Sunday, 13 November 2016 00:00

‘ሰውየው’ ሰተት ብለው ገቡ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እንግዲህ ጉዳያችን አድርገነው የለ… የእውነት እኚህ ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ ተመረጡ! ሰዉ ሁሉ ‘ሲደነግጥ’ እኔ የማልደነግጥሳ! መሀል ከተማ አካባቢ ያሉ ጫማ ጠራጊዎች እንኳን የሰውየው ‘ነጩ ቤተ መንግሥት’ መግባት መክፈቻ ነበሩ፡፡ አንድ ጊዜ  ሰውየው ምን ብለው ነበር አሉ መሰላችሁ…
“ከተመረጥኩ ፕሬዝዳንት አልሆንም ልል እችላለሁ…” ብለው ነበር፡፡ እንደ ልባቸው ተናግረው ሰተት ብለው ገቡ፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛም ዘንድ እኮ እንደልባችን ተናግረን በየቦታው ‘ሰተት ብለን’ የምንገባ አለን፡፡ “ይሄ ሰውዬ በቃ አፉ ለከት የለውም!” እየተባለ በየድራፍቱና በየማኪያቶው ስንወገዝ ከርመን፣ መጨረሻ የፈለግነው ቦታ ሰተት ብለን መግባት ነው፡፡
እኔ የምለው… ሰውየው እንኳንም የእኛን ሚዲያ ሲሰሙ አልከረሙ፡ ጉዳችን ይፈላ ነበራ! እንደ እኛ ‘አንዳንድ’ (ለዲፕሎማሲ የገባች ቃል…) የኤፍኤም የአሜሪካ ምርጫ ትንታኔዎች ቢሆን ኖሮ፣ ትረምፕ አይደለም በሰማይ ጠቀስ ህንጻቸው መቀመጥ፣ እኛን ጥገኝነት ይጠይቁ ነበር፡፡ ልክ ነዋ!…እኛ እኮ አስቀድመን አሸናፊዋን ተናግረን ነበር፤ የሚሰማን አጣን እንጂ! ሰውየው ዋጋ እንደሌላቸው፣ በጠቅላላ የአሜሪካ ህዝብ እንደማይወዳቸውና በሂላሪ በዝረራ እንደሚሸነፉ ተናግረን ነበር፤ የሚሰማን አጣን እንጂ!
ሀሳብ ለመስጠት ያህል በ‘ከት ኤንድ ፔስት’ የምንተነትናቸውን ዓለም አቀፍ ዜናዎች ምንጮች…አለ አይደል… በዛ ብናደርጋቸው አሪፍ ነው፡፡ ‘ነጻ ሚዲያ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ገለልተኛ ሚዲያ የሚባል ነገር የለም’ የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናም እነኚህ ታላላቆቹ ቻነሎች ‘ከላይ ተቀብተው የተላኩ’ ይመስል… “የሚናገሩት ሁሉ መሬት ጠብ አይልም” አይነት እምነት አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…እኚህ ትረምፕ የሚሏቸው ሰውዬ፤ አንድ ጊዜ ስለ ሴት ልጃቸው ኢቫንካ እንዲህ ብለው ነበር…
“ኢቫንካ ልጄ ባትሆን ኖሮ፣ አወጣት ነበር፡፡”
እናማ… እንዲህ እንደ ልባቸው ተናግረው፣ ‘ሰተት ብለው’ ገቡ፡፡ አለ አይደል…“እንዴት፣ እንዴት ቢያስቡ ነው የገዛ ልጃቸው ላይ እንዲህ አይነት ነገር የሚናገሩት!” አልን፤አላልን ሰተት ብለው ገብተዋል፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እነኚህ የዜና ምንጭ ያደረግናቸው ቻነሎች አቀራረባቸው አሪፍ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አቅራቢዎቹ… አለ አይደል… እንደ አንደኛ ምናምን ክፍል…
