Sunday, 13 November 2016 00:00

የአዲሱ ካቢኔ ተስፋዎችና ፈተናዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚገመቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የሟቾች ቁጥር ተጋንኗል የሚለው መንግስት በበኩሉ፤የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አልካደም፡፡ በተቃውሞው በርካታ የመንግስትና የግል ባለሃብቶች
ንብረትም እንደተቃጠለና እንደወደመ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይሄን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ነው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፤የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሹም ሽር የሚያካትት “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች እንደሚመልስ በ2008 መጠናቀቂያ ላይ ቃል የገባው፡፡ በዚህ መሃል በኦሮሞ ባህላዊ የምስጋና ቀን “እሬቻ” በዓል ላይ በተከሰተው አስደንጋጭ የበርካታ ዜጎች ህልፈት ሳቢያ
ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም በተለይ የውጭ ባለሃብቶችን ክፉኛ ያስደነገጠ ውድመትና ዘረፋ በፋብሪካዎቻቸው፣በእርሻቸው፣በአጠቃላይ በንብረቶቻቸው ላይ ተፈጸመ፡፡ ይሄን ተከትሎም የዛሬ ሦስት ሳምንት መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚል ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታወቀ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 200ገ ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔት በመበተን፣ከወትሮው በተለየ መንገድ
በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ የመሰረቱ ሲሆን 9 ሚኒስትሮች ብቻ ባሉበት ሲቀሩ 16 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 5 የሚሆኑት የፓርቲ አባል አይደሉም
ተብሏል፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ለተወካዮች ም/ቤት የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን
ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የንግድ ባለሙያዎች በአዲሱ ሹም ሽር ዙሪያ አስተያየታቸውን ጠይቋቸዋል፡፡

“የካቢኔ ቡድኑን መምራት በጠ/ሚኒስትሩ ብቃት ይወሰናል”
ኢ/ር ፀደቀ ይሁኔ

    ከግንባሩ ፖለቲካ ውጪ የሆነ የካቢኔ ውይይት ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ብዙዎቹ አሁን ወደ ካቢኔው የገቡ በግንባሩ ፖለቲካ ውስጥ ብዙም ተሳታፊ ያልነበሩ ስለሆኑ፣ ምናልባት አብላጫውን በመያዝ ጠ/ሚኒስትሩ ከተለመደው የፖለቲካ ድባብ ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች እንዲለመዱ ይረዷቸዋል ብዬ አስባለሁ። ከአዲሱ ካቢኔ ምን ውጤት ይገኛል የሚለውን አሁን መተንበይ አይቻልም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሄን የካቢኔ ቡድን እንዴት እንደሚጠቀሙበት ማየት ያስፈልጋል። ይህ ቡድን እንዴት ይመራል የሚለው፣ የጠ/ሚኒስትሩን ብቃት ነው የሚወስነው፡፡
አሁን በካቢኔው የተካተቱ እንደነ ኢንጂነር ስለሺ፣ ኢ/ር አይሻ፣ ዶ/ር ነገሪ ዓይነት ሰዎች ያላቸው ብቃት፣ ካቢኔው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በደንብ ውይይት እንዲያደርግ ያግዛል፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሰዎች መግባታቸው፣ በካቢኔ ደረጃ ለውይይት የሚቀርበውን አጀንዳም ከፍ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ እኔ መንግስት ምሁራኖችን ለካቢኔው ሊያሳትፍ ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፤ ነገር ግን ምሁራኑ የዚህን ያህል ፍቃደኛ ይሆናል ብዬ አልጠበቅሁም ነበር፡፡
የእነዚህ ሰዎች ፍቃደኛ መሆን ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተለይ አሁን የፖለቲካ ትኩሳቱ ባየለበት ሰዓት ፈተናው ስለሚበዛ፣ እነዚህ ሰዎች እሺ ላይሉ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እሺ በማለታቸው ተደንቄያለሁ። መንግስት በካቢኔው እንዲካተቱ በመጠየቁ ብዙም አልተደነቅሁም፡፡

==================================

“የተለየ ሀሳብ ያላቸው ቢካተቱ ጥሩ ነበር”
አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ (የግል ቢዝነስ መሪ)

