Monday, 05 December 2016 08:47

“በፊደል ካስትሮ “ቴርሞሜትር” ከኢትዮጵያ እስከ ካናዳ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(9 votes)

 ካስትሮን ያደነቀ ሰው፣ “የአንድ ፓርቲ አገዛዝን እቃወማለሁ” ቢል …. ውሸት!
              
     ብታምኑም ባታምኑም፣ በአለማቀፍ ደረጃ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት “የሰብአዊ መብት ተቋማት” መካከል፣ አንጋፋው አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣... ፊደል ካስትሮን ያደንቃቸዋል። አምንስቲ ምን ቢናገር ጥሩ ነው? ጥሩ አልተናገረም፡፡ “ካስትሮ፣ የኩባዊያንን ሰብአዊ መብት አሻሽለዋል” በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡
አምንስቲ፣ “የመብት” ብሎ የዘረዘራቸው ነገሮች፣ … ነፃ ህክምናና፣ ነፃ ትምህርት ናቸው። የዜጎችን ንብረት በሙሉ የወረሰ ሶሻሊስት መንግስት፣ ትምህርትና ህክምና በነፃ እያቀረበ ህዝቡን አንበሻበሸው? ፋርማሲዎቹ ግን ኦና ናቸው። በ50 ዶላር ደሞዝ፣ የድህነት ኑሮ የሰለቻቸው የህክምና ዶክተሮችም አገር ጥለው ለመሰደድ ይጣጣራሉ፡፡ ሌላው ይቅርና፣ ወደ ድሃዋ ኢትዮጵያ መጥተው ለመስራት የሚመኙ ብዙ ናቸው፡፡ እና አምንስቲ ይህንን ያደንቃል? አሳዛኝ ነው፡፡ አንጋፋ የሰብአዊ መብት ተቋም፤ እንዲህ አይነት መግለጫ የሚያወጣበት አሳዛኝና አስቂኝ ዘመን ላይ ደርሰናል።
እንግዲህ አስቡት፡፡ ኩባ ከ60 ዓመት በፊት፣ ከብዙዎቹ የዓለማችን አገራት የተሻለች … በኢኮኖሚ ከደቡብ ኮሪያና ከታይዋን በእጥፍ የምትሻል፣ በትምህርትና በጤና ከነ ጣልያንና ከስፔን በእጅጉ የምትበልጥ አገር ነበረች፡፡ ያኔ፣ … በደቡብ ኮሪያ፣ ከ1000 ህፃናት መካከል 130 ያህሉ የአምስት ዓመት እድሜ ላይ ሳይደርሱ ይሞቱ ነበር፡፡ በኩባ ግን፣ የሟች ህፃናት ቁጥር 50 ገደማ ብቻ ነበር፡፡ ያኔ፣ … ከካስትሮ በፊት፣ ኩባ በጤናና በትምህርት ቀዳሚ ተብለው ከሚጠቀሱ አገራት መካከል አንዷ ነበረች።
እንዲህ በአብዛኞቹ መስኮች ደህና የነበረች አገር ላይ ነው፣ የሶሻሊስቱ የፊደል ካስትሮ አብዮት የወረደባት፡፡ ከዚያማ፣ አገሪቱ ቁልቁል ወረደች። የአገሪቱ ኢኮኖሚ በመንግስት እጅ ውስጥ ገብቶ ተንኮታኮተ፡፡ እነ ኮሪያና እነ ታይዋን በካፒታዝም አቅጣጫ እጥፍ ድርብ እየበለፀጉና የፖለቲካ ነፃነትን እያስፋፉ ሲገሰግሱ፣ ኩባ ወደ ገደል!
“የግል ስራ” ብሎ ነገር ለአመታት የተከለከለባት፣ ሩብ ያህሉ ህዝብ በስደት የሸሻት፣ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ በአዋጅ የነገሰባት፣ ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ወንጀል የሆነባት፣ ምርጫና ዲሞክራሲ የተንቋሸሹባት አገር ናት - ኩባ። ይሄው ነው የኩባ የሶሻሊዝም ታሪክ፡፡
የዚህ ታሪክ መስራችና መሪ ደግሞ፣ ፊደል ካስትሮ ናቸው።
አሁን ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ካስትሮንና ለ50 ዓመታት ኩባን ያንኮራኮተ የሶሻሊዝም ታሪክን እናደንቃለን? የምናደንቅ ከሆነ፣ … የፖለቲካ ነፃነትና የብልፅግና አድናቂ ልንሆን አንችልም፡፡ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ብንልም፣ የውሸት ይሆንብናል።
ታዲያ፣ ዛሬ ካስትሮን ሲያደንቅ የሰማነው የሰብአዊ መብት ተቋም፣ ነገ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ፣ ስለ ፖለቲካ ነፃነትና ስለ ዲሞክራሲ እልፍ አእላፍ መግለጫ ቢያሰራጭ፣ ከምር ነገሬ ብለን ለመስማት እንደፍራለን? መግለጫው ሁሉ፣ የውሸት የውሸት አይሆንብንም? ይሄ ብቻ አይደለም፡፡
ከሳምንት በፊት የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት፣… “ሰብአዊ መብት፣ የፖለቲካ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲ ስርዓት... እንዲሻሻል እንፈልጋለን…” ማለታቸው ተዘግቧል። በእርግጥ፣ እንደ ቀድሞው፣ ስለ ፖለቲካ ነፃነትና ስለ ግለሰብ መብት ጠንከር ያለ ነገር አልተናገሩም። ይሁን ግድ የለም፡፡ በለዘብታም ቢሆን ተናግረዋል።
ግን ምን ዋጋ አለው? የካናዳው ጠ/ሚኒስትር፣ ቀንደኛ የፊደል ካስትሮ አድናቂ መሆናቸውን ሰሞን በይፋ ገልፀዋል። የካናዳው ጠ/ሚኒስትር ካስትሮን ባደነቁበት አንደበት፣ … ዞር ብለው ደግሞ፣ ስለ ግለሰብ መብትና ስለ ፖለቲካ ነፃነት ቢያወሩ፣ ከባዶ አየር የበለጠ ክብደት ይኖረዋል?
