Monday, 05 December 2016 09:08

መልካም ልደት - ሉሲ!

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

     (ህዳር - HADAR)
ድንቅነሽ (ሉሲ) በያዝነው ህዳር ወር መገኘቷን መነሻ በማድረግ፤ ተራኪ ቱሩጁማኑ፤ ከኃይማኖታዊው የፈጣሪና ፍጥረት ‹‹እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ›› በተለየ (ባፈነገጠም) መልኩም ቢሆን በ LUCY AND HER TIME ጥራዝ ውስጥ ከተካተቱ ሳይንሳዊ ትንታኔዎች መሀል ለመቆንጠር መሻቱ፤ አንድም ‹‹ሁሉን መርምሩ መልካሙን ያዙ››ን በመመርኮዝ፤ አንድም የሳይንሱ አለም በራችንን ማንኳኳቱን፣ ወሰኑን ማስፋቱን ጠንክሮ በገፋበት በዚህ ዘመን፤ ለመመርመር፣ ለመደመም፣ ለመደገፍ ለመቃወም ፤ ‹‹አሉ››ም ቢሆን፤ የሌላውን ጽንፍ ማወቅ ቢጠቅም እንጂ ... ከሚል ትህትና እንዲቆጠር፤ ያውም በኛው ሀገር ቅርስ ዙሪያ ተጽፎ፡፡ በተረፈ ቅይጣዊነትም ሆነ ጉራማይሌነት (የቋንቋም የሀሳብም) ቢስተዋል፤ ኦሪጂናሌው ምንጭ የፈጠረውን ብርቱ ተጽእኖ ከወዲሁ በመጠቆም፤ አብሮም ደግሞ ምናልባት ገጹ ያለወትሮው በስዕል አሸብርቆ መታየቱ፤ የዛሬው ንባባችን ልደቷን በማስመልከት በመሆኑ ነው፡፡ እነሆ . . .
       SPIRAL TIME - ጊዜ ዙሪያ ጥምጥሙ
ለጥንትም ጥንት አለውን @ - የሳይንስ ምሁራኑ WHAT WAS BEFORE THERE WAS A BEFORE ?! ብለው በመጠየቅ፤ጓዘ ቅጥልጥሉ የሥነ ፍጥረት ሂደት ጅማሬ ዘመኑ ሲሰላ፤ ታሪካዊ ዳራው ሦስት ቢሊዮን አመታት የኋሊዮሽ ይከነዳል ይላሉ፡፡ይኸውም ምድር ከተመሰረተች (4.5 ቢሊዮን አመታት) በኋላ ‹ጥቂት› ዘግይቶ ነው፡፡ (ሊቃውንቱ ጥቂት የሚሉት 1.5 ቢሊዮን አመታትን መሆኑ ነው፡፡) ቀደምቶቹ ህያው ክስተትም ራሳቸውን የማባዛት ተፈጥሮ የነበራቸው ቅንጣቶች Molecules ነበሩ፤ እነርሱ ቆይተው ወደ Bacteria ረቂቃን ነፍሳት፤ ከዚያም ከዛሬ 1 ቢሊዮን አመታት በፊት ዘር nucleus ወደ ቋጠረ ህዋስነት ደረሱ፤ ይላሉ፡፡
ውኃ - ቀዳማይ መኖሪያ - ህይወት ከሶስት ቢሊዮን አመታት በፊት  በባህር ውስጥ ተጀመረ፡፡ ጥንታዊያኑ ህያዋን ከነጠላ ህዋስነት ተነስተው በባክቴሪያነትና በጥንታዊው አልጌነት አዝግመው፤ ከ1 ቢሊዮን አመት በፊት ደግሞ እርስ በርስ እየተቆራኙ ባለ ብዙ ህዋስ (algae, sponges, jellyfish) ቅርጾችን ፈጠሩ፡፡ ያኔ በፍጥረታቱ ብዛት ውቅያኖሶች ተጨናነቁ፡፡ የሚላወሱበት አቅል (organ) ያቆጠቆጡቱ ብቅ ብቅ እስካሉበት ከዛሬ 700 ሚሊዮን አመት ድረስም የሁሉም መኖሪያ ከዚያው ነበር። ከ500 ሚሊዮን አመታት በፊት ታዲያ፤ ለየት ያሉቱና ጎባጣ ዘንግ መሰል የተደራጀ አካል