Print this page
Sunday, 30 October 2016 00:00

‘ፍጥጥ’ ብለው ሲያዩን…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ያየናት ጥቅስ ነች፡፡ “አንድዬ፣ አሳልፍልኝና ሰዎች ይግረማቸው።” በቃ፣ ጊዜው እንዲህ ነዋ! “አሳልፍልኝ” ከተባለ በኋላ… አለ አይደል… ‘አራት ነጥብ፣’ ‘ተፈጸመ’ ምናምን ማለት እያለ… “ሰዎች ይግረማቸው” የሚሏት ቅጥያ አትገርምም! አለ አይደል…ልክ እኮ “እኔ አልፎልኝ አይተው ይግረማቸውና ከፈለጉ የተላጠ ኮረንቲ ይጨብጡ!” አይነት ነው የምትመስለው!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በየቦታው ‘እንጀራ በወጥ’ ስንበላ ስጋት አስቸገረንሳ! ልክ ነዋ…እንጀራው ሲቆረስ የቆርቆሮ ፋብሪካ አይነት ድምጽ ሲያወጣ… “ጄሶ ሲያልቅባቸው ሲሚንቶ ጨመሩበት እንዴ!” ብለን እንሰጋለን፡፡ ዘንድሮ እኮ…“የፈለገ ቢሆን  በጭራሽ ይህ ሊሆን አይችልም!” የሚባሉ ነገሮች እየቀነሱ ነዋ!
እናላችሁ…መሥሪያ ቤት በአንድም ይሁን በሌላ ‘ሰበብ’ የተጠራ ስብሰባ እንገባለን፡፡ ምንም ወደ ኋላ ሳትሉ የመሰላችሁን ሀሳብ መናገር ትችላላችሁ’ አይነት ነገር ሲባል ፈታ እንላለን፡፡
“አመራሩ ከፍተኛ የአቅም ችግር አለበት…”
“በበጀት እጥረት እስክሪብቶና ወረቀት የለም እየተባለ ሰባት፣ ሰባት ሶፍትፔፐር የታደለን ለእሱ ልዩ በጀት አለ እንዴ?” (ቂ…ቂ…ቂ…ቂ የሰማችሁት ሀሳብ አቅራቢው ሳይሆን ዘጋቢው ነው፡፡)
“መሥሪያ ቤቱ በሁሉ በኩል እየደከመ ነው…” ምናምን እያልን ‘የመሰለንን’ ለፍልፈን እንወጣለን፡፡ በሩ ላይ ምን ቢፈጠር ጥሩ ነው…ልባችን በሴከንድ ሀምሳ መምታት ትጀምራለች፡፡ እናማ…ስጋት ሆዬ እላያችን ላይ አርባ ስድስት ፎቅ ይሠራል፡፡
“አለቆቹ በመዋቅር አሳበው አውጥተው ለጅብ ይወረውሩኝ ይሆን!”
“የተናገርኩት ስለ እሱ መሆኑን ፔርሶኔሉ አውቆብኝ ይሆን!”
“ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጠረፍ ላይ ወዳለ ቅርንጫፍ ያስፈነጥረኝ ይሆን!”
“የንብረት ክፍሏ ሴትዮ ታስጠቁረኝ ይሆን!”
… ምናምን እያልን እንሰጋለን፡፡ ዘንድሮ፤ “አይዞህ፣ ሀሳብህን ስለገለጽክ ምንም አትሆንም!” ብሎ ሮማንቲክ ኮሜዲ ምናምን የለም፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…  “አንተ፣ እስካሁን ድረስ እዚሀ አገር ነህ!” የሚሏት ነገር አለችላችሁ፡፡ አለ አይደል…ጥያቄ ይሁን፣ መገረም ይሁን ግራ ያጋባላ! ምናልባትም እኮ… “ይሄን ሰውዬ እስካሁን አልነቀለንም!” አይነት ነገር ሊሆን ይችላላ! እናማ እንደዛ ሲሆን እንሰጋለን። “የእኔ እዚሀ አገር ‘እስካሁን’ መኖር ሰበር ዜና የሆነበት ምክንያት ለምንድነው?” ብለን እንሰጋለን። እንዲሀ ባለ በአራተኛው ቀን ደውሎ “ስማ ሃይ ስኩል እያለን የቀማኸኝ ገርልፍሬንድ ትዝ ትልሀለች!” ቢል ነገር አለ ማለት ነው፡፡
ወይ ደግሞ “ስማ ኮንዶሚኒየም ደርሶኝ ቅድሚያ ለመክፈል ገንዘብ እያሰባሰብኩ ነው። ካላስቸገርኩህ አንድ ሀያ ሺህ ብር…” ከዛ በኋላ ያለውን አትሰሙም፡፡ ቀዶ ጥገናው ጠረዼዛ ላይ የተኛው በሽተኛም እንደዛ አይደነዝዝም፡፡ አሀ…አሜሪካ አምስት ምርጫዎች ከተካሄዱ በኋላ ተገናኝታችሁ ሀያ ሺህ ብር!
