Sunday, 13 November 2016 00:00

አልማዝ አያና በ2016 ዓለም ኮከብ ሴት አትሌት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና በ2016 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ ሴት አትሌት ምርጫ ከመጨረሻ 3 እጩዎች አንዷ ሆና የቀረበች ሲሆን የምታሸንፍበት ሰፊ እድል መያዟን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሴቶች ምድብ አልማዝን የሚፎካከሯት ሌሎቹ እጩዎች ጃማይካዊቷ የአጭር ርቀት ሯጭ ኤላኒ ቶምሰንና ፖላንዳዊቷ መዶሻ ወርዋሪ አኒታ ውሎዳርስያስክ ናቸው፡፡
በወንዶች ምድብ የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት የጃማይካ አጭር ርቀት ሯጭ ዩሴያን ቦልት፤ እንግሊዛዊው የረጅምር ርቀት ሯጭ ሞ ፋራህ እና፤ ደቡብ አፍሪካዊው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ዋይዴ ቫን ኒክሬክ ናቸው። የአይኤኤኤፍ የ2016 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከ3 ሳምንታት በኋላ በፈርንሳይቷ ከተማ ሞናኮ የሚካሄድ ነው። የመጨረሻ እጩዎቹ ምርጫ ባለፉት ሁለት ወራት  በ3 ሂደቶች ያለፈ  ሲሆን 50 በመቶ በአይኤኤኤፍ ምክርቤት፤ 25 በመቶ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበረሰብእንዲሁም 25 በመቶው ከስርት አፍቃሪው በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች  በተሰበሰበው ድምፅ ነው፡፡
አትሌት አልማዝ አያና በውድድር ዘመኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንፀባራቂ ኮከብ ለመሆን የበቃች ሲሆን በተለያዩ ዘገባዎች የ2016 የዓለም ኮከብ ሴት አትሌት ለመሆን ሰፊ እድል እንዳላት የሚገለፀው ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች፤ሜዳልያዎች፤ ሪከርዶች  እና የውጤት ደረጃዎችን በመንተራስ ነው፡፡
በ2015 በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን በመሆን የሻምፒዮኑን ክብረወሰንን በ14፡29.83 በማስመዝገብና  የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ስኬቷን ከጀመረች በኋላ ብርቀቱ የሚስተካከላት ጠፍቷል፡፡ በ31ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ትልቁን ታሪክ የሰራች ሲሆን  በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሪከርድ በማስመዝገብ ነበር፡፡ ይህ ሰዓቷ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሪከርድ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡  
በ29 ደቂቃዎች ከ17.45 ሰከንዶች የተመዘገበ ሲሆን ለ23 ዓመታት ሳይሰበር የቆየና   በ14 ሰኮንዶች ያሻሻለችው ነበር፡፡ በተጨማሪ ደግሞ በ31ኛው ኦሎምፒያድ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡   በ2016 የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ ደግሞ በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር 4 ውድድሮች አድርጋ በሰበሰበችው 50 ነጥብ  የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ እና የ43ሺ ዶላር ተሸላሚ ለመሆንም በቅታለች፡፡ በዳይመንድ ሊጉ በኳታር ዶሃ በ3ሺ ሜትር፤ በሞሮኮ ራባት በ5ሺ ሜትር፤ በጣሊያን ሮም በ5ሺ ሜትር እንዲሁም በቤልጅዬም ብራሰልስ በ5ሺ ሜትር አሸናፊ ነበረች፡፡
በተለይ  በሮም ጣሊያን በተደረገው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 14፡12.59 የሆነ ጊዜ የዳይመንድ ሊጉ ሪከርድ ሆኖ ከመመዝገቡም በላይ በምንግዜም የፈጣን ሰዓት ደረጃ ሁለተኛ ላይ የተቀመጠ  ነው፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ የውድድር ዘመኑ የውጤት ደረጃ ላይም በሁሉም የትራክ ውድድሮች  በሴቶች ምድብ በ1476 ነጥብ ፤ በ10ሺ ሜትር በ1429 ነጥብ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር በ1403 ነጥብ  ከዓለም 1ኛ ደረጃ እንደያዘችም ታውቋል፡፡
በ2016 የዓለም ኮከብ ሴት አትሌት ምርጫ ላይ አልዝማ አያናን የሚፎካከሩት አትሌቶች ውጤት በመመዘንም ለማሸነፍ ያላትን ሰፊ እድል ማመልከት ይቻላል፡፡ ጃማይካዊቷ ኤላኒ ቶምሰን በውድድር ዘመኑ በ100 እና 200 ሜትር የኦምሎፒክ ሻምፒዮን ከመሆኗም በላይ የዓመቱን ፈጣን ሰዓቶች በሁለቱም ርቀቶች በማስመዝገብ፤ በኦሎምፒክ 4 በመ100 የብር ሜዳልያ እንዲሁም በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የነሐስ እንዲሁም በ100 ሜትር የዳመንድ ሊግ አሸናፊ ናት፡፡
ፖላንዳዊቷ መዶሻ ወርዋሪ አኒታ ውሎዳርስያስክ በውድድር ዘመኑ የኦሎምፒክና የአውሮፓ ሻምፒዮንነት ክብሮችን የተጎናፀፈች ሲሆን፤ በአይኤኤኤፍ የመዶሻ ውርወራ ቻሌንጅ ያሸነፈች ሁለት የዓለም ክብረወሰኖች ያመዘገበች እና በ12 ውድድሮች ያልተሸነፈች ናት፡፡

Read 1563 times