Sunday, 27 November 2016 00:00

የስፖርት ውርርድ በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካና በዓለም ዙርያ…

Written by 
Rate this item
(33 votes)

• አክሱም ቤቲንግ በአዲስ አበባ 7 ቅርንጫፎች ከፍቶ፤ በ60 ዓይነት ውርርዶች ከ100 በላይ ስፖርቶች እያጫወተ ነው፡፡
• በ20 ብር ትኬት ከ1 እስከ 20 ጨዋታዎችን በአክሱም ቤቲንግ መወራረድ ይቻላል ፤ ከፍተኛው ሽልማት እስከ 250ሺ ብር ነው፡፡
• በዓለም ዙርያ እስከ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡
• በአፍሪካ በ27 አገራት የስፖርት ውርርድ እየተካሄደ ሲሆን የውርርድ ተቋማት ብዛታቸው 2ሺ ይደርሳል፡፡ በደቡብ አፍሪካ፤ ናይጄርያና ኬንያ ተስፋፍቷል፡፡

የስፖርት ውርርድ ሁሉንም ማህበረሰብ ሊያሳትፍ የሚችል በስፖርት ውጤቶች ላይ በመንተራስ የሚካሄድ አዝናኝና ገቢ የሚያስገኝ ጨዋታ ነው፡፡ የውርርድ ተጨዋቾች እና ተሳታፊዎች የስፖርት ውድድሮችን በመመልከት ከሚኖራቸው መዝናናት ባሻገር፤ በተለያዩ የመወራረጃ መስፈርቶች በሚሰጧቸው ግምቶች የገንዘብ ተሸላሚ የሚሆኑበትን እድል ይፈጥርላቸዋል። አወራራጅ ተቋም በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የውርርድ ዝርዝሮችን በመግለፅ እና የሚሸልመውን ገንዘብ በማሳወቅ የሚሰራ ሲሆን አጠቃላይ አካሄዱም በህግና ስርዓት የተመራ ነው፡፡ በስፖርት የተለያዩ ሁኔታዎች በመወራረድ በህጋዊ መንገድ እየተዝናኑ መጫወት፡፡ ለሀገር የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ  የስራ እድሎችን የሚፈጥር መስክ ነው፡፡ የስፖርት ውርርዱን በህጋዊ መንገድ መካሄዱ በህብረተሰቡ ዘንድ ህገወጥ በሆነ መንገድ በመወራረድ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ችግሮች ለመከላከልም የሚያግዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ  የሚካሄዱ የስፖርት ውርርዶች በሌሎች የአፍሪካ  አገራት ባሉበት ደረጃ ላይ አይገኝም። ከ4 ዓመታት በፊት ዳጉ ቤት ኢትዮጵያ በተባለ ተቋም በፈርቀዳጅነት ቢጀመርም፤ ብዙ የዘለቀ አልነበረም።  ባለፉት 8 ወራት  ግን ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ መስራት በጀመረው አክሱም ቤቲንግ የተባለ የስፖርት ውርርድ ተቋም መስኩ መነቃቃት ጀምሯል፡፡የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር  የስፖርት ውርርድን ለማካሄድ የሚያስችል መመርያ በኢትዮጵያ መንግስት ያፀደቀው ከ5 ዓመታት በፊት ነበር፡፡  ፍቃድ የሚያገኙ ድርጅቶች በህግ ማዕቀፍ ሆነው ውርርዱን እንዲያጫውቱ የሚያደርገው የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አፈፃፀሙን በመከታታል በመቆጣጠር አብሮ ይሰራል፡፡ የትኛውም ድርጅት፤ ተቋም ወይም ግለሰብ ለስፖርት ውርርድ ህጋዊ ፈቃድን ማግኘት እንደሚችል  የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደሩ ያስታወቀ ሲሆን የሚሰጠው ፍቃድ በየዓመቱ የሚታደስ ነው፡፡
አክሱም ቤቲንግ እና እንቅስቃሴዎቹ