ወይ ደግሞ… “ስማ ለካ የዋዛ አይደለህም፣ ጉድህን ሁሉ አሁን አይደል እንዴ የምሰማው!” ሲል…ምን አለፋችሁ… “ምን ማለቱ ነው?” ብላችሁ የምትመራመሩትን ያህል አምፖል የፈጠረው ሰውዬም አልተመራመረም፡፡ (ዘንድሮ እኮ አምስት ሰዎች ስለ እናንተ ማንነት ቢያወሩ ሰባት አይነት ሰብእና እንዳላችሁ ትረዳላችሁ፡፡ ዘመኑ ነዋ!)
እናማ… የሆነ ሰው ድንገት ጠበቅ አድርጎ “አንተ፣ እስካሁን ድረስ እዚሀ አገር ነህ!” ሲለን እንሰጋለን፡፡”
እግረ መንገዴን….ይቺን ስሙኝማ… የሆነ ሰው ታገኙና ከብዙ ዓመት በፊት ሁለታችሁ ታውቁት ስለነበረ ሰው ያነሳባችኋል፡፡
“ስማ እሱ ሰውዬ አለ እንዴ! ምነው አላየው!”
“እሱ ስንት ዓመቱ… አሪ ቬዴርቺ ብሏል፣” ትላላችሁ፣ ነገሩን ለስለስ ለማድረግ፡፡
“አትለኝም!...ሮም ነው ሚላን የሄደው?” ሰውየው ምን ነካው!
“ኧረ… ወደ ላይኛው ቤት ከሄደ ሀያ አንድ ዓመቱ…”
እሱዬው ይደነግጣል፡፡ ወይም የደነገጠ ይመስላል፡፡ “ኦ ማይ ጋድ! ምን ነካው?”
“ያመው ነበር መሰለኝ…”
“ምኑን?” ሰውዬ፣ ሀያ ምናምን ዓመት የሆነውን ነገር የማስታውስልህ እኔ የሆስፒታሉ መዝገብ ቤት ነኝ!
“እሱ እንኳን ትዝ አይለኝም…”
ከዛም “አይ የሰው ነገር…ሁላችንም እንዲህ ነን እኮ!” ምናምን አይነት ነገር ይልላችኋል፡፡ በዚሁ በቃ ስትሉት…አለ አይደፐል… “እኔ የምልህ አግብቶ ነበር እንዴ!” ‘ማግባት’ የሚለውን ቃል መሰረት አድርጎ ስንት እርግማን መደርደር እንደሚቻል ትዝ የሚላችሁ ያኔ ነው፡፡
ገደብ ይደረግልን…አንድ ሰው ለእስከወዲያኛው ኩሼ ካለ ከዓመት ከሰባት ወር በኋላ በዝርዝር ማንሳት አይቻልም ይባልልንማ!
ደግሞላችሁ…‘ዓይነ ውሀው ደስ ያላለን ሰው’ አፍጦ ሲያየን እንሰጋለን፡፡ እንክት አድርገን ነዋ! ስንት የሚፈጠጥባቸው… አለ አይደል…‘በትእዛዝ የተፈጠሩ’ የሚመስሉ እንትናዬዎች እያሉ፣ እኛ ላይ ሲያፈጥብን ለምን ግራ አይገባንም! (“ሰው ዓይን ለመግባት ተፈታተህ እንደገና መገጠም አለብህ…” ያልከኝ ወዳጄ፣ ያወራኽው ስለ ኦሮጂናሌ ዕቃ ነው ስለ ሞዲፊክ! አይ… ብዙ ነገር ላይ ‘ኦሪጆናሌ’ና ‘ሞዲፊኩ’ ስለተቀላቀለብን ነው!)  