  አዲስ የተሾሙትን የካቢኔ አባላት እምብዛም አላውቃቸውም፡፡ ስለዚህ ብዙ አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡ ነገር ግን የመንግስት አካላት እነዚህን ሰዎች በደንብ ያውቋቸዋል፡፡ በደንብ  መርምረው፣ ተጨንቀው ተጠበው መርጠዋቸዋል፡፡
ነገር ግን አሁንም ያልተለወጠ አንድ ባህል አለ። በስራው ዓለም ከመንግስት ውጪ የተፈተኑ ሰዎች አላየንም፡፡ አንድ ሀገር በምሁራንና በፖለቲከኞች ስብጥር ብቻ ምናልባትም በታጋዮች ----- (በነሱ ስብስብና በነሱ ልምድ ብቻ) ለምን እንድትመራ ይደረጋል? ምናልባት የሚፈለጉት የጥያቄዎቹ መልሶች የሚገኙት እነሱ ጋ ብቻ ይሆን? ኢህአዴግ በሀሳብ የሚሞግቱትንም ሆነ የተለየ ሀሳብ አለን የሚሉትን እያስገባ አብሮ መስራት ቢለመድ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከሹመኞቹ የበለጠ በጣም የሳበኝ፣ ጠ/ሚኒስትሩ በተወካዮች ም/ቤት ንግግራቸው፣ የምርጫ ህግ ሥርዓት መሻሻልን በተመለከተ ደህና አድርገው የገለጹት ጉዳይ ነው።
“አሸናፊው ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ የመውሰድ ነገር አለውና እንደገና ልንፈትሸው የሚገባ ነው፤ 51 በመቶ የምርጫ ውጤት ያገኘ መቶ በመቶውን ይውሰደው፤ የሚለው እንደገና ሊታይ ይገባዋል” ብለዋል።  
49 በመቶው በምን ይወከል የሚለው አሳስቧቸውም፣ ይሄን እንዴት እናስተካክለው - ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ስለዚህ ወደፊት ከተሸናፊዎችም የፓርላማ ተወካዮች ይኖራሉ ማለት ነው። የሚደግፍና የሚቃወም የፓርላማ አባላት ስብጥር ይኖራል ማለት ነው፡፡ ግን እስከ መጪው ምርጫስ፣ እንዴት ይሁን? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይሄን ለማስተካከል የኢህአዴግ አባል ያልሆኑ፣ የተለየ ሀሳብ ሊያፈልቁ የሚችሉ ሌሎች ሰዎችም በካቢኔው ቢካተቱ ጥሩ ነበር፡፡ እንደኔ አንዳንድ ነገሮች ትንሽ ለወጥ ቢሉ ደስ ይለኛል፡፡፡ ግን አሁን የተደረገውንም ቢሆን በመጥፎ አላየውም፡፡  

==================================

“ሹም ሽሩ የህዝብ ተቃውሞ ውጤት ነው”
የሸዋስ አሰፋ
(የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

   በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ሹም ሽር የመጣው በህዝብ ተቃውሞ ምክንያት ነው፡፡ በህዝቡ መቶ በመቶ ተመረጥኩ ቢባልም፣ ህዝቡ ጥያቄ አንስቶ ካቢኔ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እስከ መለወጥ ተደርሷል፡፡ የህዝቡ ዋነኛ ጥያቄ የፖሊሲ ለውጥ ነው። መሰረታዊ የስርአትና የፖሊሲ ለውጥ እንጂ የሰዎች ሹም ሽር አይደለም፡፡ ስለዚህ መልሱ ከጥያቄው በተቃራኒ ነው፡፡ ሁለተኛ አዲሶቹ ሰዎችም ቢሆኑ እዚያው አብረዋቸው የነበሩ፣ በስርአቱ ፖሊሲ የተጠመቁ ናቸው፡፡
አሁን ትምህርታቸው ነው እንደ ትልቅ ነገር ሲጠቀስ የነበረው፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ ላይ የተማረ ሰው ስለጠፋ አይደለም፤የማያሰራ ሁኔታ ስላለ እንጂ፡፡ ብዙ ችግር የተፈጠረው ሹመቶች ችሎታንና እውቀትን ሳይሆን ጎሳን፣ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ስለነበሩ ነው፡፡
እንደኔ የነበሩትን ሰዎች አስቀምጠው፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቢያደርጉ የተሻለ ይሆን ነበር። አሁን ግን ዝም ብሎ የሰዎች ለውጥ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ከሚኒስትርነታቸው የተነሱ ሰዎች ምን ሆነው ነው የወረዱት? የሚለው አልታወቀም፡፡ በምን ጥፋት ነው? በምን ድክመት ነው? ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ ያጠፋውም መቀጣት ይገባዋል፡፡
ለፖሊሲው ለውጥ መልሱ የሰው ለውጥ ነው የሆነው። በዚህ ምክንያት እኔ ብዙ ለውጥ አልጠብቅም፡፡ ግን አሁን የተደረገው ለውጥ ሁሉ የህዝቡ ትግል ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መንግስትም ምላሽ ለመስጠት እየሞከረ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን በፍጥነት ወደ መሬት ማውረድ፣ የእውነት ማድረግ ይጠበቅበታል። የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል የተባለው ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ፣ እኛም ስንጠይቀው የነበረ በመሆኑ በበጎ የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡
=================================

