Sunday, 20 November 2016 00:00

‘ሰው ያልረገጠው’ የውቅያኖስ መሀል ደሴት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…አንድ ጊዜ የሆኑ የግብጽ ዲታ ደሴት እገዛለሁ ብለው አልነበር!፡ ሀሳብ አለን… የሆነ ውቅያኖስ አካባቢ ባለቤት የሌለው ደሴት አማረንማ! አለ አይደል… ‘ሰው ያልረገጠው’ መሬት ፈልጎ ‘ፉርሽ ባትሉኝ’…ብለን ይዞታ ማጠናከር አማረንማ!
“ስማ፣ ኑሮን እንዴት ይዘኸዋል?”
“ምን እይዘዋለሁ፣ እሱ ጠፍሮ ይዞኛል እንጂ! ገንዘብ እንዲህ አቅም ያጣበት ዘመን!”
“ሁላችንም ነን እባክህ፣ ልጄ አፍተር ሼቭ ተቀባብተን ብንወጣ… አለ አይደል… ቤት ውስጥ ጭልፋ ላይ ቀባ የምናደርጋት ሹሮ ማግኘቱ እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ የጓዳችንን ጉድ እኛ ነን የምናውቀው…”
“እባክህ የእኔን ያህል የሚሆን የለም፡፡ አሁን አሁንማ ቤታችን ሁሉም አንድ ሁለቴ ጎረስ የሚያደርጋት ቲማቲም ከተገኘች የዓመት በዓል ያህል ነው የሚሰማን፡፡”
አንተ ቲማቲም ትላለህ…እኔ ቤት ጤፍ እንደ ስኳር ሁለት ኪሎ፣ ሦስት ኪሎ እያልን ልንገዛ ምንም አልቀረን…”
እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡ በተገናኘን ቁጥር ፈታ የሚያደርግ፣ መንፈስ የሚያረጋጋ ነገር ከመጨዋወት ይልቅ ስለ ኑሮ መወደድ፣ ስለ ዕቃዎች ዋጋ ጣራ መንካት፣ ህይወት ተስፋ አስቆራጭ ስለመሆኗ የማናወራበት፣ ነጋ ጠባ፣ ስለኑሮ መወደድ ብቻ የማናወራበት፣ ነጋ ጠባ “ዛሬ ደግሞ ምን የእህል አይነት ጨምሮ ይሆን?” እያልን የማንሰጋበት፣ “እኔስ ግዴለም ልጆቼን ምን ላብላ የማንባባልበት ‘ሰው ያልረገጠው’ የውቅያኖስ መሀል ደሴት አማረን፡፡
ነገሩ ሁሉ…አለ አይደል…“ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል…” እየሆነብን ተቸግረናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዓመት ከሰባት ወር ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ ቅቤ ውስጥ ተነከረው የኖሩ የሚመስሉትም፣ ሰባት ዓመት ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ “ንቅንቅ ትልና አንተን አያድርገኝ!” ተብለን ዱቄት ሲነፋብን የከረምን የምንመስለውም ስለ ኑሮ “እሪ!” ስንል ነገሩ እንዴት ነው ብሎ የሚያጠና፣ የሚመራመር ምናምን ጠፋሳ!
እናላችሁ …የሆነ ቦታ ሻይ ቡና ለማለት ተቀምጣችኋል፡፡ አሥራ ምናምን ደቂቃ የሚታዘዛችሁ አታገኙም፡፡ እናንተ ከአሁን፣ አሁን አዩኝ ብላችሁ ቁልጭ፣ ቁልጭ ስትሉ የሆኑ ሰዎች ይገባሉ፡፡ እነሱን ለመታዘዝ አምስት አሳላፊ ይደነቃቀፋል፡፡ የቤቱ ‘ሥራ አስኪያጅ’ ሁለት እጁን ወደ ሁዋላ ቆልፎ ይሽቆጠቆጣል…እነሱ ‘የቤት ሰዎች’ ናቸዋ! (ብዙ ቦታዎች… ‘የቤት ሰዎች’ ካሉ እናንተን ከመጤፍ የሚቆጥራችሁ አታገኙም፡፡) እናማ…በገንዘባችሁ ከማንም እኩል መስተናገድ ሲገባችሁ… ‘ለቤት ሰዎች’ ቅድሚያ የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች ሲበዙብን…አለ አይደል… ‘ሰው ያልረገጠው ደሴት’ የማንመኝሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሄደን የአንዳንድ ሠራተኞች ግልምጫና፣ አቀባበል እያንገበገበን ተቸግረናል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩል እዚህ አገር የሆነ ደህና ነገር ብልጭ ብሎ ደግሞ ድርግም የሚል ነገር አለው።  አንዳንድ ቦታ ሻል ሲል፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ብሶበት ቁጭ ይላል፡፡
“ስሚ አንቺ በየቀኑ ነው እንዴ እዚህ መሥሪያ ቤት የምትመላለሺው!”
“አንቺስ ያው አይደለሽ!”
“ምን ሆነሽ ነው?”
