Monday, 05 December 2016 08:57

“…እናያለን ሁሉን ሲወጣ ሲወርድ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(17 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል……እዚች ከተማ ውስጥ ያለ ጮሌነት እንዴት ‘መልኩን እየለዋወጠ እንደሚመጣ የሚገርም ነው፡፡ እና… ‘ያላወቀ ማለቁ’ ነው፡፡
በቀደም ይሄ ትርፍ ሳይጭን ሦስት፣ ሦስት ሰው የሚደረድረው ታክሲ መጨረሻ ወንበር ላይ ነበርኩ። “ኋላ ጠጋ በሉ…” ተብሎ አንዲት ‘የዘመናችን ሰው’ የምትመስል ልጅ አጠገብ ተቀመጥኩ፡፡ ለጥቂት ሴኮንዶች ሰላም ነበር፡፡ ድንገትም ደህና ትመስል የነበረችው ሴት ድንገት መወራጨት አይነት ነገር ጀመረች፡ አንዴ ወዲህ፣ አንዴ ወዲያ እጥፍ ዘርጋ እያለች እንደማቃሰትም ሞካከራት፡፡፡ ኮሚኩ ነገር በፊት ቁልጭ ብላ እንኳን የሚያወራጭ የጤና ችግር የገጠማት ቀርቶ አቅመ ቢስ ጉንዳንም የቆነጠጠቻት አትመስልም ነበር፡፡
ከዚያም ድክም ያለች ሞባይል አውጥታ ወደ እኔ ዘረጋችና “ደውልልኝ…” አለችኝ፡፡ እኔም ለመንግሥተ ሰማያት በር ብቃት ማረጋገጫ እንዲያግዘኝ ተቀብዬ…
“ማን የሚለውን ልደውል…?” አልኩ፡፡ መልስ አልሰጠችኝም፡፡ ደግሜ “ማን የሚለውን እንድደውል ነው የምትፈልጊው…?” አልኳት፡፡
“አንዱን ቁጥር…” አለች፡፡
እኔም ስልኩን እየከፈትኩ “ምን ልበላቸው…?” ስላት መልስ እንደመስጠት ትከሻዬ ላይ ደገፍ አለች። (ትከሻ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈበት የሚመስላችሁ ወዳጆቼ አንዳንዴ እኮ እንዲህ በዋልድባም ይዘፈናል!) ከዛም እጆቿ ከክልላቸው አልፈው መዘረጋጋት ጀመሩ፡፡ ይሄኔ አንድ ሁለት ነርቮች የማስጠንቀቂያ መልእክት አስተላለፉ፡፡ ብዙ የታክሲ ላይ… ጉድ እንሰማ የለ!
ገፋ አድርጌ ትከሻዬን ከራሷ ነጻ አወጣሁና ስልኳን እጇ ላይ አስቀመጥኩላት፡፡ በሚያስደንቅ ፍጥነት መወራጨቷ ቆመ! (ትከሻው ይሆን እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…)
ከዛላችሁ…ጥግ የነበሩ ሁለት ሴቶች ሲወርዱ እኔ ወደ ጥግ አፈገፈግሁ፡፡ (አንዳንዴ ጥግ መያዝን የመሰለ ነገር የለም!)