ያላቸው አዳዲስ ፍጥረታት ከች አሉ፡፡ መቸም ባህር ከተፈጠረች እንዲህ ያለ አከርካሪ (vertebrate) ያለው ጉድ አይታ አታውቅም ነበር፤ አሉ፡፡ እንደ  ልብ ወዲያ ወዲህ ለመንሸራሸር መጨናነቁ (traffic jam) በበዛ ጊዜም ፤ ለውኃ ውስጥ ነዋሪ (aquatic) ተዋንያኑ እንዳሻቸው መወናኘት ከባድ ሆነባቸው፡፡ መፍጨርጨርና መወራጨታቸውን ቀጠሉ፡፡ መድረኩ ከጠበባቸው መካከል ነቄ የሆኑቱ ባለ ሳንባዎቹ ተዋንያን፤ በውኃ ውስጥም ውጪም መተንፈስ እንደሚችሉ ሞክረው አረጋገጡ፡፡ (አሁን እንግዲህ prison break አይነት ፊልም ሊጀምር ነው!) በተንጠራሩ ቁጥር ለጥንቱ እግር መፈጠር መነሻ የሆነውንና እንደ ክንፍ/ክንድ መሰል ያሉ አካሎችን አጎጠጎጡ፡፡ ከዚያስ... እየተንፈራገጡ ከውኃው ውስጥ ለቅጽበት ሹልክ ብለው (በህቡእ) የየብስን ዙሪያ- ገብ ቃኘት (ስለላ ቢጤ) እያደረጉ መመለሱን ተያያዙት፡፡ ፓሊዮዞይክ (Paleozoic Era) በሚባለው ዘመንም ኃይልና ወኔያቸውን አስተባብረው ውኃውን ለቅቀው ወጥተው እብስ አሉ፡፡ እኒያ ፈር ቀዳጆቹ ጎበዛዝትም ከእነሱ በኋላ ወደ መጡት ወደ የውሀም የብስም ፍጥረት (amphibians) ወደእነ እንቁራሪትነት ለመለወጥ ባጁ፡፡ እናስ...አንድ ጊዜ የቤት/ውኃ ልጅነታቸውን ከተዉ በኋላማ ማን ሀይ ይበላቸው፤ ማንስ ከልካይ ኖሮባቸው፤ በቃአ የውኃ ነዋሪዎች የነበሩቱ ፍጡራን በየጥሻውና ጥቅጥቅ  ጫካና ደኑ ተንሰራፍተው መቦረቅ፡ አሽኮለሌና እሽንደረሬ ሆነ፡፡ በወቅቱ ተክሎችና ነፍሳትም በየራሳቸው ሂደት ቀደም ብለው ከውኃ ወጥተው፣ ሜዳና ተራራውን አካልለውት ነበር፤አሉ፡፡
JURRASIC PARK MOVES ON
የእነ ዳይኖሰር ዘመን ደረሰ፤ የአጥቢዎቹ
በደረቁ የብስ ላይ ከራርመው ደግሞ፤ ቆራጦቹ ተዋንያን ወደ ተሳቢ ፍጥረትነት (reptiles) መለወጡን ተያያዙት፡፡ ከጥቂት ሚሊዮን (‹‹ጥቂት - ሚሊዮን!››) አመታት በኋላም በሜሶዞይክ ዘመን (Mesozoic Era) ሳይሆን አይቀርም፤ በ JURRASIC PARK ፊልም እንዲሳተፉ ለኮከቦቹ ተዋንያን የክብር ጥሪ የሚደርሳቸው። ያኔ ነበራ ከመካከላቸው ብርቱዎቹ ወደ ዳይኖሰርነት (Dinosaur) ራሳቸውን ያሸጋገሩት፡፡ በዚያ አጋጣሚም ነው፤ ተክሎችም አበባና የዛፍ ፍሬ የሚሰጡ ሆነው ለአጥቢ ፍጡራኑ (Mammals) ምግብነት የዋሉት፤ ከዛሬ 55 ሚሊዮን አመታት በፊት፡፡ አጥቢዎቹ ከዛሬ 30 ሚሊዮን አመት በፊት ጀምሮ በምድር ዙሪያ ተስፋፉ። ጥንታዊያኑ የኛዎቹ ምንጅላቶች የሆኑት ቀደምት የሰው ዘሮች (Hominids) ‹‹መጥተናል! ደርሰናል!›› ብለው ያወጁት ከዛሬ 15 ሚሊዮን አመታት በፊት ነበር። ድንቅነሽ (ሉሲ) እና የሷ ዝርያዎች በአድማሱ ጫፍ ብቅ ብለው የታዩት በጣም አርፍደው የዛሬ 4 ሚሊዮን  አመት ገደማ ነበር፡፡ (አሁን በቅርቡ!) በዚህ ሁሉ ታላቅ የፍጥረታት ታሪክ ሂደት ሰፊ የተውኔት ድርሳን ውስጥ፤ የዘመናዊው የሰው ልጅ የትወና ድርሻ በጣም አጭር ነው። አንድ ሚሊዮን አመት እንኳ አይሞላም፡፡ ይኸውም እሷኑ ድንቅነሽን (ሉሲ) ለምስክርነት ቆጥረን ነው፡፡
