Monday, 05 December 2016 09:31

ዋልያዎቹ ከተበተኑ 2 ወር አልፏቸዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በፌዴሬሽኑ አዝኗል
      የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ  የነበረው ገብረመድህን ኃይሌ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ክብር የሚነካ አሰራር እንዳሳዘነው ለስፖርት  አድማስ ገለፀ፡፡ የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ሲመረጥ በከባድ ሃዘንና ከፍተኛ የቤተሰብ ችግር ውስጥ እንደነበር ያስታወሰው አሰልጣኙ፤ በወቅቱ ሃላፊነቱን ብሄራዊ ግዴታ መሆኑን በማክበር መቀበሉን ገልፆ፤  ፌደሬሽኑ ከመስከረም 30 በኋላ ጊዜያዊ የቅጥር ውሉ እንዳቋረጠ በደብዳቤ ያሳወቀበት መንገድ ስሜቴን ነክቶታል ብሏል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር  በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ሰሞኑን ያስታወቀ ሲሆን፤ ውድድር የለም በሚል ብሄራዊ ቡድኑ ተበትኖ ያለ ዋና አሰልጣኝ  ከሁለት ወራት በላይ መቆየቱ የስፖርት ቤተሰቡን የሚያነጋግር ሆኗል፡፡  
ፌደሬሽኑ ከ6 ወራት በፊት   ታዋቂውን የቀድሞ ተጨዋች እና አሰልጣኝ  ገብረመድኅን ኃይሌ በጊዜያዊነት አሰልጣኝ በቀጠረበት ወቅት የነበረውን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን በውጤት ማጣት ምክንያት ከኃላፊነት ማንሳቱን በማስታወቅ ነበር፡፡ ከዮሃንስ ሳህሌ በኋላም  በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በምድብ 10 ብሄራዊ ቡድኑ በነበሩት  ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች  አሰልጣኝ ገብረመድህን በጊዜያዊነት ሲሾም  ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ  ጠባቡን የማለፍ እድል እንዲሞክር ታስቦም ነበር፡፡ በዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን የተመራው ብሄራዊ ቡድኑ በሁለቱ ቀሪ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በማሸነፍ 100 በመቶ ሃላፊነቱን ለመወጣት ችሏል። በ5ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ ከሜዳ ውጭ በሴትሶቶ ስታድዬም ሌሶቶን በጌታነህ ከበደ ሁለት ጎሎች  2ለ1 እንዲሁም በ6ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ በሃዋሳ ስታድዬም በጌታነህ ከበደእና ሳላሃዲን ሰይድ ጎሎች 2ለ1 ሲሸልስን በማሸነፍ ነበር። ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ አልጄርያ ምድቡን በ16 ነጥብ እና በ20 የግብ ክፍያ በመምራት በ2017 ጋቦን ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ 10 በአንደኛነት ማለፏን ስታረጋግጥ፤ ኢትዮጵያ በ11 ነጥብ እና በ3 የግብ እዳ ሁለተኛ_ ሲሸልስ በ4 ነጥብ እና በ6 የግብእዳ 3ኛ እንዲሁም ሌሶቶ በ3 ነጥብእና በ11 የግብ እዳ 4ኛ  ደረጃ በመያዝ ጨረሱ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ10ሩ ምድቦች ምርጥ ሁለተኛ ደረጃ ለሚያገኙ ቡድኖች በሚሰጠው የማለፍ እድል በግብ ልዩነት ተበልጦ ሳይሳካለት ቀረ፡፡  በአጠቃላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያልቻለባቸው ምክንያቶች ለእያንዳንዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ረጅም የልምምድና የዝግጅት ጊዜ አለማድረጉ፤ አስፈላጊ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተገቢው አለማግኘቱ እንዲሁም በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሲሰለጥን የቆየው ቡድኑ አስቀድሞ በነበሩት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች አንድ ብቻ አሸንፎ ሁለት አቻ ወጥቶ በአንዱ ደግሞ በሰፊ የጎል ልዩነት በመሸነፉ  ነውማለት ይቻላል፡፡ በዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ የተደረጉት ቀሪ ሁለት የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች መርሃግበሩን