Monday, 05 December 2016 09:34

ዛፉን ሳይሆን ዛፉ ላይ ያለውን ጎጆ እይ!

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የሚከተለው ተረት በአበሻም አለ፡፡ የህንዱ ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን አይጦች ከባድ ሰብሰባ አደረጉ፡፡ የስብሰባው ዓላማ በየጊዜው በድመት የሚደርስብንን ጥቃት እንዴት እንከላከል? የሚል ነው፡፡
ሀሳብ ብዙ ከተብላላ በኋላ እንድ ዘዴ ለመዘየድ ተወሰነ፡፡ ይኸውም፤ ‹‹ድመት ሁልጊዜ ባልታሰበ ሰዓት እየመጣ አይጦችን የማጥቃት ስልት ስላለው፤ ይኼ እንዲሰናከል ማድረግ የሚቻለው፤ ድመት አንገት ላይ ቃጭል በማሰር ነው፡፡ ይህም የሚጠቅመው ድመት አድፍጦ ሲመጣ ቃጭሉ እየጮኸ እንዲያጋልጠው ነው! ተባለ፡፡ ያኔ እኛም በየጎሬያችን ጥልቅ እንላለን፡፡››
 ሁሉም አጨበጨቡ፡፡
‹‹ለዘመናት ስንታመስ የነበረበት ሁኔታ ዛሬ መላ ተመታለት!›› በሚል ሆታውና ዕልልታው ደራ!
በመካከል ግን አንድ አስተዋይ አይጥ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አነሳ፡-
‹‹ለመሆኑ በድመት አንገት ላይ ቃጭሉን የሚያስር ጀግና አይጥ የቱ ነው?
እስቲ አስተያየት እንስጥበት››
ፀጥ ፀጥ ሆነ፡፡ ‹‹ማነው ደፋር?›› አለና ቀጠለ አስተዋዩ አይጥ፡፡ ወደ አንዱ አይጥ ዞር ብሎም፤
‹‹አንተ ትሻል ይሆን? ሲል ጠየቀው፡፡ አይጡም፤
‹‹እኔ የአይጥ ቅድመ- አያቶቼ ከባድ ግዝት አለብኝ፡፡ እድመት አጠገብ ከደረስክ የተረገምክ ሆነህ ቅር ብለውኛል!›› አለ፡፡
ሁለተኛው አይጥ ተጠየቀ፡፡ እሱም፤
‹‹እኔ ወደ ድመት ከተጠጋሁ የሚጥል በሽታ አለብኝ፡፡ እዛው ክልትው ነው የሚያደርገኝ!›› አለ
‹‹አንተስ?›› ተባለ ሶስተኛው፡፡
‹‹እኔ ከዚህ ቀደም በድመት ተይዤ ድመቶች ችሎት ቀርቤ፤ ሞት ተፈርዶብኝ ነበር፡፡ ዕድሜ ለእናንተና አባቴ፣ ጥበብ አስተምረውኝ ስለ ነበር አስቀድሜ የሞትኩ መስዬ ለጥ አልኩ፡፡ ልፍስፍስ ብዬ ተኛሁ፡፡ ቢያነሱኝ፣ ቢሸከሙኝ፣ ቢያገላብጡኝ ትንፍሽ ሳልል ወድቄ ቀረሁ፡፡ ሞቷል ብለው በማሰብ ቃሬዛ ሊያመጡ ሲሄዱ እኔ ፈትለክ አልኩ! ስለዚህ አሁን ድመት ሰፈር በምንም መልኩ ቢሆን ዝር ማለት የለብኝም!›› አለ፡፡
ሁሉም አይጦች በየተራ እየተነሱ ከባድ ከባድ ሰበቦችን እያቀረቡ ተቀመጡ፡፡  
አንድ አይጥ አንድ አዲስ ሀሳብ አመጣ፡-
‹‹ለምን ድመቱ ሲያንቀላፋ ሄደን ቃጭሉን አናጠልቅለትም?›› አለ፡፡
አስተዋይ አይጥ ግን ሀሳቡን ተቃወመና እንዲህ አለ፡-
‹‹የህንድ ድመት የአነር ዝርያው ይበዛል፡፡ የህንድ አነር በአፈ-ታሪክ እንደሚታወቀው፤ ሲተኛ አንድ ዓይኑን ጨፍኖ፣ አንድ ዐይኑን ገልጦ ነው፤ ይባላል፡፡ ስለዚህ አድፍጠን ብንሄድ እንኳ በሚያየው ዐይኑ ይይዘናል›› አለ፡፡
 ‹‹ታዲያ ምን በጀን?›› አሉት ሌሎቹ፡፡
አስተዋዩ አይጥም፤
‹‹የሚሻለው አንድ የአነር ጥናት ያጠኑ የገዳም አባት አሉ፡፡ እሳቸውን እንጠይቅ›› አለ፡፡
