ከአልጋዬ ሳልወርድ ጆሮዬ የገባው
የወፎች ዜማ ነው
አይኔም ቀድሞ ያየው፣
ጸሃይ ስትወጣ ወርቃማ
ጨረሯ በመስኮት ገብቶ ነው፤
ህብረ ዝማሬያቸው ሁሉም “ይቻላል” ነው፡፡
ታዲያ የኔ “አይቻልም” ከየት የመጣ ነው?
ጸሃይ አላለችም፤ ወፎች እንዲያ
ብለው ፍጹም አልዘመሩም፤
“ይቻላል” ነው ያሉት በሚያምር
ድምጻቸው ወፎች የዘመሩት፤
የጸሃይ ጨረሮች ምድር ላይ የረጩት፣
“ይቻላል” ነው ያሉት፡፡
ታዲያ አይኔ ያላየውን፣
ጆሮዬ ያልሰማውን ከየት አመጣሁት?
ከአልጋዬ ላይ ሳልወርድ “አይቻልም” ያልኩት፡፡