Print this page
Sunday, 13 November 2016 00:00

ጭልፊቱ

Written by  ድርሰት፡ ጂኦቫኒ ቦካቺዎ ትርጉም፡ በተፈራ ተክሉ
Rate this item
(10 votes)

     ፍሎረንስ ውስጥ የሚኖር አንድ በሀብቱ ብዛት፣ በጦር ስልቱና በጨዋነቱ የሚታወቅ ፌዴሪጎ የሚባል ወጣት ነበረ፡፡ ሁሉም ጨዋ ሰዎች እንደሚያጋጥማቸው ሁሉ፣ እሱም ሞና ጆቫኒ ከምትባል በቁንጅናዋ በመላው ፍሎረንስ ከታወቀች ሴት ጋር ፍቅር ያዘው፡፡ ፍቅሯን ለማሸነፍም በፈረስ ላይ ሆኖ የጦር ግጥሚያዎችን ያደርጋል፣ ድግስ ይደግሳል፣ ገንዘቡን ያለ ስስትም ይረጫል፡፡ እሷ ግን ለነዚህ ሁሉ ነገሮች ደንታ አልነበራትም፡፡
ፌዴሪጎ በቅጥ የለሽ ብኩንነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብቱ ተመናመነ፡፡ ለሞና የነበረው ፍቅር እየበረታ ቢሄድም በከተማዋ ውስጥ እንደቀድሞው ለመኖር አቅም እንደሌለው ተገነዘበ፡፡ ወደ ካምፒ  ሄዶ በዚያ በቀረችው ትንሽ የእርሻ መሬቱ ላይ የድህነት ኑሮውን መምራት ጀመረ፡፡ ብቸኛ ጓደኛውም በዓለም ምርጥ ዝርያ የተባለ አንድ ጭልፊት ነበር፡፡
አንድ ቀን የሞና ጆቫኒ ባለቤት በጠና ታመመ። ሞት አፍጥጦ እንደመጣበት ሲያውቅም በጊዜ ተናዘዘ፡፡ ባለቤቷ እጅግ ባለጸጋ ነበረና፣ ሀብቱን በሙሉ በፍጥነት እያደገ ለመጣው ልጃቸው አወረሰው፡፡ ሞናን በጣም ይወዳት ነበረ፡፡ ምናልባት ልጁ ሳይወልድ ከሞተ፣ እሷ ወራሽ እንድትሆንም ተናዘዘላት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱ አለፈ፡፡
ባላቸው የሞተባቸው ሴቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ ሞና ጆቫኒ፣ ዓመቱን የፌዴሪጎ የእርሻ ቦታ አቅራቢያ በሚገኘው የገጠር ቤቷ ውስጥ ለማሳለፍ ከልጇ ጋር ሄደች፡፡ ልጇም ከፌዴሪጎ ጋር ወዳጅነት መሥርቶ፣ ከውሾችና ከጭልፊት ጋር መደሰት ጀመረ። የፌዴሪጎ ጭልፊት ሲበር እየተመለከተ በእጅጉ ከመደመሙ የተነሳ የራሱ ሊያደርገው መመኘቱ አልቀረም፡፡ ነገር ግን ፌዴሪጎ ለጭልፊቱ ያለውን የተለየ ፍቅር በመገንዘቡ ለመጠየቅ አልደፈረም፡፡ ትንሽ ቆይቶም ልጁ ታመመ፡፡
እናት ብቸኛ ልጇ ስለነበር ደነገጠች። ያልወሰደችው ሃኪም ቤት የለም፡፡ ሆኖም ሊሻለው አልቻለም፡፡ ቢቸግራት የሚፈልገው ነገር ካለ፣ እንዲነግራት ትለማመጠው ጀመር፡፡ ከብዙ ውትወታ በኋላ ልጁ የሚፈልገውን ጠየቃት፡- “እናቴ፤ የፌዴሪጎን ጭልፊት ልታመጭልኝ ከቻልሽ በፍጥነት የሚሻለኝ ይመስለኛል፡፡”
እናት ለአፍታ በዝምታ ተውጣ ምን ማድረግ እንዳለባት ማሰብ ጀመረች፡፡ ፌዴሪጎ ረዘም ላለ ጊዜ ያፈቅራት እንደነበር ታውቃለች፡፡ ይሁንና አንድም ቀን የእግዜር ሰላምታ እንኳን ሰጥታው አታውቅም፡፡ “እንዴት አድርጌ ነው ይህንን ጭልፊት ስጠኝ ልለው የምችለው? እንደምሰማው ጭልፊቱ ብቸኛው  የሕይወቱ አጋር ነው፣ እንዴት አይነት ሀሳብ የለሽ ብሆን ነው፣ ከዚህ ውጭ ደስታ ከሌለው ጨዋ ሰው ላይ ይህንን ነገር የምውሰደው?”