“ሁሉ ነገሩ አልቆ መፈረም ብቻ የቀረው ደብዳቤ ለመውሰድ ይኸው ስመላለስ አምስተኛ ቀኔ…”
“ጉዳይሽ ችግር አለው አሉሽ እንዴ…”
“ምንም ችግር የለውም፡፡ የሚፈርሙት ሰዎች የሉም፡፡ አንደኛው “ስብሰባ ሄዷል” ይባላል፣ ሌላኛው “ዛሬ አልገባም ነገ ነይ…” ይባላል፣ በማግስቱ ስመጣ፣ “ጉዳይ ገጥሞት አሁን ወጣ…” ይባላል…አሁንስ ምርር ነው ያለኝ…”
“ይኸው እኔ ከተከፈተ አራት ወር እንኳን ያልሞላው ፋይል አልተገኘም ተብዬ ስመላለስ ሳምንት ሊሆነኝ ነው፡፡”
እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
የምር ግን…ይሄ የአገልግሎት አሰጣጥ ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡ የሆነ ቦታ ለጉዳይ ሄደን “ነገ ጠዋት ልክ በሦስት ተኩል…” እንባላለን፡ እኛ ደግሞ ልክ በሁለት ሰዓት ተኩል ከች እንላለን፡፡ ሦስት ተኩል ያልፋል፣ አራት ተኩል ያልፋል፣ አምስት ተኩል ያልፋል… ለምን እንደማንስተናገድ እንኳን ዘርዝረው ምክንያቱን ሊነግሩን፣ በቅጡ እንኳን የሚያናግረን አጥተን እንደተቁለጨለጭን ምሳ ሰዓት ይደርሳል፡፡
እንዲህ አይነት ነገሮች ሲበዙብን…አለ አይደል… ‘ሰው ያልረገጠው ደሴት’ የማንመኝሳ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአለቆችና አንዳንድ እንደ አለቃ የሚያደርጋቸው ሰዎች ‘ጆብ ዲስክሪብሺን’ ላይ… “እንደፈለገው መሆን…” “እንዳሰኘው መሆን…” ምናምን የሚሉ ሀረጎች አሉበት እንዴ!
እናማ…መብታችንን ለማግኘት፣ ግዴታችንን ተወጥተን አገልግሎት ለማግኘት በሰው ፊት የማንንገበገብበት፣ “ኦፋ! ኤጭ!…” እየተባልን የማንመናጨቅበት፣ ‘ሰው ያልረገጠው’ የውቅያኖስ መሀል ደሴት አማረን፡፡
ነገሩ ሁሉ…አለ አይደል…“ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል…” እየሆነብን ተቸግረናል፡፡
“ስማ ሰዉ ምን ነካው?”
“ምን ነካው ብሎ ነገር እንዴት ነው!…”
“እዛ ማዶ ሆኖልህ የኦለምፒክ አሎሎ ውርውራ ውድድር ይመስል ምራቁን እግርህ ስር ይወረውርብሀል…”  
“እሱንማ እኔ አልነግርህም፤ ትናንትና አንዱ በሰፊው መንገድ መሀል ትከሻዬን ብሎ ያንገዳግደኛል። አይደለም ይቅርታ ሊጠይቀኝ፣ ጭራሽ ገላምጦኝ ሄደልህ…”
“እሱማ በየቀኑ የሚገጥም ነው…ደግሞልህ በሰማንያ ምናምን ኪሎው ሰበብ ፈላጊ ስቲኪኒ እግርህ ላይ ቆሞ ምንም ነገር የነካ አይመስለውም። እንደውም አንተ ይቅርታ እንድትጠይቀው ይጠብቃል…”
እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምግባር ምናምን የሚባለውን ነገር በዕዳ አስይዘነዋል እንዴ! ሰፊ የመኪናው መንገድ እያለለት፣ እግረኛ መንገድ ላይ ዘሎ ገብቶ ድንብርብራችንን የሚያወጣ ክንዱን የተነቀሰ፣ የምናምን ሺህ ብር መነጽር የሰካ ዕድሜ የጠገበም፣ ያልጠገበም ‘ስልጡን’ የፈላባት ከተማ ሆናለች እኮ! መኪናውን አቁሞ ወርዶ የሆነ ተቋም ግምብ ስር እጁን ወደ ዚፑ የሚሰድ ‘ስልጡን’ እየበዛ፣ እየተባዛ ያለባት ከተማ ሆናለች እኮ!…እንዲህ አይነት ነገሮች ሲበዙብን…አለ አይደል… ‘ሰው ያልረገጠው ደሴት’ የማንመኝሳ!
እናማ…የሰዎች ምግባር አድሮ ምናምን የማይሆንባት፣ ስልጣኔ ሂዩማን ሄይርና፣ የክንድ ላይ ንቅሳት ያልሆነበት፣ ‘ሰው ያልረገጠው’ የውቅያኖስ መሀል ደሴት አማረን፡፡
ነገሩ ሁሉ…አለ አይደል…“ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሸጦ አህያ ይገዛል…” እየሆነብን ተቸግረናል። እናማ በብዙ ምክንያቶች…‘ሰው ያልረገጠው’ የውቅያኖስ መሀል ደሴት አማረን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Read 4283 times