Monday, 05 December 2016 09:15

ከፍተን ብናየው? ሻእቢያና ኦነግ - መስተፋቅር!

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(27 votes)

እንደመግቢያ
ዛሬ ትንሽ መጻፍ የፈለኩት በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በኢሳያስ አፈወርቂ መካከል ያለውን የቆየ ጥብቅ ትስስር በመጠኑ ለመፈተሽ ነው። መነሻ የሆነኝ እንግሊዝ አገር ሎንዶንና አሜሪካ፤ አትላንታ፣ ጆርጂያ የኦሮሞ “ምሁራንና ብሔርተኞች” ያደረጉት ስብሰባና የሰጡት መግለጫ ነው። ያ ራሱን ችሎ መነገር ያለበት ስለሚመስለኝ እመለስበታለሁ። የዚህኛው አላማ እዚያ ስብሰባ ላይ ተካፋይ ከነበሩት “ነፃ አውጭዎች” አንዱን፣ ኦነግን በጨረፍታ ለመታዘብ ነው።
እዚያ ከመዝለቄ በፊት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመግባቢያ ያክል በመጠኑ መዳሰስ፤ ማየትና ማሳየት እሞክራለሁ::
ብዙ የአፍሪቃ መሪዎች (ፕሬዝዳንቶች) “የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት” (President for Life) የሚል ማእረግ ነበራቸው። እኔ ወድጅዋለሁ! በየአራት ወይ ስድስት ዓመቱ ምርጫ እየተባለ ጊዜም ገንዘብም ከሚባክን “ወደዳችሁ ጠላችሁ የራሳችሁ ጉዳይ” ብሎ እቅጩን መናገርን የመሰለ ነገር የለም። ከዚያ ውስጥ አንዱ፤ ጂን ቤዴል ቦካሳ (Jean-Bédel Bokassa)፤ የመካከለኛ አፍሪቃ ሬፐብሊክ “ንጉሠ ነገሥት!” (Emperor) ሆኖ አረፈው። እሱም እውነቱን መናገሩ ነበር። አንድምታውን  ወዲያ ትተን፣  “የእድሜ  ልክ ፕሬዚዳንትም ማለት  ያው ንጉሠ ነገሥት ማለት አይደል!?” ማለቱ መሰለኝ።
ይህ ነገር የኛው የነበረውን፣ አሁን የጎረቤት “አገር” “ፕሬዚዳንት” የሆነውን ኢሳያስ አፈወርቂን አስታወሰኝ። “የኛው የነበረውን” ያሰኘኝ የደሴ ልጅ መሆኑ፤ የቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረ መሆኑ፤ ከሁሉም በላይ ጣሊያን ኤርትራ ብሎ የሰየማት የባህረ ነጋሽ ልጅ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ተረት፣ ትንግርት (Mythology) ተብሎ የሚነገረው አብዛኛው የተሸመነው ባሕረ ነጋሽ ነውና። የዚህ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረራት ዘመን፣ 1928 ዓ.ም፣ የተመሠረተው የ“ጥቁር አንበሳ” ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሌተና ኮሎኔል በላይ ኃይሌለአብም ኤርትራዊ ነበር። የጥቁር አንበሳ  ሕገመንግሥት አንቀጽ አንድ፤ “ሕዝበ ኢትዮጵያ ንሰአ ወልታ ወኩናት ወተንስእ ውስተ ረደትየ“ ይላል። የአቶ ታደሰ ሜጫን “ጥቁር አንበሳ” መጽሐፍ ያነቧል። የአቶ ሐዲስ አለማየሁን ትዝታ ማንበብም ስለ ሌተና ኮሎኔል በላይ ኃይሌለአብም ያለንን ዕውቀት የበለጠ ያጠነክረዋል:: “የትዝታ ፈለግ” በሚለው መጽሐፌ ውስጥ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለነበረው መለስ ዜናዊ የጻፍኩትን ግልጽ ደብዳቤ ማንበቡም የተሻለ የሚያብራራው ይመስለኛል። (እግረ መንገዴን መጽሐፍ ማሻሻጤ ይሆን?) አባቱ፣ አቶ አፈወርቂም የመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ አልነበሩም? በልጃቸው ምክንያት ተጠርጥረው ታስረው ኖሮ፤ “አባት በልጁ ምክንያት አይታሰርም!” ብሎ፣ ለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነግሮ ያስፈታው የደኅንነት ሚኒስቴር የነበረው ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ አልነበረም? የግንኙነታችንን ጥልቀት ለማስታወስ ያክል ነው። ያ ጥልቀት የማታ-ማታ አጓጉል ሆኖ አረፈ ለማለትም ነው!
ኢሳያስ አፈወርቂን ያክል ለረዥም ዘመናት ንጉሰ ነገስት ሆኖ የቆየ መሪ አፍሪቃ ውስጥ አሁን ያለ አይመስለኝም። ኃይለ ሥላሴ ነበሩ። እሳቸውም ባልጠበቁት መንገድ “ነበሩ!” ሆኑ።
ኢሳያስ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ በረሀ ገባ። ሸፈተ። ከ50 አመት በፊት ነው። ጀበሐ Eritrean Liberation Front (ELF) ሆነ። ጀበሀን በላ!  ሻእቢያን (EPLF) ፈጠረ! ከዚያ በኋላ ያልሆነው ነገር የለም። የሆነውን ሁሉ፣ እንኳን እኔ እሱም ሳይጠፋው አይቀርም።    

       ከፍተን ብናየው!