ብዙ አወጣች አወረደች፡፡
ብትጠይቀው ጭልፊቱን እንደማይከለክላት ብታውቅም፣ ምን ብላ መጠየቅ እንዳለባት ግራ ስለገባት፣  ኀፍረትም ስለተሰማት፣ ለልጇ ፈጣን መልስ ልትሰጠው አልቻለችም፡፡  በመጨረሻ ግን ለልጇ ያላት ፍቅር አሸነፋት፡፡ በምንም አይነት መልኩ የልቡን ሞልታለት፣ ከበሽታ መፈወስ እንዳለበት ወሰነች፡፡
“አይዞህ ልጄ፤ አንተን ይሻልህ እንጂ ነገ በጥዋት ሄጄ ላመጣልህ ቃል እገባለሁ፡፡” አለችው፤ በእርግጠኝነት፡፡
ልጁ ማመን አልቻለም፤ በደስታ ፈነጠዘ። ከህመሙም ትንሽ የተሻለው መሰለ፡፡ እናቱ እንዳለችውም፤ በጥዋት አንዲት አጃቢ አስከትላ፣ ወደ ፌዴሪጎ ጎጆ አመራች፡፡ ያለፉት ጥቂት ቀናት የአየር ሁኔታ ለአደን አመቺ  ስላልነበረ፣ ፌዴሪጎ ጭልፊቱን ይዞ ከመውጣት ተቆጥቦ፣ ጓሮው ውስጥ በሌላ ሥራ ተጠምዶ ነበር፡፡ የሞና ጆቫኒን ድምፅ ሲሰማ፣ በእጅጉ ተደንቆና ተደስቶ፣ ወደ በሩ እየከነፈ ሄደ፡፡ እንዳየችው በማራኪ ፈገግታ ተሞልታ፣ እንደናፈቀ ሰው ሰላምታ ሰጠችው፡፡ ፌዴሪጎ ጨዋነት ያልጎደለው ሰላምታ አቀረበላት፡፡   
“እንዴት ነህ  ፌዴሪጎ? ዛሬ እዚህ የመጣሁት እኔን ከልክ በላይ አፍቅረህ የደረሰብህን ጉዳት ለማካካስ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ካንተ ጋር እራት ለመብላት አስቤያለሁ፡፡” አለችው፤ሞና፡፡
“እመቤቴ” አለ ፌዴሪጎ በትህትና፤ “በአንቺ ምክንያት የደረሰብኝ የማስታውሰው ጉዳት የለም፤ ነገር ግን ብዙ ጥሩ ነገር አግኝቼ ነበር፤ እኔም ዋጋ ነበረኝ ከተባለ ምክንያቱ አንቺና ላንቺ የነበረኝ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ደግ የሆነ ጉብኝትሽ ለኔ ውድ ከመሆኑ የተነሳ፣ ያጠፋሁትን ነገር ሁሉ እንደገና አጠፋው ነበር፤ ነገር ግን አሁን የመጣሽው እልም ያለ መናጢ ድሃ ሰው ቤት ነው፡፡”
ይህንን ብሎ በትህትና ወደ ቤቱ ይዟት ገባ፡፡ ከዚያም ወደ ጓሮው ተያይዘው ወጡ፡፡
“እመቤቴ፤ እናንተ እዚህ አረፍ በሉ፤ እኔ አንዳንድ ነገር አዘጋጅቼ እመለሳለሁ፡፡” ብሏት ወደ ውስጥ ገባ።
ሃብቱን ሁሉ አባክኖ ያጣ የነጣ ድሃ መሆኑ እንደዛሬው ተሰምቶት አያውቅም፡፡ ለዚች እመቤት ክብር የሚመጥን ነገር በቤቱ ውስጥ አስሶ አስሶ አጣ፡፡ በጸጸት ተቃጠለ፡፡ ገንዘብም ሆነ በአራጣ የሚያሲዘው ነገር አጥቶ አቅሉን እንደ ሳተ እብድ፣ እላይ ታች ሮጠ፡፡ የሚያፈቅራትን እመቤት በመስተንግዶ ለማስደሰት በእጅጉ ጓጉቷል፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ቆሞ ሳለ፣ድንገት ዐይኑ በሳሎኑ የብረት ዘንግ ማረፊያው ላይ እተቀመጠው ጭልፊት ላይ አረፈ፡፡ ወፉን አውርዶ በዓይንና በእጁ መዘነው፡፡ ለዚች አይነት እመቤት ሊመጥን የሚችል ምርጥ ምግብ ነው ብሎ ወሰነ፡፡ ከዚያም ያለ ምንም ማቅማማት፣ አንገቱን ቆለመመው፡፡ ላባውን ነጨት ነጨት አድርጎም፣ መጥበሻ ላይ ሰክቶ ያገላብጠው ጀመረ፡፡ እጅግ ነጭ የሆነ የጠረጴዛ ልብስ ገበታው  ላይ አንጥፎ፣ ፊቱ በደስታ  እየተፍለቀለቀ፣ ጓሮ ሄዶ  እመቤቲቱ ወደ ውስጥ እንድትገባ ጋበዛት፡፡  