አክሱም ቤቲንግ በ300ሺ ዶላር ካፒታል  የተቋቋመ የስፖርት ውርርድ ተቋም ሲሆን 18 ሰራተኞችን በሂሳብ ሰራተኝነት፤ በሱቆች ማናጀርነት እና በሹፌርነት በመቅጠር የሚያስተዳድር ነው፡፡   በኢትዮጵያ በስፖርት ውርርድ መስክ ከፍተኛ አቅም መኖሩን የተገነዘበው ይህ ተቋም በመስኩ ዘላቂ እቅዶችን በመንደፍ እየሰራ መሆኑን ምክትል ሥ/አስኪያጁ ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡ የአክሱም ቤቲንግ ምክትል ሥ/አስኪያጅ፤ የዴቨሎፕመንት እና ሪሰርች ሃላፊ አብርሃም ተክለማርያም ይባላል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛ፤ የእግር ኳስ አሰልጣኝ፤ ቀድሞ በደቡብ አፍሪካ ሱፐርቤቲንግ ከተባለ የስፖርት ውርርድ ተቋም ጋር በመስራት ልምድ ያካበተ ነው፡፡ ለስፖርት ውርርድ ኢትዮጵያ አመቺ መሆኗንም በተለያዩ ማስረጃዎች ማመልከት ይቻላል፡፡ ከ90 ሚሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ያለባት ሀገር መሆኗ አንዱ ትልቅ አቅም ነው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ከተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ዜጎች መናሀሪያ መሆኗም መስኩን ለማንቀሳቀስ ማመቸቱም ይጠቀሳል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የክልል ከተሞች የስፖርት ውርርዶች የመዝናኛ አማራጮች መሆን እንዳለባቸው ለስፖርት አድማስ አስተያየት የሰጠው አብርሃም ተክለማርያም፤ የምስራቅ አፍሪካ፤ የአፍሪካን ገበያ ከዚያም አልፎ እስከ ኤስያ አህጉር በመሻገር በስፖርት ውርርድ መስክ ኢትዮጵያ ገበያውን ለመቆጣጠር እንደምትችል በማመን በአክሱም ቤቲንግ እየሰራን ነው ሲል ይናገራል። በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ባሻገር በበርካታ ሀገራት የስፖርት ውርርዶችን እየሰራ የሚገኘው አክሱም ቤቲንግ  በቤለሩስ፣ በሰሜን ኢራቅ፣ በሞልዶቫ፣ በቆጵሮስ፣ በኬንያ፣ በዩጋንዳና በጋና የሚንቀሳቀስ ሲሆን በቀጣይ ወር ደግሞ በታንዛኒያም ቢሮውን የሚከፍት ይሆናል፡፡
ባለፉት 8 ወራት አክሱም ቤቲንግ በኢትዮጵያ የስፖርት ውርርድ ለማስፋፋት ቴክኒካዊ ስራዎችን መሰረት በማስያዝና በማስተዋወቅ ላይ አተኩሮ እየተንቀሳቀሰ ቆይቷል፡፡   ድረ ገፁን በዘመናዊ በዘመናዊ ዲዛይን በተጠቃሚዎቹ በሚመች መልኩ አደራጅቷል። የስፖርት ውርርዶችን ማካሄጃና ውድድሮችን መመልከቻ ስፍራ በዋና መስርያ ቤቱ  22 ከአውራሪስ ሆቴል ፊት ለፊት መክፈቱን ጨምሮ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ሰባት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ እነዚህ ቅርንጫፎቹ ሳሪስ አዲስ ሰፈር እናት ባንክ ፊትለፊት፤ በጎተራ ኮንደሚኒዬም በሚገኘው ግቢ ላውንጅ እና ስፖርት ባር፤ ወሎ ሰፈር አካባቢ ሚና ህንፃ ላይ በሚገኘው ፍሬንድስ ኤንድ ባር ሬስቶራንት፤ ቦሌ ማተሚያቤት ጀርባ በሚገኘው ፊደል ባርና ሬስቶራንት፤ መስቀል ፍላወር አካባቢ በዋን ሞር ናይት ላውንጅ እንዲሁም አዲስ አበባ ስታድዬም ዙርያ በዛብሎን ትርጉም ቤት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የአክሱም ቤቲንግ  ምክትል ሥ/አስኪያጅ አብርሃም ተክለማርያም ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው፤ በወቅቱ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ችግር ሳቢያ የነበረ እቅዳቸው ቢስተጓጎልም ከአዲስ አበባም ውጪ በባህርዳር፤ በጎንደር፤ በመቀሌ፤ በአዳማ  እና ሀዋሳ ከተሞች ቅርንጫፎቻቸውን ለመክፈት ፍላጎት አላቸው፡፡
