Saturday, 05 November 2016 11:22

በ24 ሰአት እስከ ሙሉ የሻይ ማንኪያ ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(60 votes)

አንዲት ሴት በተፈጥሮዋ የማህጸን ፈሳሽ ይኖራታል። ከዚያ ባለፈ ግን የፈሳሹ ሁኔታ ወደ ሕመም ደረጃ ከተለወጠ ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ግንኙነትዋን ሊያበላሸው ይችላል። ስለዚህ ሴቶች በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል የሚለውን የሕክምና ባለሙያዎች ምክር በመከተል በዚህ እትም ጠቃሚ ነጥቦችን ለንባብ ብለናል። ማብራሪያውን የሰጡት ዶ/ር ሙህዲን አብዶ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ አሁን የሚሰሩት በኢትዮ ጠቢብ ጠቅላላ ሆስፒታል በሐኪምነት እና በሐያት የህክምና ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ህክምና ትምህርት መምህር ናቸው።
ዶ/ር ሙህዲን እንደሚሉት ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ በሁለት ይከፈላል። ይኼውም፡-
አንዲት ሴት ከየትኛው እስከየትኛው እድሜ ጤናማ በሆነ ሁኔታ ፈሳሽ ሊኖራት ይችላል?
አንዲት ሴት ከብልት የሚወጣ ፈሳሽዋ ምን ሲሆን ነው የታመመ ነው የሚባለው?
ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ለይቶ በማየት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን መንገድ ለመጠቆም ያስችላል።
የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ነው ሲባል ምንጩም ፡-
የማህጸን በር ከሚያመነጨው እጢ ወይንም ሴል፣
ከማህጸን ግድግዳው ላይ እየተቀረፉ የሚወጡ ሴሎች፣
በግብረስጋ ግንኙነት ጊዜ ከደም ወደብልት የሚፈስ ፈሳሽ እና ከመሳሰሉት ተፈጥሮአዊ የሚመነጭ ነው።
እነዚህ ሴሎች በየጊዜው እየሞቱ በሌላ የሚተኩ ሲሆን በዚህም ወቅት ፈሳሽን ያመርታሉ። ያ ፈሳሽ የሴት ልጅን ብልት ትክክለኛ ወይንም ኖርማል የሆነ እርጥበት እንዲኖረው ያስችላል። እርጥበቱም ብልት እንዳይደርቅና በድርቀቱም ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እንዳይጋለጥ የሚረዳ ሲሆን የፈሳሹ ይዘትም አሲድ ያለው ስለሆነ ሊከሰቱ የሚችሉትን አጥቂ ሕዋሳቶች በሕይወት እንዲኖሩና ጥቃት እንዳይፈጽሙ የሚከላከል ነው። ይሄ አሲድ ያለው ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ የሚባለው ሁሉም ሴቶች በተወሰነ ደረጃ የሚያመነጩት ነው።
አንዲት ሴት በተፈጥሮዋ በ24 ሰአት ውስት ከግማሽ የሻይ ማንኪያ እስከ ሙሉ የሻይ ማንኪያ ወይንም ከ1-4 ሚሊ ሊትር የሚደረስ ፈሳሽ ይኖራታል። ይሄ እንግዲህ ጤናማ የሚባለው ፈሳሽ መጠን ነው። መልኩም ነጭ እና አንዳንድ ጊዜም ንጹህ ውሀ አይነት ሆኖ የመጎተት ባህርይ ያለው እና የህመም ስሜት የማይሰጥ ወይንም ደግሞ ጠረኑ የሚያስከፋ ያልሆነ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ ፈሳሽ ከተለያዩ ኢንፌክሽኖች የሚከላከል እንዲሁም በድርቀት ምክንያት አካሉ ለሌላ ችግር እንዳይጋለጥ ይረዳል።
ዶ/ር ሙህዲን አብዶ እንደገለጹት ይህ ተፈጥሮአዊ የማህጸን ፈሳሽ አንዲት ሴት ልጅ ገና እንደተወለደች በአራት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ደም የተቀላቀለ ትንሽ ፈሳሽ ከማህጸንዋ ሊታይ ይችላል። ይህም ከእናትየው ሆርሞን የሚመጣ ቅመም ፈሳሹን እንዲያመርት ስለሚሆን እንደችግር የማይቆጠር ተፈጥሮአዊ ነው። ከዚያም ወደጉርምስናው ሲገባ ፈሳሹ ከሌላ ጊዜ ትንሽ ጨመር ባለ መልኩ ሊስተዋል ይችላል። ተፈጥሮአዊው የማህጸን ፈሳሽ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችል ባለሙያው እንደሚከተለው ያብራራሉ።
ለምሳሌም፡-
በእርግዝና ጊዜ ከሰውነት ተፈጥሮአዊ ቅመሞች መጨመር ጋር ተያይዞ፣
የእርግዝና መከላከያ ማለትም ሆርሞን የያዙ መከላከያዎችን መጠቀም፣
በወር አበባ ኡደት ግማሽ ላይ በአስራ አራተኛው ቀን አካባቢ እንቁላል አኩርታ በምትወጣበት ጊዜ፣
ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ተፈጥሮአዊው ከብልት የሚወጣ ፈሳሽ መጠኑ የሚጨምር ሲሆን በተለይም በወር አበባ ኡደት ምክንያት መጠኑን ጨምሮ የሚታየውን ፈሳሽ ጥንካሬውንና ጥራቱን በመከተል የማኩረት አቅምን ለመገምገም የሚያስችል የምርመራ ውጤት ለማግኘትም ይረዳል።
የሴት ብልት ውስጥ ብዙ ባክሪያዎች እና ጀርሞች አሉ። እነዚያ ባክሪያዎች እና ጀርሞች የራሳቸውን ቁጥር የጠበቁ እና ተመጣጥነው ያሉ ናቸው። ከባክሪያዎቹ ውስጥ በብዛት የሚገኘው Lactobacillus የሚባለው ሲሆን ይህ ባክሪያ ዋና ስራው የማህጸን ግድግዳ ወይንም ብልት ከተለያዩ ጀርሞች ይከላከላል። ባክቴሪያ (Lactobacillus)፣ ቁጥሩ የሚያንስ ከሆነ ግን ሌሎቹ ማለትም የማይፈለጉት ባክሪያዎች ይበልጥ ይራቡና ወደፈሳሽ ይለወጣሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ መጥፎ ጠረን ያለው እና ብዛት ያለው ፈሳሽ መፍሰስ ይጀምራል። ይህ ጤናማ ያልሆነ የብልት ፈሳሽ በሚታይበት ጊዜ ችግር መኖሩን ያመላክታል። አንዲት ሴት ፈሳሽ መጠኑን ጨምሮ ሲገኝ እንዲሁም በብልት አካባቢ ማሳከክ ወይንም መቅላት የማቃጠል ስሜት ሲያመጣ እንዲሁም ቀለሙን ሲለውጥ፣ መጥፎ ጠረን ሲያመጣ፣ ግብረስጋ ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ሕመም መሰማት፣ የማህጸን የታችኛው ክፍልና የጀርባ ሕመም የሚሰማ ከሆነ ወደሕክምና ተቋም ሄዶ ምርመራ ማድረግ ይገባል።
የማህጸን ፈሳሽ ከተፈጥሮአዊው ይዘቱ ውጭ ሲሆን ወይንም ሲታመም የሚያሳየው መልክና ጠረን እንደሚከተለው ተዘርዝሮአል።
1/ ነጭ፣ ግራጫ ወይንም ብጫ የሆነ መልክ እና አሳ አሳ የሚል ሽታ፡-
 በብልት ወይንም በማህጸን ጫፍ በር ማሳከክ ወይንም ማቃጠል አካባቢው የመቆጣት የመቁሰል ስሜትን የሚያሳይ ነው።
2/ ቡናማ ወይንም የደም ቅልቅል የሚመስል ፈሳሽ፣
 ይህ ፈሳሽ የተዛባ የወር አበባ ኡደት ሲኖር ወይንም የማህጸን በር ሕመም መከሰቱን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በዚህም ወቅት ትክክል ያልሆነ በብልት የሚታይ ደም መሰል ነገር እና የጀርባ ሕመም ጎልቶ ይሰማል።
3/ አረንጉዋዴ ወይንም ግራጫማ መልክ ከመጥፎ ሽታ ጋር፣
 ሽንትን በመሽናት ጊዜ ማሳከክ እና የህመም ስቃይን ያስከትላል።
4/ ብጫ ወይንም ደመናማ መልክ ያለው ፈሳሽ፣
 በአገራችን አጠራር ጨብጥ የሚባለው ሕመም ምልክት ሲሆን የጀርባ ሕመም ወይንም በሽንት መሽኛ አካባቢም መጥፎ ስሜትን ያስከትላል።
5/ ወፍራምና ነጭ መልክ ያለው ፈሳሽ፣
 በማህጸን ጫፍ አካባቢ ስቃይ ያለው ሕመም የማሳከክና በወሲብ ግንኙነት ወቅት ሕመም ይኖራል።
የማህጸን ፈሳሽ ተፈጥሮአዊ ከመሆን አልፎ ወደሕመም ሲለወጥ እና ከላይ የተጠቀሱትን መልኮች ሲያሳይ እንደምክንያቱ የተለያየ ነው።
የመጀመሪያው ከኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። ከኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሲባልም አንደኛው ከባክሪያ ጋር የሚገናኝ ነው። ባክሪያዎቹ የተለያዩ እንደመሆናቸው ባህሪያቸውም ብዙ አይነት ነው። ከኢንፌክሽን ከሚከሰተው የብልት ፈሳሽ ከ40-50% የሚሆነው በባክሪያ ምክንያት የሚከሰት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ፈንጋል ኢንፌክሽን ወይንም ይስት ከሚባለው የሚከሰት ፈሳሽ አለ። ይህም ከ20-25% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል።
በሶስተኛ ደረጃ ከኢንፌክሽን መካከል የሚጠቀስ አንድ ፕሮቶዝዋ አለ። ይህም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ሊተላለፍ የሚችል ነው። ይህም ከ15-20% የሚሆነው የፈሳሽ አይነት የሚከሰትበት ነው።
 ስለዚህም ሶስቱ በኢንፌክሽን ምክንያት የሚከሰቱ የፈሳሽ አይነቶች በባክሪያ፣ በፕሮቶዝዋ እና በፈንገስ ምክንያት ናቸው። በብዛት በInfection ወይንም በጀርም አማካኝነት የሚመጣው ፈሳሽ እንደመንስኤው ሁኔታው ይለያያል። ይህ ችግር በአባላዘር በሽታ ወይንም ከአባላዘር በሽታ ጋር ባልተያያዘ መንገድም ሊከሰት ይችላል።
ለፈሳሽ ጤነኛ አለመሆን በምክንያትነት የሚጠቀሱት ምንድናቸው?
ሴቶች ተፈጥሮአዊው የማህጸን ወይንም የብልት ፈሳሽ ወደ ሕመምነት እንዳይለወጥ ምን ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል?

Read 31943 times