እመቤቲቱና አጃቢዋ፣ በፌዴሪጎ ወደር የለሽ አስተናጋጅነት፣ የቀረበላቸውን ያንን ምርጥ የጭልፊት ጥብስ አጣጥመው ተመገቡ፡፡ ማእዱ ተነስቶ እየተጨዋወቱ ጥቂት ጊዜያት ካሳለፉ በኋላ፣ እመቤቲቱ የመጣችበትን ጉዳይ ልትነግረው መለሳለስ ያዘች፡-
 “ፌዴሪጎ፤ እርግጠኛ ነኝ ዋና የመጣሁበትን ጉዳይ ስትሰማ ዐይን ባወጣው ድፍረቴ ትደነቃለህ፡፡ ነገር ግን የወላጅነት ፍቅርን እንድታውቅ የሚያስችልህ ልጅ ቢኖርህ ኖሮ፣ በመጠኑም ቢሆን ይቅር ልትለኝ እንደምትችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን አንተ ባይኖርህም እኔ ልጅ እንዳለኝ ታውቃለህ፤ እናም ከተለመዱት የእናትነት ሕጎች ማምለጥ አልችልም፡፡ በእነዚህ ሕጎች ተገድጄ - ደንቦችንና ሥነምግባሮችን ጥሼ፣ አንድ ነገር በስጦታ እንድትሰጠኝ ልጠይቅህ መጥቻለሁ፡፡ ጭልፊቱን ነው፡፡ ለአንተ ውድ ንብረትህ መሆኑ አልጠፋኝም፤ ምክንያቱም ትቶህ የጠፋው ሀብትህ ምንም አይነት ሌላ ደስታ፣ መዝናኛና  መጽናኛ እንዳልተወልህ አውቃለሁ፡፡ ግን ደግሞ ለልጄ ይሄን ጭልፊት  ካልወሰድኩለት የያዘው በሽታ ተባብሶበት ላጣው እችላለሁ፡፡ ስለዚህ ልለምንህ፤ ምንም ባላስገኘልህ ለኔ በነበረህ ፍቅር ሳይሆን በብዙ ሰዎች በማይስተዋለውና በአንተ በተንፀባረቀው ታላቅ ክቡርነትህ ብትሰጠኝ ደስ ይልሃል፣ ወስጄው በዚህ ስጦታ ምክንያት የልጄን ሕይወት አተረፍኩ ማለት እንድችልና ላንተም የዘላለም ታዛዥ እንድሆን ያደርገኛል፡፡”
ፌዴሪጎ አንዲትም ቃል ሳይተነፍስ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፡፡ እመቤቲቱም በመጀመሪያ የለቅሶው መንስዔ ከሚወደው ጭልፊቱ ጋር ሊለያይ በመሆኑ አዝኖ መስሏት፣ ጥያቄዋን ለመተው ጫፍ ላይ ደርሳ ነበር፡፡ ነገር ግን ራሱን ከለቅሶው ገትቶ፣ መልስ እስኪሰጣት በትዕግስት ጠበቀችው፡፡ እንባውን እየጠራረገም ምክንያቱን ነገራት፡-
“እመቤቴ፤ እግዚአብሄር ፈቅዶት ፍቅሬን ባንቺ ላይ እንዳሳርፍ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ዕድል ከእኔ በተቃራኒ እንደሆነች ይሰማኛል፤ በዚህም ሳዝን ቆይቻለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ካደረገችው ጋር ሳነጻጽረው ያለፉት ሁሉም ብርሃን ነበሩ ማለት