‹‹አሁን የተሾሙት የፖሊሲ አስፈፃሚዎች ናቸው››
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ (የፍልስፍና ምሁር)

   ከዚህ ቀደም በብሄር ተዋፅኦ ወይም በፓርቲ አባልነት ሳይሆን በሙያቸው፣ በስነምግባራቸው የታወቁ ሰዎች መርጠን እናካትታለን ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ግን ያየነው ነገር ሁለት መስፈርት የያዘ ነው፡፡ አንደኛ የብሄር ተዋፅኦ ነው ጎልቶ የታየው፡፡ ሰዎቹን ሲያስተዋውቁም መጀመሪያ ብሄራቸው ነበር ሲነገር የነበረው፡፡ የብሄር ተዋጽኦ ትልቁን ቦታ መያዙ በዚህ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛ ትልቁን ቦታ የያዘው የፓርቲ ቅርበት ነው፡፡ በጠቅላላ ማለት ይቻላል፣ እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት ከኢህአዴግ ጋር ለረዥም ጊዜ አብረው የሠሩ፣ሌሎችም በተለያየ መልክ ከፓርቲው ጋር ሲሰሩ የቆዩ ናቸው፡፡
ምሁር የሚባለው እንደኔ ከአንድ ሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ የሲቪል ሰርቪስ ተመራቂዎች ናቸው። ብዙም አዲስ ነገር የለውም፡፡ አሁን የተሾሙት የፖሊሲ አስፈፃሚዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ የዘረጋው መስመር አለ።
ሃሳቤ ልክ ነው፤ ፖሊሲዬ ልክ ነው፤ ችግር ያለብኝ አተገባበር ላይ ነው፤ብሎ ነበር፡፡ መንገዳቸውን፣ ፖሊሲያቸውን እንደገና የመመርመር ነገር አይታይም። ስለዚህ በግሌ ከዚህ ካቢኔ ብዙ አልጠብቅም፡፡ በተለመደው መንገድ ነው የሄዱት፡፡


======================================
‹‹ያጠፋው አካል በግልፅ ለህዝብ መቅረብ አለበት››
አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት)

    የንስርና የእባብ መታደስ ልዩነት አለው፡፡ መሠረታዊ ለውጥና አሸልቦ መነሳት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የሹም ሽረቱም ጉዳይ አሸልቦ የመነሳት ነው፡፡ በፊት የነበሩትን ከመድረኩ ዘሪያ ገለል ያደርጉና በሌላ መልኩ ሾልከው ወይ ዞን፣ ወይ ወረዳ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ነው አካሄዱ፡፡ በፊት በር ያጣውን ነገር በጓሮ በር ያገኘዋል፡፡ ከስልጣን ወረዱ የተባሉ በጓሮ በር ያንን ስልጣን ያገኙታል፡፡ የኢህአዴግን የ25 አመት ጉዞ ስናየው፣ አንድ ግለሠብ ከስልጣን ይወርዳል፤ ሰውየው በምን ምክንያት ወረደ፣ ችግሩ ምንድን ነው? ያጠፋውስ? ቅጣቱ ምንድን ነው? ይሄ አይታወቅም፡፡ ለህዝብ በግልፅ አይነገርም። ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል ከተባለ፣ ያጠፋው አካል በግልፅ ለህዝብ መቅረብ አለበት፡፡ መሠረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ምንም ምክንያት ሳይጠቀስ የሚደረግ ማናቸውም ነገር ለውጥ የሚያመጣ አይሆንም፡፡
ከዚህ አንፃር እኔ ከአዲሱ ካቢኔ ምንም አልጠብቅም። ያለውን ፖሊሲና ተግባር የሚያከናውኑ አመራሮች ናቸው አሁንም የተሾሙት፡፡
 በዚህ መልኩ ብዙ ለውጥ ይመጣል ብዬ አልጠብቅም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ነው፡፡ አሁን የተደረገው ግን አንዱ ስልጣን ከአንዱ ወደ አንዱ የማዘዋወር ነገር ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው በመሰረታዊ ለውጥ ነው፡፡ የፖሊሲና የአሰራር ጉዳዮች ላይ በቁርጠኝነት ነው መሰራት ያለበት፡፡  ሰዎችን መለዋወጥ ሳይሆን ሲስተሙና አሰራሩን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡  
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመቱን በሰጡ ወቅት፣ “ከዚህ በኋላ ተሿሚዎች የራሳቸው ብሄርን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ማገልገል ነው ያለባቸው” ማለታቸው በተደጋጋሚ ስንጠይቀው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡

