Monday, 05 December 2016 08:54

የዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰር አነጋጋሪ ሆኗል

Written by 
Rate this item
(15 votes)

 · “በመናገር ነፃነት ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው” አምነስቲ
        · “የታሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣሳቸው ነው” መንግስት
               
     የአንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰር የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ትኩረት የሳበ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የታዋቂው ፖለቲከኛ እስር  በእጅጉ ያሳስበኛል ብሏል፡፡ ዶ/ር መረራ አመራር አባል የሆኑበት መድረክ በበኩሉ፤ ጠንካራ መሪውን በእስር ማጣቱ የአመራር ክፍተት እንደሚፈጥርበት ጠቁሟል። ከ20 ዓመታት በላይ በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት የዘለቁት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር መረራ፤ የታሰሩት “ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት መፍጠር ክልክል ነው” የሚለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንቀፅ በመተላለፋቸው ነው ብሏል - መንግስት፡፡ የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በሰጡት አስተያየት፤ ዶ/ር መረራ በመድረክ ውስጥ የድርጅት ጉዳይን በኃላፊነት ይከታተሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ መታሰራቸው በድርጅቱ ስራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና የአመራር ክፍተት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
“ዶ/ር መረራ በሌለበት የተሟላ ድርጅታዊ ስራ ልንሰራ አንችልም” ያሉት ፕ/ር በየነ መድረክ በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርጎ በቅርቡ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጣ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እስካሁን ድረስ ወጥ አቋም ያለው ፖለቲከኛ አልገጠመኝም፤ ብዙዎቹ ተለዋዋጭ አቋም ነው ያላቸው›› ያሉት ፕ/ር፤ “መረራ ግን ወጥ አቋም በመያዝ ጠንካራ የፖለቲካ ፅናት ያለው መሪ ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኤፌኮ) ሊቀመንበር፤ እንዲሁም የመድረክ ምክትል ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው ዶ/ር መረራ፤ መታሰራቸው በእጅጉ ያሳስበኛል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ‹‹እስሩ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገር መብት ላይ የተቃጣ እርምጃ ነው” ሲል ኮንኗል፡፡
በኢትዮጵያ ይፈፀማል ስለሚባለው የሰብአዊ መብት በቤልጂየም ብራሰልስ ተገኝተው ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ እማኝነታቸውን እንዲሰጡ የፓርላማው አባል በሆኑት እና ጎሜዝ እንደተጋበዙ የተነገረላቸው ዶ/ር መረራ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ አውሮፓ አምርተው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ማብራሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ከብራሰልስ ወደ አገራቸው የተመለሱ መረራ፤ የዚያኑ ዕለት ምሽት 2 ሰዓት ገደማ አሸዋ ሜዳ በሚባለው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦፌኮ አመራሮች ተናግረዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር ይኖሩ የነበሩ ሁለት ወጣቶችም መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ዶ/ር መረራ በተጋበዙበት በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ  በ“አሸባሪነት” የተፈረጀው የ“ግንቦት 7” መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና  በየሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር አትሌት ፈይሳ ሌሊሳም ተጋብዘው ነበር ተብሏል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀፅ 1 ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ክልከላ ጥሰው ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በማድረጋቸው መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትን ጠቅሶ ኢቢሲ ከትላንት በስቲያ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ዶ/ር መረራ፤ በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምስክርነታቸው እንደሰጡ ጋብዘዋቸዋል የተባሉት አና ጎሜዝ በበኩላቸው፤ የፖለቲከኛው መታሰር ቢያስደነግጠኝም አላስገረመኝም ብለዋል፡፡ መረራ መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን ከትላንት በስቲያ ለቪኦኤ የተናገሩት ጎሜዝ፤ እስካሁን ህብረቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የመለሳለስ አካሄድ ሲከተል መቆየቱን ጠቅሰው ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለህብረቱ ኮሚሽን መፃፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የህብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ መሰረት ያለው መሆኑን ገልፆ ግንኙነቱ ይሻክራል የሚል ስጋት እንደሌለው ጠቁሟል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤
‹‹ዶ/ር መረራ ጉዲና ለእስር የተዳረጉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በመገኘታቸው ህግ ለማስከበር ሲባል ነው›› ብለዋል፡፡
በደርግ አገዛዝ ሥርዓቱን በመቃወማቸው መንግስት 8 ዓመታት ያሰራቸው ዶ/ር መረራ፤ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን ሲታሰሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው ተብሏል፡፡  

Read 7332 times