Tuesday, 08 November 2016 13:55

“ልጄ፤ አዲስ ፀጉር አበቀልኩ” “እዛው ቆዳህ ላይ?” “አዎ ልጄ፤ ባታውቀው ነው እንጂ ቆዳዬ’ኮ ሰፊ ነው”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

አንድ የኢራኖች ተረት የሚከተለውን ይላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ብዙ ጫጩት የምትፈለፍል አንዲት ዶሮ ነበረች፡፡ የዶሮዋ ባለቤት አንድ ቀን፣ “የምትወልጂውን ጫጩት እንድትነግሪኝ እፈልጋለሁ” አላት፡፡
ዶሮዋም፤
“ምኑን ነው ስለ ጫጩቱ ማወቅ የፈለግኸው?” ብላ ግልፅ እንዲያደርግላት ጠየቀችው፡፡
ባለቤትየውም፤
“ወንድ ይሁን ሴት? ለእርባታ የሚሆን ወይስ የማይሆን? መልኩስ ምን ይመስላል?” ብሎ አብራራላት፡፡
ዶሮዋም፤
“ይሄንን ሁሉ እኔ አላውቅም፡፡ የታቀፍኩት ዕንቁላል በቀኑና በራሱ ጊዜ መፈልፈሉን ብቻ ነው የማውቀው”
ባለቤትየው፤
“እኔ የምፈልገውን ዓይነት ጫጩት ካልሰጠሺኝ እስከ ዛሬ ከእኔ ጋር መኖርሽ ከንቱ ነው ማለት ነው፡፡ አሁንም አታዋጪኝም፡፡ ብታስቢበት ይሻላል” አላት፡፡
ዶሮይቱም፤
“የጠየቅኸኝ እጅግ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ጫጩት እያፈራሁልህ ማመስገን ሲገባህ ገና የሚወለዱትን ካላወቅሽ ብለህ ውለታዬን ሁሉ ያለ ዋጋ ማስቀረትህ አሳዝኖኛል”
ባለቤትየው፤
“እስከ ዛሬ የወለድሻቸውስ ወዴት ሄዱ?”
ዶሮይቱ፤
“እሱን መመለስ ያለበት፤ ትላንትና እራሱ ነው”
ባለቤትየው፤
“ወደፊት ስለምትወልጂያቸው አዳዲስ ጫጩቶችሽ ምንም ማወቅ አልችልም ማለት ነው በቃ?”
ዶሮይቱ፤
“ለማለት የምችለው አንድ ነገር ብቻ ነው”
ባለቤትየው በጥድፊያ፤
“ምን? እባክሽ ንገሪኝ?” አላት፡፡
ዶሮዋም፤
“ስለአሮጌዎቹ ጫጩቶች ትላንት እንደነገረን ሁሉ፤ ስለ አዲሶቹ ጫጩቶች ደግሞ ነገ ይነግረናል”
ብላ መለሰችለት፡፡
*    *    *
በአንድ ሀገር ላይ የሚደረግ ለውጥ በአንድ ጀምበር የሚገኝ አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ እና በሂደት የሚሆን ነገር ነው፡፡ ለውጥ አጓጊ የመሆኑን ያህል በጥድፊያ ካልሆነ ብለን ሱሪ በአንገት ብናደርገው “የቸኮለች አፍሳ ለቀመች” የሚባለው ተረት ይመጣል፡፡ “አትሩጥ አንጋጥ” ማለት ያስኬዳል፡፡ “ለውጥ የእረፍትን ያህል እፎይታን ይሰጣል” ይላሉ አበው፡፡ አዋቂዎች፤ “a change is as equal to rest” እንዲሉ በፈረንጅኛው፡፡ ለውጥ አስተሳሰባችንን መቀየር ይሻል፡፡ በጎታች አስተሳሰብ ከተያዝን የለውጥንም መምጣት የኋሊት እንጎትተዋለን፡፡ ለረዥም ጊዜ ስንጠይቀው የነበረው “ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ ይቀመጥ” (The right man at the right place) ጊዜውን ጠብቆ እየመጣ ይመስላል፡፡ የሰሞኑ ሹም ሽር ይሄን ያመላክታል ብለን እንገምታለን። ቢያንስ ብሔረሰባዊ ምደባን ብዙም ያማከለ አለመሆኑ ደግ ነው! ሆኖም አብረን ማየት ያለብን መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው፤ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ሲሰራበት የነበረው የቆየ ልማድ፣ ለአዲሱ ሹም እንቅፋት እንዳይሆንበት ምን ማሻሻያ ሊደረግ ይችላል? የሚለው ነው፡፡ ጎታች ባህል አዲሱንም ኃይል የመጎተት አቅም ሊኖረው እንደሚችል አለመዘንጋት ነው፡፡ የሚያሰራ ሁኔታ መኖር አለበት እንደማለት ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ከዚህ ቀደም ገዢ መሬት ሆኖ የቆየውን፤ ፖለቲካውን ቀዳሚ፣ ሙያተኝነትን ተከታይ አድርገን እናይበት የነበረውን የአስተሳሰብ መነፅር መቀየር እንደሚገባን ማስተዋል ነው፡፡ አለበለዚያ “አዲስ ወይን በአሮጌ ጋን” እንደሚባለው ይሆንብናልና ነው፡፡ በምንም ዓይነት ሙያተኝነት (professionalism) ቀዳሚ መሆን አለበት!! ሶስተኛው፤ ገና የቀስ በቀስ ለውጥ (evolution) ላይ እንጂ አብዮታዊ ለውጥ ውስጥ (revolution) እንዳይደለን ማጤን ነው፡፡
