Monday, 05 December 2016 09:33

ጉርምስና... አይቀርም!

Written by  ላንቺና ላንተ
Rate this item
(8 votes)

 • ጉርምስና ሲመጣ የሚታየው የሰውነት ለውጥ አስደንጋጭና ያልተለመደ ቢመስልም...ግን ሁሉም ሰው ላይ             ሊደርስ የሚችል እንጂ የግል ጉዳይ አይደለም።
        • ጉርምስና አመታት ቆይቶ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም ግን ከ9 እስከ 17 አመት ባለው እድሜ መካከል ቆይታ             ሊያደርግ ይችላል።
        • ልጃገረዶች ከወንዶች ቀደም ብለው ጉርምስና ይጀምራሉ።

              ጉርምስና በሴቶች ሰውነት ምን ለውጥ ያሳያል?
የሴቶች የጉርምስና እድሜ ከ9-14 አመት ድረስ ነው ተብሎ ይገመታል። ሴቶች ጉርምስና ከሚባለው የእድሜ ክልል ሲደርሱ በፍጥነት የሰውነት እድገት ለውጥ ያሳያሉ። አንዳንድ ልጃገረዶች በዚህ በሰውነት ድንገተኛ ለውጥ ምክንያት ጥሩ ስሜት ወይንም ምቾት ላይሰማቸው ይችላል። ይህ ሂደት ምን ያህል ይቆያል የሚለው የሚወሰነው በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም በተለይ ግን በቤተሰብ ውስጥ ያለው ተፈጥሮአዊ ውርስ አንዱ ነው።
ሴቶች በጉርምስናቸው ወቅት የጡት መጠንና ቅርጻቸው ይለወጣል። የጡት ጫፍ እንደመ ወፈር እና ሲነኩትም የህመም ስሜት ሊኖረው ይችላል። ቀስ በቀስ ዳሌአቸው ይሰፋል። በብብት ስር እና በብልት አካባቢ ፀጉር ይበቅላል። በብብት ውስጥ ከባድ ጠረን ያለው ላብ ይጀምራል። በፊት ላይ ቡጉር ሊወጣ ይችላል። በጉርምስና እድሜ ሴቶች የወር አበባ ያያሉ። ሴቶች ጉርምስናን የሚጀምሩት ወንዶች ከሚጎረምሱበት አንድ ወይንም ሁለት አመት ቀድመው ነው።
ጉርምስና ፈታኝ እና አስቸጋሪ ወቅት ነው ተብሎ በብዙዎች ይገመታል። ነገር ግን ይህንን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ካለመረዳት የሚመነጭ አስተሳሰብ ስለሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች መጋለጥ ይኖራል። ለምሳሌም ሴት ልጆች ጉርምስና እድሜ ከገቡ በሁዋላ የስነ ተዋልዶ አካላት እድገት ስለሚኖር ምናልባትም ከመጀመ ሪያው የጉርምስና ምልክት በሁዋላ በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ለእርግዝና ዝግጁ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይህ እንግዲህ ሴትዋ ገና በእድሜዋ ሳትበስል የሚከ ሰት በመሆኑ ሌላ ተያያዥ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አይጠረጠርም።
 ጉርምስና በወንዶች ሰውነት ምን ለውጥ ያሳያል?
በልጃገረዶቹ እንደተመለከትነው ወንዶችም በጉርምስና እድሜያቸው የተለያዩ ለውጦችን በሰውነታቸው ላይ ያሳያሉ። ወንዶች ለጉርምስና ደረሱ የሚባለው ከ10-17 አመት እድሜ ክልል ሲሆን በዚህን ጊዜም ከሚያሳዩዋቸው የሰውነት ለውጦች መካከል የስነተዋልዶ አካል ማደግ በብብትና በብልት አካባቢ ፀጉር ማውጣት ይኖራል። እንዲሁም በጉርምስናው እድገት ምክንያት በክንድና በቅልጥም አካባቢ የህመም ስሜት ሊፈጠርባቸው ይችላል። የድምጽ መወፈር ወይንም መጎርነን ሊኖር ይችላል። ጺም እንዲሁም የደረት ፀጉር ማብቀል ይኖራል። በብብት ውስጥ ላብ የመፈጠርና የላቡ ጠረንም ከበድ ያለ እንደሚሆን ይገመታል። በደረታቸው ላይ ያሉት ጡቶች መኖራቸውን በሚያሳይ መልኩ የጡት ጫፎቹ ጠንከር የሚሉበትና አካባቢውም የሚደረጅበት ሁኔታ ይታያል።
ወንዶች የጉርምስና እድሜያቸው ከሴቶች ዘግየት ብሎ የሚጀምር ሲሆን ጊዜውም ከ10-12 አመት ድረስ ሲሆን ይህ ጉርምስና እስከ 20 አመት ድረስ ሳይቋረጥ ቀስ በቀስ ለውጥ እያሳየ የሚቀጥል ይሆናል።
ስለዚህም በጉርምስና ወቅት ሴቶች የጡት መጠን መጨመር፣በብልትና በብብት ላይ ጸጉር ማብቀል፣ የወር አበባ መታየት፣ የሰውነት ቅርጽ መቀየር፣...ወዘተ የሚታይባቸው ሲሆን በወንዶች የዘር ፍሬ ማመንጫና የብልት ማደግ፣ የብልትና ብብት ጸጉር መብቀል፣ የድምጽ መጎርነን ፣ ፐርም ማፍሰስ...ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች ይታያሉ። በተጨማሪ የሰውነት መግዘፍ ፣ቁመት መጨመር ፣ከፊት ላይ ቡጉር ማውጣት... በፍጥነት የሚታይ ለውጥ ከመሆኑ በተጨማሪ የስነአእምሮ ወይንም የስነተዋልዶአዊ ለውጦች በታዳጊዎቹ ላይ ይታያል። እነዚህ ለውጦች የሚታዩት እድሜውን ተከትለው በሚመነጩ አዳዲስ ሆርሞኖች ምክንያት ነው። ይህንን የሰውነት ለውጥ የሚያመጡትን ሆርሞኖች አፈጣጠር በሴቶች ላይ ስንመለከት ከእንቁላል ማኩረቻው ወይንም ከኦቫሪ የሚመነጩ ሆርሞኖች ናቸው ። እነዚህን ሆርሞኖች የሚያመ ነጨው ክፍል ሴቷ ስትወለድ ጀምሮ አብሮ የሚፈጠር ነው። ነገር ግን ሆርሞኖች ስራቸውን መስራት የሚጀምሩት አብዛኛውን ጊዜ እድሜያቸው ከ8-11 ባለው ጊዜ ነው። ይህንንም እንዲያደርጉ የሚታዘዙት ከአእምሮ በሚመነጩ ሆርሞኖች አማካኝነት ነው። (ምንጭ ... Medical news today)