አዲስ ተሳፋሪ፣ ልጅቷ አጠገብ ተቀመጠች። ወዲያውኑ መወራጨቷን ጀመረች፡ ጊዜ ሳታጠፋ ልጅቷ ትከሻ ላይ ዘፍ ብላ ስልኳን አውጥታ ሰጠቻት። ልክ እኔን እንዳለችኝ… “አንዱ ጋ ደውይልኝ…” ትላታለች፡፡ ልጅትም የሆነ ስልክ ደውላ…
“ማን ልበላቸው?” ስትላት… መጀመሪያ “ቅድስት” አለችና ወዲያውኑ ደግሞ “ትእግስት” አለች፡፡ ልጀቱም ደውላ አናገረችና ትዕግስት የሚባል ሰው አናውቅም ይላሉ አለቻት፡፡ ይሄኔ “ሌላ ቦታ ደውይ…” ብላ እጆቿን እንደማቀፍ ስታደርጋቸው፣ የልጅቷ ማስጠንቀቂያ ደወሎች ደወሉ መሰለኝ … ገፍትራት ስልኳን ወረወረችላት። መወራጨቱም ቆመ፡፡
ፒያሳ ደርሰን ስንወርድ በሽተኛዋ አካሄዷን ስታዩ ለፋሺን ትርኢት የምትለማመድ ነበር የምትመስለው፡፡ በኋላ እንደሰማሁት ዘዴው ምን መሰላችሁ… እንግዲህ ልጅቷ ‘ታማለች’ አይደል… ራሷን ትከሻ ላይ ብታስደግፍ፣ እጇቿን እያወራጨች ወደ ደረትና ወደ ቦርሳ አካባቢ ብትሰድ ማንም፣ ምንም ነገር ይፈጠራል ብሎ አይጠረጥርም፡፡ በሽተኛ መወራጨቱ አይቀርማ!  በጣም የታመመ በሽተኛ በጣም ሊወራጭ ይችላላ! “ደውልልኝ…” መባሉ ደግሞ የዛን ሰው ሀሳብ ለመስረቅ ነው፡፡ ይሄኔ የበሽተኛዋ እጆች ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡
የምር የሚያሳዝነው ነገር በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሁሉንም እየተጠራጠርን የእውነት ህመም የገጠመውን ሰው መርዳት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አንድ ወዳጄ ይህን ሳጫውተው ሴቶች ጮሌዎች ታክሲ ላይ የሚሠሩትን ገና ምን አይተህ ነው ብሎኛል፡፡
እናላችሁ…ጮሌነት በጣም በዛ፡፡ ነገርዬው ሁሉ…
“ቤታችን ተሠርቶ በመንታ መንገድ
እናያለን ሁሉን ሲወጣ ሲወርድ”
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን ትዝ ብሎኝ ነው… እነኚህ ዛራና ቻንድራ የሚሏቸው ሰዎች… እንደው ዘላለም ዓለማቸውን ነገራቸው “አጠቃቀስኩ…” አይነት ጠጋ ብሎ መለስ ሆኖ ሊቀር ነው! ልክ ነዋ! መቶ ምናምን ክፍል ድረስ ገና ብሔረ ጽጌ ጭር ወዳለበት ቦታ እንኳን አይሄዱም! እኔ የምለው በቀደም “ልጅ…” ምናምን ሲሉ የነበሩት… ሞቅ ያለ የዘመድ ሰላምታ እንኳን የሚያክል ነገር ሳናይ ልጅ የሚሉት ነገር ከየት የመጣ ነው! ኮሚክ እኮ ነው… ‘ልጅ’ በሪሞት ኮንትሮል ይመጣ ጀመር እንዴ!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የሆሊዉድ አይነት የእሷ የእሱ ‘የቀለጠው መንደር’ እኛ ፊልሞች ላይ ቢጀመር… ምን አለፋችሁ… አይደለም መቶ ሰባ ምናምን ክፍል ሊደርስ፣ ፊልሙ ጀምሮ የተሳታፊዎቹ ስም ተጽፎ ሳያልቅ አገር ይቀወጥ ነበር፡፡ እንዲህ ነና!  ፈጣኖች ነና!  ሁሉንም ነገር ደረጃ በደረጃ ሳይሆን እስከ ጥግ ድረስ መሄድ እንወዳለና! እናላችሁ… ምን ይመስለኛል…ነገርዬው እኛ ፊልሞች ላይ ቢጀመር ቤቢ ፓውደር ምናምን የሚሸጥባቸው ቦታዎች የሚታዩ ታዋቂ ሰዎች ቁጥር ‘ጣራ የሚነካ’ ይመስለኛል፡፡