የያዝነው ለጥያቄዎች ሙያዊ ምላሽ የምንሰጥበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ያም በሙያዊ ተሐድሶ (Technocratic reform) ነው፡፡ አዝጋሚ ይሁን እንጂ በንቃት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለውጥ የጥንቱ ሌኒን፤ “አንድን ህዝብ ከአሥር ዓመት የፖለቲካ ትምህርት ይልቅ፤ የአንድ ዓመት እንቅስቃሴ የተሻለ ንቃት ይሰጠዋል።” የሚለውን አለመርሳት ነው፡፡ ይኸው ሊቅ፤ ‹‹ታላቅ ለውጥ የሚመጣው ፓርቲው ራሱን ሲቀጣ ወይም ሲያስወግድ (The party purges itself)” ነው ይለናል፡፡ ለሚካሄደው አዎንታዊ ሁኔታ አዎንታዊ አመለካከት መኖር ገንቢ ነው፡፡ ዜጎች፣ የሲቪል ማህበራትና ቡድኖች፤ ተቺና ጠያቂ የመሆናቸውን ያህል የሚያምኑበትን የመደገፍ ባህልም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እንደ ሙሽራይቱ፤ ሁሌ ‹‹ካልታዘልኩ አላምንም›› እያሉ መጓዝ ላያዋጣ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችን የምሁራን ሀብታም ሆና ሳለ፣ የሚያሠራ ሁኔታ በመጥፋቱ ዕውቀት በየሥርቻው ተቀርቅሮ፣ በየፊፋው ተንሸራቶ፤ ወይም አንድያውን ተገልሎ የከረመበት ሁኔታ መኖሩ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ለዛሬ አዎንታውያን ‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው›› የሚለው ብሂል መልካም ተስፋ ነው፡፡ በዚያም ብቻ አያልቅም፡፡ ከበደ ሚካኤልን ማዳመጥ ደግ ነው፡-
‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው፣ ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር፤ በተገናኘን፤
ሞት እራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆነ››
ድህነትን ጨርሶ ለመገላገል ገና ብዙ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ጣጣችን ከባህል ነገረ-ሥራችን ተሠናሥሎ፤ ካልተሻሻለ ውሃ-ወቀጣ ይሆንብናል! ጥረት፣ ማስተዋል፣ ጥበብ ነው የሚያሳድገን፡፡ አለበለዚያ፤ ነገን መጠራጠርም ግድ ይሆናል፡-
ነገ
‹‹ነገ፤ እባክህ አትምጣ እኔው እመጣለሁ
ደሞ፣ ዛሬ ብዬ፣ እሞኝብሃለሁ….››
የሚለውን ያገራችንን ገጣሚ ረቂቅ መልዕክት እንድናስብ እንገደዳለን! ዞሮ ዞሮ፤ ‹‹የወደቀ ሁሉ ጨዋ ነው›› ከሚል የአስተሳሰብ እሥረኛነት ነፃ መሆን የዕድገታችን መሽከርክሪት ነው! ‹‹የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታልም›› የሚለው ተረት፤ ጨካኝ ላልሆነ ትውልድ እንደማይሠራ ማስተዋል ግድ ሆኗል!!
በመጨረሻ ማስተዋል ያለብን ትልቅ ቁም ነገር፤ አዳዲስ ሹማምንት አገኘን ማለት ወደ ፒራሚዱ ታህታይ መዋቅር ካልወረዱ አደጋ መሆኑን፤ ለውጥ አዳጊ እንጂ ያለቀ ጉዳይ አለመሆኑን፤ ነገ ገና ውጤቱን የምናውቀውን ጉዳይ ዛሬ ካልዳኘን ብለን አለመወራጨቱ፤ መገንዘብ ዋና ነገር መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የለውጥን ሀሳብ በአዎንታዊ መንገድ ማሰብና አሉታዊ ነገሮችን ማስወገድ ትልቅ ኃይል አለው! ሼክስፒር፤ ‹‹Do good and shame the devil›› ያለው ይሄንን ነው፡፡ ‹‹መልካም ሥራና ሠይጣን ይፈር! ጉድ ይሁን!›› እንደ ማለት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ አዲስ ነገር የተፈጠረበት ጊዜ ነው ስንል በሚዲያ ከልኬቱ በላይ አናጋንነው፡፡ ሥራውን ሳናይ አናናፋው! ሆኖም አዲስ መንፈስ መፈጠሩን በርቱዕና ሀቀኛ መንፈስ ለሚያየው እንደ ዕድገት መሆኑን እናስብ! ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች አሏት!
ብቁ ንቁ፡፡ አራማጅ፡፡ ተራማጅ፡፡ ለውጥ ፈጣሪ! ይህን እሳቤ የያዘ ሰው፤
‹‹ልጄ፤ አዲስ ፀጉር አበቀልኩ›› አለ፤ አባት፡፡
‹‹እዛው ቆዳህ ላይ?›› አና ጠየቀ ልጁ፡፡ ‹‹አዎ ልጄ፤ ባታውቀው ነው እንጂ፣ ቆዳዬ‘ኮ ሠፊ ነው!!” አለ አባት። ያልተለየ ያልተፈተሸ … ማንም ልብ ያላለው ቦታ አለኝ ማለታቸው ነው! ኢትዮጵያ ሰፊ ናት፡፡ አዋቂዎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም አያያዝ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ያልተጠቀምንበትን ኃይል እንጠቀምበት፡፡ ሁሉም ሊያግዛቸው ይገባል!! መማር የዕውቀት ፍፃሜ አይደለም፡፡ ተግባር ፈተና ነው፡፡ በፈተናው ማደግም፣ መለወጥም ይቻላል። ለማንኛውም ቀና አስተሳሰብን የመሰለ ነገር የለም!

Read 3231 times