ሰሞኑን 22 አካባቢ ከአውራሪስ ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን የአክሱም ቤቲንግ የስፖርት ውርርድ ቤት ጎብኝተን ነበር፡፡ ባለ 45 ኢንች የሆኑ 18 ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥኖች አሉ፡፡ የሂሳብ ሰራተኞች በኮምፒዩተሮቻቸው ፈጣን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ምቹ የማረፊያ ስፍራዎች ሻይና ቡና በነፃ ነው፡፡ የስፖርት ውድድሮችን በመመልከት ጎን ለጎን ውርርድ የሚካሄድበት ይህ ቤት፤ በእረፍት ቀናቶች በሩ ለሁሉም ክፍት ነው፡፡ የስፖርት ውርርድ ተሳታፊዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ገብተው ውድድሮችን በነፃ እየተመለከቱ የስፖርት ውርርዳቸውን እየተጫወቱ ሊስተናገዱበት ይችላሉ፡፡ የአክሱም ቤቲንግ የስፖርት ውርርዶች www.axumbet.com በሚለው ድረገፅ የሚካሄዱ ናቸው፡፡  ከ100 በላይ የስፖርት ውርርዶችን እያጫወቱ ሲሆን እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ መረብ ኳስ፣ ቴኒስ፣ ራግቢና ኪርኬት … የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
በኢትዮጵያ ስለ ስፖርት ውርርድ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ተፈጥሯል ለማለት አይቻልም፡፡ በርካታ እንቅስቃሴዎች ገና ያስፈልጋሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰቡ በስፖርት ውርርድ  ላይ እምነት ማሳደር አለበት፡፡ ከዚያም በኋላ ገንዘቡን አውጥቶ በነፃነት ሊጫወት ይችላል፡፡ ምክትል ሥ/አስኪያጅ አብርሃም ስለ አክሱም ቤቲንግ የግብር አከፋፈል ለስፖርት አድማስ ባደረገው ገለፃ ተቋማቸው ከጠቅላላ ገቢው 15 በመቶ ለብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር፤ 10 በመቶ ለገቢዎች እና ጉምሩክ እንዲሁም 15 በመቶ የአሸናፊነት ክፍያ በመቅረጥ ገቢ ያደርጋል፡፡   ትልቁን ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለው የግብር አከፋፈሉ የንግድ መስኩን ለማፋፋት የሚያበረታታ አለመሆኑ ነው፡፡  
የስፖርት ውርርድ የሚያካሂድ ተቋም  ፍላጎት የሚሆነው ከተጣራ ትርፍ 15 በመቶ ለመክፈል ነው፡፡ አሁን ባለው አሰራር ከሚያስገባው ያልተጣራ ትርፍ እስከ 15% ግብር ይከፍልበታል፡፡ ይኸው የግብር አከፋፈል የስራ መስኩን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጓትት ነው የአክሱም ቤቲንግ ሃላፊዎች የሚያስረዱት፡፡ የንግድ መስኩ በበቂ ሁኔታ ከተስፋፋ በኋላ አገሪቱን በከፍተኛ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅሱት የአክሱም ቤቲንግ ሃላፊዎች ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ግልፅ መግባባት ፈጥረን ለመስራት ጥረት ማድረጋችን ይቀጥላል ይላሉ፡፡ የስፖርት ውርርድ ላይ  ወዲያውኑ የሚከፈል ነገር የለም፡፡ ተሳታፊዎች ምን ያህል እንደሚያስይዙ፤ በምን ያህል ውርርዶች ላይ እንደሚሳተፉ ወዲያውኑ ማወቅ አይቻልም፡፡ ይህም ገቢዎችን ሰብስቦ ግብር ለመክፈል በሚኖረው ሂደት ላይ ትዕግስት እንደሚያስፈልገው ያመለክታል። ህጋዊ ፈቃድ አውጥተን መስራታችን በሀገሪቱ ህግ መሰረት መንቀሳቀሳችን የስፖርት ውርርድን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት በምናደርገው ጥረት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር  ድጋፍ ወሳኝ ነው በማለት የአክሱም ቤቲንግ ሃላፊዎች ለስፖርት አድማስ ተናግረዋል። በቀጣይ አክሱም ቤቲንግ ከስፖርት ሚዲያዎች ጋር የመስራት እቅዶችንም ይዟል፡፡ ከሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር እየተነጋገረ ሲሆን በሌሎች የኤፍኤም ራዲዮ ጣቢያዎችም ከስፖርት ውርርድ ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞችን ለመስራት ድርድር እያደረጉ ናቸው፡፡  