እናላችሁ… ቀልባችን ያልወደደው ሰው ሲያፈጥብን…አለ አይደል… ምን ትዝ የማይል ነገር አለ! ለምሳሌ ከሚስት አፋትታ ‘ለመጠቅለል’ ያሰበች ሴትዮ… “እስቲ የትና ከእነማን ጋር እንደሚውልና እንደሚያመሽ አጥናልኝ፣” ብላ ሊሆን ይችላል።  ወይም ደግሞ… ፊልም ላይ የሮሚዮን ገጸ ባህሪይ ሊሰጠን ያሰበ ዳይሬክተር ሊሆን ይችላል።  ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…‘ሥራም’ ሆነ፣ ‘ጊዜ ማሳለፊያ’ም ሆነ፣ ‘ሀሳብ ጭልጥ አድርጎ ይዞ ሄዶም’ ሆነ… ሰውን አፍጥጦ ማየት አሪፍ አይደለም፡፡ የማያዩ መስለው ማየት እያለ! ቂ…ቂ…ቂ… ወለሉን እያዩ መስለው ‘ሌግ’ ምናምን ‘መመዘን’ እያለ! (ስሙኝማ… እግር የቻይና ‘ቾፕስቲክ’ ምናምን መስላ…አለ አይደል… ብጥሌ ቀሚስ ጣል የሚያደርጉ እንትናዬዎች አድናቂ ነኝ፡፡ ልጄ ‘ወረፋ ወደማይበዛበት’ ጠጋ ነው፡፡)
እናላችሁ…የሆነ ቦታ ማኪያቶውን ሁለት ጊዜ ፉት ብላችሁ ቀና ስትሉ፣ ሰባት ምናምን ሰው ወደ እናንተ ሲያፈጥ ታያላችሁ፡፡ ቴሌቪዥኑ ያለው ሌላኛው ግድግዳ ላይ!
እናማ… ‘ፍጥጥ’ ብለው ሲያዩን እንሰጋለን!
ደግሞላችሁ…መብራት ‘እንደፈለገው’ ሲበራና ሲጠፋ፣ እንሰጋለን፡፡ ልክ ነዋ…በስንት ስለት የተገዛች አሥራ ምናምን ኢንች ቴሌቪዥን ‘ጧ’ ትላለች ብለን እንሰጋለን፡፡ “ይቺም ፍሪጅ ሆና ያልቅላት ይሆን!” ብለን እንሰጋለን፡፡ አሀ…ለማን አቤት ይባላል! ልክ ነዋ…አንድ ጊዜ አብስለን ለአሥራ አምስት ቀን ‘እየጨለፍን’ የምንበላው ፍሪጅ ስላለች አይደል! የምር ግን… ባለፉት ጥቂት ወራት የመብራቱ አጠፋፍና አበራር…አለ አይደል… ‘ኦድ’ የሚሉት አይነት ነገር ሆኗል፡፡ ምንም ነገር መብራት አለ ብሎ ‘ሀሳብን ጥሎ’ መሥራት ህልም እየሆነ ነው። አሁን በቃ ኦማር ታየርን እጅ ከፍንጅ ያዘው ብለን ልባችን ሲሰቀል … መብራት ድርግም ይላል! (“የኤሊፍና የኦማር እጣ ፈንታ ምን ይሆን!” እያልን ከምንሰጋውና…“የመን ያለችው እህቴ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን!” ብለው ከሚሰጉት የትኛው ወገን እንደሚበልጥ ቆጠራ ይካሄድልንማ!)
በዓይናቸውም ይሁን፣ በሀሳባቸውም ይሁን፣ በነገርም ይሁን፣ በጄሶ እንጀራቸውም ይሁን…‘ፍጥጥ’ ብለው ሲያዩን እንሰጋለን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4767 times