በፊደል ካስትሮ ዘመን፣ ኩባ በትምህርትና በጤና መስኮች ወደፊት ገስግሳለች በማለት የተናገሩት ደግሞ፣ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ባንኪ ሙን ናቸው። የካስትሮ አብዮታዊ ሃሳቦች የሁሉንም ሰው ትኩረት የሚስቡ እንደሆኑ ባንኪሙን ጠቅሰው፣ ካስትሮ “ለማህበራዊ ፍትህ ድምፃቸውን ያስተጋቡ መሪ ናቸው” በማለት አድንቀዋቸዋል። “ማህበራዊ ፍትህ” የሚለው ፈሊጥ፣ አንዳች ጥልቅ ትርጉም የያዘ እንዳይመስላችሁ፡፡ “ሰዎችን በሀብት ወይም በድህነት እኩል የማድረግ አላማን” ነው ማህበራዊ ፍትህ የሚሉት፡፡ ጎበዙና ሰነፉ፣ ታታሪውና ልግመኛው፣ ቆጣቢውና አባካኙ፣ እኩል አይነት ኑሮ እንዲኖራቸው መመኘትን፣ … እንደ ቅዱስ ነገር ይቆጥሩታል፡፡
በሌላ  አነጋገር፣ ከታታሪው፣ ከቆጣቢውና ከአምራቹ ሰውዬ፣ ሀብትና ንብረት እየነጠቁ፣ በታክስ ጫና ኪሱን እያራቆቱ ወይም በአዋጅ ንብረቱን እየወረሱ፣… ለአዳሜ እኩል የማከፋፈል ህልም ነው፣ ማህበራዊ ፍትህ፡፡ ወይም ደግሞ ሁሉንም ሰው የመንግስት ባሪያና የመንግስት ተደጓሚ እንዲሆን የማድረግ ዓላማ ነው፣ ማህበራዊ ፍትህ ማለት፡፡ ታታሪና አምራች ሰዎች፣ የመንግስት አገልጋይ ባሪያ ይሆናሉ፡፡ የስራ ፍሬያቸውን በታክስ ወይም በውርስ ለመንግስት ይገብራሉ፡፡ ሌላው ህዝብ ደግሞ የመንግስት ተደጓሚ ጥገኛ ይሆናል፡፡ የትምህርትና የጤና አገልግሎትን በድጎማ አገሬውን የማንበሽበሽ ህልም መሆኑ ነው፡፡ በአጭሩ “የሶሻሊዝምን አስተሳሰብ የማድነቅ አባዜ” ልንለው እንችላለን፡፡
ታዲያ አምራቾችን እያራቆቱ በማዳከም፣ ህዝቡን በብልፅግና የማንበሽበሽ ህልም እውን ሊሆን አይችልም፡፡ የሶሻሊስት ህልም፣ ቅዠት ነው። እንዴት? በተቃራኒው የብልፅግና እድልን ይዘጋል። በኩባ እና በመሰሎቿ ሶሻሊስት አገራት ላይ፣ እነ ካስትሮ ያወረዱት መዘዝም ይሄው ነው፡፡ እና፣ ባንኪ ሙን ይህንን ያደንቃሉ? የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊው? ዘይገርም! ጉደኛ ዘመን ላይ ነን፡፡  
የሂዩማን ራይትስ ዎች አቅጣጫ፣ ትንሽ ለየት ይላል። ካስትሮን አላደነቀም። “በአፈና ኩባዊያንን አሰቃይተዋል” በማለት ካስትሮን ወቅሷል፡፡ ከወቀሳው ጋር የአድናቆት ገለፃ አልቀላቀለም፡፡ ነገር ግን፣ የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ ውስጥ፣ ዋናው ተወቃሽ ካስትሮ አይደሉም፡፡ አብዛኛው ወቀሳ ያነጣጠረው በአሜሪካ ላይ ነው።
የአሜሪካ መንግስት፣ ማዕቀብ በመጣል በኩባ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ፣ ለካስትሮ ጠቅሟል፤ … የስልጣን እድሜ ለማራዘምና አፈና ለማስፋፋት ሰበብ ሆኖላቸዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች። ምን ማለት ነው? ይሄም የጉደኛው ዘመን አንድ ምልክት ነው፡፡ አሜሪካ በካስትሮ ላይ ተፅእኖ ለማሳደር በመሞኮሯ ነው፣ ዋና ጥፋተኛ ሆና የተጠቀሰችው። ነገ ከነገወዲያ፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸውን መግለጫዎች ስንከታተል ደግሞ፤ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ በኢትዮጵያና በሌሎች አገራት ላይ ተፅእኖ እንዲያሳድሩ ጥሪ ሲያቀርብ ትመለከቱታላችሁ። “ብርቱ ተፅእኖ ለማሳረፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” እያለም ይወቅሳቸዋል። አምነስቲ ካስትሮን ያደንቃል፡፡ ይሄኛው ደግሞ አሜሪካን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡  
የራሺያና የቻይና፣ የሰሜን ኮሪያና የሶሪያ መንግስታት፣ ፊደል ካስትሮን በአድናቆት ቢያንበሻብሹ፣ ወይም በአስደናቂ አክሮባት አሜሪካን ተወቃሽ ቢያደርጉ አይገርምም። የአንድ ፓርቲ አገዛዝን በማስፈን ገናና ሆነው ለመቀጠል የሚፈልጉ መንግስታት፣ ካስትሮን ማድነቃቸው ምኑ ይገርማል? በአንድ ፓርቲ የአገዛዝ ስርዓት ለ50 ዓመት በገዢነት የዘለቁ አንጋፋ ፖለቲከኛን፣ ማለትም ካስትሮን … በዚህም በዚያም ሰበብ ደርድረው ለማወደስ ይሽቀዳደማሉ። ካስትሮ ቅዱስ ጀግና ከሆነ … “እኔም ጀግና ነኝ፤ እኔም ቅዱስ ነኝ” የሚል ትርጉም ለማስተላለፍ ይጠቅማቸዋል። የአገሬውን ኢኮኖሚ በአብዛኛው በመንግስት እጅ ውስጥ ለማስገባት፣ የዜጎችን ህይወትና የእለት ተእለት ኑሮ በቁጥጥሩ ስር ለመደፍጠጥ የሚመኝ ፓርቲና ፖለቲከኛ፤ ፊደል ካስትሮን ቢያደንቅ፣ ግራ አያጋባም።
ፍላጎታቸውና አድናቆታቸው፣ እርስ በርስ አይጣረዝም። አምባገነንነትን የሚፈልግ ሰው፣ አምባገነንነትን ቢያደንቅ፣... ሃሳቡና ስሜቱ፣ አላማውና ንግግሩ፣ አብሮ ይሄዳል። እርስ በርስ ይደጋገፋል።
“የፖለቲካ ነፃነትን፣ የኑሮ መሻሻልን፣ የህግ መከበርን እፈልጋለሁ” የሚል ሰው ወይም ተቋም፤ በአደባባይ፣ ፊደል ካስትሮን የሚያደንቅ ከሆነ ግን፣... አንድም የተጣረዘ የምናብ አለም ውስጥ የገባ አላዋቂ ነው፡፡ ወይም ደግሞ፣ የፖቲካ ነፃነት፣ የብልፅግና እድልና የህግ የበላይነት … እያለ የሚለፈልፈው የውሸት ነው፡፡ ሁለት ወዶ አይሆንማ፡፡
አምባገነንነትን አልያም የፖለቲካ ነፃነትን፣ የብልፅግና እድልን አልያም እኩል ድህነትን፣ የህግ የበላይነትን አልያም የአንድ ፓርቲ ገናናነትን … የፊደል ካስትሮ የሶሻሊዝም ታሪክን አልያም የአሜሪካ የካፒታሊዝም ታሪክን … አንዱን መምረጥ የግድ ነው፡፡
ለዚህም ነው፣ ፊደል ካስትሮ እንደ ቴርሞ ሜትር ያገለግላሉ የምለው፡፡ የዜጎችን ወይም የፖለቲከኞችን፣ እንዲሁም የአገሪቱን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዝንባሌ፣ የእውነት ለማወቅ ከፈለጋችሁ፣ ይሄውላችሁ ጥሩ ዘዴ!
በሰበብ አስባቡ የአሜሪካ የካፒታዝም ታሪክን እያንቋሸሸ፣ ፊደል ካስትሮን በሰበብ አስባቡ የሚያደንቅ ፖለቲከኛ ወይም ምሁር ከበዛ፣ … ለአምባገነንነት፣ ለአንድ ፓርቲ አገዛዝና ለድህነት የተመቻቸ አገር አገኛችሁ ማለት ነው ልክ እንደ ኢትዮጵያ፡፡

Read 4019 times