ኢሳያስ አፈወርቂን በአካል ያየሁት ነሐሴ 1981 ወያኔና ሻንጣ ተሸካሚዎቹ አዲስ አበባ ገብተው ባዘጋጁት “የሰላምና ዲሞክራሲ ጉባዔ” ላይ አፍሪቃ አዳራሽ ነበር። ነገሩ፣ ማለትም ስብሰባው ሠላምንም ዲሞክራሲንም ለመቅበር መሆኑ አሁን ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ያኔ ጥርጣሬ ብቻ ነበረኝ።
ያዘጋጁት፣ ወይም ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ያዘጋጁት ፖል ሔንዝና  (Paul Hanze) ሔርማን ኮኸን (Herman Cohn) ይመስሉኛል። ፖል ሔንዝ ዝነኛ የሲ.አይ.ኤ (CIA) ሰላይ ነበር። የነመለስ ዜናዊ የነፍስ አባት (Godfather) ነኝ ብሎ የጻፈውን አንብቢያለሁ። ኮኸን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) የአፍሪቃ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር። አሁን ደሞ ስለ ኢትዮጵያ ሲያላዝን ሰማሁት። አዲሱ ጭምብል (Mask) መሆኑ መሰለኝ።
ሁለቱም የረዥም ጊዜ የሥራ ውጤታቸውን ለመመረቅ አዲስ አበባ መጥተው ነበር። ፖል ሔንዝ ሊያገኘኝ ፈልጎ ሰው ቢልክብኝ “ይቅርብኝ!” አልኩት። ኮኸንን  ግን ብሔራዊ ቤተመንግስት (ኢዩቤልዩ ይባል የነበረው) ግቢ ከመለስ ዜናዊ ጋር ለብቻቸው ፈንጠር ብለው ሲነጋገሩ ጣልቃ ገብቼ  አነጋገርኩት። መለሰ ዜናው በዐይኑ ሊገስጸኝ ሞክሮ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ተግሳጽም አይገባቸውም መሰለኝ። እዚያ ውስጥ ሳልመደብ የምቀር አይመስለኝም።
ሌላ ስለ ፖል ሔንዝ ትዝ የሚለኝ፣ አሜሪካ የመጣሁ ሰሞን ካላገኘሁት ብሎ የሕግ ትምህርት ቤቱ መሥራችና የዩንቨሪስቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩት በዲን ፓል በኩል ቢጨቀጭቀኝ፤ እሳቸውም “ሊረዳህ የሚችል ሰውኮ ነው! ብቻ ጠንቀቅ በል!” ብለውኝ ላገኘው ቢሮው ተቀጣጠርን። ሔንዝ ሥራው ዋሽንግተን ዲ.ሲ Rand Corporation የሚባለው ግዙፍ የስለላ ማቀነባበሪያ ኩባኒያ    ውስጥ ነበር። ምሳ ሊጋብዘኝ እምድር ቤት ይዞኝ ወርዶ፣ የመጀመሪያ ጥያቄ “ከየትኛው ጎሳ (Tribe) ነህ?” የሚል ነበር። ገርሞኝ  “አልገባኝም!” አልኩት። “እንደምታውቀው ኢትዮጵያ ሁሉም ጎሳ አለውና …” ሲለኝ “ያንተስ?” አልኩት “እኔማ አሜሪካዊ ነኝ! አለኝ “እኔም እትዮጵያዊ …!” በዚህ ፈግጠው! ፈግጠው! ተባብለን ምሳዬንም ሳልበላ ተለያየን። የነፍስ አባቴ (Godfather) ሊሆን ፈልጎ ይመስለኛል። ይኸው ሳልጠመቅ ተለያየን!
  ይኸኛው ነገርን ነገር ያነሳዋል መሆኑ ነው።
***
በዚህ “የሰላምና ዲሞክራሲ” የአፍሪቃ አዳራሽ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሶስት ቀን ተጠናቀቀና አራተኛው ቀን ለኤርትራ ተመደበ። ይህ ከመሆኑ አንድ ቀን በፊት ለቡና እረፍት ተደርጎ የነበረ ጊዜ የቢ.ቢ.ሲ (BBC) ተወካይ የነበረ ላስት(Last) የሚባል ጋዜጠኛ አገኘኝና፤ “ምስኪን አሰፋ፤ እንዴት ታሳዝናለህ” (Poor Assefa I pity You!) አለኝ። ከአንድ ወር በፊት Ominibus በሚባል የቢ.ቢ.ሲ ፕሮግራም ለተላለፈ ቃለ መጠይቅ አድርጎ “ምስኪን እስረኛ!” ብሎ ገንዘብ ብጤም ሰጥቶኝ የነበረ ነው። “ምን ሆኜ ነው የማሳዝነው?” አልኩት። “ይህንን ሶስት ቀን ሙሉ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት (ኦነግ) ከእናንተ ጋር ያሉ መስሎህ ስትዳክር!” አለኝ:: “ታዲያስ?” ስለው “ሎንዶን ለተዘጋጀው ስብሰባ ከመሔዳቸው በፊት ወያኔ  ሻእቢያና ኦነግ- ኤርትራ፤ ተሰነይ ከተማ ተሰብስበው የመጨረሻውን ውሳኔ ሁሉ ተስማምተው ነው የመጡት። ከእናንተ ጋር ሳይሆን ኦነግ ከወያኔና ከሻእቢያ ጋር ነው የወገነው!” አለኝ። ጨስኩ! ሌሎችም ለሶስት ቀን ግራ አጋብተውኝ የነበሩት ጭብጦች ፍንትው ብለው ታዩኝ። ስብሰባው እንደገና እንደተጀመረ በኦነግ ተወካዮች፣ በማውቃቸው ወዳጆቼና በኔ ስር ሆነው ይሰሩ በነበሩት ላይ ፈነዳሁ። ከኔ ፍንዳታ ይልቅ ጎልቶ ትዝ የሚለኝ የሲዳማው የአቶ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ነበር። ጣቱን ኦነግ መቀመጫ ላይ ሰትሮ “ትላንት ለምንሊክ፣ ዛሬ ደግሞ ለትግሬዎች ሸጣችሁን!” አለ። ይህ ሁሉ በወቅቱ በድምጽም በምስልም የተቀረጸ ስለሆነ አጥኝዎች ቢፈልጉት ሊያገኙት የሚችሉ ይመስለኛል።
ይህ ኢሳያስ አፈወርቂን በተጨማሪ መነጽር እንድምለከተው ሌላ ቀዳዳ ከፈተልኝ!
