Saturday, 10 March 2012 12:05

ፑቲን የሩስያ ፕሬዚዳንትነት ከፓርቲ ነፃ እንደሚሆን ቃል ገቡ

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው እሁድ በዓለማችን ትልቋ ሀገር ሩስያ ተካሂዶ በነበረው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ቭላድሚር ፑቲን፤ ከትናንት ወዲያ ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጋር ሲነጋገሩ ፓርቲ አልባ መሪ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፑቲን በመጪው ሚያዝያ 29 የፕሬዚዳንትነት መንበሩን ከ”ተሰናባቹ” ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ይረከባሉ፡ ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬዚዳንት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ለተሰናባቹ ፕሬዚዳንትም “ፕሬዚዳንት ለፓርቲ ያልወገነ መሆኑን ዛሬ ላይ ማስታወስ ያሻል፡፡” ብለዋቸዋል፡፡

ከሶቭየት ኅብረት የተረፈችውን ሩስያ፣ ከሚካኤል ጎርባቾቭ የተረከቡት ሟቹ ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ካደረጓቸው ወዲህ በመንበረ ሥልጣኑ ላይ የቆዩት ፑቲን፣ የእሁዱን ምርጫ ሲያሸንፉ ከሠርቶ አደሩ ያገኙት ድምፅ ከሌኒን ጊዜ ወዲህ በሩስያ ታይቶ የማይታወቅ በጣም ከፍተኛ ተብሎላቸዋል፡፡

የቤተሰባቸው ብቸኛ ልጅ የነበሩት የስለላ ድርጅቱ ኬ.ጂ.ቢ. የቀድሞ መኮንን ፑቲን፤ የሩስያ ፖለቲካ እምብርት ወደ ሆነው ክሬምሊን ቤተመንግስት እግራቸውን ያስገቡት የአባታቸውን ሥራ በመሸፈን እና በመተካት ነው፡፡ ተቃዋሚዎቻቸውን ቀስ በቀስ “እየቀነሱ” የመጡት ፑቲን ለሥልጣኔ ያሰጉኛል ያሉዋቸውን ሁሉ ገለል እያደረጉ ከዚህ ደርሰዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በተቀናበረ ሴራ ሳይሆን አይቀርም በተባለ የሂሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው አሌክሳንደር ሌቤድ እና በእስር የሚገኙት የነዳጅ ባለፀጋው ሚካኤል ኮዶኮቭስኪ ይገኙበታል፡፡ ሌላውን ተቃዋሚአቸውን ባለፀጋውንና በእሁዱ ምርጫ ሦስተኛ በመውጣት ግርምት የፈጠሩትን ለውጥ አራማጅ ተቀናቃኝ ሚካኤል ፕሮካኖቭን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸውን እንደገና ሲጀምሩ ሚኒስትር በማድረግ “ዝም ለማሰኘት” አስበዋል መባሉ መነጋገሪያ አድርጓቸዋል፡፡

የሩስያ መሪ በፓርቲ መታቀፍ አያስፈልገውም የሚሉት ፑቲን ይህን ይበሉ እንጂ የገዢው የተባበረች ሩስያ ፓርቲ ሊቀመንበር እንደሆኑም ይታወቃል፡፡ እሳቸው ግን “የየትኛውም ፓርቲ አባል ብሆን የመላ ሩስያውያንን ፍላጎት ላይ ተንተርሼ እሰራለሁ” ብለዋል፡፡

ፑቲን መጠንም ተቃውሞ እየተበራከተባቸው ነው፡ ዛሬ 50ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በሳቸው ላይ ተጠርቷል፡፡

ይህ ደግሞ በተጫረችው ክብሪት ቤንዚን በማርከፍከፍ መንበሩን ለመረከብ ለሚቋምጡትና በዘንድሮው ምርጫ ሁለተኛ ለወጡት የሩስያ ኮሙኒስት ፓርቲ ሊቀመንበር ጌናዲ ዡጋኖቭ መልካም አጋጣሚ ነው ተብሏል፡፡

የዛሬውን የተቃውሞ እሳት የሰላይነት እውቀታቸውን በመጠቀም ወደ ሳይቤርያ በረዶ ይቀይሩት ይሆን ወይስ እንደ አራቱ የአረብ ሀገራት መሪዎች “አሁንስ አበዙት … በቃን!” በሚሉ የፌስቡክ ሰልፈኞችና ተቃዋሚዎች፣ ሥልጣን ይለቁ ይሆን?

 

 

Read 3217 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 12:09