HOMINIZATION - የሚያማልል ግን የተሳሳተ መልክ
ሰዎች እጹብ ድንቅ ናቸው፤ ፍጥረተ አለሙ ሁሉ የእነርሱ የብቻቸው ነውና፡፡ ጊዜ መቆጠር ከጀመረበት አንስቶ ያጠነጠነው የረዥሙ ዝግመተ ለውጥ ታሪክ ሁሉ፣ ብቸኛ ግቡም ያው አንድ እና አንድ ብቻ ነው - የሰው ልጅ።
ያም ሆኖ በስእሉ የምናየው የዘረ ሰብ ሂደት ማሳያ (HOMINIZATION) ግንዛቤ የተሳሳተና፤ ሌሎቹን በረዥሙ የዝግመተ ለውጡ ሂደት ውስጥ ድርሻ ያላቸውን በርካታ የጦጣ ዝርያዎችን ያላካተተ ነው፡፡ በዚህ ያረጀ ቀመር መሰረት፣ ፍጹም የሆነውን የዝግመታዊ ለውጥ የመጨረሻ ደረጃ የተቆናጠጡት ባለ አእምሮ (እና ትልቅ) ራስ ቅላቸውን ከአካላቸው በላይ በኩራት ቀጥ አድርገው መቆም የሚችሉት የሰው ልጆች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ ነው የተሳለው፡፡ ሆሚናይዜሽን የክብር ውዳሴውን የሚያዥጎደጉድለት በርግጥም ድንቅ ለሆነው፤ ሆኖም ግን በአዝጋሚው ለውጥ ሂደት ውስጥ እምብዛም ላልተመላላሰው ሰው ብቻ ነው፡፡ እና ከላይ ያየነውን የተሳሳተ ስእል ወደ ጎን ገፋ እናድርግና ቀጣዩን እጅግ መሳጭ የትውልድ ትስስሮሽ ማሳያ የሆነውን ስእል በመመልከት፣ እውነተኛ ግንዛቤ ለመጨበጥ እንችላለን፤ ይላሉ፡፡
‹‹ብዙም ማራኪ ባይሆንም ግን የእውነት›› የሚባለው
ያለጥርጥር፤ የሰው ልጆች ራሳቸውን እንደ ልዩ እድለኛ ጦጣዎች ማየት የሚችሉበት በቂ ምክንያቶች አሏቸው፡፡ ነገር ግን  ዝንጀሮዎችና ጦጣዎችም...አእምሯቸውን ዘልቆ ማየት የሚችል ቢኖር፤ ምናልባት እነርሱም ስለ ራሳቸው ከዚህ ያነሰ አያስቡም ይሆናል፡፡ ዛሬ የምናያቸው ዝንጀሮዎች ሁሉም የዝግመተ ለውጥ ውጤት ናቸውና፡፡ በእናት ተፈጥሮ አይን ካየነው ደሞ፤ የትኛውም ፍጡር ከሌላው የበለጠ ወይም ያነሰ ኋላቀር ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ የለም። በዚህም መሰረት ማናቸውም፤ ሌላው ቀርቶ ከኛጋ የቅርብ ዝምድና ያላቸውም ቢሆኑ እንኳ፤ ከሉሲ ወይም ከሌሎቹ ምንጅላቶቻችን ጋር የሚመሳሰል አንዳችም ነገር የላቸውም፡፡ ማንም ቢሆን የጥንታዊያኑ ቤተሰቦች - የልጅ ልጅ ልጅ ልጅ ከመሆን ባለፈ ወንድማቸው ወይም የአክስት የአጎታቸው ልጅ መሆን አይቻለውም፡፡
ቅሪተ አካላቱ እነ ድንቅነሽ (ሉሲ) ያላቸው ሁለንተናዊ ባህርያት በሁሉም የ‹‹ቤተሰቡ›› አባላት (ወላ በቺፓንዚ፡ በሰው ወይም በጉሬላ) ላይ የሚገኙ ናቸው። እያንዳንዳቸውም ደግሞ የየራሳቸው ልዩ ባህርያት አሏቸው፡፡ ይህም የአያት ቅድማያት ምንጅላቶቻችን ማራኪ ውበት ነው፡፡