ስሙኝማ…አሁን፣ አሁን ዘጠኝ ቁጥር ማቆሚያ ሳያስገትሩ፣ ልዑል መኮንን በር ላይ በጸሀይ ሳያንቃቁ ምናምን-----በራስ ተነሳሽነት የሚመጡ እንትናዬዎች በዝተዋል ነው የሚባለው፡፡ እኛ ደግሞ፣ አይደለም ፈገግ ተብሎልን አንዷ ከሦስት ሴከንድ በላይ ዓይኗን ጣል ካደረገችብን እጅ ለመስጠት ፈቃደኞች ነን፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንዲህ ነገርዬው ሁሉ መንገዱ ጨርቅ ምናምን በሆነበት፣ አንዳንዱ ሰው ልቡን የወሰደችውን በእጁ ለማስገባት የሚያወጣው ወጪ መለስተኛ ማተሚያ ቤት ሊከፍት ምንም አይቀረውም ነው የሚባለው፡፡
ስሙኝማ…ሰውየው ከሚስቱ ጋር ሀኪም ቤት ይሄዳል፡፡ ሚስቱ ውጪ እንድትጠብቀው አድርጎ ሀኪሙ ዘንድ ይገባል፡፡ ሀኪሙም ምርመራ ካደረገለት በኋላ…
ጤንነትህንና ደስታህን የወሰደብህ አንድ ክፉ ነገር ገጥሞሃል ይለዋል፡፡ ይሄኔ ሰውየው ምን ቢያደርግ ጥሩ  ነው… አፉን እየተመተመ…
“ኸረ ዶክተር ቀስ ብለህ ተናገር፣ ደጅ ነች ትሰማሀለች!” አለውና አረፈው፡፡ የምር ግን….እኛ አገር ጥናት ቢካሄድ…“…ደጅ ነች፣ ትሰማሀለች!” “…ደጅ ነው፣ ይሰማሀል!” የሚሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው። ለዚህ ነው ‘ሰማንያ ቀደዳ’ የበዛው!
“ቤታችን ተሠርቶ በመንታ መንገድ
እናያለን ሁሉን ሲወጣ ሲወርድ”
እናላችሁ…ዘንድሮ አስቸጋሪ ሆኗል…ማጭበርበሩ፣ ማታለሉ…ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ሆኗል፡፡ ምን አለፋችሁ… የሆነ ነገር ‘በጨረር’ ምናምን የለቀቁብን ነው የሚመስለው፡፡
እናማ…እንደ በፊቱ የአንድን ሰው አነጋገርን፡ ፈገግታን፣ አቀራረብን አይቶ…
“እሱ ታማኝ ሰው ነው፡፡”
“እሷ እኮ ፈጣሪን የምትፈራ ነች፡”
“አይደለም በገንዘብህ፣ በነፍስህም የምታምናቸው ሰው ናቸው…”
ምናምን ብሎ ነገር ታሪክ ሆኗል፡፡
ደግሞላችሁ… ዘንድሮ ጮሌነት የዕድሜ ክልል እንኳን የለውም፡፡ እንደውም…የ‘ባለ ሁለት ጸጉር’ ጮሌ ብዛት የሚገርም ሆኗል፡፡ የታክሲ ጮሌ ያለውን ያህል የቢሮም ጮሌ በዝቶላችኋል፡፡ ዋናው ነገር ትከሻ ላይ ደገፍ የሚል ራስ ሲመጣ ነቃ ማለት ነው፡፡ የምር…የሆነ ነገር ‘በጨረር’ ሳይለቁብን አልቀረም፡፡
እናማ… ታክሲ ላይም ሆነ ሌላ ቦታ… ትከሻ ላይ ሌላ ራስ ሲያርፍ ነቃ ማለት አሪፍ ነው፡፡
“ቤታችን ተሠርቶ በመንታ መንገድ
እናያለን ሁሉን ሲወጣ ሲወርድ”
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4948 times