በጉርምስና ጊዜ የሚኖር ባህርይ፡-
በኮረዳነት ወይንም ጉርምስና እድሜ ላይ የሚኖረው ባህርይ ትንሽ ለየት ያለ ነው። በመጀመሪያ ስለጉዳዩ እውቀቱ ከሌላቸው በሰውነታቸው የተለያዩ ክፍሎች እና በድም ጻቸው በሚኖረው ለውጥ ምክንያት ግራ የመጋባት ሁኔታ ይታይባቸዋል።ከዚህ ውጪ ግን በዚህ እድሜ የሚታየው ...ነገሮችን የመሞከር ወይንም ፍተሻ የማድረግ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ተለዋዋጭ ደስተኛና ብስጩ የመሆን ባህርይ ሊኖራቸው ይችላል። ብዙ ጊዜ በባህሪያቸው መለዋወጥ እና በሚኖራቸው ተገቢ ያልሆነ ፍላጎት ምክንያትም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መስማማት ሲያቅታቸው ይታያል። በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ቤተሰብ ትልቅ ድርሻ አለው። በግልጽነት ከልጆቹ ጋር መወያየት እና ስለሁኔታው በግልጽ ማስረዳት ይጠበቅበታል። ልጆቹ ይህንን ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በሚገባ አውቀው ዝግጁ ሆነው እንዲጠባበቁ የሚያስችላቸውን እውቀት ሊያገኙ ይገባል። ከቤተ ሰብ ውጪም ትምህርት ቤቶች በበኩላቸው ተገቢውን ነገር ለህጻናቱ ማስረዳት አለባ ቸው። ኮረዳነት ወይንም ጉርምስና ወሲብ ለመፈጸም ፍላጎታቸው የሚነሳሳበት ወቅት እንደመሆኑ ቤተሰብ ወይንም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው ህጻናቱን ከተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ኤችአይቪን ጨምሮ ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ምክሩን መለገስ ይገባዋል። ልጆቹ ከዚህ ድርጊት እንዲዘገዩ ወይንም ደግሞ እራስን መጠበቅ የሚቻልባቸው መንገዶች መኖራቸውን በግልጽ ከወላጆቻቸው ወይንም ከሚያምኑዋቸው ሰዎች ማግኘት አለባቸው። ይህ ካልተፈጸመ ልጆቹ ጉዳት ላይ ሊወድቁ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። (ምንጭ ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት)

