Sunday, 30 October 2016 00:00

“ወዳጄ፤ ለመሆኑ ብሣና ይሸብታል ወይ?” ብሎ ቢጠይቀው፣ “ለዛፍ ሁሉ ያስተማረ ማን ሆነና ነው” አለው

Written by 
Rate this item
(8 votes)

በሩሲያ የሚነገር አንድ ተረት አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የውሃ ክፍል ኃላፊ ሁለት የበታች ሰራተኞቻቸውን ይጠሩና፤
“ያስጠራኋችሁ አንድ አጣዳፊ ሥራ ስላለ ነው” ይላሉ፡፡
“ምንድን ነው ጌታዬ? እኛ ሥራውን ለመፈፀም ዝግጁ ነን” ይላሉ ሠራተኞቹ፡፡
አለቅየውም፤
“በጣም ጥሩ፡፡ ነገ ሹፌራችን ወደሚያሳያችሁ ቦታ ትሄዱና አንዳችሁ ቦዩን ትቆፍራላችሁ፡፡ አንዳችሁ ደግሞ ቧምቧ ትቀብራላችሁ፡፡ ሥራው ረዥም ርቀት ላይ የሚሰራ ስለሆነ ማለዳ ወፍ ሲንጫጫ ሄዳችሁ ነው ስራውን መጀመር ያለባችሁ” ሲሉ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡”
ሰራተኞቹ፤
“በሚገባ እንፈፅማለን” ብለው ወደየክፍላቸው ይሄዳሉ፡፡
በነጋታው ጠዋት ግን ቧምቧ እንዲቀብር የታዘዘው ሰራተኛ፤ ሹፌር ከቤት ሊወስደው ሲሄድ፣
“ዛሬ አሞኛል ሥራውን ልሰራ አልችልም” ብሎ ከነቧንቧው ቤቱ ይቀራል፡፡
ቦዩን እንዲቆፍር የታዘዘው ሠራተኛ ግን ወደተባለው ቦታ ሄዶ መቆፈር ይጀምራል። ሆኖም አቆፋፈሩ ያስገርማል፡፡ የተወሰነ ርቀት ይቆፍርና መልሶ አፈሩን እየመለሰ ይደፍነዋል፡፡ እንዲህ እያደረገ ቀኑን ሙሉ ሲቆፍርና ሲደፍን ውሎ የተባለውን ርቀት ጨርሶ ወደመሥሪያ ቤቱ ይመለሳል፡፡
አለቃው፤
“እህስ ጨረሳችሁ ወይ?” ሲሉት
“አዎ ጌታዬ፤ እኔ የተባለውን ርቀት ቆፍሬ ጨርሼ መጥቻለሁ”
“ባልደረባህስ የታለ?”
“እሱ ቧምቧውን እንደያዘ አሞኛል ብሎ ቤቱ ቀርቷል፡፡ እኔ ግን የታዘዝኩትን ቦይ ቆፍሬ መልሼ አፈሩን በሚገባ ደፍኜ ኃላፊነቴን ተወጥቼ ተመልሻለሁ ጌታዬ” አለ፡፡
*   *   *
የምንሰራው ሥራ ዓላማ ሳንገነዘብ ኃላፊነት መወጣትም ሆነ ከተጠያቂነት እድናለሁ ብሎ ማሰብ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ “እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች” የሚባለው ተረት ዓይነት ነው፡፡ አንድም በሥራ መለገም፣ አንድም ዓላማ ቢስ ሥራ መስራት፤ ከተጠያቂነት አያድኑም፡፡ ባለቧንቧው ይታመም አይታመም ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ቧንቧውን ቢያንስ ለሥራ ባልደረባው አለመስጠቱ ግን ፍፁም ከተጠያቂነት አያድነውም፡፡ ቆፋሪው ቧንቧውን ይዞ ለመሄድ አልሞከረም፡፡ በመቆፈር ያፈሰሰው ላብ ቢያሳዝንም መልሶ በመድፈኑ ቢያንስ ለጅልነቱ ዋጋ ይከፍላል፡፡
ዋናው ነገር ግን ሥራው ሳይሠራ ቀርቷል፡፡ በዚህ ዓይነት የባከነ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ቧንቧው ሊሰጥ ይችል የነበረው አገልግሎት፤ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በሀገራችን ሁሌ እንደ ችግር ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ ብክነት ነው፡፡
አንድ ብክነት አለ ሲባል በተያያዥነት የሚነሱ እንደ ሠንሠለት የተሳሰሩ አያሌ ተመላካች ነገሮች እንደሚኖሩ አንዘንጋ፡፡ በቡድን የሚሠሩ ሥራዎች አንድ ሰው ሲጎድል ወይም ኃላፊነቱን ሲያጎል ቀጥ ይላሉ፡፡ የሥራ ፍሰት ምሉዕነት (System flow) ይዛባል፡፡ አንደኛው የሥራ ክፍል ኃላፊነቱን ሲወጣ ሌላኛው ክፍል ሥራውን ካልሠራ፣ የመሥሪያ ቤቱ ድፍን የሥራ ሂደት ሽባ እስከመሆን ሊደርስ ይችላል። የአመራር ደካማነት፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የአልምጥ ሠራተኞች መብዛት፣ ስህተትን አንዱ ባንዱ ላይ መላከክ (Blame-Shifting)፣ የራሴን ከተወጣሁ ምን ቸገረኝ ማለት፤ ነገርን ከሥሩ አለማየት፣ ችግሮችን በወቅቱ አለመፍታት፣ ወገናዊነትን አለማስወገድ፣ ተቋማዊ ጥንካሬን ማጣት ወዘተ የተለፋበት ሥራ፣ የተደከመው ድካም ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጋል፡፡ ይህ በፈንታው የሀገርን ሀብት ለብክነት ይዳርጋል፡፡ ዕድገትን ያቀጭጫል፡፡ ህዝብ ትክክለኛ አገልግሎት እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ በዚህ ላይ ነጋ ጠባ የምንወተወተው የናጠጠው ሙስና ሲጨመር፣ ምን ያህል የኢኮኖሚ ዝቅጠት ውስጥ እንደሚከተን ማስላት ነው፡፡
ለመልካም ሠራተኞች ምን ያህል የሞራል ድቀት እንደሚያመጣ ማስተዋል ነው። ልብ መባል ያለበት ድክመቶችና ጥፋቶች የበታች ሠራተኞች ላይ ብቻ የሚታዩ ክስተቶች አድርጎ መቁጠር ስህተት መሆኑ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ የበላይ ኃላፊዎችም፣ በማን አለብኝነትም ሆነ በዕውቀትና ልምድ ማነስ ጥፋት ይፈፅማሉ። በሥልጣን ይባልጋሉ፡፡ ሙስና ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ሆነ ብለው ሥራ የሚያጓትቱና ተገልጋይን ህዝብ የሚያጉላሉም ይኖራሉ፡፡ መፈተሽ አለባቸው፡፡ ‹‹ወዳጄ፤ ለመሆኑ ብሣና ይሸብታል ወይ?›› ብሎ ቢጠይቀው፤ ‹‹ለዛፍ ሁሉ ያስተማረ ማን ሆነና ነው?›› አለው፤ የሚለው ተረት የሚጠቁመን ይሄንኑ ነው!


Read 5399 times