“ውጣና ተንኮለኛው ከበደን አንብብ…” አይነት አነባበብ ሳይሆን ስለሚናገሩት ነገር የሚያውቁ ናቸው፡፡ እህ ብለን የምንሰማቸውም ለዚህ ነው። ግን ደግሞ ከጀርባ የባለቤቶችና የ‘ሼርሆልደሮች’ ፍላጎት፣ የትልልቅ ማስታወቂያ አስነጋሪዎች ፍላጎቶች እንዳሉ ማወቁ አሪፍ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ሀይለኛ ‘የቃላት ጨዋታ’ እንዳለም ማወቁ አሪፍ ነው፡፡ በ‘መስመሮች መሀል ማንበብ’ የሚሏትም ነገር አለች፡፡ እናማ…የሚዲያ ሰዎቻችን፣ ‘ከት ኤንድ ፔስት’ የመሰለ ‘ጊዜ ቆጣቢ ዘዴ’ ባይኖርም፣ በ‘መስመሮች መሀል ማንበብ’ መልመዳችን አሪፍ ይሆናል፡፡ በአሜሪካ ምርጫ ዘገባዎች ላይ ብዙ፣ በጣም ብዙ የተሳሳቱና የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሆኑ መረጃዎች ስንሰማ ከርመናል፡፡ ልጄ ነገርዬው ፈረንካ ነው፡፡ የትልልቆቹ ቻነሎች ዋና ግብ የተመልካች ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ እናማ… ከአንድ ምንጭ ብቻ ከመውሰድ ከተለያዩ ምንጮች መውሰዱ አሪፍ ነው፡፡
እናላችሁ… አንድ ጊዜ እኚሁ ጋሼ ትረምፕ እንግዶች ይመጡባቸዋል፡፡ እናማ… አንዲት ሴት ሠራተኛቸው፣ እንግዶቹ ለምሳ ምን ይፈልጉ እንደሆነ መጠየቅ ትጀምራለች፡፡ ይሄኔ ትረምፕ እሷን አባረው በሌላ ተኳት፡፡ ለምን መሰላችሁ…ሴትዮዋ ቆንጆ አልነበረችማ!
ሁዋይት ሀውስ ያለሽ ምድረ ‘አስቄ’ ሁሉ ወዮልሽ! ቂ…ቂ…ቂ… እኛ ዘንድ “አፍንጫ ጎራዳ…”  ምናምን የሚያዋድሱ ዘፈኖች መኖራቸውን ብትሰማ ኖሮ የትረምፕ ሠራተኛ ‘አሳየለም‘ ጠይቃ ነበር! ቂ…ቂ…ቂ… (ታየኝ!)
እግረ መንገዴን…ይቺን ስሙኝማ፣ሰውየው ድንገት ሳይታሰብ የሆነች አሪፍ መኪና ይገዛል፡፡ የቅርብ ጓደኛውም ሲያገኘው ግራ ይገባዋል፡፡
“ብለህ ብለህ መኪና መዋስ ጀመርክ?”
“እባክህ፣ የእኔ መኪና ነች፡፡”
ጓደኛ ሆዬ በድንጋጤ ኮሌስተሮሉ፣ ወይ የሆነ ነገሩ ከፍ ይላል፡፡
“እውነት የአንተ መኪና ነች!”
“አዎ፣ ምን የሚያስገርም ነገር አለው?” ሲል ሰውየው ይመልሳል፡፡
እሱዬው እኮ አይደለም መኪና የመግዛት አቅም ሊኖረው በኮንትራት ታክሲ እንኳን የሚሄደው ሌላ ሰው ከከፈለለት ነው፡፡ ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“በአየር ካርታ ላይ የማይታይ ገንዘብ ከየት አመጣህ!”
አረፍ አይደል! እናላችሁ… ‘በአየር ካርታ’ ላይ ሳይታዩ ምድር ላይ ከች የሚሉ ነገሮች መአት ናቸው።
እኔ የምለው…እኛ መካከለኛ ገቢ ለመግባት ስንት ዘመን ወረፋ ይዘን እየጠበቅን… መካከለኛ ገቢ ስንደርስ ምን አይነት ኑሮ እንደሚኖረን በ‘ፋንታሲ’ እየዋኘን… አለ አይደል… ሰዉ በየት እያቋረጠ ነው ጫፍ የሚወጣው! አራት ኪሎን ወደ ጎን ትቶ በእሪ በከንቱ አቋርጦ እንደሚመጣ ታክሲ…መካከለኛ ገቢን በየት በኩል ነው ወደ ጎን ትተው፣ የፈረንካ ክምር ላይ የሚቀመጡት!
