መመርመር ያስፈልጋልን?

ዶ/ር የጡት ካንሰር መኖር ያለመኖሩን ለማወቅ በተደረገ ምርመራ አሁን የለም ማለት ለወደፊቱ ካንሰሩ አይከሰትም ማለት አይደለም፡፡ ሌላውንም በሽታ በሚመለከትስኩዋር...ደም ግፊት...ወዘተ በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ክትትል ካልተደረገ አንዴ የለም ስለተባለ ብቻ ሁልጊዜ አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ የጡት ካንሰርንም በሚመለከት በሽታው ተከስቶ እንዳይቆይ ማንኛዋም ሴት የማሞግራም ምርመራዋን በሁለት አመት አንድ ጊዜ ማድረግ ይገባታል፡፡ የጡት ካንሰር በምርመራ አለመኖሩ ከተረጋገጠ በሁዋላ እስከ ሁለት አመት የመቆየት ምክንያቱ ካንሰሩ እስኪከሰት እና በምርመራ ማረጋገጥ የሚቻልበትን ጊዜ ለማግኘት ሲባል ሲሆን ልክ ምርመራ እንደተደረገ ቢፈጠር እንኩዋን በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ሴትየዋን ለከፋ አደጋ ስለማያጋልጥ ነው፡፡

ጥያቄ፡ የጡት ካንሰር ገና ሲጀምር ማወቅ እና ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ አለ?

ዶ/ር የጡት ካንሰርን ገና በጅምሩ ደረጃ ላይ እያለ ማወቅ ይቻላል፡፡የጡት ካንሰር እንደማንኛውም ካንሰር በጡት አካባቢ የሚፈጠሩና የሚሞቱ ሴሎች የሚኖሩት ሲሆን እነዚህ ሴሎች አንዳንድ ጊዜ መከላከያ ሳይኖራቸው የሚራቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ሴሎቹ በሚራቡበት ጊዜ እያደጉ የሰውነትን ሲስተም ከመረበሻቸውም በላይ ገደብ በሌለው መልክ መራባትና ማደጋቸው ለጡት ካንሰር ምክንያት ይሆናል፡፡  ካንሰሮች ከኢንፌክሽን ፣ከቫይረስ ጋር የተያያዙም ስለአሉ የተወሰኑትን በክትባት መከላከል ይቻላል ፡፡

ከዚህ ውጭ የሚከሰተውን የጡት ካንሰር  ግን መከላከል አይቻልም፡፡ በእርግጥ ጉዳት ሳያደርስና ለህልፈት ሳይዳርግ ማከም እና ማስወገድ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሴቶች ሕመሙን በእባጭ መልክ  እስኪያገኙ ድረስ ሳይቆዩ ወደሐኪም ቀርበው ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸ ዋል፡፡ የጡት ካንሰር በዚህ ምክንያት ሊመጣ ይችላል ወይንም በዚህ ምክንያት አይመጣም ብሎ የራስን ግምት እየሰጡ ከመጨነቅ ወደሐኪም ዘንድ በመቅረብ ማማከር ይመከራል፡፡ የጡት ካንሰርን በእንጭጩ ለማስቀረት እና ሕይወትን ለማትረፍ እንዲቻል ማንኛዋም ሴት በየሁለት አመቱ የምርመራ ፕሮግራም ሊኖራት ይገባል፡፡

 

 

Read 4174 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:33