በዓለም ዙርያ የሚደረጉ የስፖርት ውርርዶችን ለመወራረድ ወይንም ለመጫወት በአክሱም ቤት ዋና መስርያ ቤት ወይም በቅርንጫፎቹ በመገኘት የጨዋታውን ዝርዝር ወስደው በመመልከት ለመጫወት የፈለጉትን ቡድንና የጨዋታ አይነት ይመርጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በድረገፅም በቀጥታ መጫወት ይችላሉ። ድረገፆቸውን ከፍቶ የምዝገባ ቅፅ መሙላት ከዚያም ስልክ ቁጥር ማስገባት፤ የምስጥር ጥያቄ መመለስ፤ ለመወራራጃ የሚያፈልገውን ገንዘብ ገቢ ማድረግ ከዚያም ውርርዱን መጀመር ነው፡፡ በአክሱም ቤቲንግ ማንኛውም ሰው በ20 ብር አንድ ቲኬት በመግዛት ከ1-20 ጨዋታዎችን መወራረድ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ የስፖርት ውርርድ ተቋሙ ከ60 በላይ የውርርድ ጨዋታዎችን ለደንበኞቹ የሚያቀርብ ሲሆን ከፍተኛው ሽልማት እስከ 250ሺ ብር ነው፡፡ ውርርዱ የሚካሄድባቸው መንገዶች - አሸናፊውን ቡድን በመገመት መወራረድ - ትክክለኛ ውጤት በመገመት መወራረድ - የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሸ ውጤት በመገመት መወራረድ - ቀድሞ ጐል የሚያስቆጥረውን ክለብ በመገመት መወራረድ - በመጀመርያው ግማሽ፤ በሁለተኛው ግማሽ እና በሙሉው የመደበኛ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሚገቡ ጎሎች ብዛት በመገመት መወራረድ - እንዲሁም ሌሎች። በአክሱም ቤቲንግ የውርርድ መመርያ መሰረት በ90 ደቂቃ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር ውጤት መወራረድ የሚቻል ሲሆን፤ ነገር ግን ውርርዱ የተጨማሪ ሰዓት (30 ደቂቃ) እና የመለያያ ምትን አያጠቃልልም፡፡ ሁሉም ውርርድ የሚካሄደው ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ይሆናል፡፡
ለስፖርት ውርርድ አፍሪካ ምቹ እየሆነች መጥታለች
የስፖርት ውርርድ በዓለም ዙርያ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን ትርፋማ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡  በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሱ  የስፖርት አወራራጅ እና አቋማሪ ኩባንያዎችን  በየዓመቱ ከ55ሺ በላይ የስፖርት ውድድሮችን ተንተርሰው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።  በተለያዩ ጥናታዊ ዘገባዎች እንደሚጠቀሰው በዓለም ዙርያ የስፖርት ውርርድ  በየዓመቱ እስከ  3 ትሪሊዮን ዶላር በሚንቀሳቀስበት ገበያ እየተጧጣፈ ነው፡፡ በህጋዊ እና ህገወጥ የስፖርት ውርርዶችን የሚያካሂዱ አወራራጅ ተቋማት በዓለም ዙርያ ገቢያቸው ከ 700 ቢሊዮን እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ በመላው ዓለም የስፖርት ውርርድ 65 በመቶ የገበያውን ድርሻ የተቆጣጠረው የእግር ኳስ ስፖርት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው 12 በመቶ የገበያ ድርሻ በመያዝ የሚከተሉት የቴኒስ እና የክሪኬት ስፖርቶች ናቸው፡፡