ሁሉም ተስማሙና ወደ ጠቢቡ ሄዱ፡፡ ጠቢቡም፤
‹‹አይጦች ሆይ! የአነር-ክልስ ድመት የዋዛ እንዳይመስላችሁ፡፡ ፀባዩ ህብረ-ቀለም ነው፡፡ ዓይኑን የሚጨፍነው ወተት ከሰጣችሁትና ሲጠግብ ብቻ ነው፡፡ በዛች ደቂቃ ብቻ ነው ቃጭሉን ልታጠልቁለት የምትችሉት!›› አሉ፡፡
ጥያቄው ግን ቀጠለ፡-
‹‹ወተቱንስ እንዴት ነው የምናቀርብለት? ማንስ ነው የሚያቀርበው?››
‹‹ወተቱንማ መጀመሪያ ንፁህ ወለል ላይ አፍስሳችሁ እናንተ ትበርራላችሁ፡፡ እሱን ሲልስ ቀጣዩን ወተት በሳህን ትገፉና ትጠፋላችሁ፡፡ ወደ ዋናው የወተት መድረክ ሲገባ ትጠብቁታላችሁ፤ ሲጠግብ ዓይኑን ይጨፍናል፡፡ ያኔ ነው የቃጭሉ ማንጠልጠል ሰዓት!››
አሏቸው፡፡
እንደተባለው አደረጉ፡፡ ቀናቸው፡፡
ግን ክፋት አይቆምምና ያ ድመት ሌላ ጊዜ ጓደኛውን ይዞ መጣ፡፡ እሱ ባንድ ጉድጓድ በኩል ቃጭሉን እያንቃጨለ ይመጣል፡፡ በሌላኛው የጉድጓዱ ጫፍ ግን ቃጭል የሌለውን ድመት ይልከዋል፡፡ አገር አማን ነው ብለው በዛኛው ጉድጓድ ብቅ የሚሉት አይጦች ዋጋቸውን አገኙ!
* * *
እንግዲህ ባለ ቃጭልና ቃጭል አልባ ድመት በሀገራችን በብዛት አለ፡፡ አንድ ችግር ሲፈታ ሌላ ችግር ይፈልቃል። ጀርሙ ከሥሩ- ስላልተነቀለ ነው! የጋንግሪን ልክፍት ይመስላል፡፡ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፡፡ ጠማጁና ተጠማጁ ይፋጃሉ፡፡ አንዱ የልማት መላ ሲፈጥር፣ ሌላው የጥፋት መላ ያደራጃል፡፡ እስከ ሚቀጥለው ስብሰባ ይሄው እርቅ- ወ-ጠብ ሥርዓት ይሆናል፡፡ ይቀጥላል፡፡ ‹‹ማንም ከማንም አይማርም›› ይላል ሎሬት ፀጋዬ፡፡
‹‹ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል!›› ይላሉ ገጣሚና ፀሀፌ-ተውኔት መንግሥቱ ለማ! አንድን ግምገማ እንዴት ነገሬን በሆድ አምቄ ፈተናውን ልለፈው? ከሆነ ጥረታችን፤ ለውጥ ወደሚቀጥለው ዓመት ግምገማ ያልፋል እንጂ የተመኘነው የተሻለ ሥርዓት አይመጣም! መቅሰስ እንጂ እራት አይሆንልንም፡፡
ብዙ በሥልጣን የባለገ ሰው መቀነሳችን ቀናነት ካለው፤ ጎጂ አይደለም፡፡ የምንተካውንም በቅንነት ማሰብ ግን ወደድንም ጠላን ይጠበቅብናል፡፡ በዕሙናዊ ባህሉ ግምገማን የመሰለ ነገር የለም! በሒሳብ ገፅታው ግን ማናቸውንም አምባገነናዊ ጥፋት ለመፈፀም በሩ ክፍት ነውና ያሳስባል፡፡ ከትናንት በስቲያ ምን ነበርን? ትናንትስ? ዛሬስ? ብለን መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ክልሎች እርስ በርሳቸው ሲጋጩ ከርመው፣ ዛሬ ችግሩ ተፈታ ስንል የትላንቱ መሰንበቻ ግጭታቸው መረጃ ተደብቀን ነበርን? ብሎ መጠየቅ ዛሬን እንድንገመግም ያግዘናል፤ የአመራሮቻችንንም ሀቀኛ ባህሪ እንድናገናዝብ ቀኝ እጅ ይሆነናል፡፡ የአመራሮች ችግር ተፈታ ስንል የህዝቦች ምሬትና ያልተፈቱ ጥያቄዎች መፍትሔ ማግኘት ጉዳይ መላ ይኖረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን! ዕውን ተስፋችን ተስፋ አለውን!?
