Sunday, 27 November 2016 00:00

“ነገሩ ነው እንጂ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
 ‘ሰውየው’ ተመረጡ የተባለ ሰሞን ነው፡፡ የሆነ አገልግሎት መስጫ ቦታ ላይ ነበርን፡፡ ቢሮው ውስጥ ሲ.ኤን.ኤን. እስከ ጥግ ተለቆ አማሪካን “ጉድ! ጉድ”! እያለች ነበር፡፡ ታዲያላችሁ…አጠገቤ የነበሩ እናት፣ እንኳን ስለ ዶናልድ ትረምፕ ሊያውቁ ዓለም ላይ ከኢትዮጵያ ሌላ  አገር የሌለ የሚመስላቸው አይነት እናት ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“ይሄ ከይሲ ተመረጠና አረፈው!”
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ለአማሪካን ምርጫ ትረምፕን ‘ቀንድ ቀንዳቸውን’ በማለት ከፍተኛ ተሳትፎ አሳይተን፣ የተሳትፎ ሰርተፊኬት እንኳን አይሰጠንም!
ደግሞላችሁ…አንድ ወዳጃችን እንዲሁ ከአካባቢዋ በስተቀር ስለሌላ አካባቢ እምብዛም የማታውቅ ሴት የምረጡኝ ቅስቀሳው ሰሞን…
“ሰውየው ሲሳደብ ለምንድነው ዝም የሚሉት… አያስሩትም እንዴ!” አለች ሲለን ነበር፡፡
ልክ ነዋ… “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” ይል ከነበረ ህብረተሰብ ውስጥ የወጣች ነቻ! የከተሜው ስድብ ግራ የገባው ገጠሬ… አለ አይደል… “አዲስ አባባ ገዳይ ጠፋ እንጂ፣ ሟችስ ሞልቶ ነበር…” አለ ከሚባልበት ህብረተሰብ ውስጥ የወጣች ነቻ!
ስሙኝማ…እንደ ዘንድሮው ‘አሳዳሪዎቻችንን’ ታዝበናቸው አናውቅም፡፡ ሮምኒ የሚሏቸው ሰውዬ እንደዛ ጥምብርኩሳቸው እስኪወጣ ተሰድበው፣ “ተንበርከክ ብለው ይንበረከክ ነበር…” ምናምን እየተባሉ፣ ሲዘለፉ፣ እንትን የነካው እንጨት ሲደረጉ ከርመው “ና!” ሲባሉ ተንደርድረው ሄዱ አይደል! ለካስ ሰውየው… “ተንበርከክ ብለው ይንበረከክ ነበር…” ያሉት ከመሬት ተነስተው አይደለም ያሰኛል፡፡
እናማ… ገንዘብ እስከተገኘ፣ ጥቅም እስከተገኘ፣ ስልጣን እስከተገኘ… “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” አይነት ‘ጊዜ ያለፈበት’ ነገር አይሠራማ!
እናላችሁ…ጊዜው እንደዚህ ሆኗል፡፡ ዓለማችን እንደዚሁ ሆናለች፡፡ እኛም እንደዚሁ ሆነናል፡፡ አዲስ አባባን ብታዩዋት እንደ ስድብ ‘የረከሰ ሸቀጥ’ የሌለባት ከተማ ሆናለች፡፡ ዕድሜ፣ ዕውቀት፣ ሀብት ምናምን የሚሏቸው ነገሮች መለያ ሆነው ቀርተዋል፡፡ መሳደብና መሰደብ በእኩልነት የተዳረሰን ነው የሚመስለው፡፡
እናማ…ተሰድበን፣ ‘ጸሎት ስፍራ የገባች ቡቺ’ ምናምን ተደርገን  “ና!” ሲሉን የምንሄድ ሆነናል፡፡ እንደ ውሻ “ተንበርከክ ብለው ይንበረከካል…” ምናምን  ከተባልን በኋላ “ጃስ!” ሲሉን ተስፈንጥረን የምንነሳ ሆነናል፡፡ ጊዜው ነዋ!  ዓለም እንዲህ ነቻ! ሀብት፣ ስልጣን፣ ክትፎ በቅቤ ምናምን የሚሏቸው ነገሮች ከስድብ ጋር ‘እንድንቻቻል’ አድርገውናላ!
እናማ… ገንዘብ እስከተገኘ፣ ጥቅም እስከተገኘ፣ ስልጣን እስከተገኘ… “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” አይነት ‘ጊዜ ያለፈበት’ ነገር አይሠራማ!
ስሙኝማ…ትራፊኩ ትንሽ የተጨናነቀበት አካባቢ ለትንሽ ደቂቃ ቆም በሉማ፡፡ የመኪና አሽከርካሪዎች የስድብ አይነት ታያላችሁ፡፡ ያቺ የፈረደባት መሀል ጣት ከሁሉ ረዝማ ተፈጠረችና  ቂ…ቂ…ቂ… በየመስኮቱ እንደ ሰንደቅ መስቀያ ስትወነጨፍ ነው የምትውለው። ወላ ኮሌጅ የበጠሰ፣ ወላ የኢትዮጵያን ዕድሜ ጣሪያ የበጠሰ፣ ወላ የሂዩመን ሄይር ዋጋ ጫፍ የበጠሰች…ብቻ ምን አለፋችሁ… ነገሩ ሁሉ ‘ጣት በመስኮት’ ሆነናል፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት ማለዳ አካባቢ ነው። ሰውየው ሁለት በግምት ሰባት፣ ስምንት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ህጻናትን ይዞ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል፡፡ የሆነ የተንቀዠቀዠ ‘የውበት እስረኛ’ ታክሲ (ቂ…ቂ…ቂ…) ያስደነግጣቸዋል፡፡ እንዲያውም ሆኖ ባለ ታክሲው በእሱ ብሶ…“እያየህ አትሄድም…” ምናምን ማለት ሲጀምር፣ ልጆቹን የያዘው ሰውዬ የደረደረው የስድብ አይነት ‘የስድብ ውልደትና ዕድገት በምስራቅ አፍሪካ’ ምናምን ከሚል የጥናት ወረቀት ላይ የሚያነብ ነበር የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው… የፈለገ ቢናደድ የያዛቸውን ልጆች እንዴት ማሰብ ያቅተዋል! በዚህ አላበቃም… ታክሲው ቀስ ብሎ በአጠገቡ እያለፈ እያለ በመስኮት በኩል ተፋበት፡፡ ባለታክሲው ዝም ብሎ መንገዱን ቀጠለ፡፡
እዩልኝማ…የያዛቸው ልጆች ምን ይዘው እንደሚያደጉ!