THE EVOLUTION OF EVOLUTION
የዝግመተ ለውጡ አዝጋሚ ለውጥ
የተፈጥሮና ፍጡራን በዝግመተ ለውጥ ውስጥ የማለፍ ሂደቱም በራሱ አዝጋሚ ለውጥ ያለው ነው፤ ይላሉ፡፡ የእግዚአብሔርን ፍጹምነት እንዴት መጠራጠር ይቻላል? ሲባሉም ከሂደቱ እየጠቀሱ የትየለሌ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡ ጥቂቶቹን እንይ...የጋሊሊዮን  መሬት በፀሐይ ዙሪያ እንደምትዞር ማረጋገጥና የኒውተንን የህዋ ስበት ህግ ተከትሎ፤ የጠፈርና ከዋክብቱ በስበት ህግ መመራት ጉዳይ የሳይንቲስቶቹን ትኩረት ሳበ፡፡ ፍጡራንም በዚሁ የስበት ህግ ተጽእኖ ስር ናቸው ተባለ፡፡ የሰማይና ምድር እና ሰራዊታቸው አፈጣጠርም በመጽሐፉ እንደሰፈረው የአንድ ሳምንት ገቢረ -ህላዌ ሳይሆን የሚሊዮንና ቢሊዮን ዘመናት ዝግመታዊ ለውጥ ሂደት ውጤት ነው እንጂ! አሉ፡፡ የላማክን (Jean Baptiste Lamarck) መላምት ያስደግፋሉ፤ ለምሳሌ ቀጭኔ ከረዣዥም የዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ቅጠል ለመበጠስ በተንጠራራች ቁጥር አንገቷ ረዘመ፤ በማለት ፍጡራን ከአካባቢያቸው ጋር ያላቸውን መስተጋብር በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ በተለይም ታላቅ ባለ አእምሮ ሰው (Most Dangerous Man) የተሰኘውና በዝግመተ ለውጥ ምርምር ዘርፍ ቀዳሚ ተጠሪ ምሁሩ ዳርዊን፣ ከስንዴም ሆነ ከውሻ አይነቶች የተሻሉ ዝርያዎችን በመፍጠር ላይ የተሰማሩ ተመራማሪዎች  ተግባር ቀልቡን ይስበው ነበር፡፡ በኋላም ‹‹ብዙ ወላዶቹ ጠቅመውናል፤ በረሀብና ጦርነት ጊዜ የሚገበሩ የሟቾችን ፍጆታ ስለሚያስገኙ፤ እንዲሁም ቤተሰባቸውን ለመቀለብና ለማስጠለል የተፈጥሮን ሀብት ለመቀራመት ፉክክር ስለሚያስነሱም፤ ለዝግመተ ለውጡ መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡›› የሚለውን ከእርሱ ቀደም ብሎ በማልፈስ (Thomas Malthus) በህዝብ ቁጥር ዙሪያ የቀረበውን ጥናታዊ ጽሁፍ አነበበ፡፡ እሱ በተራው ያቀረበው ‹‹ከፍጡራኑ መካከል ከወደረኞቻቸው ልቀው የተገኙቱ ‘’more fit’’ ናቸው በአሸናፊነት መዝለቅ የቻሉት/የሚችሉት “Survival of the fittest›› የሚለው እሳቤው በስፋት ናኘ፡፡ ሆኖም ግን አያቱም የዝግመታዊ ለውጥ አቀንቃኝ የነበሩት ዳርዊን፤ በ1859 ባቀረበው በዚህ ጥናታዊ ጽሑፉ On the Origin of Species ውስጥ አሁን ያሉት ፍጥረታት በረዥም ዘመናት ሂደት እየተዋለዱና እየተለወጡ፣ ከሌሎች የተሻሉቱ እዚህ መድረስ ቻሉ፤ አለ እንጂ፤ በቀጥታ፤ ሰው የጦጣ ወይም የዝንጀሮ የልጅ ልጅ ልጅ ነው አላለም። ተከታዮቹ ግን፤ ‹‹በቃ ሰው የተገኘው ከጦጣ ነው!›› ለማለት አፍታም አልፈጀባቸው፡፡