ከመጨረስ እናባለው ጠባብ የማለፍ እድልሙከራ የተደረገባቸው ነበሩ። በአጠቃላይ  በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ  ላይ ብሄራዊ ቡድኑ በ6 ጨዋታዎች  11 ጎሎችን አስቆጥሮ 14 ጎሎች ተቆጥሮበታል፡፡ 3 የግብ እዳ ከዚህ የተወራረደ ነው። የዋልያዎቹ አጥቂ ጌታነህ ከበደ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠር የማጣሪያው ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ማጠናቀቁ ብቻ አንዱ ስኬት ሲሆን ሳላዲን ሰኢድ 2 ጎሎች ሲያቆጥር ፤ ዳዊት ፍቃዱ፤ ጋቶች ፓኖም እና ስዩም ተስፋዬ የተቀሩትን 3 ጎሎች አስመዝግበዋል፡፡
‹‹በዋና አሰልጣኝነቱ ለመቀጠል የተለየ ጉጉት ባይኖረኝም በአጭር የሃላፊነት ቆይታዬ የምለካው በውጤት ከሆነ ሁለቱንም ጨዋታዎች አሸንፊያለሁ የሚለው ገብረመድህን ሃይሌ፤ በመጀመርያ ጨዋታ ስናሸንፍ በማለፍ ያለማለፍ የነበረው ተስፋ ለመለመ። ከዚያም ሁለተኛውን ጨዋታ ደግመን አሸነፍን። ይሁንና በጎል እዳምክንያትሌሎች ጥሩ ሁለተኛ ደረጃ በማመዘገቡ ቡድኖች ተበልጠን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ሳንችል ቀረን፡፡ ይህ ደግሞ ከእኔ በፊት በሌላ አሰልጣኝ  በተደረጉ ጨዋታዎች በተመዘገቡት ውጤቶች የመጣ ነው››ሲል አብራርቷል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በጊዜያዊነት የነበረኝ የቅጥር ውል መስከረም 30 ላይ መቋረጡን  ያሳወቀበት መንገድ ውሳኔው ግልፅነት እንደሚጎድለው ያመለክታል በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጠው ገብረመድህን፤ ‹‹ከሃላፊነት መነሳቴን በጋዜጣዊ መግለጫ ማብራራት እንዲሁም በጊዜያዊ ቆይታዬ ላይ ግምገማ ማድረግ ያስፈልግ ነበር›› ይላል። የምሥጋና  እና ሌሎች ላከናወንኳቸው ተግባራት እውቅና የሚሰጥ ደብዳቤም አለመሰጠቱም አስገርሞኛል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል በፌደሬሽኑ እንደተለመደው መደረግ በነበረባቸው የማበረታቻ ሽልማቶች ላይ አሰልጣኝ ገብረመድህንና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ቅሬታ እንዳላቸው ለመገንዘብም ተችሏል፡፡ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከሌሶቶ ጋር ባደረጉት ጨዋታ  ማሸነፋቸውን ተከትሎ ፌደሬሽኑ  ለእሱ 25 ሺ ብር ለተጨዋቾች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 20 ሺብር ሸልሞ እንደነበር ያስታወሰው ገብረመድህን፤ በምድብ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታ ሃዋሳ ላይ ሲሸልስን ካሸነፍን በኋላ የፌደሬሽኑ ሰዎች በማግስቱ ቡድኑን ሰብስበው የማበረታቻ ሽልማቶች እንደሚኖሩ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱ የሚያሳዝን ነው ብሏል፡፡
የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ መስከረም 30 ላይ የገብረመድህንን ውል ካቋረጠ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑን በትኖታል ማለት ይቻላል፡፡ ሰሞኑን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ማሰቡን ያስታወቀ ቢሆንም ከሁለት ወራት በላይ ብሄራዊ ቡድኑ እንደተበተነ መቆየቱ እንዲሁም ያለ ዋና አሰልጣኝና ምክትል አሰልጣኝ መቀጠሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ውድድር ኖረም አልኖረም ብሄራዊ ቡድኑ ያለ ዋና አሰልጣኝ መቆየት የለበትም በማለት ለአዲስ አድማስ አስተያየቱን የሰጠው ገብረመድህን ሃይሌ፤ በመላው አገሪቱ የሚካሄዱ የክለብ ውድድሮችን በመታደም፤ አዳዲስ እና ነባር ተጨዋቾች የሚያሳዩትን ብቃት መከታተል እንደሚችል፤ በሌሎች የእድሜ ደረጃዎች የሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖችን እና አሰልጣኞቻቸውን በመደገፍ መስራት እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልግ ነበር ብሏል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ግን ገብረመድህን ሃይሌ በሚለው አቅጣጫ ከመስራት ይልቅ ብሄራዊ ቡድኑ ለ1 ዓመት ወደ ውድድር ሊገባ እንደማይችል በመገመት መቀጠል አልነበረበትም፡፡

Read 2014 times