***
ከዚያም የስብሰባው ሊቀመንበር የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኢሳያስ አፈወርቂን ንግግር በጥሞና እንድናዳምጥ መመሪያ ሰጠንና ተዘጋጅቼ ማዳመጥም መመልከትም ጀመርኩ። መጀመሪያ ልብ ያልኩት የኢሳያስን አቀማመጡንና የሰውነቱን አያያዝ (Body Language) ነበር። የተቀመጠው በቀኝ በግራው በሰዎች ተከቦ፣ ወጣና ጎላ ያለ ወንበር ላይ ነበር። የተኮፈሰና የሚኮፈስ (Preposterous and pompous) መሰለኝ። ፊታቸውን አኮሳትረው፣ “ትንፍሽ ትይና ወዮሊሽ!” የሚል መልክ ይዘው ክፍል የሚገቡ አንዳንድ አስተማሪዎችን አስታወሰኝ። ከዚያ ንግግሩን በትግሪኛ ጀመረ።
የመጀመሪያው የአማርኛ አስተርጓሚ ዶክተር በረከት ሐብተሥላሴ ነበር። ዶክተር በረከት ሐብተሥላሴን አውቀዋለሁ። በንጉሱ ዘመን እዚሁ አፍሪቃ አዳራሽ የቀድሞው የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር (Alumni Association) ያዘጋጁት ስብሰባ ላይ በረከት ተናጋሪ፣ እኔ አዋኪ ሆነን ተለያይተናል። ሕግ ትምህርት ቤት ነበርኩ። እንደገና ሲያገኘኝ፤ “አሰፋ እንደገና አፍሪቃ አዳራሽ ተገናኘን!” አለኝ። “ልክ ነው! ሆኖም በተለያየ በር ነው የመጣነው!” አልኩትና ተሳሳቅን። የመጀመሪያ አስተርጓሚው በረከት ነበር ብያለሁ። አንድ አምስት ደቂቃ አንዳስተረጎመ ኢሳይያስ “አልቻልክም!” ብሎ አስወገደውና፣ በሌላ አጠር ባለ ሰውዬ ተካው። ይህ አጠር ያለ ሰው አንድ 7 ደቂቃ አስተረጎመና “አልቻልክም!” ተብሎ ተወገደ። የዚያን ጊዜ መለስ ዜናዊ፣ ከወዲያ ማዶ ከሊቀ መንበርነቱ ወንበር እጁን አውጥቶ “እኔ አስተረጉማለሁ!” አለና ተፈቅዶለት! ቀጠለ! አንድ አራት ደቂቃ እንዳስተረጎመ “አልቻልክም!” ተብሎ ተወገደ።። አራተኛ ሌላ ሰው መጣና የኢሳያስ ንግግር ተፈጸመ። የተጨበጨበ መሰለኝ። ልብ አላልኩም! እኔ ልቤም ማስተዋሌም ያተኮረው ኢሳያስ አፈወርቂና እዚህ አሳዛኝና አስቂኝ ቲያትር (Tragic Comedy) ላይ ነበር። ከይዘቱ ይልቅ ቅርጹ ላይ!
አስቂኝነቱ ቀርቶ አሳዛኝነቱ ጎልቶ የሚወጣው ይህ ሁሉ የሚደረገው “የጋራ ቤታችን!” ላይ መሆኑ ነው!
  በአብዛኛው የአሁኑ ወጣቶች ዶክተር በረከት ሐብተሥላሴን ላያውቁት ይችላሉ። በረከት የሐረር ልጅ፤ የግእዝ ሊቁ የአለቃ ሐብተሥላሴ ልጅ ነው። ስለዚህም የቤተክህነት ትምህርትም አለው። እንደ አለቃ ለማ እንደ መንግሥቱ ለማ! ማለት ነው። ዶክተርነቱ በሕግ ከእንግሊዝ አገር ነው። እንግሊዝ ልከው እንዲማር ያደረጉት ኃይለ ሥላሴ ነበሩ ተብሏል። የሐረር ልጅ  ናቸውና! አባቱንም ያውቃሉና!
በረከት በንጉሱ ዘመን የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ነበር። ሕግ ትምህርት ቤትም ያስተምር ነበር። መጀመሪያ ያየሁት ለአለም አቀፍ ዝምታ ፍርድ ቤት (International Moot Court Competition) የሕግ ተማሪዎች የማጣሪያ ወድድር ስናደርግ፣ ከፈረንጆች ጋር ዳኛ ሆኖ የመጣ ጊዜ ነበር። በደርግ ዘመን ደግሞ የመርማሪ ኮሚሽን ሊቀ መንበርም ሆኖ ነበር። ሊቀ መንበር እያለ ነው ሻቢያን የተቀላቀለውና አማካሪ የሆነው። ስለ ሻቢያም ስለ ኢትዮጵያም መጽሐፍት ጽፏል። ከዚያ ሁሉ በኋላ ኢሳያስ ሌላው ይቅርና ለአስተርጓሚነት እንኳን አትበቃም ብሎ ጣለው።
በረከት ሐብተስላሴ ተምሳሊት (Template) የሚሆን ይመስለኛል። የአስቆሮቱን ይሁዳንም ያስታውሰኛል። ወንጌሉ እንደሚለው፤ ይሁዳ ጌታውን የሸጠበትን ሰላሳ ብር አልበላባትም! አልጠጣባትም! ይልቁንም ራሱን ሰቀለ! ገንዘቡንም “ራሱን የገደለ ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ አይሆንም” ብለው የመቃብር ቦታ ገዙበት።  “አልቄዳ” የሚባለው ነው። የደም መሬት! ወያኔ ይህንን “የደም መሬት!” ትእይንት አድርጎት አቅርቦታል  ልበል? ጎበዝ! ጠንቀቀ ነው ደጉ!