ዝግመታዊ ለውጥን በስነ ልቦናዊ ግንዛቤው ያጎለበተው ደግሞ እውቁ የሥነ አእምሮ ጠይቡ ፍሮይድ ነው፡፡ የሰው ልጅ የአእምሮ ህመም በሚገጥመው ጊዜ የሚስተዋሉበት ከሰብአዊነት ደረጃ የዘቀጡ ሁናቴዎች የእንስሳ/አውሬያዊ ቅድመ ማንነታችን ‘’Savage’’ state ነጸብራቅ ናቸው፡፡ እንዲሁም ሁለት እጅግ ፍጹም የተለያዩ (ቅዱስና እርኩስ፤ ርህራሄና ጭካኔ ...ወዘተ) ባህርያት ባሉት የሰው ልጅ ውስጥ የሚኖሩት የተራራቁ ሰብእናዎችም  ‘’Spilit’’ personality እንዲሁ፤ ይላል ፍሮይድ፡፡ ለዚህ ገና በቅጡ ላልተፍታታና ጭጋግ ያጠላበት ሀሳብ አጋዥ ምሳሌ ሆኖ በምሁራኑ የቀረበው በስቲቨንሰን (Robert Louis Stevenson) የተጻፈው The Strange Case  of Dr. Jekyll and Mr, Hyde ረዥም ልቦለድ ውስጥ በመሪ ገጸ ባህሪነት የተሳለውና  አንድ ጊዜ ደግ ሀኪም፣ ወዲያውም ወደ ግድንግድ ነፍሰ ገዳይ ጦጣነት የሚቀያየረው ሰው ነው፡፡ (በጋሽ ስብሀት ወጎች መሀል አጋጥሞን ይሆናል፤ወይም ራሱ መጽሐፉ፡፡)
THE MISSING LINK - የተበጠሰው  ቋጠሮ
ድንቅነሽ (ሉሲ) ከዛሬ 42 አመታት በፊት እ.አ.አ 1974 ልክ በያዝነው ወርኃ ህዳር ፣ ሀዳር ሸለቆ ውስጥ - በአፋር - ኢትዮጵያ ተገኘች መባሉን ተከትሎ፤ ባለቤቷ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ፤ አንዲት ወይዘሮ፤ ‹‹የሰው ልጅ ከጦጣ መሰል እንስሳ የተገኘ ነው፡፡›› የሚለውን ዜና በሰማች ጊዜ፤ በድንጋጤ ክው! ብላ፤ ‹‹ኦ! አምላክ ሆይ! እውነት አይሁን!!! ሆኖ ቢሆን እንኳ ወሬው እንዳይናፈስ ተግተን እንጸልይ!›› ብላ ነበር፡፡ በእርግጥ አሁንም ቢሆን ስለዚህ ሀቲት እውነተኛነት ማንም አፉን ሞልቶ መናገር እሚችልበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም፡፡ ስለዬህ፤ የሰው ልጅ ከጦጣ መሰል ዘር መምጣቱ ቢረጋገጥ፤ እንዲህ ባለው ደረጃ መላ ምቶቹን ለማንሸራሸር በትህትና እንደደፈርነው ሁሉ፤ ምርምሩ በአመርቂ ማስረጃ ተደግፎ ብናገኘው፤ በነጻነት ‹‹እኛኮ የተገኘነው ከጦጣ ነው›› ከማለት የማንገደበውን ያህል፤ ያም ሆኖ ግን አሁን ምንም የተጨበጠ ነገር አለመኖሩንና የሳይንስ ምሁራኑ ‹‹የሰውን ዘር ከጥንታዊ ማንነቱ የሚያስተሳስረው ሰንሰለት›› የሚሉት ጉዳይ  ዛሬም ድረስ ጥርት ያለ ሀቁ ከራሳቸው ከተመራማሪዎቹም ቋጠሮ ውሉ የተሰወረ  መሆኑን እናስተውልም ዘንድ ነው፡፡ ፍለጋው ቀጥሏል፡፡ THE MISSING LINK - IT’S STILL MISSING!  

Read 3391 times