Sunday, 27 November 2016 00:00

ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና እህት ኩባንያዎች ከ450 በላይ ሰራተኞችን ቀነሱ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(14 votes)

    ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና እህት ኩባንያዎቹ ከውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከአዳዲ ስራዎች አለመገኘት ጋር በተያያዘ 500 ያህል ሰራተኞችን ቀነሱ፡፡ ለቅነሳው ምክንያቱ የፕሮጀክቶች መጠናቀቅ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና አዳዲስ ስራዎች አለመገኘት መሆኑን የታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፉ አምባዬ፣ የተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጎይቶም ወ/ገብርኤል እና የይበል ኢንዱስትሪያል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃ አፅበሀ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ከተአኮን 364፣ ከይበል ኢንዱስትሪያል 98፣ ከታፍ ኮርፖሬት ግሩፕ 16 በድምሩ 478 ያህል ሰራተኞች መቀነሳቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ችግሮቹን ለበርካታ ወራት ይዘናቸው ብንቆይም ከዚህ በላይ በዚህ ሁኔታ መቀጠል በድርጅቱ ህልውና ላይ አደጋ መጋበዝ ነው ሲሉም አቶ ሰይፉ አምባዬ ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ ተሰናባች ሰራተኞች በበኩላቸው፤ በድርጅቶቹ በቆዩባቸው ጊዜያት በጣም ደስተኛ እንደነበሩ ጠቁመው ድንገት ከስራ መቀነሳቸው ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ውስጥ ለአምስት ዓመታት ሲሰራ እንደቆየ የገለፀ አንድ የግንባታ ባለሙያ፤ “በድርጅቱ ደስተኛ ነኝ፤ ዓመታዊ የደሞዝ ጭማሪ፣ ጉርሻና የደረጃ እድገት በማድረግ ድርጅቱን የሚስተካከለው የለም” ካለ በኋላ በቅርቡ አተረፍኩ ብሎ ጉርሻና ማበረታቻ የሰጠ ድርጅት ስራ አጣሁ ብሎ ይሄን ሁሉ ሰራተኛ መቀነሱ አስደንጋጭ ነው” ብሏል፡፡ ሌላው ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ ተሰናባች በበኩሉ፤ “ድርጅቱ ወደ መንገድ ግንባታ ለመግባት 500 ሚ. ብር ማሽነሪዎችን ካስገባ አራት ወራት እንኳን እንዳልሞላው ገልፆ የህንፃ ግንባታና የመንገድ ግንባታ መጠነኛ ልዩነት ቢኖራቸው እንኳን በስልጠና ሰራተኛውን ወደዚያው ማዞር ይቻል ነበር ብሏል፡፡
ሌላዋ የድርጅቱ ተሰናባች ለአዲስ አድማስ በሰጠችው አስተያየት፣ ድርጅቱ አራት ኪሎ ሳይት ላይ በጀመረው አዲስ ግንባታ አዳዲስ ሰራተኞችን እየቀጠረ ባለበት ሁኔታ ነባሮቹንና በድርጅቱ ውስጥ ልምድ ያዳበሩትን መቀነስ ተገቢ አለመሆኑን ተናግራለች፡፡
ሰራተኞቹ ባነሷቸው ነጥቦች ዙሪያ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ የ500 ሚሊዮን ብር ማሽነሪዎች ማስገባታቸውን አምነው መሳሪያዎቹ የገቡት ከአራት ወራት በፊት ሳይሆን ከአንድ ዓመት በፊት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከሁለትና ከሶስት የመንገድ መስሪያ ዶዘሮች በስተቀር 99 በመቶው የህንፃ ግንባታ ማሽነሪዎች መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል። ለአዳዲስ ስራዎች መጥፋት ምክንያቱን ጠይቀናቸው፤ አዳዲስ የውጭ ተወዳዳሪ ኮንትራክተሮች መብዛት እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ “እኛ በአብዛኛው የሚያሰራን መንግስት ነው” ያሉት አቶ ሰይፉ፤ መንግስት በብዛት ጨረታ የሚያወጣው ከጥር በኋላ እንደሆነ ጠቁመው እስካሁን አዳዲስ ስራዎች እንዳላገኙና ወደፊት ስራዎቹ ሲገኙ እነዚሁኑ ሰራተኞች መልሰው እንደሚቀጥሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አዳዲስ ሰራተኞች መቅጠራቸውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የተአኮን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎይቶም ወ/ገብርኤል፤ “አራት ኪሎ ላይ አዳዲስ ሰራተኛ አልቀጠርንም፤ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ስናገኝ በስልጠናና በልምድ ኢንቨስት ያደረግንባቸውን መልሰን እንቀጥራለን እንጂ አዳዲስ አንቀጥርም” ሲሉ መልሰዋል፡፡ በቀጣይ የሚሰናበቱ አሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ኃላፊው፤ በጥናትና በተረጋጋ ሁኔታ ድርጅቱ ለጊዜው መቀነስ ያለበትን ቀንሶ መጨረሱንና በቀጣይ የሚቀነስ ሰራተኛ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረቱም ሆነ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች አለመገኘት ወቅታዊና ብዙ የማይቀጥል የማይቀጥል ነው ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡  


Read 8833 times