እንዳልኩት በረከት አገርን ለከዱ፤ ለሚከዱ ሁሉ ተምሳሊት (Template) የሚሆን ይመስለኛል!!
ለመሆኑ ኢሳያስ አፈወርቂ ያንን ሁሉ አስተርጓሚ “አልቻላችሁም!” የሚለው ምኑን ነበር? ትግርኛውን አይመስለኝም! ወይም በኔ ደረጃ ያለ ትግሪኛ አትረዱም ማለት ይሆን? አማርኛ አትችሉም ነው? ይህን ማለት  ደግሞ ኢሳያስ አማርኛ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እስኪያርም ጠንቆቆ ያውቃል ማለት ይሆናል። ወይም “ማን አለኝ ከልካይ!” መሆኑን፣ በዚህ መድረክ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ላስመስክር ይሆን? ወይም ይህ መሪያችሁ ነኝ የሚለውን መለስ ዜናዊን እንኳን እንደ መሪ ከመጤፍም አልቆጥረውም የሚል መልእከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መላኩ ይሆን? ወይም ማንንም ምንንም በአደባባይ ለማዋረድ ብቃትና እውቀት ያለኝ ሰው ነኝ፣ እወቅሉኝ ይሆን? በዚያም በዚህ ብትሉ የኔን ያክል አዋቂ ቀርቶ እኔ የምለውን፤የምናገረውን መረዳት የሚችል እንደሌለ እይሉኝ ነው?  
የሥነልቡና አዋቂዎች (Psychaitrists) ምን ይሉ ይሆን? በሽተኛ መሆኑን ይቀበላሉ! የበሽታውን አይነት ምን ይሉት ይሆን? አንዳንዱ የአንጎል፣ የአእምሮ፣ የህሊና ህመም-- ታክሞ የማይድን ነው ይሉታል። ለምሳሌ Sociopath የሚሉት! “እቡይ!” እንደ ማለት!  “እቡየ ዐይን ወስሱሀ ልብ ኢይትሀወር ምስለየ”
በኢሳይያስ ንግግር ወቅት በኔ ጭንቅላት፣ በኔ ህሊና፣ በኔ አእምሮ የሚተራመሱት ይህንና ይህንን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ነበሩ።
****
አሁን የኢሳያስንና የኦነግን የቆየና “የፀና” ግንኙነት በዘመን ረድፍ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ::
በዘመነ ደርግ በድርቅ ከተጠቁ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ከወሎ ሠፋሪዎች አሶሳ ሰፍረው ነበር። አንድ ምሸት የሰፈሩበት መንደርም፣ ሠፋሪዎች ጭምር በጥይትና በእሳት ጋዩ። ይህንን ያደረገው የሻእቢያና ኦነግ ሕብረት ነበር። መንገድ መሪ ኦነግ መሆኑ በወቅቱ በሕዝብ መገናኛዎች እስኪሰቀጥጥ ተነግሯል። የሚገርም ሌላም ነገር አለ።  አሶሳ ወለጋ ክፍለ አገር ውስጥ ይሁን እንጅ ኦሮሞም የኦሮሞ መሬትም አልነበረም! አይደለምም! “ነፃ አውጭ” ነን ቢሉ እንኳን ኦሮሞን እንጅ ቤኒሻንጎልን አይደለም። ሌላው የሚገርመው በወቅቱ የኦነግ መሥራችና መሪ ባሮ ቱሙሳ ምንሊክ ግቢ ከደርግ ጋር እየሰራ ነበር። ከምእራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ነፍሰ ገዳይ ፍለጋ ኤርትራ በረሀ ድረስ ምን ወሰዳቸው? የሐሳቡ አመንጭ ኦነግ ነው ወይስ ሻእቢያ? ጭካኔ የነፃ አውጭነት አንደኛው ባሕርይ ነው?
የሚቀጥለው የተሰነይ ስብሰባ ነው። መለሰ ዜናዊ፣ ኢሳይያስ አፈወርቂና ሌንጮ (ዮሐንስ) ለታ በአንድ ግንባር ስር ለንዶን ለመጓዝ እንደተስማሙ የሚያሳይ የሚጨባበጡበት ፎቶግራፍ በድረገጾች ታይቷል። ምን ነበር የመገናኛና የአንድነት መሠረቱ (Point of Convergance)? ነጥባቸው? ኢትዮጵያን በሚመለከት ማለቴ ነው!