===================================
“የምርጫ ስርአቱ እንዲስተካከል ስንጠይቅ ነበር”

ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚዳንት)

ጥልቅ ተሃድሶ የሚባለውን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተን ምን ይፈጠር ይሆን የሚለውን ስንከታተል ነበር፡፡ ያየነው ግን ጥልቅ ተሃድሶውን በሰዎች ለውጥ ነው፡፡ የአሁኑን ምናልባት ከበፊቱ ለየት የሚያደርገው ምሁራኖችን ማካተቱ ሊሆን ይችላል፡፡ በኛ ግምገማ ይሄም ቢሆን በእርግጠኝነት ነፃና ገለልተኛ ሆነው የሚሰሩ አይነት ሰዎች ስብስብ አይመስለንም፡፡ ባለን መረጃ የኢህአዴግ አባል የሆኑ ሰዎች ናቸው የተሾሙት፡፡ ስለዚህ ከፓርቲያቸው የሚነገራቸውን ከመፈጸምና  ፖሊሲውን ከማራመድ ውጪ የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡
አመራሮች እንዳሉ ሆነው የማያሰሩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በጥልቀት መገምገም ይሻል ነበር፡፡ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ደንቦችና መመሪያዎችን ሊያመጣ የሚችል፤ የፓርቲ ፕሮግራም ከሚመስል አጠቃላይ ፖሊሲ ለየት ብሎ ልማታዊ አቅጣጫ ያለው ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡ በአጠቃላይ የፖሊሲ ለውጥ ነው እኛ የምንጠብቀው፡፡ ይሄንን ማድረግ ካልተቻለ እነዚህ ሰዎች የፈለገ ተመራማሪና ምሁራን ቢሆኑ፣ የማያሰራ ፖሊሲ እስካለ ድረስ የኢህአዴግን መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ አዲስ የሚሰሩት ነገር አይኖርም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አለብን የተባለውን በተመለከተ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ለስራ ማነቆ የሆነውን ነገር ሊፈታ የሚችል መላ በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡ ያለበለዚያ አዲሶቹ ሚኒስትሮች ከ6 ወር በኋላ መስራት አቅቷቸው ተናደው ጥለው ሊወጡ ይችላሉ፡፡
የምርጫው ስርአት ይሻሻላል መባሉ የሚደገፍ ነው። ለረዥም አመታት እኛም ስንጠይቀው  የነበረ ነው። ከዚህ በፊት ስለ ምርጫ ስርአቱ በጥናትም ጭምር አስደግፈን ለጋራ ም/ቤቱ አቅርበን ነበር፤ሆኖም ውድቅ ተደረገ፡፡ ምርጫ 2007 ላይ እንዲተገበር ሁሉ ጠይቀን  አልተቀበሉትም፡፡ አሁን ለቀጣዩ ምርጫ ይሻሻላል ተብሏል፡፡ እንደኔ ይሄ በጣም የመሸበት ይመስላል፤ወደ ተግባር ይቀየር ከተባለም በአስቸኳይ ወደ ድርድርና ንግግር መገባት አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ አዋጁን 6 ወር ሳይፈጅ ቶሎ አጥፎ፣ህብረተሰቡን ወደ ማረጋጋትና ውይይት መገባት ይኖርበታል፡፡ በነገራችን ላይ በፊት የጣሉትን የምርጫ ሥርዓት ሃሳባችንን አሁን ማምጣታቸውን፣በበጎ ነው የምንመለከተው፡፡ አንድ የዲሞክራሲ ሂደት መገለጫ ነው ብለን እናምናለን፡፡  

Read 1922 times