እናላችሁ…የቫቲካኑ ጳጳስ ፍራንሲስ ስለ ትረምፕ ተወዳዳሪነት የተጠየቁ ጊዜ…
“የትም ይሁን የት ግንቦች ስለ መገንባት የሚያስብና ድልድዮችን የማይገነባ ሰው ክርስትያን አይደለም…” ይላሉ፡፡ ትረምፕ ሆዬ ምን ቢለው ቢመልሱ ጥሩ ነው…
“ቫቲካን ጥቃት ሲሰነዘርባት ጳጳሱ፣ ዶናልድ ትረምፕ ፕሬዝደንት ሆኖ በተመረጠ ኖሮ ብለው ይመኙና ይጸልዩ ነበር፡፡”
ትረምፕ እንደ ልባቸው ናቸዋ! እኔ የምለው…እነሱ ጋ “እንዲህ እንዳትል፣ እንዲህ እንዳታደርግ ገዝቼሃለሁ…” ምናምን አይነት ነገር የለም እንዴ! እኟ ስንት ነገር “ይቅርብኝ…” ብለን የተውነው ግዝት ፈርተን አይደል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞላችሁ…እንግዲህ ትረምፕ አሪፍ ነጋዴ አይደሉም…በቢዝነስ ዘመናቸው 1‚900 ጊዜ ከሳሽ የነበሩ ሲሆን፣ እሳቸው ራሳቸው 1‚450 ጊዜ ተከሰዋል።
ትረምፕን የከሰሳችሁ ሁሉ ሰውየው ትዝ ያላቸውና አብሿቸው የተነሳች ዕለት እናንተን አያድርገኝ፡፡  ቂ…ቂ…ቂ… (ለነገሩ የአሜሪካ ‘ቦተሊካ’ ለዚህ፣ ለዚህ አይነት ነገር አይመችም መሰለኝ፡፡)
በአንድ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ወደ አንዱ ጥቁር ደጋፊያቸው ጣታቸውን ጠቁመው ምን ቢሉ ጥሩ ነው…
“የእኔን አፍሪካ አሜሪካዊ ተመልከቱት…” ብለዋል። ይሄ ልክ “የእኔን አገልጋይ (‘አሽከር’ የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ነው)  እዩት እንደማለት ነው…” ተብለው የትችት ናዳ ወርዶባቸው ነበር። ይኸው… አንደኛውን ነጩ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገብተው አረፉት!
አንድ ጊዜ እንደውም ስለ‘እንትናቸው’ መጠን ወይም ‘ልኬት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ሲፎክሩ ነበር ተብሏል… (አይ አማሪካን!)
እናላችሁ… እኚህ እንደ ልባቸው ናቸው የሚሏቸው ትረምፕ፣ ተናገሯቸው ከሚባሏቸው ነገሮች መሀል እነኚህን እዩልኝማ…
ሜክሲካውያንን፡- “አስገድዶ ደፋሪዎች” ብለዋል…
ጽንስ የሚያቋርጡ ሴቶች፡- “መቀጣት አለባቸው” ብለዋል…
የኔቶ አባሎችን፡- “መዋጮአችሁን ቁጭ አድርጉ” ብለዋል፡፡ (አሁን እንግዲሀ ጉዱ ሊለይ ነው፡፡)
የዘረኛው ኬ.ኬ.ኬ. መሪ ዴቪድ ዲዪክ ሲደግፋቸው፣ ወዲያውኑ ራሳቸውን ከእሱ አላራቁም ብለዋቸዋል…
ለእሳቸው በጎ ያልዘገቡ ጋዜጠኞች፣ በቅስቀሳ ዘመቻዎቻቸው እንዳይገኙ ከልክለዋቸዋል…
ምርጫ ቢያሸንፉ ከ500 ያህል የንግድ ተቋማቶቻቸው አንዱንም እንደማይሸጡ ተናግረዋል..…
በትዊተር ገጻቸው ላይ 239 ተወዳዳሪዎችን፣ ድርጅቶችን፣ ሥራ ላይ ያሉ ፖለቲከኞችንና ታዋቂ ሰዎችን ሰድበዋል…
ወላጆቻቸው በህገ ወጥ መንገድ አሜሪካ የገቡ ልጆችን አስወጣለሁ ብለው ዝተዋል…
11 ሚሊዮን ወረቀት የሌላቸው ስደተኞችን አባርራለሁ ብለዋል…
“የጥቁሮች ህይወት እዚህ ዋጋ ከሌለው፣ እንግዲያው ወደ አፍሪካ ተመለሱ…” ብለዋል…
ጆን ማኬይንን፡- “እሱ ጀግና አይደለም፡፡ ጀግና የሚሆነው ስለተማረከ ነው? ያልተማረኩ ሰዎችን ነው የምወደው” ብለዋል…
እናማ የሰውየው ነገር ገና ነው፡፡ ካለፈው፣ የሚመጣው ባይብስ ነው! …ማስታወቂያው ላይ ያለችው ሴትዮ እንደምትለው…
‘ተረቱ… ይቀጥላል!’
ደህና ሰንብቱልኝማ!







Read 5169 times