የሎንዶኑን ስብሰባ ያዘጋጀው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) ነበር። ሔርማን ኮኸን እዚያው ነበር። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃን፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉን ቢልልኝ ማንደፍሮንና ዶክተር ግርማ ወልደስላሴን ጨምሮ ሎንዶን ደርሰዋል።
ስለ ኢትዮጵያ መልእከተኞች ጉዳይ የአቶ ተፈራ ኃይለሥላሴን The Ethiopian Revolution መጽሐፍ ማንበቡ ጥሩ ነው። አቶ ተፈራ በወቅቱ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለነበር የታዘበውን ጽፏል። “ለስደት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው መጡ እንጅ ለውይይት አልነበረምም! አይመስልምም” ይላል። እንዳለውም አቶ ተስፋዬና ቢልልኝ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ አመሩ። እዚያም ሲደርሱ እነ ዶከተር ግርማን ጣጥለው ወደሚሔዱበት ሔዱ። እኔ መጀመሪያ ዋሺንግተን ዲ.ሲ ያገኘሁት ዶክተር ግርማን ነበር። “አሰፋ፤ እኔ ያደረጉኝን ያድርጉኝ እንጂ ወደ ኢትዮጵያ እመለሳለሁ!” እንዳለው ተመለሰ። ከንክኖኝ አንዳንድ ነገር ለመጠየቅ የሚሠራበት የዓለም ባንክ ቢሮ ሔጄ አቶ ተስፋዬ ዲንቃን አነጋገርኩ። ጸሐፊው ቡና አመጣችልኝና ጠጥቼ ብዙም ሳልጠይቅ ወጣሁ። “ለመሆኑ ምንና ምኑ ይጠየቃል?” ብዬ መሆን አለበት!
የሎንዶኑ ስብሰባ፣ ስብሰባ ካልነው፣ የአሜሪካን መንግስት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፈጸመው ታላላቅ ደባዎች ውስጥ ቀዳሚነት  የሚኖረው ነው። ሌላው ሶማሌ ወርራ ድሬዳዋ ልትገባ ስትገሰግስ የጦር መሣሪያ ማእቀብ በኢትዮጵያ ላይ መጣሉ  ነው።
የሎንዶኑ ስብሰባ ሌላ ትልቅ ምስልም ነበረው። መንግስቱ ኃይለማርያም ከነቤተሰቡ ዚምባቡዌ እንዲሰደድ፣ ጄነራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ፕሬዚዳንት እንዲሆን፣ የኢትዮጵያን ጦር ሠራዊት “እጅህን ለወያኔ ስጥ!” እንዲል፣ መለሰ ዜናዊ፣ ሥዩም መስፍንና ጓደኞቹ በሱዳን የጸጥታ ጉዳይ ሚኒስትር ጀነራል አልፋቲህ አርዋ በሚነዳ አውሮፕላን አዲስ አበባ እንዲገቡ፣ እነ ሌንጮም የተሰጣቸውን “የቤት ሥራ” በትክክል እንዲወጡ ማድረግ የአሜሪካን መንግስት የተቀነባበረ ሥራ ነበር። የረዥም ጊዜ ሴራ ውጤት ነበር!!
በትክክል ሥራ ላይ ማዋሉን ለመከታተል አዲስ አምባሳደር ባስን (Baas) አዲስ አበባ በአስቸኳይ ላኩ። የነፍስ አባትየው (The Godfather) ሔርማን ኮኸንም የድል ምሸቱ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ መጣ። አምባሳደር ባስም ኢትዮጵያን እስክለቅ ድረስ ብርቱ ወዳጄ ሆኖ ሰንብቷል። ሁለት የአሜሪካን ሴናተሮች ለጉብኝት መጥተው ኖሮ ለነጻነታቸው በዓል July 4th 1991 አሜሪካን ኤምባሲ የጋበዘው ኢትዮጵያዊ እኔና ባለቤቴን ብቻ መሆኑን አስታውሳለሁ። የፖል ሔንዝ ተልእኮ አይነት የሚያጣ አይመስለኝም!
ለዚህ የሰላምና ዲሞክራሲ ስብሰባ የመጣም፣ ያመጡትም፣ ደጅ ጠኝውም፣ የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆን ያኮበኮበውም፣ መናኸሪያችን አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ነበር። ከወያኔና ሻእቢያ በስተቀር! የወያኔ ጭፍሮቹ የት እንደሰፈሩ አላውቅም። ሻእቢያ የሰፈረው የጄኔራል ተፈሪ በንቲ መኖሪያ የነበረው ነው ተባልኩ። ግራ የገባኝ የኦነግ አባሎች የት ደረሱ? በሚል ነበር። ስብሰባ ላይ ሳገኛቸው “እነዚህ ሰዎች ከኛ ነጠሏችሁ!” እላለሁ። በዚያ በስብሰባው መካከል የደቡብ ሕብረት ለመመሥረት ማታ ማታ እንነጋር ስለነበር እንዲገቡበት ፈልጌ ነበር። በኋላ የቢ.ቢ.ሲው ላስት ተሰነይን ሲነግረኝ ግልጽ ሆነልኝ። የኦነግ አባሎች፣ ሌላው ቀርቶ ከኔው ጋር ማእከላዊ የነበሩት ጭምር ሰፈራቸው ከሻእቢያ ጋር ጄነራል ተፈሪ በንቲ መኖሪያ የነበረው ሆኖ ተገኘ። እንዲህ አንድ ጡት ጠብቶ ያደጉ የሚያስመስለው ፍቅር፣ ሌሎቻችንን እንዲሸሹ ያደረገው ፍቅር፣ ከየት ወረደ? የሚያሰኝ ነበር። ምን ይሆን? የኢትዮጵያስ ይቅር እውነት የኦሮሞ መሠረታዊ ጥቅም ነው? ጫወታው ሌላ መሆኑ  በጥቂት ወራት ታየ! እመለስበታለሁ!