ነገሬ ብላችሁ እንደሆነ ሰው በዛ ያለባቸው የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች… ወይ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ወይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች የሚናገሩትን ሰምታችሁልኛል!…
በዛ ሰሞን አንድ መሰል አገልግሎት መስጫ ቦታ፣ ሰው በዝቶ ትርምስ ቢጤ ነበር፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ሰዎች በስነ ስርአት የተራ ቁጥር ቢሰጡ ኖሮ የማይፈጠር ነገር ነበር፡፡ የሆነች ፀሀፊ ትሁን ምን… የተራ መያዣ ቁጥሮችን የት እንዳደረገችው ምናምን የሚል ቀሺም ምክንያት ነበር፡፡ አያሳፍርም! አሮጌ ወረቀት ሰብስቦ እኮ መጻፍ ይቻል ነበር፡፡ እንዲህ ሆኖ እያለ አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ምን ያንጫጫችኋል…”
እናላችሁ….እዛ ቦታ ደግሞ አንድም ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ምናምን የሚባል ሰው አልነበረም። እናላችሁ… እንዲህ አይነት መሰደብም አለ፡፡ ሌላው ገራሚ ነገር አንድም ሰው… አለ አይደል… “እንደዛ ልትሳደብ አትችልም…” ምናምን ያለም፣ ሊልም የሞከረም የለም፡፡
“ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” ብሎ ነገር ‘ጊዜው ያለፈበት’ ተረት ሆኗላ!
እናላችሁ…‘ክሩክድ ሂላሪ፣’  ‘ላዪንግ ቴድ፣’  ‘ሊትል ሩቢዮ’… እያሉ ሁሉንም ልክ ልኩን ሲያጠጡ የከረሙ ሰውዬ፣ አሁን እነኛው የተሰደቡት ሰዎች “ና!” ሲባሉ ‘የማለዳው በራሪ አውቶብስ ሳያመልጣቸው’ ለመድረስ ሲጣደፉ ስታዩ…አለ አይደል… “ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” ብሎ ነገር ጊዜው እንዳለፈበት ታያላችሁ፡፡
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ከፊት ለፊቱ ስድብ ሌላ የተዘዋዋሪ ስድቦች እኮ እንደ ልብ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ጸጉር ለሌለው ሰው የማበጠሪያ ስጦታ የሚሰጥ ሰው…በተዘዋዋሪ እንደተሳደበ ይቆጠራል፡፡ ከሰጡ ብሩሽ ምናምን አይሰጡም! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ዘንድሮ ስድብ መልኳን እየለዋወጠች ትመጣለች፡
እናላችሁ…ለምሳሌ የሆነች እንትናዬ ሰውዬዋ ‘ሂዩመን ሄይር’ ገዝቶ ቢሰጣት መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ዘላ እሱ ላይ መጠምጠም ሊሆን ይችላል፡፡ “በወር አራት ጊዜ ብቻ…” የሚባሉ ነገሮችን “በወር አሥራ አምስት ቀን…” ምናምን የሚል ‘የፖሊሲ ማስተካከያ’ ልታደርግም ትችላለች፡፡  (ቂ…ቂ…ቂ…) ግን ኮሚኩ ነገር እኮ… አለ አይደል… በተዘዋዋሪ “ጸጉሯ ቀሺም ስለሆነ እኔንም ሰው ዓይን እንዳትከተኝ…” ብሎ የገዛላት ሊሆን ይችላል፡፡ እሷም እንዲህ ተብሎ ቢነገራት መልሷ… “ይሁና!” የሚል ይሆናል፡፡
“ነገሩ ነው እንጂ ጩቤው ሰው አይጎዳም…” ብሎ ነገር ‘ጊዜው ያለፈበት’ ተረት ሆኗላ!
እናላችሁ…ዘንድሮ ስድብ መልኳን እየለዋወጠች ትመጣለች፡
እነኚህ ማኪያቶ በደብል ውስኪ ዋጋ የሚሸጥባቸው ቤቶች ስትገቡ፣ መጀመሪያ ከጫማችሁ ጀምሮ ነው የምትታዩት፡፡ ይሄኔ…
“ምን አይነቱ ዓይን አውጣ ነው፣ ሎካል ጫማ አድርጎ እዚህ ይገባል እንዴ!” የሚሉ እንትናዬዎችና እንትናዎች ይኖራሉ፡፡ በተዘዋዋሪ ስድብ አይደል!
ይቺን ስሙኝማ…ባልና ሚስት ማታ ይጣላሉ፡፡ ይሄኔ ባል ተናዶ ምን ይላል…
“አሁን ያስጠላኝ ነገር ቢኖር ያንቺን ፊት ማየት ነው…” ይላታል፡፡
እሷዬዋ ምን ብታደርግ ጥሩ ነው…ተነሳችና መብራቱን አጠፋቸው — ፊቷን እንዳያያት…
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Read 4927 times