የስፖርት ውርርድ በአሜሪካ አህጉር ተጀምሮ፤ በአውሮፓ እና በኤስያ አህጉራት በከፍተኛ ደረጃ ከተስፋፋ በኋላ ነው ወደ አፍሪካ አህጉር የመጣው፡፡ ዓለም አቀፍ የስፖርት ውርርድ ተቋማት በአፍሪካ  አህጉር ላይ ባለፉት 5 ዓመታት በትኩረት መስራት ጀምረዋል፡፡  ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የመጀመርያው ምክንያት ከአፍሪካ አህጉር አጠቃላይ የህዝብ ብዛት እድሜያቸው ከ15 እስከ 27  እድሜያቸው የሆኑ ከ200 ሚሊዮን በላይ መሆናቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል በአህጉሪቱ የየሞባይል አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱ፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጎች በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅነት ማግኘታቸው፤ በየአገራቱ በስፖርት ውርርድ ተቋማት ገቢ ላይ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አህጉራት ያነሰ የግብር ክፍያ መኖሩም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ አህጉር በ27 አገራት የስፖርት ውርርድ እየተካሄደ ሲሆን በህጋዊ እና ህገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ብዛት ከሁለት ሺ በላይ መሆናቸውን  መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአፍሪካ የስፖርት ውርርድ ገዝፎ የሚታይባቸው እና የተስፋፋባቸው  3 አገራት ደቡብ አፍሪካ፤ ናጄርያ እና ኬንያ ናቸው፡፡ የኬንያው ስፖርትፔሳ፤ የደቡብአፍሪካ ሱፓቤትስ እና የናይጄርያው ቤት9ጄኤ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ግዙፉቹ የስፖርት ውርርድ ተቋማት ግንባር ቀደም ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡  ፕራይስዎተርስኩፐርስ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ከዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ጥናት በ3ቱ አገራት የስፖርት ውርርድ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑ ተጠቅሶ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የኢንዱስትሪው ገቢ በዓመት እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተመልክቷል። በአፍሪካ እየተንቀሳቀሱ ያሉት የስፖርት ውርርድ ተቋማት አንድ ተሳታፊ ለሚያስይዘው 1 ዶላር በአማካይ እስከ 500 ዶላር በሚሸልሙበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በአፍሪካ ደረጃ የስፖርት ውርርድ በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድባት አገር ደቡብ አፍሪካ ስትሆን በየዓመቱ 21 በመቶ እድገት እያሳየ የሚገኝ ኢንዱስትሪዋ ነው፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው የደቡብ አፍሪካ የስፖርት ውርርድ ተቋማት መካከል ሱፓቤትስ፤ ስፖርትቤት፤ላድብሮክስ የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የስፖርት ውርርዶች በእግር ኳስ፤ በራግቢ፤ በክሪኬት፤ በአትሌቲክስ ስፖርቶች በስፋት የሚካሄዱ ሲሆኑ የኢንዱስትሪው ዓመታዊ ገቢ 25 ሚሊዮን ዶላር መድረሱንም መረጃዎች ያመልክታሉ። ይህም ከአገሪቱ የስፖርት መስክ ገቢ 14 በመቶ  ድርሻ ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል የስፖርት ውርርድ በምእራብ አፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋ ሲሆን በተለይ በናይጄርያ እና ጋና እየገዘፈ መጥቷል፡፡ ናይጄርያ ውስጥ በተለይ በስፖርት ውርርድ እድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚሆኑ ከ60 ሚሊዮን በላይ የውርርድ ደንበኞች እስከ  9 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ በነፍስ ወከፍ በየቀኑ  15 ዶላር በማያዝ ተሳትፎ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡
የኬንያ የስፖርት ውርርድ ተቋማት
ከምስራቅ አፍሪካ አገራት የስፖርት ውርርድ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋባት አገር ጎረቤታችን ኬንያ ናት፡፡ በርግጥ አንዳንድ መረጃዎች በአፍሪካ አህጉር በስፖርት ውርርድ ፈርቀዳጅ መሆኗንና በ1950ዎቹ በዓለም አቀፍ የጎልፍ፤ የቴኒስ፤ የእግር ኳስ እና ሌሎች የስፖርት ውድድሮች መጀመሯን ይጠቅሳሉ፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በኬንያ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋው የስፖርት ውርርድ ላይ ስኬታማ በመሆንና በየጊዜው እድገት በማሳየት በተለይ 4 የውርርድ ተቋማት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያንቀሳቅሱ ናቸው፡፡
በመጀመርያ ደረጃ የሚጠቀሰው የውርርድ ተቋም በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳሆን በመላ አህጉሪቱ ከሚንቀሳቀሱት መሰል ተቋማት ግንባ ቀደም ተጠቃሽ የሆነው ስፖርትፔሳ የተባለው የውርርድ ተቋም ነው። ስፖርትፔሳ በ2013 እኤአ ላይ ፔሳን ኢስት አፍሪካ ሊሚትድ በተባለ ኩባንያ የተጀመረ ሲሆን በድረገፁ          አንድ ሚሊዮን በክፍያ የተመዘገቡ ደንበኞች በማፍራት እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር በዘርፉ እያንቀሳቀሰ የሚገኝ ነው።  የውርርድ ተቋሙ ድረገፅ በኬንያ ብዙ ጎብኝ ካላቸው 10 ድረገፆች አንዱ ሆኖም ይጠቀሳል።
ስፖርትፔሳ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ ዩሮፓ ሊግ ውድድሮችን በመደበኛነት የሚያወራርድ ሲሆን ሌሎች የአውሮፓ ሊጎችን ጨምሮ፤ በቅርጫት ኳስ፤ በቴኒስ እና በራግቢ የሊግ እና የዓለም አቀፍ ውድድሮችም ይሰራል፡፡ ስፖርትፔሳ በስፖርት ውርርዱ ባለፉት አመታት ባገኘው ስኬት ተምሳሌት ሆኖ ሊጠቀስ የሚበቃ ሲሆን በስኬታማነቱ በአንድ ወቅት የኬንያ የሊግ ውድድር ስፖንሰር ለማድረግ የቻለ፤ ከሞባይል አገልግሎት ተቋማ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መስኩን ትልልቅ ፌስቲቫሎችን በማካሄድ የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ በኬንያ ከስፖርትፔሳ ባሻገር ሌሎች የስፖርት ውርርድ ተቋማትንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው በጃምቦ ቤቲንግ ሊሚትድ ከ4 ዓመታ በፊት ተመስርቶ መንቀሳቀስ የጀመረው ቤትዌይኬንያ ነው፡፡ ይህ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና ያለውና፤ በማልቲስ እና ግራኒሴይ ተቀማጭነቱን ባደረገው እንዲሁም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለብ የሆነውን ዌስትሃም ስፖንሰር የሆነው ቤትዌይ ቅርንጫፍ ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሰቃቀሰው ቤትዌይ ሊሚትድ በተባለ ኩባንያ ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ደግሞ ቤቲንኬንያ የተባለው የውርርድ ተቋም ሲሆን፤ በአፍሪካ እና በአውሮፓ ትልቁ የስፖርት ውርርድ ተቋም ጎልድቤት ስር የታቀፈ እና በኬንያ ጋምኮድ በተባለ ኩባንያ የሚሰራ ነው፡፡ ቤት የቱ፤ ሚቼዛ፤ ኤሊት ቤት ዌይ፤ ጀስትቤት፤ ላኪ2ዩ እና ኬንያ ስፖርት ቤት ሌሎቹ በኬንያ የሚነቀሳቀሱ ህጋዊ የስፖርት ውርርድ ተቋማት ናቸው፡፡

Read 16548 times