Sunday, 30 October 2016 00:00

ሰማያዊ ፓርቲ፤አባላቶች እየታሰሩብኝ ነው አለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አመራሮቼ፣ አባላትና ደጋፊዎቼ እየታሰሩብኝ ነው አለ፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ተሰማ፤ በአዲስ አበባ ከታሰሩት አመራሮች መካከል የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ሚኒሊክ ሆስፒታል የታመመ አባል ለመጠየቅ በሄዱበት ለእስር መዳረጋቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ከስራ አስፈፃሚዎች መካከል አቶ አበበ አካሉ፣ የፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሪት ብሌን መስፍን፣ የብሄራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት መርከቡ ሀይሌ፣ እያስቤድ ተስፋዬ፣ አቶ አወቀ ተዘራና የፓርቲው የቀድሞ የህግ ጉዳይ ኃላፊ አቶ አዲሱ ጌታነህ እንደሚገኙበት ገልፀው፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ከዋግህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ አቶ አበበ አየለና ሞገስ አበጀ የተባሉ አባላትም ታስረውብናል ብለዋል፡፡
ከአርሲ ዞን ደግሞ አቶ አበራ ታደሰ፣ አቶ ጀዋሮ ገልገሎ የታሰሩ ሲሆን ከደብረብርሃን አቶ አስራት እሸቴ፣ ከባህርዳርና አካባቢው አቶ በላይነህና አቶ ማሩ መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡
“አቶ በላይነህና አቶ ማሩ የተባሉት አባሎቻችን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊት ቢታሰሩም እስካሁን ፍ/ቤት የመቅረብ መብታቸውን ተነፍገዋል” ያሉት አቶ ሰለሞን ሌሎቹ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ለእስር መዳረጋቸውንና እስካሁን ፍ/ቤት አለመቅረባቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡ ከአመራሮች፣ ከስራ አስፈፃሚዎችና አባላት በተጨማሪም የፓርቲው ደጋፊ የሆኑ፣ አርቲስቶች፣ መፅሀፍ አሳታሚዎችና የህትመት ውጤቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ለእስር ተዳርገውብናል ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ለምሳሌ ደጋፊያችን አትሌት ግርማ ገርባባ ስፔን ለውድድር ሄዶ እንደተመለሰ ባልታወቀ ምክንያት ታስሯል ብለዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት አፈሳው፣ ወከባውና እንግልቱ በፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል” ያሉት ኃላፊው በምን ምክንያት እንደታሰሩ ለማወቅ የሚጠይቅም መልስ የሚሰጥም አካል የለም›› ሲሉ አማርረዋል፡፡ “አንድ ሰው ፍ/ቤት ቀርቦ የክስ ቻርጅ ሲደርሰው ቢያንስ ያጠፋው ይታወቃል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹አመራሮቻችን ከሶስት ሳምንት በላይ ቢታሰሩም ፍ/ቤት አለመቅረባቸው የህገ - መንግስቱን አንቀፅ 29 በእጅጉ ይቃረናል ብለዋል፡፡
‹‹መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ የሚያደርሰውን የመብት ጥሰት እንዲያቆምና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም የህገ መንግስቱን መርሆዎች እንዲከተል እንጠይቃለን›› ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች በያሉበት ቦታ ፍ/ቤት ቀርበው የተከሰሱበትን ምክንያት እንዲያውቁ፣ መብታቸው እንዲከበር፣ እንዲፈቱና ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እንጠይቃለን›› ብለዋል፡፡ 

Read 1499 times