እችላለሁ፡፡ ሀብት ተትረፍርፎበት የነበረውን ቤቴን አይመጥነኝም ብለሽ አለመጎብኘትሽና አሁን በዚች የድሃ ጎጆዬ መጥተሽ፣ ትንሽ ስጦታ ስትጠይቂኝ ዕድል እንድሰጥሽ አለመፍቀዷን ሳስበው፣ መቼም ቢሆን ከዕድል ጋር ሰላም እንደማላወርድ ይሰማኛል። ለምን ልሰጥሽ እንደማልችል በአጭሩ ልንገርሽ፡- በደግነት ከኔ ጋር እራት ለመብላት እንደፈለግሽ ከነገርሽኝ በኋላ ለአንቺ የሚገባሽ፣ ለክብርሽ የሚመጥንሽ  ምርጥ ምግብ ሳሰላስል፣ የጠየቅሽኝን ጭልፊት አስታወስኩት፤ እናም  ለእራት ጠብሼ አቀረብኩት፤ የተመገብሽው እሱን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ወፉን የፈለግሽው ከነሕይወቱ መሆኑን ተረዳሁኝ፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ ያንን ማድረግ አለመቻሌ መቼም ቢሆን ሰላም ሲነሳኝ ይኖራል፡፡”
ይህን ካለ በኋላ ለማረጋገጫ የጭልፊቱን ላባዎች፣ እግሮችና መንቆር አሳያት፡፡ እመቤቲቱም ይህን ሁሉ ነገር ስትሰማና ስታይ በመጀመሪያ ለአንዲት ሴት ምግብ ለማዘጋጀት ብሎ ያንን የመሰለ ጭልፊት በመግደሉ ኮነነችው፡፡ ከዚያም ምንም ዓይነት ድህነት ሊያጠፋው ያልቻለውን የነፍሱን ታላቅነት በልቧ  አመሰገነች፡፡ ነገር ግን ለልጇ የተመኘችውን ጭልፊት የማግኘት ተስፋዋ ጨልሞ እያዘነች  ወደ ልጇ ተመለሰች፡፡ ብዙም ቀናት ሳይቆይ ልጇ በመሞቱ ጥልቅ ሐዘን ውስጥ ወደቀች፡፡
 እያነባችና እያማረረች ጥቂት ጊዜያት ገፋች። የተትረፈረፈ ሀብት እያላት ገና በወጣትነቷ ራሷን መጣሏ ያልተዋጠላቸው ቤተሰቦቿ፤ እንደገና ባል እንድታገባ ወተወቷት፡፡  እሷ ማግባት ባትፈልግም እነሱ ግን አልተዋትም፡፡ በመጨረሻ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣ፣ ለማግባት መወሰኗን ለቤተሰቦቿ ነገረቻቸው፡-
 “እንዳላችሁት ለማግባት ወስኛለሁ” አለቻቸው ለቤተሰቦቿ፤ “ነገር ግን ሌላ ሰው ሳይሆን ፌዴሪጎን ነው ማግባት የምፈልገው”
ይህን ስትል ቤተሰቦቿ ሳቁባትና፤ “ምን እያወራሽ ነው አንቺ ሞኝ? በዚህ ዓለም ላይ ቤሳ ቤስቲን የሌለው ሰው ለምን ታገቢያለሽ?” ሲሉ ጠየቋት፡፡
እሷ ግን እንዲህ አለቻቸው፡- “ወንድሞቼ፤ እንዳላችሁት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ነገር ግን በደንብ የሚያስተዳድረው ሰው ካጣ ገንዘብ ይልቅ፣ ገንዘብ የሚፈልግ ሰው እመርጣለሁ”
ቁርጠኝነቷን የተመለከቱትና የፌዴሪጎን ጥሩ ጎኖች የሚያውቁት ቤተሰቦቿ ፣ ከእነ ሀብቷ ከምስኪኑ  ፌዴሪጎ ጋር በጋብቻ አጣመሯት፡፡ የማታ ማታ ፌዴሪጎ፣ ፍቅርም ሃብትም እጁ ገባ፡፡ ከዕድልም ጋር እርቅ አወረደ፡፡   

Read 3983 times