Monday, 05 December 2016 08:48

በልደታ ኮንደሚኒየም “ጭፈራ ቤቶች” ነዋሪዎች ተማርረዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

 ‹‹አካባቢው ወደፊት የዝሙትና የረብሻ መናኸሪያ እንዳይሆን እንሰጋለን›› - ነዋሪዎች
                       
    በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 8፣ ልደታ ኮንዶሚኒየም ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች፤ በየመኖሪያ ህንፃቸው ስር በተከፈቱ መጠጥ ቤቶዎችና ጭፈራ ቤቶች ሁካታ ሳቢያ ሰላም ማጣታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ። “አካባቢው ወደፊት የዝሙት፣ የዳንኪራና የሴተኛ አዳሪነት መናኸሪያ እንዳይሆን እንሰጋለን” ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡
እስከ ሌሊቱ ስምንትና ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ከጭፈራ ቤቶቹ የሚወጣው ሁካታ፤ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎችን በተለይ ህፃናት ልጆቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚረብሽ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በኮንዶሚኒየሙ የተለያዩ ብሎኮች ሥር የተከፈቱ “ጭፈራ ቤቶች” ሰላማዊ ህይወትን ከማናጋታቸው በተጨማሪ ለህፃናት ልጆች አስተዳደግ ፈተና እየሆኑ መሄዳቸውንም ነዋሪዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
የስድስት ልጆች እናት መሆናቸውን የተናገሩት አንዲት የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪ፤ በዚህ ሁኔታ ልጆቻቸውን በጥሩ ስነ-ምግባር አንፀው ለማሳደግ እንደማይችሉ ጠቁመው፤ ወደፊት ነዋሪው በምሬት እየለቀቀ ፎቆቹ ወደ አልቤርጎነት መቀየራቸው አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አዛውንት ሲናገሩ፤ “ቀን በአድካሚ ስራ ላይ ውዬ ምሽቱን ለማረፍ ወደ ቤት ስመለስ ሌላ ድካም ይጠብቀኛል፤ የሙዚቃው ጩኸት፣ ጭፈራና ዳንኪራው ሰላሜን ይነፍገኛል” ይላሉ፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ሥፍራው ከመኖሪያ ቦታነት ይልቅ የቀለጠ መንደር ይሆናል ብለዋል፡፡
በመሸታና ጭፈራ ቤቶቹ ክፉኛ መረበሻቸውን የገለፁት የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች፤ ጉዳዩን ለወረዳ 8 ሥራ አስፈፃሚና ለክ/ከተማው ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ማመልከታቸውንና ኃላፊዎቹ መጥተው ማስጠንቀቂያ ሲሰጧቸው፣ ለአንድ ሁለት ቀናት ሁኔታው ተስተካክሎ ወዲያው ወደነበረበት እንደሚመለስ በምሬት ተናግረዋል፡፡
የልደታ ክ/ከተማ አካባቢ ጥበቃ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ገ/ማሪያም ወ/አረጋይ ችግሩ መኖሩን እንደሚያውቁ ገልፀው፣ በአካባቢው ከፍተኛ የድምፅ መጠን ከሚጠቀሙ ሰባት ድርጅቶች መካከል በሶስቱ ላይ ‹‹ዴሲቤል›› በተሰኘው የድምፅ መለኪያ መሳሪያ ድምፁ ተለክቶ ከተገቢው በላይ መሆኑ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አንዱ ድርጅት እንዲዘጋ ከወሰንን በኋላ “ከጥፋቴ እማራለሁ፤ አስተካክላለሁ” ብሎ ይቅርታ ስለጠየቀ ምህረት ተደርጎለት ነበር ብለዋል፡፡  በቀሩት ድርጅቶች ላይ ልኬቱን አካሂደን እርምጃ እንወስዳለን ያሉት ኃላፊው፤ የድምፅ ብክለት ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ እሴትን የሚፈታተኑ አስነዋሪ ድርጊቶች እንደሚካሄዱ መስማታቸውንም ገልፀዋል፡፡ “ከወረዳው ስራ አስፈፃሚና ከንግድ ፅ/ቤት ጋር በመመካከር ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድና በማህበረሰቡ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት በዝግጅት ላይ ነን” ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
ብዙ ነዋሪዎች ባሉበትና ለመኖሪያነት በተከለሉ ቦታዎች ላይ ለጭፈራ ቤቶች የንግድ ፈቃድ መስጠት አግባብ ነው ወይ? ተብለው የተጠየቁት የወረዳው የንግድ ጽ/ቤት፤ መጀመሪያ ፈቃድ ሲጠይቁ ለካፌ፣ ለምግብ ቤት፤ ለግሮሰሪና ለመሳሰሉት እያሉ ስለሚወስዱ ነው እንጂ ለጭፈራ ቤት ፈቃድ አይሰጥም ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ቀን ቀን በምግብ ቤትነትና በካፌነት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው፣ ማታ ወደ ጭፈራ ቤትነት የሚቀይሩበት አሰራር እንዳለ ጠቁመው፣ በዚህ መልኩ ሲሰራ በነበረ አንድ ድርጅት ላይ የወረዳው ስራ አስፈፃሚ እርምጃ ወስዶበታል ብለዋል፡፡

Read 5717 times