ጉርምስና በፍጥነት ከመጣ የሚያስከትለው ችግር፡-
የአንዳንድ ሀገራት የጥናት ውጤት እንደሚያመላክተው ጉርምስና ቀደም ሲል ከሚጠበቅበት እድሜ ፈጠን ብሎ እየተከሰተ ይስተዋላል። ይህ ሁኔታ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልግበት ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ ሐገራት በተለይም በአሜሪካ በተደረገው ጥናት እንደታየው ሴቶች ልጆች የወር አበባ የሚያዩት በአማካይ ወደ 12 አመት ሲደርሱ ሲሆን ይህ ላለፉት 40 አርባ አመታት የቆየው እውነታ አሁን መልኩን በመለወጥ ላይ ነው። ባደጉት አገሮች ባለፉት ሃያ እና ሰላሳ አመታት በተደረገው ጥናት እንደታየው ከእድገት ጋር በተገናኘ የወር አበባ የመምጫው ጊዜ በየአስር አመቱ በአ ማካይ ሶስት ...ሶስት ወር እየቀነሰ አሁን ካለበት ደርሶአል። ስለዚህ ዋናው የቤተሰብ ውርስ ሲሆን ከዚህ ውጪ ግን የአኑዋኑዋር ሁኔታ ...ምቾት የመሳሰሉት ነገሮች ይወስኑታል። ምቾት ማጣት ወይንም ድህነት የወር አበባ መምጫውን ሊያዘገዩት ይችላሉ የሚል ግምት አለ።
ጉርምስና ለሴቶች በ7 እና 8 አመት እድሜ እና ለወንዶች ከ9 አመት በፊት የሚከሰት ከሆነ ጊዜውን ያልጠበቀ ቀድሞ የመጣ ጉርምስና ሊባል ይችላል። ሴቶች ጡታቸው ከ4-6 ወር ባልበለጠ ጊዜ እድገቱን የሚያፋጥን ከሆነ ወይንም ወንዶች ብልታቸው እና ሌላም ሰውነታቸው በፍጥነት የሚያድግ ከሆነ የህክምና እርዳታ ሊያስፈልገው ይችላል።

የጉርምስና መዘግየት፡-
ሴት ልጅ በ14 አመትዋ ጡትዋ የማደግ ምልክት ካላሳየ ወይንም በ16 አመት እድሜዋ የወር አበባ የማታይ ከሆነ እንዲሁም ወንድ ልጅ በ14 አመቱ የብልት ማደግ ካልታየበት ወደሕክምና ባለሙያ መሔድ ያስፈልጋቸዋል።ይህ ጉዳይ ከአመጋገብ መዛባት ወይንም ታይሮይድ ከተሰኘው እጢ እድገት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ከተለያዩ ሕመሞች ...ማለትም እንደ ስኩዋር ፣የኩላሊት ሕመም ወይንም አስም ወይንም ዝርያ የመሳሰሉት ጉርምስና እንዲ ዘገይ ሊያደርጉ ይችላሉ። የጉርምስና መዘግየት በትክክለኛው መንገድ የሚታከም ስለሆነ ቸል ማለት አይገባም።
በአጠቃላይም ጉርምስና በአካል ላይ ከለውጥ ማምጣት ባሻገር የባህርይንም ለውጥ የሚያ ስከትል በመሆኑ ጊዜው እስኪያልፍ ድረስ ሊያስቸግር ይችላል። ሆኖም ግን በጉርምስና እድሜ ማለፍ ሰዎች መርጠው የሚያመጡት ባለመሆኑና የተፈጥሮ ግዴታ በመሆኑ ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል። በተለይም ቤተሰብ፣ ህብረተሰብ ፣ትምህርትቤቶች እና የተለያዩ የሚመለከ ታቸው ክፍሎች አስቀድመው አውቀው በዚህ የእድሜ ክልል የገቡ ታዳጊዎችን ስለሁኔታው አስቀድመው እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል።
ጉርምስና አይቀርም። ስለዚህም ወላጆች ልጆችን ከመውለድ ባሻገር በጉርምስና ወቅት ምን ሊከሰት እንደሚችልና ልጆቻቸው በተገቢው ሁኔታ ጊዜውን አልፈው ጥሩ ስብእና እንዲኖራቸው ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። (ምንጭ --MedicineNet.com)

Read 9796 times