ከአፍሪቃ አዳራሹ ስብሰባ በኋላ የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ምክር ቤት ተቋቋመ። ለጥቂት ወራቶች የሽግግሩ ምክር ቤት አባል ነበርኩ። ኦነግ 8 መቀመጫዎች ነበሩት። በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መጠን ማለት ነው! አራት ሚኒስትሮችም ተሾሙ። ከዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚታወሰኝ፣ ምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት የኦነግ ተወካዮች፣ ሌንጮ ለታና አብዩ ገለታ ሥራ ነበር። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሠራዊት አፍራሽ ኮሚቴ ሊቃነ መናብርት ሆኑ። የኢትዮጵያ ሠራዊት አይሉትም።      “የደርግ  ወታደር!” ይሉታል። ለማስረዳት ሞከርኩ። “ደርግ መንግስት ነው። መንግስት ሠራዊት የለውም። አገር ነው ሠራዊት ያለው። ከዚህም ሌላ ወንጀለኞች ቢኖሩ በማስረጃ ማረጋገጥና መጠየቅ እንጅ የአገር ሠራዊት ይፍረስ ተብሎ አይታወቅም!” ከንቱ ጩኸት ሆነ።
ቢቸግረኝ አንድ ቀን  ሌንጮንና አብዩን ቡና ጋብዤ “ይህ ይፍረስ! ይፍረስ! የምትሉት ሠራዊት ኦሮሞኮ ነው። አሁን በደመወዝ መተዳደር የለመደ፤ ከግብርናውም የተፋታውን በትነን በጭፍን እስር ቤት መክተትና ለማኝ ማድረግ…” አልኩኝ። “ማነው ኦሮሞ ነው ያለህ?” “ይህማ ግልጽ ነው! አንደኛ ሠራዊቱ አብዛኛው የተመለመለው ከደቡብ ነው። ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ ኦሮሞ አብላጫ ቁጥር አለውና…” አልሰሙኝም! ሊሰሙኝም አልፈለጉም! አይችሉምም! እነሱ የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጅ ባለጉዳይ አልነበሩም! ብቻ የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈርሶ፣ ወደ ልመናና ወደ ስደት ተዳረገ! መፍረሱ አይቀሬ ነበር!  የዚያን ዘመን የምክር ቤት ውይይት ያዳመጠ፣ አፍራሹ ኦነግ መሆኑን ያያል። ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው!
የትምህርት ሚኒስቴር ሆኖ የተሾመው ኢብሳ ጉተማ ነበር። ሀ ብሎ ያረቀቀው አዋጅ ኦሮሚኛ በላቲን ፊደል እንዲጻፍ ነበር። ወዳጄ ስለነበረ ቢሮው ሔጄ “ኢብሳ አብደሀል እንዴ! ኦሮሞን ወደ ቅኝ ግዛትነት ልትመልሰው ነው!?” አልኩኝ “እንዴት?” ቢለኝ  “ቅኝ ግዛት የነበሩት ሁሉ የሚጽፉትና የሚናገሩት በላቲን ነው!”  አልኩኝ።  የሆነ የነፍጠኛ ደጋፊ የሚል ቀልድ ሲያመጣ “ይህ የአማርኛ ፊደል የአማራ ፊደል አይደለም! የመጀመሪያውና ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው! ልንኮራበት ይገባል …” አልኩት። አልሆነምና የሆነው ሆነ!
ምክር ቤቱ ውስጥ የኢሕአዴግ አባል የሆነ “የኢትዮጵያ መኮንኖች ግምባር” የሚባል ባለ 8 መቀመጫ ድርጀት ነበር። ምርኮኛ የነበሩ መኮንኖች ማለት ነው። አንድ ሁለት ሶስት ቀን ያክል ምክር ቤቱ ውስጥ አላያቸውም። አንድ ጥዋት ቡና እረፍት ላይ ሥዩም መስፍንን፤ “ሥዩም እነዚህ መኮንኖቻችን አላያቸውምሳ?” አልኩት። ከት ብሎ ስቆ “አቶ አሰፋ፤ ሚናቸውን ጨርሰው ተሽኝተዋል!” አለኝ። “ታዲያ 8ቱ መቀመጫ ምን ይሆናል?” አልኩት። “ወያኔ ወስዶታል!” አለኝ። ሌላ ጥያቄ ከመጠየቄ በፊት ሔደብኝ።
 የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ልክ የመኮንኖቹ ዓይነት ዕጣ ደረሰባቸው። ታህሳስ ይሆን ጥር 1982 መመሪያ ተሰጣቸው። “ከዛሬ ጀምሮ ምክር ቤቱ ውስጥ ያላችሁን ድርሻ ፈጽማችኋል! ከዛሬ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ምድር እንድትወጡ! ካልወጣችሁ ወህኒ ቤት ትወርዳላችሁ! ምርጫውን ለእናንተው እንተዋለን!” ተባሉ። ከተሰጣቸው ሁለት ምርጫ ኢትዮጵያን ለቀው መውጣትን መረጡ። አህያ የተጫነችውን ታደርሳለች እንጅ አትበላውም! እንዲሉ።
ከወያኔ ጋር አዲስ አበባ እንደገቡ አሁን “የኦነግ ተዋጊ ኃይል ነው የምትሉትን ሁሉ ከነመሣሪያው ጦር ካምፕ አስገቡ!” ተባሉ። በታዘዙት መሠረት አስገቡ። “ከአገር ቤት መውጣት ወይ እስር ቤት” ምርጫ ሲሰጥ፣ጦር ካምፕ ውስጥ በቁም እስረኝነት ያስረከቧቸው ተዋጊዎች ደረጃ ወደ ሙሉ እስረኝነት ተሸጋገረ። እጃቸውን ራሳቸው ላይ አድርገው፣ በወያኔ ወታደሮች እየተነዱ እስር ቤት ወረዱ። እስከ ዛሬ እጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ፣ ከምን እንደደረሰ የጠየቀም፣ ያስረዳም የለም!