የሀገራችን ዓለማቀፋዊ ግንኙነትንም ከክልል ልቀንና ባሻገር አይተን ዕጣ-ፈንታችን ምን ይሆን? የበለፀገችው አሜሪካ ከእኛ ከድሆቹ እኩል ‹‹ምርጫ ተጭበርብሯል›› በሚባልበት ዘመን ወዴት እየተጓዝን ነው? ብሎ መጠየቅ ክፍት አእምሮ ያላቸው አገሮች ጥያቄ ሊሆን ይገባል! ያለ ዓለማዊ ግንኙነት ብቻችንን ደሴት ሆነን አንኖርምና የዓለምን ጠረን ማሽተት፣ መልኩን ማየት፣ ጣዕሙን መቅመስ፤ አካሉን መንካት ብቻ ሳይሆን በስድስተኛ ህዋሳችንም ቢሆን (with our sixth sense too) ለማጣጣም መሞከር አለብን፡፡ በአለም ላይ በሚከሰት ሂደት ሳቢያ እያንዳንዱ ሀገር ብቻ ሳይሆን በውስጡ የሚኖር ህልው ከጉዳይ መፃፍ አለበት፡፡ የህዝብ ብዛት መጨመር ለህልውናችን ምን ያህል አስጊ ነው የምንለውን ያህል፤ የህዝብ ቁጥር መቀነስስ ታላላቅ ሀገሮችን አያሳስባቸውም ወይ? ወደብ ያላቸውና የሌላቸው አገሮችስ በውሃ ላይ ካለ ባህራዊ ኃይል ጋር ምን ያህል ህልውናቸው ስጋት ላይ ነው? ታላላቅ አገሮች የንግድ ግንኙነታቸው ሲዛባ እኛን አይመለከተንም ወይ? ሰደትን የገቢ ምንጭ ያደረጉ እንደኛ ዓይነት አገሮችስ ኢኮኖሚያቸው ምን ይውጠው ይሆን? (ለምሳሌ እንደሜክሲኮ የአንበሳውን ድርሻ ለስደት ድርጎ (Remittance) ያደረጉ አገሮች የሚሰማቸው በቀል ነው የጎረቤት አገር ፍቅር?...) የራስን ኢኮኖሚ በራስ ማስተዳደር ይቻላልን? ማስተዋል የሚያሻቸው አያሌ ሂደቶች የሥጋቶቻችን እኩያ ናቸው! ጥገኛ ኢኮኖሚ የራሱን አደጋ ማስተዋል አለበት። ከአፍንጫ ሥር የራቀ መሆን አለበት፡፡
በአሜሪካና በአውሮፓ አያሌ ዛፎች አሉ፡፡ በነዚህ ዛፎች ላይ ደግሞ አያሌ የወፍ ጎጆዎች አሉ፡፡ ከአፍሪካም፣ ከእስያም፣ ከላቲን አሜሪካም የመጡ ወፎች ያረፉባቸው ዛፎች አያሌ ናቸው፡፡ የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖት፣ የአመለካከት ወዘተ ባለቤት የሆኑትን ወፎች ለመግፋት ወይም ለማባረር የዓለም ኃያላን መሪዎች ያኮበከቡ በሚመስልበት በአሁን ወቅት ዕሳቤያችን ምን መሆን አለበት? ብሎ ማሰብ ደግዬ መንገድ ነው፡፡ ቀኝና ግራ ሳይባል የአክራሪዎች መንገድ ሊከሰት የሚችልበት አሳቻ ሁኔታ ሊታይ ይችላል፡፡ ‹‹ዛፉን ሳይሆን ዛፉ ላይ ያለውን ጎጆ እይ›› የሚለው አባባል የሚያሻን እዚህ ላይ ነው፡፡ ልቡና ይሰጠን!

Read 5823 times