***
ኦነግ፣ ኢሳይያስ አፈወርቂና የአትላንታ ስብሰባ
የአትላንታ፣ ጆርጂያ የኦሮሞ “ምሁራንና ብሔርተኞች” ስብሰባ አንድ ግብ አስቀምጧል። “የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለነጻነት የሚበቃ፤ እንደ ኤርትራ፤ ትግሬና ደቡብ ሱዳን መሆን አለበት!” ይላል። ጎበዝ! “ቸር ተመኝ! ቸር እንድታገኝ!” ይባላል። ፈረንጅ ደግሞ “ለከዋክብቱ አነጣጥር ብትስት እንኳን የባህር ዛፉን አናት ትመታለህ!” (Aim to the Stars! If you miss, You Will Hit the Top of the Tree!) ይላል። ኢሳያስ መላው አለም ማእቀብ አድርጎበት፣ ከዛሬ ነገ የአለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባል እየተባለ የሚባንን ጉድ ነው። ወያኔም ጭንቅ ላይ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን የሚባለው አገር የከሸፈ አገር (failed State) ነው ወይስ አገር ነው? እየተባለ ነው። በቃላት እንኳን ቢሆን ለዚህ ለታላቁና ገራ-ገሩ የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ የተሻለ አድማስ መቅረጹ በተገባ ነበር። የአትላንታውን ስብሰባ አድማስ መፈለጊያ መነጥር መሰለኝ። የተሻለ መነጽር ባይኖር ወይ መግዛት ወይም መዋስ በተገባ ነበር።
ወያኔ “ከኢትዮጵያ ጥፉ!” ብሎ ካባረረ ከ1982 ጀምሮ ኦነግ ብዙ የውስጥ ትርምስ የገጠመው ይመስለኛል። አንዴ ስለታዘብኳቸው ዝርዝሩን ብዙም አልከታተልም። “ወትሮም የኦሮሞ ሳይሆን የአንድ መንደር ሥልጣን ፈላጊዎች ጥርቅም ነበር!” በሚል ማን ይምራ ማን የሚል ትርምስ የተፈጠረ ይመስለኛል። አብዩ ገለታ ዋሽንግቶን ዲስ የነበሩትን የኦነግ ልጆች ቢሮ ነጥቆ “እኔን ሹም!” አለ። አንድ ቀን በአካባቢው ነበርኩና ልጠይቀው ቢሮ ሔድኩ። ልክ ለኢሳያስ እንዳልኩት ተኮፍሶ ጠበቀኝ። የዚህ የምክር ቤቱንና የማባረሩን ጉድ ያነሳብናል በሚል ፍርሐት በሩን መዝጋቱ መሰለኝ። ሥራ የበዛበት ለማስመስል ብዙ አስጠበቀኝ። በኋላ ቢሮው ስገባ የጄነራል ታደሰ ብሩን ፎቶግራፍ በትልቁ ግርግዳው ላይ አየሁና፣ ፈገግ ብዬ፤ “እኒህ ደግሞ ማናቸው?” አልኩት። ገርሞት “አታውቃቸውም እንዴ? ጄነራል ታደሰ ብሩ ናቸው!” አለኝ። “ኦነግ ነበሩ እንዴ?” አልኩት፡፡  ጄነራል ታደሰ ብሩ ኦሮሞን ለማስተማርና ንቃተ ህሊናውን ከፍ ለማድረግ የጀመሩት ጥረት ተጣሞ ተተርጉሞ  የታሰሩ፣ በኋላም በአሳሳቾች ለአጉል ወሬ የተዳረጉ፤ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነበሩ። በስም መነገድ የሚባለው የዚህ አይነቱ ይሆን?
ሌላው የኦነግ ቅርንጫፍ የተከፈተው ኤርትራ፣ አስመራ ነበር። መሪዎች ነን የሚባባሉት የተፈራረቁ ይመስለኛልና በሙሉ አላውቃቸውም። አሁን ካሉት፣ ወይም አለን ከሚሉት አንዱ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ነው። በኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን የኦሮሞ ሕዝብ አመጽ የምመራው እኔ ነኝ የሚል መግለጫ ባለፈው ወር ሰጥቶ፣ አንብቤ ድፍረቱን አደነቅሁ። ዳውድ ኢብሳ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢሳያስ የማይጠረጥረው የኢሳያስ ታማኝ ነው። ታማኝ መሳሪያ ነው አላልኩም! አሁን ለመሳሪያነት ብቁ ሆኖ አልተገኘም! በንግድ ስራ ተሠማርቶ መካከለኛው ምስራቅ ይመላለሳል። አሥመራ ውስጥ ቆንጆ መኪና ከሚነዱት ውስጥ አንዱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ያችን መኪና ለተስፋዬ የሸጠው ዳውድ ነው።
የአትላንታው ስብሰባ ለዳውድ ልክ በወያኔ ቋንቋ አንድ “ኮማንድ ፖስት” ሰጥቶታል። የምእራብና የምስራቅ ኮማንድ ፖስት ይለዋል።
ሌላው የደቡብ ኮማንድ ፖስት፣ ቦረናን፣ ባሌንና አርሲን የሚያጠቃልለው ኮማንድ ፖስት አዛዥ ጀነራል ከማል ገልቹ ነው። ከማል ገልቹ በምርኮኝነት ተይዞ፣ ኦፒዲኦ የሆነ የወያኔ ሰው ነበር። እስከ ዛሬ ሶስቴ ከድቷል ማለት ነው! ከማል ገልቹ “ጀነራል ሁን ተባለ፤ ጀነራልም ሆነ!” የምንለው ነው። “ብርሐን ይሁን አለ ብርሐንም ሆነ!” መጽሐፍ እንዲል። የአርሲ ልጅ ነው።
ከማል ገልቹ አሁን አምባሳደር ነው። የኢሳያስ አፈወርቂ አምባሳደር ሆኖ፣ ለተልእኮውምሥራቅ አፍሪቃ  ከተላከ  ሰንብቷል። በአርሲ አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ነው የተላከው። ይህ የአትላንታው ጉባዔ የሰጠውን ኮማንድ ፖስት ማጠቃለሉን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
ከማል ገልቹ ዩጋንዳ ከመላኩ በፊት ታማኝነቱን ለማረጋገጥም፣ አንድ የበላይ አካል ተቆጣጣሪም ስለሚያስፈልገው ኢሳይያስ አንድ የሻቢያ ጄነራል ልጅ  ድሮለት ሚስቱም አብራው ሔዳለች። ለተጨማሪ ጥንቃቄ ሲባል፣ ከማል ገልቹ ሳያውቅ፣ የከማል ገልቹን አንድ ልጅ ከኢትዮጵያ አስመጥቶ በመያዣነት አስቀምጦታል። ልጁ መያዣ መሆኑን ከማል ገልቹ አያውቅም ነበር። አሁን ማወቅ አለማወቁን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
እንግዲህ ከዚህ ተነስተን የግድ መድረስ ያለብን ድምዳሜ ያለ ይመስለኛል። ሁሌም 2+2=4 ነውና! ይህም፣ ከማል ገልቹና የአትላንታ ስብስብ በአንድ “ኮማንድ ፖስት” ይመራሉ ማለት ነው። ያ ከሆነ ደግሞ “የኮማንድ ፖስቱ” ጀነራል ኢሳያስ አፈወርቂ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ የአትላንታው ስብሰባ ኢሳያስ አፈወርቂን እንደ ፈር ቀዳጅ የትግል ተምሳሌት  (Role Model) አድርጎ ተቀብሎታልና! ይህ በጽሁፍ ማስረጃ የተደገፈ ነው ማለት ነው። ይሰውረን!
ከዚህ ሌላ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ላይ ካደረጋቸው ደባዎች ጥቂቶችን፤ የምታውቋቸውን ልጠቃቅስ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)ን መሠረተ እንኳን ማለት ባይቻል የኢትዮጵያን አየር መንገድ አውሮፕላን አምስት ጊዜ አስጠልፏል። አለቃቸው የነበረው ክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” በሚለው መጽሐፍ ገልጾታል።
በብርሀነ መስቀል ረዳ የሚመራው የኢሕአፓ ሠራዊት ከሻቢያ ጋር በመሆን ለሁለት አመት የኢትዮጵያን ጦር ወግቷል። “ይድረስ ለባለታሪኩ” የሚለውን እዚያው የነበረውን፣ የተስፋዬ መኮንንን መጽሐፍ ማንበብ ነው።
ብርሐነ መስቀልንና ጓደኞቹን አሲምባ ያስገባው የካቲቲ 25፣ 1967 የኢትዮጵያ የገጠር መሬት የታወጀ ዕለት ነው። ስላቁ ደግሞ እነ ብርሐነ መስቀል መሬት ላራሹ እያሉ ወይም እያስመሰሉ ሲዘምሩ የነበሩ መሆናቸውና መሬት ለአራሹ የሆነ ዕለት አሲምባ መግባታቸው ነበር።
ለማጠቃለል
ይህ ነገር የራሱ እግር አውጥቶ አልጠቃለል ብሎኛልና በግድም ቢሆን መቆም ያለበት ይመስለኛል። ከፈለኩት በላይ ረዘመብኝ።
ኢሳያስ ይህንን ለምን ያደርጋል? ነው። ከህመሙ ሌላ፣ በረከት ሐብተ ሥላሴን አስተርጓሚ አትሆንም ይበለው እንጅ ምክሩን ተቀብሎታል። የዶከተር በረከት ምክር፣ መጽሐፍ የጻፈበትም፣ኢትዮጵያ የምትባል አገር በሰላም ከኖረች፣ ኤርትራ ጠንካራና ታይዋን አይነት ልትሆን አትችልም ነው። አሁን ያንን ወያኔ ወደማሳካቱ ተቃርቧል። ከማል ገልቹ አምባሳደርም የሆነው ለዚሁ እቡይ ተልእኮ ነው።
ዋናው፤ በጣምም የሚያሳዝነኝ የኦነግ ጉዳይ ነው። ኦሮሞ “ኦሮሚያ” የሚባል አገር መሥርቶ “መንግስት ይሁን!”  እንኳን ቢባል ከራያና አዘቦ አንስቶ እስከ ባምባሲ መሬት ወይም መሬታቸው ያደረጉት አላቸው። አኩሪና ዝነኛ ታሪክ ያለው ላለፈው 600 አመታት ብዙ ዝነኛ የኢትዮጵያ ነገሥታትም  የጦር መሪዎችም ያፈራ ታላቅ ሕዝብ ነው። ይህንን፣ የዚህን ሕዝብ ስምና ዝና አንግቦ ሻንጣ ተሸካሚ፤ ደጋግሞ ሻንጫ ተሸካሚ መሆን፣ ሕዝቡን የሻንጫ ተሸካሚነቱ አካል፣ አምሳል ማድረግ የሕዝቡን ክብር ዝቅ ማድረግ ወይም የራስን የታመመ የሥልጣን ጥማት ቅድሚያ መስጠት ይመስለኛል።
መውደድ፣ ማፈር፣ መናደድ፣ መኩራት፣ መደሰት--- ተፈጥሮ በተፈጥሮ ለሰው ልጅ የለገሰችው ስሜቶች ናቸው። እነዚህ የኦነግ መሪዎች ነን የሚሉት ይህ ጸጋ በተለይም ማፈር የሚሉት እንደተሰጣቸው እርግጠኛ ነኝ። ሊያስተውሉትና ሊፈልጉት፣ ተግባራዊ ሊያደርጉትም ይገባቸዋል እላለሁ! ይገባልም!
 ይህንን የምናገረው እንደ ሰው ነው። ማንም ሰው ደሴት አይደለም- No Man is an Island  የሚለው የJohn Donne ግጥም የምወደውና የማምንበትም ነው።

Read 9447 times